ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ዐርብ ግንቦት 22 ቀን 2005 ዓ.ም. (Sunday, May 31, 2013)
ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እሁድ ግንቦት 25 ቀን 2005 ይደረጋል የሚል ዜና ዘሃበሻ ድረ ገጽ ላይ ሐሙስ ምሽት ተመለከትኩት። አንድነት ፓርቲ እና መኢአድም ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በአንድነት መቆማቸውን እና መንግስት ሰላማዊ ሰልፉን መፍቀዱን ጨምሮ ይገልጻል ጽሑፉ። ወዲያውኑ ሰላማዊ ሰልፉ እንከን የለሽ እንዲሆን እጅጉን ተመኘሁኝ። የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ እንደ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ተቃውሞ በድስፕሊን የታነጸ እና ክብርን ከመንግስት ሳይቀር የሚጎናጸፍ እንዲሆን እጅጉን ተመኘሁ። የበኩሌንስ ምን አስተዋጽኦ ላድርግ ብዬ ተጨነቅኩ። ይኽን ጽሑፍ በችኮላ እንዳዘጋጅ የገፋፋኝ እሱ ነው።
የሰላም ትግልን ሊበክሉና ለአደጋ ሊያጋልጡት ከሚችሉ ተግባሮች፣ አሰራሮች እና ሁኔታዎች ውስጥ ጥቂቶቹን አንስቼ በአጭር በጭሩ ልበልና ልሰናበት።
(1ኛ) ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ በመንግስት ወይንም በመንግስት ደጋፊዎች አማካኝነት የሚፈጸምበትን የሽብር ጥቃት ለመመከት ሲል የሚፈጽመው ማንኛውም አይነት የኃይል እርምጃ ሰላማዊ ሰልፉን ሊበክል እና ውድቀት ሊያስከትልበት ይችላል። ስለዚህ የዲሞክራሲ አራማጅ የሆነው ወገን ለሽብር መልሱ ሽብር ነው ከሚለው ፍልስፍና መራቅ አለበት። ሰላማዊ ትግል ወደ ኃይል እርምጃዎች ከተንሸራተተ በሰላማዊ መንገድ ለነፃነት መታገል የጀመረው ህዝብ እምነት ሊተን ይችላል። ህዝብ ሁከት አይወድም። ለሽብር መልሱ አለመሸበር መሆን አለበት።
(2ኛ) የሰላም ትግል አመራር የወጣቶች እንዲሁም በእድሜና በተመክሮ የበሰሉ ሰዎች ቅይጥ ቢሆን ለበካዮች ቀዳዳ ላይከፍት ይችላል። በድስፕሊን የታነጸ ግራና ቀኙን የሚያይ እና ሰላማዊ ሰልፈኛው ውስጥ ጸብ ጫሪ ተግባር እንዳይፈጸም የሚጠብቅ በሰላም ትግል መርሆዎች የሰለጠነ ኃይል መሰማራት አለበት።
(3ኛ) በድርጅቶች ህብረት-አመራር ዘንድ የሚታይ ክፍፍል የሰላም ትግልን ይበክላል። ገዢው ቡድን ደጋፊዎቹን በመላክ ወይንም ከሰላም ትግል አመራር ውስጥ ህሊና ደካሞችን በጥቅም በመግዛት ወሬ እንዲያቀብሉት (informants) ሊያደርግ እንደሚችል ቀደም ተብሎ ሊታሰብበት ይገባል። እነዚህ የመንግስት ወሬ አቀባዮች ለውይይት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ሆን ብለው ስምምነት እንዳይኖር እያደረጉ ዞር ብለው ደግሞ ለሰላማዊ ታጋዩ ህዝቡ ስምምነት ጠፋ ይሉታል። ህዝብ በክፍፍሉ የተነሳ በትግሉ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ። ከፍራቻ መውጣት እና መታገል እንዲሳነው ለማድረግ። ስለዚህ የዲሞክራሲ ኃይሎች ህብረትን ማጠናከር እንዳይሳናቸው እና ጸብ ጫሪ ሰርጎ ገቦች (agent provocateurs) ምኞታቸው እንዳይሳካ መደረግ አለበት።
(4ኛ) የሲቪክ ድርጅቶች አመራሮች በአምባገነኖች ቁጥጥር ስር ከሆኑ የሰላም ትግል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተበክሏል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የመምህራን፣ የሰራተኛ፣ የወጣቶች ማህበራት አመራሮች በገዢው ቡድን ቁጥጥር ስር ከሆኑ እነዚህ ተቋሞች የመጨቆኛ አጋዥ ምሶሶዎች ሆነዋል ማለት ነው። ነፃ ማውጣት አሊያም ሊላ ትዩዩ (Parallel) ድርጅቶች መመስረት ያስፈልጋል። እነዚህ ተቋሞች የነፃነት ትግልን ኃላፊነት ለእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመበትንም ይጠቅማሉ። ወጣቱ ብቻ የሁሉም ህብርተሰብ ነፃ አውጪ ሊሆን አይችልም።
(5ኛ) በሰላም ትግል ኃይሎች የሚሰጡ መግለጫዎች አግላይነት ከታየባቸው የተገለለው ወገን ወደ ጸበኛነት እንዲሄድ በማድረግ የሰላም ትግል ሊበከል ይችላል። ለምሳሌ የአንድ ተቃዋሚ ድርጅት አባል ሲታሰር የሁሉም ድርጅቶች ጉዳይ ሊሆን ይገባል። መንግስት ሁሉንም በወዳጅ አይን እንደማያያቸው እና ቢቻል ሁሉም ቢጠፉለት እንደሚፈልግ መዘንጋት የለብንም። ጥቃቱ ተራ ጠብቆ የሚመጣ መሆኑ ታውቆ አንዱ ሲጠቃ ሁሉም እንደተጠቃ በመውሰድ በአንድነት መቆም ጠቃሚ ነው።
(6ኛ) የመንግስት ወሬ አቀባዮች (informers) ካሉበት የሰላም ትግል የመንግስት መልክተኛ ቆስቋሾች (agent provocateurs) ሰርገው የገቡበት የሰላም ትግል ይበልጥ ተበክሏል (Contaminated) ሊባል ይችላል። የመንግስት ወሬ አቀባዮች (informers) የሰላም ትግልን አቅምን እና እቅዶችን ለመንግስት ይዘግባሉ። የመንግስት መልክተኛ ቆስቋሾች (agent provocateurs) ግን ሆን ብለው የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ ወይንም እራሳቸው ድንጋይ ይወረውሩ እና ህግ አክባሪው ሰላማዊ ሰልፈኛ እንዲመታ ያደርጋሉ። በሰላም ትግል ኃይል ውስጥ ብጥብጥ ያነሳሳሉ። ለኃይል መልሱ ኃይል ነው የሚል አዝማሚያ በማራመድ የሰላም ትግል መንግስትን በደካማ ጎኖቹ እንዳይገጥመው ያደርጋሉ።
(7ኛ) ፖሊሶች ከከተማው ህዝብ ጋር ተቀላቅለው ስለሚኖሩ ጥሩዎቹን ልናርቃቸው አይገባም። ለምሳሌ ጎረቤቴ የሆነ ፖሊስ እኔ ፍጹም የሰላም ትግል አማኝ መሆኔን እንዲያውቅ አድርጌው ሳለ ድንገት ከፖሊስ ጣቢያ እከሌ ሽብርተኛ ነው እና ይዘህ አምጣ የሚል ትዕዛዝ ቢሰጠው ለአለቃው ሽብርተኛ አለመሆኔን ሊናገር ይችላል።
ለራሳችን ጊዜ ሰጥተን ቁጭ ብለን ብናሰላስል ሌሎች በርካታ ብክለት ሊጋብዙ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማግኘት እና እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ማስላት እንችላለን።
ፍጹም ሰላማዊ እና እንከን የለሽ እንዲሆን ምኞቴ ነው!