(ዘ-ሐበሻ) ቀድሞ በኢትዮጵያ ያሉትን መጽሔቶችን እና ጋዜጦችን እንደሚከስ ያስታወቀው የሕወሓት አስተዳደር ፍትህ ሚ/ር ለጋዜጠኞች የክስ ቻርጆችን ማደል ጀመረ። በዛሬው ዕለት የሎሚ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ እና ድርጅቱ ዳዲስሞስ ኢንተርቴይመንትና የፕሬስ ሥራዎች ኃ/የተ/የግል ማህበር የክስ ቻርጅ እንደደረሰው ለዘ-ሐበሻ የመጣው መረጃ አመለከተ።
በተመሳሳይ እንደሚከሰሱ የተነገራቸው የአዲስ ጉዳይ ጋዜጠኞች ሃገር ጥለው ለመሰደድ የበቁ መሆኑን ዘ-ሐበሻ በትናንትናው ዕለት መዘገቧ ይታወሳል።
በሎሚ መጽሔት አዘጋጅ ላይ የሕወሓት አስተዳደር ፍትህ ሚ/ር ያቀረበው ክስ “ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ወንጀሉና ወንጀሉ የሚሰጠውን ውጤት በመቀበል መንግስት የሚለወጠው ህገ መንግስታዊ በሆነ መርህ በምርጫ ሆኖ እያለ ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ በአመጽ ሥርዓቱን ለመጣል” የሚል ሲሆን ለክስ ያበቁት ጽሁፎችም
1ኛ. በሎሚ መጽሄት ቅጽ 3 ቁጥር 109 “በዓለም በጨቋኝነቷ አቻ የማይገኝላት የሚዲያ ምህዳር በኢትዮጵያ” የሚለው
2ኛ. ሰብ አዊ መብት የሚባል በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተረስቷል። የምንገኝበትም ዓለም በመራጮችና የለውጥ ማዕበሎች የሰፈነበት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በቀጣይ ዓመት በሚደረገው የአገራዊ አጠቃላይ ምርጫ በመንተራስ ለበርካታ ዓመታት ከዘለቀ የፍ የጭቆና አገዛዝ ለመላከክ የማይቀረውን የለውጥ ማዕበል ለማምጣት እራሳቸውን ለተጠናከረ ሕዝባዊ ዓመጽ ማደራጀት መጀመራቸው ሊበረታታ የሚገባው ነው” በሚል አረፍተ ነገር፤
3ኛ. በሎሚ ቁጥር 91 ላይ “የአሸባሪነት ፈርጦች” በሚል ር ዕስት ‘ኢህ አዴግም ከማን አንሼ በሚል ስሜት ተቃራኒ ሃሳብ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን ለስልጣኔ/ወንበሬ) ያስገኛል የሚላቸውን ጠንካራ ተቃዋሚዎችን እያደነ በአሸባሪነት ስም ወህኒ ያወርዳቸው ከጀመረ ሰንብቷል በሚል ጽፏል በሚል
4ኛ.”የኢሕአዴግ የሽብርተኝነት መመዘኛ ምንድን ነው?” “ኢህአዴግ” የሕዝብ ተቀባይነት ያገኘ አይመስለውም ሕዝብ የተቀበለውና አምነዋለው የሚለው ሰው ለኢህ አዴግ ጠላት ነው፤ ሽብርተኛ ተብሎ ይከሰሳል በማለት በሽብር ህግ ተከሰው የተቀጡ ተከሳሾች በህዝብ የሚወደዱና ለገዢ ፓርቲ ተቀናቃኝ በመሆናቸው ብቻ በግፍ የተቀጡ ንጹሃን እንደሆኑ የሚያስመስል ጽሑፍ አቅርቧል በሚል 4 ክሶች ቀርበውበታል።