የቀዶ ጥገና በሚሰራበት ወቅት የማደንዘዣ መድሃኒቶች እንደሚሰጡ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም የእነዚህ መድሃኒቶች የአሰራር ምስጢር ምን ይሆን እያልኩ ሁሌ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ለመሆኑ እንዴት ነው ሰው ሰውነቱ በስለት እየተቆራረጠ ምንም እንዳይሰማው ማድረግ የሚቻለው? በመሀል በሽተኛው ቢነቃስ ምንድነው የሚፈጠረው? እባካችሁን እስቲ በእነዚህ መድሃኒቶች ዙሪያ ማብራሪያ ስጡኝ?
ሜሮን ነኝ
ሜሮን የጠየቅሽን ጥያቄ የብዙ አንባቢዎቻችንም ጥያቄ ይመስለናል፡፡ መድሃኒቶቹ በጤናው ዘርፍ በጣም ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱና እያበረከቱም ያሉ ናቸው፡፡ የህክምና አብዮትን የፈጠሩ የእነዚህን ድንቅ የዘመናችን መድሃኒቶችን አሰራር ማወቅ ብዙ ፋይዳ አለው፡፡ እና ስለነዚህ መድሃኒቶች ማወቅ ጠቃሚ በመሆኑ ለአጠቃላይ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ እንደሚከተለው ተዳሷል፡፡
ብዙ አይነት የሰመመን መድሃኒቶች ሲኖሩ በአጠቃላይ ከአሰራራቸው አንፃር በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪያው ለከባድ ቀዶ ህክምና የሚሰጠውና ራስን በማሳት መላ ሰውነትን የሚያደነዝዘው ሲሆን ‹‹ጀነራል አንስቴዥያ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ሌላው ለመለስተኛ ቀዶ ህክምና የሚያገለግለው እና ህክምናው የሚሰጥበትን የአካል ክፍል ብቻ የሚያደነዝዘው ሲሆን ‹‹ሎካል አንስቴዥያ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ይሄኛው ራስን ሙሉ በሙሉ አያስትም፡፡ የምጥ ህመምን ለመቀነስ ከወገብ በታች የሚያደነዝዘው አይነትም(ስፓይናል አንስቴዥያ) ከዚህኛው አይነት መመደብ ይቻላል፡፡
አሰጣጣቸውም በደም ስር ወይም በጡንቻ ስር በመውጋት አሊያም በጋዝ መልክ በአፍንጫ በመሳብ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋነኛው አጠቃላይ ማደንዘዣ በሚሰጥበት ወቅት እንደየሁኔታው መድሃኒቶቹን እርስ በርሳቸው ወይም ከሌላ መድሃኒት ጋር ማጣመር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በተለይ ጡንቻን ዘና በማድረግ ለህክምናው አጋዥ የሆኑ መድሃኒቶች አብረው ይሰጣሉ፡፡
ሰውነታችን በአጠቃላይ በተለይም የነርቭ ስርዓታችን ያልተለመዱና የማይመቹ ወይም ጎኒ የሆኑ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ትንኮሳዎች የሚለይበትና ለዚህም አጸፋዊ የመከላከል እርምጃ የሚወስድበት የራሱ የሆነ ድንቅ ጥበብ አለው፡፡ በምሳሌ እንየው፡፡ የጋለ ምድጃን ድንገት ሳናስበው ብንነካው ፈጣኑ የነርቭ ስርዓታችን ይህ ክስተት አደገኛ መሆኑንና ቶሎ ካልተወገደ ከባድ ቃጠሎና ህመም እንደሚያስከትል ተገንዝቦ በድንገት ከቃጠሎው እጃችንን እንድናርቅ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው ታዲያ በሽርፍራፊ ሰከንዶች መሆኑ ይበልጥ ያስደንቃል፡፡ መልዕክቱ በቅጽበት ቆዳ ላይ ባሉ ህመምን በሚለዩ ህዋሶች ተለይቶ በነርቮች አማካይነት ወደ አንጎል ይደርሳል፡፡ እዚያም ተተርጉሞ ምላሹ ወደ ጡንቻዎችና መገጣጠሚያዎች በሌሎች ነርቮች አማካይነት ተመልሶ ራስን የማዳን አጸፋዊ ተግባር በቅጽበት ያከናውናል፡፡
ውድ ጠያቂያችን ሜሮን የማደንዘዣዎች አሰራርም ይህንን የነርቭ ስርዓት ሂደት መቀነስ፣ መገደብ ወይም ማስወገድ ነው፡፡ ስለሆነም ታካሚው በቀዶ ህክምናው ወቅት ምንም አሳማሚ ስሜቶች ሳይሰማው ዘና እንዲል ያስችለዋል፡፡ ያማ ባይሆን እንኳንስ ‹‹በተቀደሰው ቢላዋ›› መቆረጥ ይቅር እና ጠንከር ያለ ቁንጥጫስ ቢሆን ‹‹ዘራፍ!›› አሰኝቶ ያፈናጥረን የለ፡፡ ዕድሜ ለሰመመኑ እንጂ የህክምና ስታፍ ሁሉ ቡጢና ጡጫ በቀመሰ ነበር- በታካሚው ቅጽበታዊ እርምጃ አማካይነት ማለት ነው፡፡ በዚህ አይነት በጊዜያዊነት ራስን በማሳትና ጡንቻን በማዛል ካልተፈለገ የሰውነት ምላሽ ከመከላከልም በላይ ታካሚውን ካላስፈላጊ ስቃይና ጭንቀት ይታደጋሉ፡፡ ይህ መሰረታዊ የማደንዘዣዎች የአሰራር ሂደት ሲሆን እስካሁንም ብዙ ያልተደረሰባቸው የአሰራር ምስጢሮች እንዳሉት ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ተመራማሪዎችም ምስጢሩን የመፈተሽ ተግባራቸውን አላቆሙም፡፡ ሳይንስ ጥበብና ቴክኖሎጂ ምን መቆሚያ አለውና፡፡
ውድ ሜሮን ስለ ሰመመን መድሃኒቶች ሲወሳ መረሳት የሌለበት ሌላው ጉዳይ መድሃኒቶችን ስለሚሰጡት ባለሙያዎች ነው፡፡ ለዚህ ሙያ በቀጥታ የሰለጠኑ ባለሙያዎች (Anaesthetists) ሲባሉ፤ ሐኪም ሆነው በተጨማሪ በሙያው ስፔሻላይዝ ያደረጉ ከሆኑ (Anaesthetologist) ይባላሉ፡፡ በቀዶ ህክምና ቡድኑ ውስጥ በህክምናው ውጤታማነት በተለይም ማደንዘዣው የታሰበለትን ግብ እንዲመታ ከማስቻል አንፃር የእነዚህ ባለሙያዎች አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነው፡፡
ዋነኛ ተግባራቸውም ከዋናው ቀዶ ህክምና በፊት ይጀምራል፡፡ ይኸውም ከታካሚው፣ አሳካሚዎቹና ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በሽተኛው የሰመመን መድሃኒቱንና ቀዶ ህክምናውን መቋቋም የሚችል ትክክለኛ ዕጩ ስለመሆን አለመሆኑ፤ ይህን አስቸጋሪ የሚያደርጉ ተጓዳኝ በሽታዎች ከፍተኛ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ ደም ማነስ… መኖር አለመኖራቸው የመድሃኒቶች ‹‹አለርጂ›› ስለመኖር አለመኖሩ እንዲሁም ቀድሞ መደረግ ስለሚገባቸው ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች ወዘተ በማጣራት አስፈላጊውን ውሳኔና እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ በቀዶ ህክምናው ወቅትም መድሃኒቶቹን መጥኖ ከመስጠት ባለፈም የበሽታውን ደም ግፊት፣ የልብ ምት፣ የአንጎልና የነርቮች ሁኔታና ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀ መቆጣጠሪያ መሳሪያ አማካኝነት ይከታተላሉ፡፡ ጊዜአዊ የመተንፈሻ ቱቦ ማስገባትና በመጨረሻም ማስወጣትም ሌላው ተግባራቸው ነው፡፡ በመጨረሻም ታካሚው ሙሉ በሙሉ ከማደንዘዣው ተፅዕኖ መላቀቁንና መንቃቱን በማረጋገጥ ተግባራቸውን ያገባድዳሉ፡፡
በነገራችን ላይ የግድ መውሰድ ካለባቸው መድሃኒቶች በስተቀር ከባድ ቀዶ ህክምና የሚደረግለት በሽተኛ ቢያንስ ከህክምናው በፊት ከ6-12 ሰዓታት ምንም አይነት ምግብም ፈሳሽ መጠጥም መውሰድ አይፈቀድለትም፡፡
የማደንዘዣ መድሃኒቶችና አንፃራዊ ጉዳታቸው
የማደንዘዣ መድሃኒቶችም እንደማንኛውም መድሃኒት አንፃራዊ የጎን ጉዳት አላቸው፡፡ ጉዳቶቹም ከቀላል ጀምሮ ህይወትን ሊያሳጣ እስከሚችል ከባድ ጉዳት ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ከባድ አለርጂክ ሪያክሽን፡፡ ከበድ ያሉት ችግሮች ያልተለመዱና ከስንት አንዴ የሚከሰቱ ሲሆኑ ብዙዎቹ በቅድመ ጥንቃቄና ክትትል ሊወገዱ ይችላሉ፡፡ ዋነኞቹ የጎን ጉዳቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ማቅለሽለሽ፣ ማንቀጥቀጥ፣ የጉሮሮ ቁስለትና ህመም፣ የነርቭ መደንዘዝ፣ ቶሎ አለመንቃት… የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለምሳ በምሉ በመድሃኒቶቹ ሳቢያ የሚከሰት ሞት ከ200 ሺ ሰዎች በአንዱ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ግን ደም ግፊት ወይም ልብ ድካም የመሳሰሉ ተጓዳኝ በሽታዎች ባለባቸው ታካሚዎች ላይ የሞት አደጋው ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ከፍ ሊል ይችላል፡፡
ሌላው አልፎ አልፎ ሊከሰት የሚችለው ችግር በሰመመን ውስጥ ሆነውም የህመም ስሜት መሰማቱ ነው፡፡ በዚህ አይነት የተወሰኑ ታካሚዎች ላላስፈላጊ ህመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ በቅርቡ ቢቢሲ ያወጣው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ፀረ-ህመም መድሃኒቶችን በመጠቀምና በሌሎችም ቅድመ ህክምናዎች (premediatations) እንዲህ አይነቱን ህመም መቀነስ ወይም ማስወገድ ይቻላል፡፡ የመስኩ ተመራማሪዎችም ለእንዲህ አይነቱ ህመም መንስኤና መፍትሄ ፍለጋ በመትጋት ላይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ህክም ከህመምና ከስቃይ የፀዳ መሆን ስላለበት፡፡
ውድ ጠያቂያችን ሌላው ይበልጥ አስገራሚውና አሳሳቢው ጉዳይ በማደንዘዣ ውስጥም ሆኖ ንቁ መሆን (Anesthesia awareness) ነው፡፡ ይህ ያልተለመደ ቢሆንም ሁኔታው አስፈሪና አሳሳቢ ነው፡፡
በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 65 ላይ ታትሞ የወጣ።