ዕለቱ በዓለም ዋንጫ ታሪክ አንዲት ሃያል ሀገር ብቅ ያለችበት ነበር፡፡ የ‹‹በርን ተአምር›› በመባል የሚታወቀው ጨዋታ በተከናወነበት በዚያን ቀን ገና በማለዳ ዶፍ ጥሎ ነበር፡፡ እንዲያውም በዚያን ወቅት የነበሩ ጀርመናውያን እስካሁንም ዝናባማ ዕለትን የሚጠሩት ‹‹የፍሪትዝ ዋልተር የአየር ንብረት›› በማለት ነው፡፡ ዋልተር በዓለም ዋንጫው የተሳተፈው የመጀመሪያው የምዕራብ ጀርመን ቡድን አምበል ነበር፡፡ በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ሀንጋሪን ሲገጥሙ ቡድኑን እየመራ ወደ ሜዳ የገባውም እርሱ ነው፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ስዊዘርላንድ ውስጥ በምድብ ማጣሪያው ሲገናኙ ሃንጋሪ ስምንት ጎሎችን አስቆጥራለች፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ ገና 10 ደቂቃዎች እንኳን በቅጡ ሳይደፍኑ የፍራንክ ፑሽካሽ ቡድን 2-0 እየመራ ነበር፡፡ ሆኖም ፑሽካሽ በጨዋታው መሰለፍ አግባብ አልነበረም፡፡ በዕለቱ ከከፍተኛ የቁርጭምጭሚት ህመም ጋር እየታገለ ነበር፡፡ ሜዳ ውስጥ እንዲገኝ የተፈለገው በነበረው ስም ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ጀርመን ትሰለጥን የነበረው በሴፕ ኸርበርገር ሲሆን ሰውየውን በእግርኳሱ ዓለም ዝነኛ ያደረጋቸው እግርኳስን የሚገልፁበት መንገድ ነበር፡፡ ‹‹ኳስ ድቡልቡል ናት፡፡ ጨዋታው የሚፈጀው 90 ደቂቃ ነው፡፡ ሌላው ነገር በሙሉ የንድፈ ሃሳብ ጋጋታ ነው›› የእርሳቸው ቡድን ተጨዋቾችን እና ቡድኖችን በዝና ብቻ የሚያከብር አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት የሃንጋሪን የአማካይ ክፍል ገዝግዘው ጣሉት፡፡
ጨዋታው የተጠናቀቀው በሚያስደንቅ ገለፃ ሲሆን ከሀገሪቱ ማንነት ጋር እስከ መቆራኘት በደረሰውና በእንግሊዝ ኬኔት ዎልስቴንሆልም ‹‹በሜዳ ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ሰዎች ጨዋታው የተጠናቀቀ ይመስላቸዋል›› በማለት ከገለፀው ጋር በሚመሳሰል መልኩ ነበር፡፡ በወቅቱ ለጀርመን ራዲዮ ይዘግብ የነበረው ኽርበርት ዚመርማን ስርጭቱን የጀመረው ጀርመን የሚቆጠሩባትን ጎሎች ብዛት እንደምንም ልትቀንስ ትችላለች በሚል ተስፋ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ‹‹ጀርመን 3-2 እየመራች ነው፡፡ ንክ አልያም እብድ ልትሉኝ ትችላላችሁ›› ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፡፡ ዋልተርም በዚያ ዝናብ መሀል የጂሊዬ ሪሜን ዋንጫ ተረከበ፡፡
ከበርን ተአምር በኋላ በተከተሉት 60 ዓመታት የጀርመን ብሔራዊ ቡድን 10 ጊዜ ያህል ለግማሽ ፍፃሜ ደርሷል፡፡ ስድስት ጊዜ ያህል ደግሞ በፍፃሜ የመጫወት ዕድል አግኝቷል፡፡ በአንፃሩ እንግሊዝ የእግርኳስ ማህበሩ የውጪ ሀገር ተጨዋቾች የበላይነት የሚታይበትን የፕሪሚየር ሊግ መዋቅር በማፅደቅ ራስን ከማጥፋት ጋር የሚወዳደር ድርጊት ከመፈፀሙ በፊት ከጀርመን እጅግ የላቀ አማራጭ ነበራት፡፡ ሁለት ጊዜ ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰች ሲሆን አንድ ጊዜ ደግሞ ለዋንጫ ተጫውታለች፡፡ በ1992 ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ ግን እንዲህ ያለውን ስኬት ማስመዝገብ አልቻለችም፡፡
ጀርመን በዓለም ዋንጫው ለምን የበላይ እንደሆነች የሚያትቱ በተደጋጋሚ የሚነገሩ መላ ምቶች አሉ፡፡ የተወሰኑት እውነት ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል በመለያ ምት የተሻለች ሆና መገኘቷ አንዱ ነው፡፡ አስገራሚው ነገር የእንግሊዝ ክለቦች ከጀርመን ክለቦች የተሻለ ፍፁም ቅጣት ምትን የመጠቀም ሪከርድ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ መለያ ምቶችን ወደ ጎል የመቀየር ንፃሪያቸውን ለአብነት ብናወዳድር እንግሊዞቹ 82 በመቶ ሲሆን የጀርመን ክለቦች 75 በመቶ ነው፡፡ በብሔራዊ ቡድን ግን ታሪኩ የተለየ ነው፡፡ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ፍፁም ቅጣት ምቶችን የመጠቀም ንፃሬ 93 በመቶ ሲሆን የእንግሊዝ ግን 66 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ብዙዎች የ1954ቱ ድል ከ‹‹ስፓይዝ መንፈስ›› ጋር ያቆራኙታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የምዕራብ ጀርመን ቡድን ከትሞ የነበረው በሐይቅ አጠገብ በምትገኘው ትንሿ ከተማ ስፓይዝ በመሆኑ ነው፡፡ በቤሎ ሆሪዞንቴ ብራዚልን አጓጉል አድርጎ ባሸነፈው ቡድን ውስጥ የነበሩት ከግማሽ በላይ ተጨዋቾች በ2009 ከ21 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫን ያሸነፈው ቡድን አባል የነበሩ ናቸው፡፡ የቡድኑ መንፈስ ጥንካሬም በግልፅ የሚታይ ነው፡፡
ምዕራብ ጀርመን በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ በፍፃሜው ሀንጋሪን ከመግጠሟ በፊት አሰልጣኝ ኸርበርገር ተጨዋቾቻቸው ሃንጋሪ እንግሊዝን በዌንብሌይ 6-3 የደቆሰችበትን ጨዋታ እንዲመለከቱ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ እንዲህ ያለው ነገር ብዙም አልተመደበም ነበር፡፡ ነገር ግን አሰልጣኙ ተጨዋቾቹ ፊልሙን ሁለት ጊዜ እንዲመለከቱ አደረጉ፡፡ መድገሙ ያስፈለገው የማይሸነፈው የሚመስለው ቡድን የነበሩበትን ደካማ ጎኖች ለተጨዋቾቻቸው ለማሳየት ነበር፡፡ ለአዳዲስ መስራች አዲ ዳይዝለር ቅርበት ስለነበራቸውም ተጨዋቾቻቸው ተነቃይ የታኬታ ጥርስ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ አመቻቹ፡፡ ይህን ያደረጉት ብዙውን ጊዜ በበርን ዝናብ ይጥል ስለነበር ምናልባት የጨዋታው ዕለት ከዘነበ ተጨዋቾቻቸው እያንሸራተታቸው እንዳይወድቁ ረጃጅም ጥርሶችን ለመጠቀም በማሰብ ነበር፡፡ የፈሩትም አልቀረ በጨዋታው ዕለት ዶፍ ጣለ፡፡
አንድሪያ ፒርሎ ‹‹ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ይኖራሉ፡፡ አንዱ በሰሜን ሌላኛው በደቡብ›› ሲል የሰጠውን አስተያየት አስቀድሞ በማመን ዝግጅት ያደረገች ብቸኛ ሀገር ጀርመን ነች፡፡ ጣልያን እንደሌሎቹ ሀገሮች ሁሉ የከተመችው በደቡባዊ ብራዚል ነበር፡፡ በማንጋራቺባ የሚገኘው ጣልያን ያረፈችበት ካምፕ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን ካደረገችበት ማናኡስ በ1,770 ማይል፣ ሁለተኛ ጨዋታዋን ካደረገችበት ሬሲፌ 1-165 ማይልስ እንዲሁም የመጨረሻ ጨዋታዋን ካከናወነችበት ናታል 1,220 ማይልስ ርቀት ላይ ነበር፡፡ ጣልያናውያን ምንም አይነት ዝግጅት ሳያደርጉ በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል ስላለው ሙቀት እና እርጥብ አየር ሲያማርሩ ከረሙ፡፡ ትልልቅ ከሚባሉ ቡድኖች ማረፊያዋን በሰሜናዊው ክፍል ያደረገች ብቸኛ ሀገር ጀርመን ነበረች፡፡ ሁሉንም የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ያከናወነችውም በዚያ ነው፡፡ ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቷ የተነሳም 14 ህንፃዎችን፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የአካል ብቃት ማዕከል እና ሜዳዎችን ዬዘ ግዙፍ የልምምድ ማዕከል ያስገነባችው ቀደም ብላ ነው፡፡ እንደውም በዓለም ዋንጫው ከተሰሩ ግንባታዎች ሁሉ በትክክለኛ ጊዜው የተጠናቀቀው እርሱ ነው፡፡
በ1974 ምዕራብ ጀርመን ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫውን ስትወስድ ቡድኑ ያረፈው ከሃንቡርግ ወጣ ብሎ በሚገኝ ወህኒ ቤት በሚመስል ካምፕ ውስጥ ነበረ፡፡ ‹‹የነበረብን ጫና እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎቹ ተጨዋቾች ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ቤታቸው ለመሄድ ተነሳስተው ነበር፡፡ ግፊቱ የዚህን ያህል ነበር›› በማለት በርቲ ቮግት መለስ ብሎ ሁኔታውን ያስታውሳል፡፡ ‹‹በአንድ ክፍል ውስጥ የምንተኛው ሶስት ሆነን ነበር፡፡ በመተላለፊያዎች ላይ ምንም አይነት ስልክ ያልነበረ ሲሆን ፖሊሶች ደግሞ በየቦታው ነበሩ›› ሲል ያክላል፡፡ ሆኖም ፍራዝ ቤከንባወር ቡድኑን በማደራጀት እየመራ ለዓለም ዋንጫ ድል አበቃው፡፡ ከ28 ዓመት በኋላ ደግሞ ማይክል ባላክ ከዓመት በፊት በእንግሊዝ ሙኒክ ላይ 5-1 የተሸነፈውን እና የተገደበ አቅም ያለውን ቡድን ለ2002ቱ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ አደረሰው፡፡ ‹‹ባላክ ባይጎዳ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለው ነገር አይታወቅም ነበር›› በማለት በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የነበረው ሩዲ ቮለር ተናግሯል፡፡ ባላክ ቢኖርም ጀርመን ልትሸነፍ ትችል ነበር፡፡ ነገር ግን የእርሱ አለመኖር ምንም ዕድል እንዳይኖራት አደረገ፡፡
ጀርመን ከ1974ቱ የዓለም ዋንጫ በቂ ትምህርት አግኝታለች፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በተከናወነው የደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ ዮአኪም ሎው ወጣት ተጨዋቾችን የያዘውን ቡድን ይዘው ኔልሰን ማንዴላ ታስረውበት የነበረውን ሮቢን የሚባል ደሴት እና ሌሎች የመዝናኛ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ያደርጉ ነበር፡፡ እጅግ ዝነኛ የሆነው ጀርመናዊ ግብ ጠባቂ ቶኒ ሹማከር በፃፈው አውቶባዮግራፊ ላይ በስፔን ተዘጋጅቶ በነበረው የ1982 የዓለም ዋንጫ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ የነበረውን የቁማር እና የወሲብ ቅሌት አስፍሯል፡፡ ‹‹የቡድኑ አባላት ወደ ልምምድ የሚመጡት እንደ እርጥብ ጨርቅ ዛል ብለው ነበር›› በማለት አጋጣሚውን በአጭሩ ገልፆታል፡፡ በዚያ የዓለም ዋንጫ ተከስቶ የነበረው ነገር ለበርካታ ትውልድ የዘለቀ የአመለካከት ልዩነት ፈጥሯል፡፡
ይህንን የተበላሸ ገፅታ ለመለወጥ በመጀመሪያ የርገን ክሊንስማን በኋላ ላ ደግሞ የዮአኪም ሎውን ጥረት ጠይቋል፡፡ ወደ ቡድኑ ወጣት እና በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ (በእግርኳስ እና በቀለም ትምህርት) ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ አጎረፉ፡፡ በአንድ ንክኪ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት በቡድኑ ላይ አሰረፀ፡፡ አብዮቱ የተጀመረበት የ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት ዋንጫውን የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው የሚያምኑ ጀርመናውያን ከአጠቃላይ የህዝቡ ብዛት የነበራቸው ድርሻ 3 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ቡድኑ ግን እስከ ግማሽ ፍፃሜ መጓዝ ቻለ፡፡ ክሊንስማን ለቡድኑ የስነ ልቦና ባለሞያዎችን እና የተለያዩ ኤክስፐርቶችን መቅጠሩን ቤከንባወርና እና የሀገሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጋዜጣ ‹ቢልድ› ተሳለቁበት፡፡ ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር የማያልፍ ከሆነ ኦቶማር ሂትዝፊልድ የአሰልጣኝነት ስራውን መረከብ እንዳለባቸውም ተናገሩ፡፡ ጀርመን ለደረጃ የተደረገውን ጨዋታ ፖረቱጋልን በማሸነፍ ስታጠናቅቅ በብራንደን በርግ ጌት በርካቶች ደስታቸውን በታላቅ ስሜት ገልፀዋል፡፡ ያልተጠበቀ ስለነበር የድል ያህል ተቆጠረ፡፡ ነገር ግን መሰረቱ የተጣለው ከ60 ዓመት በፊት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ቡድኑ በድጋሚ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡