Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የባለሥልጣኑ የዳኝነት ችሎት በሦስት መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሰጠ

$
0
0

-ጂኦቴል የሞባይል መገጣጠሚያ ሁለት ሞዴሎችን እንዳያመርት ታገደ

-ሊፋን ሞተር ላይ የቀረበው ክስ ውድቅ ሆነ

k2.items.cache.6956c787ef5259e79426818930533811_Lnsp_589ቴክኖ ሞባይል መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሁለት የሞባይል ምርቶቹን አስመስሎ ሠርቶብኛል ያለውን ጂኦቴል የሞባይል ፋብሪካን ያልተገባ የንግድ ውድድር አድርጓል በሚል በመሠረተበት ክስ፣ ተመሳስለው የተሠሩ ናቸው የተባሉት ሁለቱ የጂኦቴል ሞባይል ቀፎዎች ምርት እንዲቆም ውሳኔ ተላለፈ፡፡

ይህንን ውሳኔ የወሰነው የሁለቱን ወገኖች ክርክር ሲመለከት የነበረው የኢትዮጵያ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ችሎት ነው፡፡ ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. የተላለፈው የፍርድ ውሳኔ መዝገብ እንደሚያመለክተው፣ ተመሳስለው የተሠሩ ናቸው የተባሉትና ከዚህ በኋላ እንዳይመረቱ ውሳኔ የተላለፈባቸው የጂኦቴል የሞባይል ቀፎ ምርቶች G340 እና G341 የተባሉት ናቸው፡፡

የክርክር መዝገቡ እንደሚያመለክተው ቴክኖ ሞባይል ጥር 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ባቀረበው የተሻሻለ የክስ አቤቱታ ከሳሽ ቴክኖ በሚል የንግድ ምልክት ከሚያመርታቸው የሞባይል ቀፎዎች ሞዴሎች 340 እና 341 የተባሉ ምርቶች እንደሚገኙበት ይጠቅሳል፡፡ ጂኦቴል ጤናማ በሆነ የንግድ ውድድር ተግባራትን ይዞ መወዳደር ሲገባው፣ G340 እና G341 የሚባሉ የሞባይል ቀፎዎቹን ማሸጊያቸውና የስልኩን የመሸፈኛ አካል (Body) ገጽታ (Layout) በከፍተኛ ደረጃ አስመስሎ ለገበያ አቅርቧል በሚል የቀረበ ክስ ነው፡፡

ቴክኖ ሞባይል ጨምሮ እንደገለጸው፣ ለሦስት ዓመታት ያህል ከሳሽ (የቴክኖ ሞባይል) የገነባውን መልካም ዝና ሀቀኛ ባልሆነና አሳሳች በሆነ መልኩ የስልኮቹ ቀፎ ታስቦበት ከከሳሽ ምርት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሆነው የተመረቱ ናቸው፡፡ ይህም ስለሆነ የቴክኖ ሞባይል ደንበኞች የከሳሽን ምርት የሸመቱ እየመሰላቸው የተከሳሽን (ጂኦቴል) ምርቶች በስህተት በመሸመት ላይ ስለሆኑ በሸማች ላይ መደናገር መፍጠሩንም የክስ መዝገቡ ያመለክታል፡፡ በዚህ ክስ መሠረትም ቴክኖ ሞባይል የዳኝነት ችሎቱን ተከሳሽ ተገቢ ያልሆነውን ድርጊት እንዲያቆምለት ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም በጂኦቴል የተመረቱት ሁለቱ ሞዴሎች ተሰብስበው እንዲወገዱ፣ በተፈጠረው መደናገር ሸማቹ ግልጽ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ ተከሳሽ በጋዜጣና በቴሌቪዥን ይቅርታ እንዲጠይቅ ይወሰንልኝ ብሎ ዳኝነት ጠይቋል፡፡ የጉዳት ካሳና ወጪ ኪሳራ እንዲተካለትም አመልክቷል፡፡

ጂኦቴል ለክሱ በሰጠው ምላሽ ሞዴሎቹን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የብቃት ማረጋገጫ በመቀበል እያመረታቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ አያይዞም የጂኦቴል ሞባይሎች እየተመረጡ በመምጣታቸው ለከሳሽ (ቴክኖ ሞባይል) እያሳሰበው በመምጣቱ እንጂ ተከሳሽ የተጠቀመው “GEOTEL” የሚል ስለሆነ ከከሳሽ ምርቶች ጋር የተፈጠረ የመደናገር ችግር የሌለ መሆኑንና ምርቶቹን ለመለየት በግልጽ መለያውን እየጻፈ መገኘቱን ጠቅሷል፡፡ ስለዚህ የተፈጠረ መመሳሰል ባለመኖሩ ክሱ ውድቅ እንዲደረግለት አመልክቷል፡፡ ግራ ቀኙን የተመለከተው የዳኝነት ችሎት ተመሳስለው ተመረቱ የተባሉት ምርቶች እንዲቆሙ የተጠየቀው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አግኝቸዋለሁ ብሏል፡፡ ነገር ግን G340 እና G341 ሞዴል የሞባይል ቀፎዎች ተሰብስበው እንዲወገዱ ከሳሽ የጠየቁትን ዳኝነት በተመለከተ የአገራችን ኢኮኖሚ እንዳይባክን ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚኖርበትና ተከሳሽም የሞባይል ቀፎዎች ማምረቱን እንዲያቆም ከተደረገ ውጤቱ ተመሳሳይነት ስለሚኖረው አልተቀበለውም፡፡

በሌላ በኩልም ከሳሽ የጉዳት ካሳ እንዲከፈል የጠየቀ ቢሆንም፣ የደረሰበት ጉዳትና የጉዳት መጠኑ በግልጽ ያልቀረበ ስለሆነ የዳኝነት ችሎቱ አልፎታል፡፡ ሆኖም ተከሳሽ በፈጸሙት ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተግባር በአዋጅ ቁጥር 873/2006 አንቀጽ 43/3 መሠረት አስተዳደራዊ ቅጣት መጣል ያለበት በመሆኑ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ መሠረት የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው የዳኝነት ችሎት በከሳሽ T340 እና T341 እንዲሁም የG340 እና G341 የሞባይል ቀፎዎች ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተግባር ነው የሚያሰኝ መመሳሰል ሁኔታ አለው ወይ? ተገቢ ካልሆነ ከሳሽ የሚገባው ዳኝነት ምንድነው? የሚሉ ጭብጦችን በመያዝ መዝገቡን መርምሮ ተከሳሽ G340 እና G341 የሚባሉ ሞዴል የሞባይል ስልኮች ማምረት እንዲያቆም ወስኗል፡፡ ከሳሽ የተመረቱት G340 እና G341 ሞዴል የሞባይል ስልክ ቀፎዎች እንዲወገዱ፣ የጉዳት ካሳ ክፍያና ተከሳሽ በሚዲያ ይቅርታ እንዲጠይቅ ያቀረቡትን ዳኝነት ግን ችሎቱ አልተቀበለውም፡፡

ተከሳሽ ተመሳሳይ ሞዴል በማምረት በሸማቾች ላይ መደናገር ሊያስከትል በሚችል ሁኔታ መገኘታቸው አግባብነት ስለሌለው G340 እና G341 የሞባይል ቀፎዎች ማምረት ከጀመሩበት ወቅት ጀምሮ ውሳኔ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ባሉት ወራት ክርክር ከተነሳባቸው ሞባይሎች ሽያጭ ተሰልቶ አምስት በመቶ ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርግም ቅጣት ጥሏል፡፡ ወጪና ኪሳራን በተመለከተ ከሳሽ ዝርዝር አቅርበው የመጠየቅ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን በመግለጽ መዝገቡን ዘግቷል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የዳኝነት ችሎት ከዚህ መዝገብ በተጨማሪ በሁለት መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አንደኛው አቶ ዘሪሁን አያሌው የተባሉ የግል ተበዳይ የሊፋን ተሽከርካሪዎች በመገጣጠም ለገበያ የሚያቀርበውን ያንግፋን ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያን የከሰሱበት መዝገብ ይገኛል፡፡ የክሱ ጭብጥ እንደሚያመለክተው ከሳሽ ከተከሳሽ ሊፋን 620 አውቶማርክ የቤት መኪና እ.ኤ.አ ኖቬምበር 20 ቀን 2010 በተደረገ ሽያጭ ውል 430 ሺሕ ብር ክፍያ ፈጽመው ቢረከቡም መኪናው የአሠራር ችግር አለበት የሚል ነው፡፡ መኪናውን ከገዙበት ጊዜ ጀምሮ ለግማሽ ሰዓት ፀሐይ ሲነካው ይጮሃል፣ በዚህም ምክንያት መሽከርከር ያቆማል፣ ለማንቀሳቀስ መቀዝቀዝ ያስፈልገዋል፣ ከዚህም ሌላ መኪናው ወደፊት እየተነዳ ወደኋላ እንደሚሽከረከር የሚያሳዩ የኋላ ማርሽ መብራቶች ይበራሉ፡፡ መኪና ውስጥ ያሉ ወደኋላ እንደሚንቀሳቀስ ያሳያሉ፡፡

እነዚህ ችግሮች እየተባባሱ በመሄዳቸው ጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ተከሳሽ ጋራዥ መኪናው ተወስዶ ተሠርቷል በሚል ሲረከቡ፣ የመኪናው የኋላ ዕቃ መጫኛ ላይ ድሮ ያልነበረ የኋላ ካሜራ ተገጥሟል፣ ይህ የመኪናውን መልክ አበላሽቷል የሚል እንደነበር የክስ መዝገቡ ያመለክታል፡፡ ለዚህ ክስ የተጠየቀውም ዳኝነት ያንግፋን ሞተርስ የመኪናውን ዋጋ 430 ሺሕ ብር እንዲመልስ፣ መኪናው ባጋጠመው እክል ችግር ስለገጠመኝ በዝቅተኛ የቀን ቤት መኪና ወጪ 250 ብር ታስቦ 273 ሺሕ ብር እንዲከፈል የሚል የዳኝነት ተጠይቆበታል፡፡

ያንግፋን ሞተርስ ለክሱ መቃወሚያና አማራጭ መልስ የሰጠ ሲሆን፣ በዚህም መቃወሚያና ምላሹ ውስጥ የአዋጅ ቁጥር 685/2002 ተፈጻሚነት ለኅብረተሰቡ ወሳኝ በሆነ ዕቃዎች እንጂ መኪናን በተመለከተ ተፈጻሚ አይደለም፣ በአዋጁ አንቀጽ 28/2 መሠረት በዕቃው ላይ የተገኘውን ጉድለት ዕቃው ከተገዛ 15 ቀን ውስጥ እንዲለውጥ ወይም እንዲመለስ መጠየቅ ነበረባቸው የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ከሳሽ በሽያጭ ውሉ አንቀጽ 4.3 ላይ በመኪናው ላይ ስለደረሰው ችግር በጽሑፍ ማሳወቅ እንዳለበት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከሳሽ ይህንን አለማድረጋቸውንና ተከሳሽ ለከሳሽ የሰጠው ዋስትና መኪናውን ከተረከበ 24 ሰዓት ያለፈ በመሆኑ ውድቅ ነው ይላል፡፡

በከሳሽ የተጠየቀው ዳኝነት ሁሉ ውድቅ እንዲሆንለት የጠየቀው ያንግፋን ሞተርስ ተከሳሽ ተመሳሳይ መኪኖችን ለሌሎች ሸማቾች እንዳይሸጥ ይወሰን በሚል ያቀረበውን ዳኝነት ጥያቄ በመቃወም፣ ሌሎች ገዢዎች መኪናውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት ስለሆነ ከሳሽ መኪኖቹን እንዳይሸጡ ዳኝነት መጠየቅ አይችሉም ብሎ ተከራክሯል፡፡ በሁለቱም ወገኖች ምስክሮችንና መረጃዎችን አቅርበው ተከራክረዋል፡፡ የዳኝነት ችሎቱም ግራ ቀኙን በመመልከት ከሳሽ መኪናው የተገዛበት ሒሳብ ከሕጋዊ ወለድ ጋር በመኪና ጉዳት መነሻ በቀን ላወጣ የምችለው ወጪ በሦስት ዓመት ተሰልቶ ይከፈለኝ፣ ተከሳሽ ተመሳሳይ መኪና እንዳይሸጥ ይታገድ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ተገቢነት ያለው ሆኖ አላገኘሁትም በሚል ወስኗል፡፡ ይኸውም መኪናው ከተገዛበት ጊዜ ጀምሮ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት እየሰጠ በመቆየቱ መሆኑን አብራርቶ፣ የካሳ ጥያቄም ቢሆን ከሳሽ ያላዩትን ወጪ መጠየቃቸው ተገቢ መስሎ አልታየንም ብሏል፡፡

የከሳሽ ክስ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 20 ሥር በንግድ ዕቃዎች ላይ ስለሚገኙ ጉድለቶች በብር የማይሸፈን በመሆኑ፣ ከሳሽ ያቀረቡትን ክስ ውድቅ አድርጓል በሚል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኘም በአዋጅ ቁጥር 8/3/2006 አንቀጽ 39/1 መሠረት በ30 ቀናት ለፌዴራል ይግባኝ ሰሚ አስተዳደር ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ የሚችል መሆኑን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሽ ላወጣው ወጪና ኪሳራ ከሳሽን የመጠየቅ መብቱን በፌዴራል ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 463 መሠረት ተጠብቋል በማለት ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል፡፡

የዳኝነት ችሎቱ በዕለቱ ውሳኔ የሰጠበት ሦስተኛው ጉዳይ ደግሞ በአንድ የግል ተበዳይ የቀረበ ክስ ነው፡፡ የክስ መዝገቡ የግል ተበዳይ ተማሪ ተመስገን ሸዋዬ ከሚክስ ማክስ ኤሌክትሮኒክስና ኮምፒዩተር ማዕከል አዲስና ጥቅም ላይ ያልዋለ ቶሺባ ላፕቶፕ በ14,600 ብር ገዝተው ሁለት ወር ሳያገለግል ሙሉ በሙሉ ተበላሽቶብኛል በሚል የመሠረቱት ክስ ነው አዲስ ኮምፒዩተር ሻጭ ነኝ ከሚለው ድርጅት የገዙት ላፕቶፕ በጀርባው ላይ “Factory Reconditioned” የሚል ዓርማ ያለው ነው፡፡ ሆኖም ተከሳሽ እንደሚለው አገልግሎት ላይ ያልዋለ ሁለተኛ ምርት ነው በማለት ሁለተኛ ምርት በመሸጥ አሳሳች ተግባር በመፈጸም ተገቢ ያልሆነ ትርፍና ጥቅም አግኝቷል በሚል የቀረበ ክስ ነው፡፡ ስለዚህ ተከሳሽ በገዛሁት ኮምፒዩተር ምትክ አዲስና አገልግሎት ላይ ያልዋለ ኮምፒዩተር ይቀይርልኝ ወይንም ኮምፒዩተሩን መልሼ የከፈልኩት ዋጋ ይመለስልኝ ብለው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ ተከሳሽም ለክሱ በሰጡት ምላሽ ኮምፒዩተሩ ከሳሽ የፈለጉት ፕሮግራም የተጫነበትና “Factory Reconditioned” መሆኑን በመግለጽ የሸጠላቸው መሆኑንና ምርቱ ሁለተኛ ምርት ያለመሆኑን ገልጿል፡፡ ኮምፒዩተሩን ይዘው በመጡ ጊዜ በባለሙያዎች የተረጋገጠው ብልሽቱ ያጋጠመው በአጠቃቀም ችግር መሆኑን የከሳሽ ምላሽ ያስረዳል፡፡ ከዚህም ሌላ ከሳሽ አስቀድመው በሁለት የተለያዩ ቦታዎች ኮምፒዩተሩን አስፈትተው እንደነበር መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ስለዚህ ክሱ ውድቅ ይሁንልኝ ብሎ ምስክሮችን በማቅረብ አስደምጠዋል፡፡ ችሎቱም ግራና ቀኝ የቀረቡትን መከራከሪያዎች በማየትና እንዲሁም “Factory Reconditioned” ማለት ከአዲስ ኮምፒዩተር ኦርጅናል ምርት ጋር ተቀራራቢነት ኖሮት እንደ አዲስ የተሠራ እንጂ፣ ሁለተኛ ምርት ያለመሆኑን በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ በጽሑፍና በአካል ማብራሪያ የተሰጠበት በመሆኑ፣ የከሳሽ ክስ የሕግና ማስረጃ ድጋፍ ስለሌለው ውድቅ ነው በማለት ውሳኔ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል፡፡ እነዚህ ሦስት ጉዳዮች የባለሥልጣኑ የዳኝነት ችሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ውሳኔ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡

Source: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>