መድረክ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ኢሕአዴግ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን እያሰረና እያሰቃየ ያለው በአምባገነናዊ አገዛዝ ለመጠቀል የነበረው ምኞት ሥጋት ውስጥ መውደቁን በመረዳቱ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ኢሕአዴግ እያካሄደ ባለው የእስር ዕርምጃ የመድረክ አባል የሆነው የዓረና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመድረክ ጠቅላላ ጉባዔ አባል የሆኑት አቶ አብርሃ ደስታ ከሚኖሩበትና ከሚሠሩበት መቀሌ ከተማ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ መደረጉን መግለጫው አመልክቷል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የታሰሩት አቶ አብርሃ በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በጓደኞቻቸው እንዲጎበኙ አለመፈቀዱንም መግለጫው ያትታል፡፡
ከአቶ አብርሃ ደስታ በተጨማሪ የአንድነት አመራር አባላት የሆኑትን የአቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ እንደዚሁም የሰማያዊ አመራር አባል የሆኑት የአቶ የሺዋስ አሰፋን እስርም መድረክ ተቃውሟል፡፡
ገዥው ፓርቲ ከወሰደው የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት እስር ጋር በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ አባላቱ ለእስር፣ ስቃይና እንግልት መጋለጣቸውንም መድረክ አስታውቋል፡፡ በተለይም በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ አባላቱ ላይ እየደረሰ ያለው እስርና ግፍ እየተስፋፋ መሄዱ፣ አገሪቱ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው አስገንዝቧል፡፡
መድረክ የኢሕአዴግ ዕርምጃ በቀጣይ ዓመት ከሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጠቁሞ፣ ዕርምጃው አስቀድሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና እንቅስቃሴያቸውን ለማዳከም ያለመ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ‹‹ዕርምጃዎቹ የጠቅላይነትና ብቸኛ ገዥ ፓርቲነት ምኞት ነፀብራቆች ናቸው፤›› ያለው መግለጫው፣ የአገሪቱን ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ውይይትን የገፋ ዕርምጃ እንደማይጠቅም አመልክቷል፡፡
ፓርቲው በመጨረሻም ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ የመቃወም ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን በመግፈፍ የሚፈጽማቸውን የማሰርና የማሰቃየት ዕርምጃዎች እንዲያቆምና ሰላማዊ ታጋዮችን በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter