Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በልደታ ለአንድ ንግድ ቤት በካሬ ሜትር 71,770 ብር የመጫረቻ ዋጋ ቀረበ

$
0
0

d90b93ac02750928f7cce1f439c89e76_Lየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ 489 የንግድ ቤቶችን ለመሸጥ አውጥቶት በነበረውና ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በይፋ በተከፈተው ጨረታ፣ በልደታ መልሶ ማልማት ለአንድ ንግድ ቤት

71,770 ብር በካሬ ሜትር ቀረበ፡፡ የንግድ ቤቱ በብሎክ 44 የሚገኝ ሲሆን፣ 44.51 ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡ አጠቃላይ ዋጋውም 3,194,482 ብር በማውጣት ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በልደታ መልሶ ማልማት ከዚህ በፊት በነበረው ጨረታ በአንድ ካሬ ሜትር 56,000 ብር ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህኛው ዙር የተሰጠው 71,770 ብር እስካሁን ከቀረቡት የመጫረቻ ዋጋዎች ከፍተኛው መሆኑን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ለኤጀንሲው ለ10ኛ ጊዜና ለዚህ ዓመት የመጀመሪያው የሆነው የንግድ ቤቶች ሽያጭ ጨረታ በአራት ኪሎ ስፖርት ማዕከል ቅዳሜ ማለዳ ተከፍቷል፡፡ በተከፈተው ጨረታ 489 የንግድ ቤቶችን ለመግዛት በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የጨረታ ሰነዱን ከ7,650 በላይ ግለሰቦችና ድርጅቶች የገዙ ሲሆን፣ የተሳተፉትን ተጫራቾች ቁጥር ለማወቅ የቆጠራ ሥራ ሰኔ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ዕለት እያካሄደ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የተጫራቾችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ጊዜ የወሰደበትን ምክንያት አንድ የኤጀንሲው ኃላፊ ለሪፖርተር፣ ‹‹አንድ ተጫራች አንድ ሰነድ ገዝቶ ሰነዱን በማባዛትና ሲፒኦ በማስያዝ 20 ለሚሆኑ ቤቶች ያስገቡ በመሆናቸው ከተሸጡ ሰነዶች ቁጥር ጋር ሰፊ ልዩነት በመኖሩ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ለሽያጭ የቀረቡት ቤቶቹ በስድስት ክፍላተ ከተሞችና በ12 ሳይቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ ስፋትና ብዛት ያላቸው ናቸው፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ በሁለት ሳይቶች የካ አያት 2 በሚባለው 269፣ በየካ አያት 3 ደግሞ 24 በድምሩ 293 ቤቶች ይገኛሉ፡፡ መንግሥታዊ የሆነው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በየካ አያት 2 ሳይት የሚገኘውንና 57.76 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን በብሎክ 367 ምድር ቤት የሚገኘውን የንግድ ቤት 25,000 ብር በካሬ ሜትር ለመግዛት ዋጋ የመጫረቻ አስገብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ይህንን ሱቅ ለመግዛት ኤጀንሲው ካወጣው የጨረታ መነሻ ዋጋ 6,742 ብር 270 በመቶ ብልጫ ያለው ዋጋ አቅርቧል፡፡

በየካ አያት 2 ከቀረቡት 269 ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ የተሰጠው ይህ ቤት በአጠቃላይ 1,444,000 ብር አውጥቷል፡፡ በዕለቱ በርካታ ተሳታፊዎችን ያስተናገዱት ሳይት የካ አያት 2 እና የካ አያት 3 ሲሆኑ፣ በርካታ ተጫራቾችን አሳትፈዋል፡፡ የሁለቱ ሳይቶች ጨረታ በተናጠል ሙሉ ቀን የፈጀ ከመሆኑም በላይ ዝቅተኛ የቀረበው ዋጋ 6,750 ብር ነበር፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሁለት ሳይቶች ሰሚትና ሰሚት 2 ከእያንዳንዳቸው 51 እና 70 ቤቶች በቅደም ተከተል በጨረታ ሲቀርቡ፣ የተጫራቾችን ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባትና ጊዜ ለመቆጠብ ተብሎ ጨረታው ለብቻው እንዲከፈት ተደርጐ ነበር፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ በድምሩ ከቀረቡ 127 ቤቶች ውስጥ በሰሚት ሥር ከተካተቱት 51 ቤቶች በብሎክ 188 የሚገኘው የቤት ቁጥር 06 ባለ 57.38 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የንግድ ቤት የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ ይህ የንግድ ቤት ከዚህ በፊት ለጨረታ ቀርቦ አሸናፊዎች ግዥ መፈጸም ባለመቻላቸው ድጋሚ ለሽያጭ የቀረበ ነው፡፡ በካሬ ሜትር 8,000 ብር ተሰጥቶበት የነበረ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተጫራቾች ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ በርካታ ተጫራቾች የተለያዩ ዋጋዎችን ቢያስገቡም፣ 33,200 ብር በካሬ ሜትር ከፍተኛው ዋጋ ሆኖ ቀርቧል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 38 ንግድ ቤቶች በአቃቂ ቃሊቲ አምስት፣ በኮልፌ ቀራኒዮ አራትና በልደታ ክፍለ ከተማ 22 ንግድ ቤቶች ለጨረታ ቀርበው በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡ በአጠቃላይ የቤቶቹ ስፋት ድምር ከ26,000 ካሬ ሜትር በላይ ሲሆን፣ ትንሹ 23.4 ካሬ ሜትር ከፍተኛው ደግሞ 98.76 ካሬ ሜትር ነው፡፡ እነዚህ ንግድ ቤቶች በልደታ መልሶ ማልማት ሳይት የሚገኙ ናቸው፡፡

የ10ኛው ዙር የንግድ ቤቶች ሽያጭ ጨረታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጫራቾች የተሳተፉበት ሲሆን፣ የአሸናፊዎች ዝርዝር በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን የኤጀንሲው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ አሸናፊዎች ውጤታቸው በይፋ ከተገለጸበት ቀን አሥር የሥራ ቀናት በኋላ ባሉ 15 የሥራ ቀናት ያሸነፉበትን ዋጋ 50 በመቶ ወይም በሙሉ በመክፈል የሽያጭ ውል እንደሚፈጽሙ ኤጀንሲው አስረድቷል፡፡

ሃምሳ በመቶ የሚከፍሉ አሸናፊዎች ቀሪውን ክፍያ ንግድ ቤቱን በማስያዣነት በመጠቀም፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአምስት ዓመት የሚከፈል የብድር አቅርቦት ተመቻችቶላቸዋል፡፡ እንደ ኤጀንሲው ገለጻ አሸናፊዎች የቤቶቹን የመጨረሻ የፊኒሺንግ ሥራ፣ የበር፣ የመስኮት፣ የመታጠቢያ ቤት፣ የወለልና የኮርኒስ ሥራ በራሳቸው ወጪ ያሠራሉ፡፡

Source: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>