Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የጋዜጠኞችና ጦማሪያን ጊዜ ቀጠሮ በመደበኛ ችሎት እንዲታይ ታዘዘ

$
0
0


-
ጉዳዩ በግልጽ ችሎት እየታየ ነው ቢባልም ታዳሚዎች ግን መግባት አልቻሉም

zone 9999በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው ከታሠሩ ሁለት ወራት የሆናቸው የጋዜጠኞችና ጦማሪያን ጊዜ ቀጠሮ ቅዳሜና እሑድ መታየቱ ቀርቶ፣ በመደበኛ የችሎት ጊዜ እንዲታይ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

የተጠርጣሪዎቹ የጊዜ ቀጠሮ በመደበኛ ችሎት እንዲታይ የታዘዘው፣ የሦስቱ ጦማሪያን ማኅሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉና አቤል ዋበላ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲቀርቡ ነው፡፡

ሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረውን የተጠርጣሪ ጦማሪያን ጉዳይ ለመከታተል በአራዳ ምድብ ችሎት የተገኙ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ የተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እንደወትሮው ሁሉ በርከት ያሉ ነበሩ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከመምጣታቸው በፊት ዳኛዋ በችሎት የተገኙ ቢሆንም፣ የምርመራ መዝገብ የሚያቀርቡት ሬጅስትራር በሰዓቱ ባለመገኘታቸው ዳኛዋ ያለመዝገብ መሥራት እንደማይችሉ ገልጸው፣ ለሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ በመስጠት የተጠርጣሪዎቹን ጠበቃ ማሰናበታቸውን ጠበቃ አመሐ መኮንን ለታዳሚዎች ተናገረዋል፡፡ ተስፋ ያልቆረጡ የችሎቱ ታዳሚዎች ባሉበት ሆነው በመነጋገር ላይ እያሉ ሬጅስትራሯ ከጠዋቱ 4፡05 ሰዓት ላይ ሲደርሱ፣ ‹‹መጡ መጡ›› ተብሎ ጠበቃውም ወደ ችሎት ተመልሰው ገቡ፡፡

በዕለቱ የተሰየሙት ዳኛ የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ በመደበኛ ችሎት እንዲታይ ያዘዙት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ለሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ተቀጥረው የነበሩት ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በሰዓቱ ቀርበው ዳኛዋም በሰዓቱ የተሰየሙ ቢሆንም፣ የምርመራ መዝገቡን የሚያቀርቡት የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር በሰዓቱ ባለመድረሳቸው ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ የሚያቀርቡትን አቤቱታ በመደበኛው ችሎት ማስመዝገብ እንዲችሉ መሆኑን ጠበቃ አመሐ መኮንን ተናግረዋል፡፡

ሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በቀረቡት ጦማሪያን ማኅሌት፣ በፍቃዱና አቤል ላይ የፌደራል ፖሊስ ለ28 ቀናት የሠራውን የምርመራ ሒደት እንዲያስረዳ ተጠይቋል፡፡ መርማሪ ፖሊስም ያልተያዙ የተጠርጣሪዎቹ ግብረ አበሮች መኖራቸውን፣ ምስክሮችን ሰምቶ አለመጨረሱን፣ ሰነዶችን አስተርጉሞ እንዳልጨረሰና የቴክኒክ ምርመራ እንደሚቀረው አስረድቶ፣ ለተጨማሪ ምርመራ የ28 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁን ጠበቃ አመሐ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የተሰየሙት ዳኛ ግን የተጠርጣሪዎቹን ጠበቃ አስተያየትም መስማት ሳያስፈልጋቸው መዝገቡ ረጅም ጊዜ የቆየ መሆኑን በመግለጽ፣ 28 ቀናት እንደማይፈቅዱ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ቀርቶኛል ለሚለው ተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ብቻ በመፍቀድ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ዳኛዋ የፈቀዱት የ14 ቀናት ማብቂያ እሑድ ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ቢሆንም፣ እሳቸው ግን አንድ ቀን በመጨመር ለሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ዳኛዋ አንድ ቀን የጨመሩበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ የቅዳሜና የእሑድ ችሎት ለአሠራር አመች ስላልሆነና በጉዳዩም ላይ ዳኞች በመቀያየራቸው ወጥነት የሌለው ነገር እየተከሰተ በመሆኑ፣ አሠራሩን ለማስተካከል መሆኑን ጠበቃ አመሐ መኮንን አስረድተዋል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ ጦማሪያን መካከል በፍቃዱ ኃይሉ ለችሎቱ ባቀረበው አቤቱታ፣ በምርመራ ወቅት እሱ የሰጠውን ቃል ሳይሆን ፖሊስ በራሱ መንገድ እየጻፈው መሆኑን ገልጾ፣ በመዝገቡ ላይ ያለው ቃል የሱ ቃል አለመሆኑ በማስረዳት ድርጊቱን መቃወሙን ጠበቃ አመሐ ተናግረዋል፡፡ ለተጠርጣሪ በፍቃዱ ምላሽ የሰጡት ዳኛዋ፣ አቤቱታውን ማቅረብ ያለበት ክስ የሚመሠረት ከሆነ በመደበኛው ችሎት ላይ መሆኑ አስታውቀው የዕለቱ ችሎት ማብቃቱን ጠበቃው ለታዳሚዎች አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ በታዳሚዎችና በፖሊስ መካከል አለመግባባትም ተከስቶ ነበር፡፡ በፖሊስ ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩት ሦስቱ ተጠርጣሪ ጦማሪያን ወደ ፍርድ ቤቱ ግቢ ሲደርሱ፣ በግቢው ውስጥ የነበሩ የችሎቱ ታዳሚዎች መጠነኛ ጭብጨባ አሰሙ፡፡ ከችሎቱ ግቢ ያስወጡናል የሚል ፍርኃት ያደረባቸው የተወሰነ ታዳሚዎች ‹‹ተው ተው አታጨብጭቡ›› ሲሉ፣ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት ተንደርድረው በመሄድ አንዲትን ልጅ ጎትተው በማውጣት እያመነጫጨቁ ሲገፏት፣ ሌላኛው ወጣት ደግሞ ‹‹እህቴ ናት ልቀቋት ምን አደረገች?›› በማለት ሲቃወም፣ ‹‹ዝም በል›› በማለት ከፖሊስ ግሰጻ ቢደርስበትም መታገስ ያልቻለው ወጣት ‹‹እኔንም ውሰዱኝ›› ሲል አንድ መገናኛ ሬዲዮ የያዘ የፌደራል ፖሊስ ‹‹አምጣው›› በማለት ወጣቱን በመገፍተር ሁለቱንም ወደ ችሎት ወስዷቸዋል፡፡ በፖሊስ የተወሰዱት ሁለቱ ወጣቶች ዮናታን ተስፋዬና ምኞት መኮንን የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ ሌሎች የፖሊስ አባላት ወደ ታዳሚዎች በመመለስ ‹‹በሕግ አምላክ ውጡ›› ሲሉ፣ የተወሰኑ ታዳሚዎች ‹‹ምን አደረግን? ዝም ብለን ቆመናል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ ፖሊሱ ‹‹እንዴት ፎቶ ታነሳላችሁ?፣ ማንም ሳያስፈቅድ ማንንም ማንሳት አይችልም፣ እንኳን ሰው ይችን (በጣቱ እያሳየ) መሬት ሳያስፈቅድ ፎቶ ማንሳት አይችልም›› ሲል ታዳሚዎች ከንዴታቸው በረድ ብለው ፈገግ አሉ፡፡ በመጨረሻም ታዳሚዎች እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ እያጉረመረሙ ግቢውን የለቀቁት የችሎት ታዳሚዎች አስፓልት ላይ በመቆም ተጠርጣሪዎቹን ሲወጡ ለመሰናበት መጠበቅ ጀመሩ፡፡ ሁኔታ ያላስደሰተው ፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያ ኤጀንሲ በኩል አስወጥቶ ወደ ማዕከላዊ መውሰዱ ሲረጋገጥ ታዳሚዎችም ወደየመጡበት ሄዱ፡፡

Source: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>