በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አካባቢ በተፈጠረ ግጭት በአካባቢው ውጥረት መፈጠሩንና በግጭቱም አሥር ያህል የሱዳን ወታደሮች መገደላቸውን ዘገባዎች አመለከቱ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃውን እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡
አፍሪካ ፕሬስ ኤጀንሲ የተባለ ድረ ገጽ እንደዘገበው ከሆነ፣ ግጭቱ ባለፈው እሑድ የተቀሰቀሰው ገዳሪፍ በተባለው የሱዳን የድንበር አካባቢ ላይ ነው፡፡
በተቀሰቀሰው ግጭትም አሥር የሱዳን ወታደሮች ሲገደሉ፣ 13 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡ ግጭቱ በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ ዘገባው ያለው ነገር የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ በኩል በግጭቱ የተሳተፉትን በትክክል ማወቅ አለመቻሉን፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ላይ ያሉ ታጣቂ ሚሊሻዎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ዘግቧል፡፡
የሱዳን መከላከያ ጦር ግጭቱ እንደተፈጠረ ለድረ ገጹ ቢያረጋግጥም፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግጭቱ ላይ እንዳልተሳተፈ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
‹‹የሱዳን ወታደሮች ከኢትዮጵያ በኩል በመጡ ያልታወቁ ታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ግንኙነት የለውም፤›› በማለት የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ኢልስ ዋርሚ ካሊድካድ መናገራቸውም በዘገባው ተካቷል፡፡
ከኢትዮጵያ ድንበር በኩል የገቡት ታጣቂዎች በሱዳን ድንበር ውስጥ የሚገኘውንና በሱዳን ጦር ሥር የሚተዳዳረውን የእርሻ መሬት ለመያዝ ሳይመጡ እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡
የሱዳን መንግሥት ጉዳዩን ለኢትዮጵያ መንግሥት ማሳወቁን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ‹‹መረጃውን እያጣራን ነው፤›› ብለዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter