በፀጋው መላኩ
በየዓመቱ የየሀገራትን የሠላም ይዞታ በማጥናት ደረጃን የሚያወጣው ኢኒስቲትዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም የ2014 የዓለም ሀገራት የሰላም ደረጃ ከሰሞኑ የለቀቀ ሲሆን በዚህም ጥናቱ ከ162 ሀገራት ኢትዮጵያን በ139ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል። ተቋሙ የአንድን ሀገር የሠላም ደረጃ ለማውጣት በርካታ የስኬት ማሳያዎች (Indicators) ግምት ውስጥ ያስገባል። ለዚሁ ልኬት ግብዓትነት ከሚውሉት መመዘኛዎች መካከል የውስጥና የውጭ ግጭቶች፣ አንድ ሀገር ከጎሬበቶቹ ጋር ያለው የግንኙነት ሁኔታ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሽብር ተጋላጭነት፣ የወንጀል መስፋፋት እንዲሁም በእያንዳንድ አንድ መቶ ሺ ሰው በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን የእስረኛ ብዛትንም በመውሰድ ደረጃውን ለማውጣት በልኬትነት ይጠቀማል። ከዚህም በተጨማሪ ከአጠቃላይ ብሄራዊው ምርት አንፃር ለሚሊተሪው ዘርፍ የሚወጣውንም የገንዘብ መጠን ታሳቢ ያደርጋል። እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ ግብዓቶችን በማካተት ነው መረጃዎቹ ተተንትነው ደረጃ ወደ ማውጣቱ ስራ የሚካሄደው።
የየሀገራቱ ደረጃ ወጥቶ በድርጅቱ ድረገፅ እንዲሁም በዘ ኢኮኖሚስት መፅሄት ለህትመት የሚበቃ ሲሆን የዘንድሮውም ሪፖርት የ162 ሀገራትን መረጃ በመውሰድ ሰፊ ትንታኔ ከሰጠ በኋላ ኢትዮጵያ በ139ኛ ደረጃ አስቀምጧል። ተቋሙ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበት ሁኔታ በመግለፅም በይደር የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑንም አመልክቷል። ኢትዮጵያ ከፀጥታ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ገንዘብ የምታወጣ መሆኑን መረጃው ጨምሮ አመልክቷል። በዚህ የሀገራት የሰላም ደረጃ አይስላንድ የመጀመሪያውን ደረጃ በመያዝ በዓለም እጅግ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ተብላለች። ዴንማርክ ሁለተኛ ስትሆን ኦስትሪያ የሶስተኝነትን ደረጃን ይዛለች።
ከ162ቱ ሀገራት 162ኛን ደረጃ በመያዝ በደረጃው ግርጌ ላይ የተቀመጠችው ሶርያ ናት። አፍጋስታን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኢራቅ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም በደረጃው የመጨረሻ ግርጌ ላይ የተቀመጡ ሀገራት ናቸው። ግብፅ 148ኛ ደረጃን ይዛለች።
ዓለም አቀፍ የሀገራት የሠላም ስኬት ደረጃ (Global peace Index) በኢንስቲትዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ ተቋም በየዓመቱ ይፋ የሚሆን ሲሆን መረጃውን በማሰባሰቡ በኩል በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰፊ ትብብርና ተሳትፎን ያደርጋሉ። ከዓለም አቀፍ ተቋማቱ መካከል የተለያዩ የተባበሩት መንግስታት አካላትም ይገኙበታል። እንደ ኮፊ አናን እና ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱን የመሳሰሉና በተለያዩ ጊዜያት ሀገራትን ከመሩ በኋላ የስልጣን ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሪዎችም የሙያ አስተዋፅዖችን የሚያበረክቱበት ተቋም ነው። ተቋሙ የሀገራትን የሠላም ደረጃ የሚያወጣው 22 መስፈርቶችን አስቀምጦ በዚያ ልኬት መሰረት ነው።
ምንጭ – ሰንደቅ ጋዜጣ (በአዲስ አበባ የሚታተም)