በዶ/ር ነጂብ አል ኢማን
ሜዲካል ጋዜጣ
ፋይብሮማያልጅያ ምርምሮች እንደሚጠቁሙት ከሆነም ሴንትራል ነርቨስ ሲስተምን የሚያጠቃ ህመም ነው፡፡ ምልክቶቹ ምንጫቸው ከየት መሆኑ በውል አለመታወቁ ሳይንሳዊ ሃኪሞችን ግራ ሲያጋባ ኖሯል፡፡
‹‹ለብዙ ወራት ባከንኩ፣ ብዙ ሌሊቶችንም በስቃይ አሳለፍኩ፡፡ ልተኛ ስል እስኪነጋ ድረስ እጓጓለሁ፣ ንጋት እስከሚደርስ ድረስ ግን ስገላበጥ አድራለሁ፡፡ ቀኖቼ በሙሉ በሃዘን የተሞሉ ነበሩ፡፡ አጥንቶቼንም የሚበላው ነገር ያለ ይመስል ሌሊቱ በስቃይ የተሞላ ነበር፡፡››
ኢዮብ በቁስል በጣም ተሰቃይቶ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ላይ የተገለጸው ሰቆቃውም በብዙዎች ዘንድ የፋይብሮማያልጂያ ቀደምት ምልክቶች ተደርገው ይታያሉ፡፡ ፋይብሮማያልጂያ በስቃይ የተሞላና እንቆቅልሽ የሆነ ህሙማንም ተስፋ ሲያስቆርጥ የኖረ ህመምም ነበር፡፡
የመፅሃፍ ቅዱሳዊ አገላለጹ ሙሉ በሙሉ የተብራራ ነው ለማለት ባይቻልም የኢዮብ ህመም ግን በዘመናችን ፋይብሮማያልጂያ እያልን የምንጠራውን የሚመስል ነው፡፡ የህመሙ ምልክት ቁርጥማት እና መረበሽ ብቻም ሳይሆን የሃዘን ስሜት፣ የድካም ስሜት፣ የሰውነት መንዘር፣ የእንቅልፍ ማጣት እና በአጠቃላይ መጥፎ ስሜት የመሰማት ሁኔታንም በብዛት ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ከአጠቃላይ የዓለም ህዝብ ውስጥ ከ2 እስከ 8 ፐርሰንት ያህሉ ፋይብሮማያልጂያ እንዳለባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተደጋጋሚ በሃኪሞች ዘንድ ቀርበው ሲመረመሩም ህመማቸው በትክክል ስለማይገባቸው አዕምሮአቸው በራሱ ጊዜ የፈጠረው ችግር ነው እየተባሉ የስነ-ልቦና ምክር ብቻ ተሰጥቷቸው ይሸኛሉ፡፡
ለብዙ ጊዜ የሚቆይ የህመም ስሜት እና ቁርጥማት መሰሉ ህመም ከተብራራ ብዙ ዓመታት ሆኖታል፡፡ ተመራማሪዎች ሒፓክራትስ ጋውት የሚባለውን ቁርጥማት መሳይ ህመም በምርምር አግኝተው ነበር፡፡ በመጨረሻም ጊሎም ቤሉ የተባለው የፈረንሳይ ሃኪም የመገጣጠሚያ እና የጡንቻ ችግሩን ሩማቲዝም በማለት ጠራው፡፡ ከዚያም ሃኪሞች የመገጣጠሚያ ቁርጥማትን እና የጡንቻ ቁርጥማትን መለየት ቻሉ፡፡ ፋይብሮማያልጂያ የጡንቻ ቁርጥማት ነው፡፡
መንስኤው ለበርካታ ክፍለ-ዘመናት ምስጢር ሆኖ የነበረ ሲሆን ክስተቱ ግን ፋይብሮሳይቲስ መሆኑ ታውቆ ነበር፡፡ ፋይብሮሳይቲስ በጡንቻ ውስጥ የሚከሰት ኢንፍላሜሽን ወይም የመቁሰል ሁኔታ ነው፡፡ መንስኤውም ስነ-ልቦናዊ ነው ሲባል ቆይቷል፡፡ አሜሪካውያኑ የዘመናዊው የውጥረት ህይወት የፈጠረው ነው ብለው የነበረ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው በሚታከሙ ህሙማን ዘንድ በሽታው በብዛት ይከሰት ስለነበር ይሄም ጦርነት ከሚፈጥረው ሃዘን እና ውጥረት ጋር አብሮ የሚከሰት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1968 ላይ አንድ አሜሪካዊ ሃኪም ህመሙን የሴቶች ብቻ ህመም ብሎት ነበር፡፡ መንስኤውም በሴቶች ውስጥ በብዛት የሚከሰተው የስሜት አለመረጋጋት ነው ነበር ያለው፡፡
በ1970ዎቹ ላይ ፋይብሮማያልጂያ የሚለው ቃል ፋይብርሳቲስ የሚባለውን ቃል ያወጡት ዶ/ር ሂይ ስሚዝም የበሽታውን ምልክቶች አጥርተው አስቀመጡ፡፡
እ.ኤ.አ በ1990 ላይም የአሜሪካ የሩማቶሎጂ ኮሌጅ ህመሙ እንዴት እንደሚጀምር በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ አወጣ፡፡ ህመሙ አለ ይባል ዘንድም ከ18ቱ ‹‹ቴንደር ፖይንትስ›› ወይም በ11ዱ ላይ መከሰት መቻል አለበት፡፡ ቴንደር ፖይንትስ ማለት ህመሙ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸው የሰውነት ክፍሎች ናቸው፡፡
የህመሙ አመራመር ሁኔታ በጥራት ሊታወቅ የቻለ ቢሆንም ጉዳዩን ከአካላዊ ሁኔታዎች ጋር ለማገናኘት ግን አልተቻለም ነበር፡፡ ጥርጣሬው ያነጣጠረው ግን በአንጎል ላይ ነበር፡፡ በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ወቅት የተከናወነው ምርምር ጥርጣሬውን ይበልጥ ለመናረጋገጥ ቻለ፡፡ የህመሙ ምንጭም ሴንትራል ነርቨስ ሲስተም ማለትም ማእከላዊው የነርቭ ስርዓት መሆኑ ታወቀ፡፡ ማእከላዊ የነርቭ ስርዓት የሚባለው ደግሞ አንጎል እና ህብለ ሰረሰር ናቸው፡፡ ፋይብሮማያልጅያ ጋር ተመሳሳይ ሊባል የሚችለው ሁኔታ ደግሞ ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም የሚባለው ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ሁኔታዎች ታዲያ ቁርጥማት ከሚያስከትሉ ሌሎች ሁኔታዎች ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኦስትዮአርትራትስ እና ሩማቶይትስ ከሚባሉ ህመሞች ማለት ነው፡፡ እነዚህ ህመሞች በርግጥ በሰውነት ላይ ተጨባጭ የሆነ ብልሽት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
የፋይብሮማያልጅያ ሳይንስ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል፡፡ ሴቶች በበሽታው ያላቸው ተጠቂነት ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር እጥፍ ነው፡፡ የፋይብሮማያልጅያ ተጠቂዎች ታላቅ ዜና ባሁኑ ወቅት ሊታከም የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ለህክምና የሚያገለግሉ በርካታ መድሃኒቶች ለማግኘት ተችሏል፡፡ ከእነዚህ ህክምናዎች መካከል ሦስቱ ከአሜሪካ መንግስት ፈቃድ ለማግኘት ችለዋል፡፡ የበለጠ ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡት ደግሞ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ ኮግኒቲቭ ብሄቪየራል ቴራፒ (አፍራሽ አስተሳሰቦችንና ባህሪያትን ለመለወጥ የሚደረግ ጥረት) እና ለህሙማን የሚሰጥ ትምህርት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጭንቀትን በመቀነስ የእንቅልፍ ጥራት ለማስተካከል ህሙማን አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡
Source- www.mahederetena.com/archives/1835