በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ተቃዋሚነት ጎራ የተሰለፉ ኃይሎች በቅድሚያ ትግላቸውን በብሔራዊ ነፃነት ዙሪያ ያድርጉ!
እኛ የሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ከሰኔ ፲፬ – ፲፭ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ.ም. (June 21 – 22, 2014) አራተኛ መደበኛ ስብሰባችንን በተሣካ ሁኔታ አካሂደናል። በሁለት ቀናት ጉባኤያችን የሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የቁጥጥርና ፍተሻ ኮሚቴዎች ያቀረቧቸውን የ፮(ስድስት) ወራት የድርጅቱን የሥራ እንቅስቃሴ ሪፖርቶችን አዳምጠን ጠቃሚ ውይይት አድርገናል። ድርጅቱ ያከናወናቸው መልካም ተግባሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ በአፈፃፀም የታዩ ድክመቶች እንዲታረሙ በማስገንዘብ፣ ለድርጅቱ ዓላማ ዳር መድረስ የሚያግዙ የሚከተሉትን አቋሞች ወስደናል።
፩ኛ) የኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነት፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም መከበር እና የግዛታዊ አንድነት መጠበቅን በተመለከተ፦
በዘረኛው የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዐላዊ መብቱን የተነጠቀ፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅምም ለባዕዳን ተላልፎ የተሸጠና የአገሪቱ ግዛታዊ አንድነት ፈጽሞ ያልተጠበቀ መሆኑን ከቀረቡት ተጨባጭ ማስረጃዎች ተገንዝበናል። የአገሪቱን የባሕር በር ወያኔ ተገዶ ሣይሆን ወዶ እና ፈቅዶ ለሻዕቢያ ከሸጠው ፳፫(ሃያ ሦሥት) ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ የተነሣም ኢትዮጵያ መተናፈሻ የሌላት ዝግ መሬት ሆናለች። ስለዚህ ኢትዮጵያ የወጪ እና የገቢ ንግዷን ጂቡቲን በመሣሰሉ ትናንሽ አገሮች መልካም ፈቃድ ላይ እንዲመሠረት በማድረጉ በዕድገቷ ላይ ከፍተኛ መሠናክል ሆኗል። «ወደብ ለሌለው አገር ስለ ዕድገት አይታሰብም» ማለት ባይቻልም እንኳን፣ የዕድገት ግስጋሴው ግን ወደብ ካላቸው ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም።
ከዚህ በተጨማሪ በመሬት ስፋት አንፃር ከአየርላንድ ሪፑብሊክ ግዛት የሚበልጥ ከ፰(ስምንት) ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሆነ የአገሪቱ ለም እና ድንግል መሬት ለ፺፱(ዘጠና ዘጠኝ) ዓመታት ለሕንድ፣ ለቻይና፣ ለፓኪስታን፣ ለግብፅ፣ ለጅቡቲ እና ለሌሎችም አገሮች ባለኃብቶች በጣም በርካሽ ገንዘብ ተሸጦ ገበሬው ጦም አዳሪ እና አገር-የለሽ ሆኗል።
ከምዕራባዊ የአገሪቱ ድንበር በቁመት ከሰሜን ወደ ደቡብ ፩ሺህ፮፻(አንድ ሺህ ስድስት መቶ) ኪ.ሜ.፣ በወርድ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ከ፶(ሃምሣ) እስከ ፷(ስድሣ) ኪ.ሜ. ጥልቀት ያለው ለሙ እና ድንግሉ መሬት ለሱዳን በገጸ-በረከትነት ተሰጥቷል።
በቋንቋ ላይ የተመሠረተው የፌደራል አገዛዝ አደረጃጀት የሕዝቡን ነባር የአንድነት እና የአብሮነት ስሜት ንዶታል። ይህንንም ወያኔ ሆን ብሎ ኃይልን በአካተተ ፕሮፓጋንዳ ጭምር በመታገዝ የሕዝቡን የአንድነት እና የኢትዮጵያዊነት ስሜት በእጅጉ እንዲሸረሸር አድርጓል።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ከዐማራ የጸዱ ክልሎች ለመመሥረት በተያዘው ዘር የማጽዳት እና ዘር የማጥፋት ዘመቻ ዐማራው የማይኖርባቸው ክልሎች ተፈጥረዋል።
ይህ አጠቃላይ ሁኔታ ተዳምሮ ሲታይ የሕዝቡ ሉዓላዊነት፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም እና ግዛታዊ አንድነት ያልተጠበቀ እና ያልተከበረ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም። በመሆኑም ዛሬ በትግሬ-ወያኔ ተቃዋሚነት ጎራ የተሰለፉት ኃይሎች የትግል ሥልታቸውን ዳግም ሊመረምሩ ይገባል። በአንድ አገር ላይ ሰላም፣ ዕኩልነት፣ ዲሞክራሲ እና ፍትኅ የሚሠፍኑት በቅድሚያ አገሪቱ ኅልውናዋ ሲጠበቅ ነው። ስለሆነም «በቅድሚያ የመቀመጫዬን» ነውና፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች የትግሉን አቅጣጫ በቅድሚያ በብሔራዊ ነፃነት ዙሪያ እንዲያደርጉት ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ጥሪውን ያቀርባል።
፪ኛ) በዐማራው ላይ የሚካሄደውን ሁለንተናዊ ጥቃት በተመለከተ፦
ባለፉት ፶(ሃምሣ) እና ፷(ስድሣ) ዓመታት ብቻ ሣይሆን፣ ከዚያም ቀደም ሲል ጀምሮ፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የተነሱ የውጭ እና የውስጥ አጥፊ ኃይሎች የመጀመሪያው የጥቃት ዒላማቸው የሚያደርጉት «ዐማራ» የተሰኘውን ነገድ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህም የረዥም ዘመናት ታሪካችን አሻራዎቻችንም ሆነ ዛሬ በዐማራው ነገድ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ አጉልተው ያሣያሉ። ባለፉት ፳፫(ሃያ ሦሥት) ዓመታት ዐማራው በኢትዮጵያ ምድር የመኖር መብቱን ተገፍፏል፤ በአገሩ ውስጥ ተንቀሳቅሶ በፈለገው እና ባሻው የሥራ መስክ ተሠማርቶ የመሥራት የዜግነት መብቱን ተነጥቋል፤ በነገዱ ማንነት ብቻ ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ በጅምላ ተሠልቧል፣ ጭፍጨፋ እና ግድያ ተፈጽሞበታል፤ እህቶቻችን እና እናቶቻችን ጡታቸው ተቆርጧል፤ ዐማራው ኃብት እና ንብረቱን ተነጥቆ፣ በአገሩ እንደ ባይተዋር ተቆጥሮ በግፍ ከመኖሪያው ተባርሯል።
ለአብነት ያህል ባለፉት የ፮ ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ካድሬዎች እና በተላላኪዎቻቸው ከተፈፀሙት ግፎች መካከል፦
· በመጋቢት ወር ሁለተኛ ሣምንት መጀመሪያ በአምቦ ከተማ አካባቢ፣ ዳኖ ወረዳ (ከምዕራብ ሸዋ) በመቶዎች የሚቆጠሩ የዐማራ ተወላጆች በኦሕዴድ ካድሬዎች አማካይነት «አገራችሁ አይደለም እና ውጡ» ተብለው ተባርረዋል፤ ፳፮(ሃያ ስድስት) ዐማሮች በአሠቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል፤ በተለይ አቶ ጌጡ ክብረት የተባሉት የዐማራ ተወላጅ በአሠቃቂ ሁኔታ በገጀራ ተቆራርጠው መገደላቸው ተዘግቧል።
· በግንቦት ወር «የአዲስ አበባን ከተማ መስፋፋት እንቃወማለን» በሚሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች በሚመራው እንቅስቃሴ ተሣታፊዎች፦ በአምቦ፣ በዓለማያ፣ በነቀምት እና በሮቤ (መዳወላቡ) ዩኒቨርስቲዎች በሚማሩ የዐማራ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት እና አልፎ ተርፎም ኢሠብአዊ ግድያ ፈፅመዋል። በተለይም በነቀምት ዩኒቨርስቲ ይማሩ የነበሩ ፯ ተማሪዎች በትግሬ-ወያኔ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ተገድለዋል። በመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ትማር የነበረችዋን የዐማራ ተወላጅ ከፎቅ ፈጥፍጠው ገድለዋታል። ግንቦት ፲፭ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ.ም. በቅፅ ፪፣ ቁጥር ፳፩ ባወጣነው መግለጫችን በይበልጥ እንደተብራራው፣ በጊምቢ ከተማ እና አካባቢው (ምዕራብ ወለጋ) ከሚኖሩት ዐማሮች መካከል በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩት ቤት፣ ንብረታቸውን ተነጥቀው እንዲፈናቀሉ ሆኗል። በአጠቃላይ በጊምቢ ከተማ እና በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩት ዐማሮች የንብረት ይዞታ ውስጥ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል። ከዚህ በተጨማሪም በግንቦት ፮ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ.ም. የአካባቢው የኦሕዴድ ካድሬዎች በዐማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። ከስቡ ስሪ ወረዳ (ምሥራቅ ወለጋ) ፪መቶ ዐማሮች ‹‹ይህ አገር የእናንተ አይደለም፣ አገራችሁ ግቡ፤›› ተብለው ኃብት፣ ንብረታቸውን ተነጥቀው ተባርረዋል። በወለጋ በአክራሪ ኦሮሞዎች እና በኦሕዴድ ካድሬዎች አማካይነት በዐማሮች ላይ በስፋት የሚፈፀመው ግፍ አሁንም ያልተገታ መሆኑን የመገናኛ ብዙሃን እስካለፈው ሣምንት መጨረሻ ድረስ የዘገቡት ጉዳይ ነው።
· በዘንድሮው ዓመት በ፪ሺህ፮ ዓ.ም. ብቻ የትግሬ-ወያኔ ካድሬዎች «ሕገ-ወጥ ግንባታ አካሂዳችኋል» እና «ቦታችሁ ለልማት ይፈለጋል» የሚሉ ሠንካላ ምክንያቶችን በመደርደር፦ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በደብረማርቆስ፣ በደሴ፣ በሐረር እና በሌሎችም ከተሞች በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን በግሬደር እና በሰው ኃይል አፍርሰዋል። የትግሬ-ወያኔዎች በየዓመቱ ይህን አረመኔያዊ ድርጊት የሚፈፅሙት ሆን ብለው የክረምትን ወቅት ጠብቀው ነው። የዚህ ድርጊት ቀዳሚ ተጠቂዎች ደግሞ ዐማሮች መሆናቸው ይታወቃል።
በአንድ ቃል በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ዐማራው በየዕለቱ የዘር ማጽዳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈፀምበት፤ ቀኑ የጨለመበት፤ ድምፁ ሰሚ ያጣበት፤ ግፉን ተመልካች ያላስተዋለለት ሆኗል።
ሐ) በዐማራው ላይ በሚደርሰው ግፍ እና በደል የተቃዋሚ ድርጅቶች እርምጃ፦
በሚያሣዝን ሁኔታ «በኢትዮጵያዊነት» ስም የተደራጁት የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች እንኳን ስለዐማራው ችግር ተቆርቁረው የሚያደርጉት ረብ ያለው ሥራ የለም። በዐማራው ላይ የሚፈፀሙትን ግፎች እና በደሎች «በዐማርኛ ተናጋሪዎች ላይ የደረሰ» እየተባሉ የሚሰጡት መግለጫዎች ዛሬ የዐማራውን ኅልውና ሆን ብለው የሚክዱ መሆኑን እና ለችግሩም የሚሠጡትን ዝቅተኛ ግምት በገሃድ ያሣያል።
መ) ዐማራው ኢትዮጵያዊነቱን ሣይለቅ በዐማራነቱ የመደራጀቱ አስፈላጊነት፦
አሁን ያለውን «የዐማራውን ጉዳይ ሆን ብሎ የማጣጣል» ሁኔታ መለወጥ የሚችለው፣ የዐማራው ልጆች ተደራጅተው «አለንልህ» ሲሉት እና ከጠላቶቹ አንፃር አቻ ወይም ጉቢ ኃይል ሲፈጥሩ ብቻ እንደሆነ የምክር ቤቱ አባላት ባደረጉት ሠፊ ውይይት ሙሉ በሙሉ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ስለሆነም ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የጀመረውን ዐማራን የማደራጀት ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ አባላት እና አካላትም ሳይሰለቹ እና ሳይታክቱ የእያንዳንዱን ዐማራ በራፍ በማንኳኳት የድርጅቱ አባል እንዲሆን፤ ድርጅቱንም በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በመረጃና በመሳሰሉት እንዲደግፍ እንዲያደርጉ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው!
ኢትዮጵያ በጀግና እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራ እና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!