-የኬንያ የቱሪዝም ባለድርሻ አካላት ከ575 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያጣሉ
መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገውና ቤንች ኢቨንትስ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም አዘጋጅ፣ በመጪው መስከረም በናይሮቢ ኬንያ ሊያካሂደው የነበረውን የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም
ወደ አዲስ አበባ ማዘዋወሩን ባለፈው ሰኞ ማስታወቁን ሐን ጊስካ አፍሪካ ኦንላይን ገለጸ፡፡ ይህንን ተከትሎም በኬንያ የሚገኙ የሆቴል ባለቤቶች፣ የቱሪዝም ባለሙያዎችና የጉዞ ወኪሎች ከኬንያ ተነጥቆ ለኢትዮጵያ በተሰጠው ዕድል ላይ ቅሬታቸውን መግለጻቸውንም የዜና ምንጩ ገልጿል፡፡
ይህ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም መነቃቃትን እንደሚፈጥር አስተያየታቸውን የሚሰጡት የዘርፉ ባለሙያዎችም፣ በዚህ መልካም አጋጣሚ ምክንያት የአገሪቱ ቱሪዝም አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ብሎ ሊቀመጥ እንደሚችልም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በአንፃሩ ኬንያውያን የዘርፉ ተዋንያኖች ግን አምስት ቢሊዮን ሺልንግ ወይም ከ575 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያላነሰ ገቢ እንደሚያጡ ተንብየዋል፡፡ ከዚህም በላይ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይና የአውስትራሊያ መንግሥታትን የሰሞኑን የጉዞ ማስጠንቀቂያ ተከትሎም የኬንያ ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ እንደሚችልም ተንብየዋል፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗ የሚነገርላት ኬንያ በዓመት ከ66 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በሚያስገኝላትና ሁለተኛው ትልቁ የአገሪቱ የገቢ ምንጭ በሆነው ቱሪዝሟ ከፍተኛ ዕውቅና ቢኖራትም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ በተፈጸሙባት የሽብር ጥቃቶች ምክንያት የቱሪዝም ገቢዋ እያሽቆለቆለ እንደሚገኝ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ከሰሞኑ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታትም አልሸባብ በኬንያ ተጨማሪ ጥቃቶችን ሊሰነዝር እንደሚችል በመጠቆም ዜጎቻቸው ወደ አገሪቱ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲገቱ ማስጠንቀቃቸው፣ የኬንያን ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳ ተጠቁሟል፡፡
እንደ አብዛኞቹ የኬንያ የቱሪዝም ባለድርሻ አካላት አስተያየት የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ከኬንያ ተነጥቆ ለኢትዮጵያ የተሰጠውም በዚሁ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ምክንያት ነው፡፡ የቤንች ኢቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማቲው ዊህስ ግን የቦታ ቅያሪው የመጣው ኢትዮጵያ ከኬንያ በተሻለ ለተሳታፊዎች ሰፊ ቦታ ስላላት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ናይሮቢ በርካታ የተሳትፎ ጥያቄ ላመጡ ደንበኞቻችን የሚበቃ ቦታ ስለሌላት አዲስ አበባ ትሻላለች፡፡ በመሆኑም በናይሮቢ ኢንተርኮንትነንታል ሆቴል ሊካሄድ የታቀደው መርሐ ግብር በሸራተን አዲስ ይከናወናል፤›› ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹በዚህም ምክንያት ሌሎችን እናስቀይማለን ብለን አንጠብቅም፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በቀሩት የአራት ወራት ጊዜ ውስጥ መርሐ ግብሩን በአዲስ አበባ በስኬት ለማካሄድ ጥረቶች መጀመራቸውንም አስረድተዋል፡፡ በናይሮቢ የሚገኘው ኢንተርኮንትነንታል ሆቴል 350 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት፣ ሸራተን አዲስ ግን 293 ክፍሎች ያሉት በመሆኑ የቦታ ጥበት ነው የሚለውን ምክንያት የማይቀበሉት ኬንያውያን የቱሪዝም አካላት፣ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቱን ማስጠንቀቂያ ሰበብ አድርገው በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
‹‹በተለያዩ ጊዜያት በጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያና በዌስት ጌት የገበያ ማዕከል የደረሰውን የሽብር ጥቃት አስመልክቶ የተፈጠረውን አሉታዊ ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት የደኅንነት ሁኔታውን በጥብቅ እየተከታተለ መሆኑን ተረድተው፣ በርካታ ቱሪስቶችን ፊታቸውን መለስ ማድረግ ጀምረው ነበር፡፡ አሁን ምን ተፈጥሮ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው? ለማንኛውም መልካም ዕድል፤›› ሲል አንድ ኬንያዊ ስሜቱን ገልጿል፡፡
ይህን ዜና ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ለመታደም የሚመጡ እንግዶች ቁጥር ከፍ እንደሚልና እስከ ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስም ባለው የምዝገባ ጊዜ ተሳታፊዎች ቅናሽ የተደረገበትን አንድ ሺሕ ዶላር ክፍያ መፈጸም እንደሚገባቸውም አዘጋጁ አካል ገልጿል፡፡ የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ከመጪው መስከረም 19 እስከ መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በሸራተን አዲስ የሚካሄድ መሆኑንም አዘጋጁ አሳውቋል፡፡
ከአራት መቶ በላይ ልዑካንና 27 ኩባንያዎችን እንዳስተናገደ በተነገረለት የአምናው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም የኬንያ ትልቁ ባለአምስት ኮከብ ሆቴልን ተጠቃሚ እንዳደረገ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ይህን መሰሉ መልካም አጋጣሚ በአዲስ አበባ እንደሚጠበቅ አዘጋጁ ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ በርካታ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ የውሳኔ ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ተገልጿል፡፡ የሸራተን አዲስን ተወዳዳሪ የዋጋ አቅርቦት ተከትሎ ተሳታፊዎች የጉብኝቱ አካል ብቻ ሳይሆኑ፣ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ተገኝተው ስለአፍሪካ ያላቸውን እይታ እንዲያሰፉ ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ኬንያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዝግጅቱን በተሳካ ሁኔታ ያዘጋጀች በመሆኗና ሁሉንም አቅርቦቶች በአማራጭነት የያዘች መሆኗን የሚገልጽ አንድ ተሳታፊ፣ በውሳኔው መበሳጨቱንና ውሳኔው የማይቀየር ከሆነም ወደ አዲስ አበባ እንደማይጓዝ መግለጹን ከኬንያ የወጡ ዘገባዎች ገልጸዋል፡፡ አዘጋጁ ቤንች ኢቨንትስ ግን ጊዜው የኢትዮጵያ ነው እያለ ነው፡፡
Source: Ethiopian Reporter