አባ ዱላ ገመዳና የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው የቁም እስረኞች መሆናቸው ከተለያዩ ምንጮች እየወጡ ያሉ መረጃዎች አመልከተዋል። የጎልጉል ምንጮች ግን ኦህዴድ ውስጥ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ እየተካሄደ ያለው ግምገማ ሲጠናቀቅ በርካታ ባለስልጣኖች ክስ እንደሚመሰርትባቸው ተናግረዋል።
በቀድሞው የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አባ ዱላ ገመዳና በአቶ ድሪባ ላይ ይህ ውሳኔ የተላለፈው አገር ጥለው እንዳይወጡ በሚል ነው። ጎልጉል በቅርቡ ካገር መውጣት የማይችሉ ባለሥልጣኖች እንዳሉ ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል። ውሳኔው የተላለፈው ሰሞኑን የአዲስ አበባን አዲስ ማስተር ፕላን ለመተግበር የኦሮሚያ ክልል ከተሞች መካተታቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ነው። ከሁለቱ ባለስልጣናት በተጨማሪ ከፍተኛ የክልልና የዞን የኦህዴድ አመራሮችም በደህንነት ቅርብ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ተሰምቷል። ካገር መውጣት የማይችሉም አሉ።
አባ ዱላ /ጃርሳው/
አባ ዱላ ኦሮሚያን ሲረከቡ በማክረር አካሄድ የሚታወቁት አቶ ጁነዲን ያዋቀሩትን ካቢኔ በመበተን ሥራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ። አዲስ ካቢኔ ሲገነቡ የመረጡት አዲስ የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎችንና በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቀናቃኝ (የተቃዋሚ) ፓርቲ አባላትን በማስኮብለል ነበር። ህወሃት ለሁለት በተበረገደበት ወቅት ለአቶ መለስ ቡድን ድጋፍ በመስጠት ቅድሚያ የያዙት አባ ዱላ ባስቀመጡት ውለታ መሰረት ኦሮሚያ ላይ ያሻቸውን እንዲያደርጉ የሟቹ መለስ ድጋፍ ነበራቸው። በዚህም ድጋፍ ሳቢያ ኦሮሚያ ላይ የሚፈልጉትን ሲያደርጉ ከተባረሩት መካከል የአሁኑ ፕሬዚዳንት ሙክታር ከዲር ይገኙበታል።
“አትደግፉን ነገር ግን የክልሉን ልማት አታደናቅፉ” በማለት አዲስ የመለመሏቸው የተለያየ አመለካከት ያላቸው አዳዲስ የኦህአዴድ አባላት ኦሮሚያን ከአባ ዱላ እጅ ተረከቡ። አባ ዱላ ፍጹም ነጻነት ይሰጡ ስለነበር ካድሬው ወደዳቸው። ስማቸው ተቀይሮ መለያ ተሰጣቸው፤ “ብራንድ” ሆኑ – “ጃርሳው” ተባሉ። በካቢኔያቸውና በሳቸው መካከል የነበረው ፍቅር በነደደበት ወቅት አባ ዱላ ክልሉን እንደሚለቁ ተሰማ። ባለፈው ምርጫ አባ ዱላ ለፌዴራል እንጂ ለክልል እንደማይወዳደሩ ይፋ ሲደረግ ካድሬው ገነፈለ። “የኢህአዴግ ምክር ቤትን ውሳኔ አንቀበልም” በማለት ተቃወመ። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ስብሰባ ቢካሄድም ከስምምነት ላይ ሊደረስ ባለመቻሉ ተበተነ። በመጨረሻም ራሳቸው አባ ዱላ በመሩት ስብሳባ ካድሬውን ተማጽነው ነገሩ ረገበ። ይሁን እንጂ ቅርሾ ግን ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ “ኦህዴድ/ኢህአዴግ በመደብ ትግል መተላለቅ ጀመረ” በማለት ዘግበን ነበር።
አባ ዱላ ኦሮሚያን ሲመሩ ቆይተው ሲመሻሸ “ይህንን ቤት ይዤ ለመታገል አይመቸኝም” በማለት ቦሌ ያስገነቡትን አስገራሚ ህንጻ ለኦህዴድ አስረከቡ። በከፍተኛ ሙስና ይታሙ ስለነበር ተናዘውና ገብረው ታለፉ። ለፌዴራል ተወዳድረው አፈ ጉባኤ ለመሆን በቁ። በወቅቱ የወ/ሮ አዜብ ድጋፍ ቢኖራቸውም የሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን የቀኝ እጅ የሆኑ ባለስልጣኖች ግን ጠምደዋቸው ነበር። ሙክታር አህመድ አንዱና ዋናው ነበሩ። ከላይ በረከት ስምዖንና አዲሱ ለገሰ አባ ዱላን ከሚቃወሙ መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚቀመጡ ናቸው።
በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ አልፈው እዚህ የደረሱት አባ ዱላ ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ህይወት የቀጠፈውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አስመልክቶ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ተማሪዎችን ከወ/ሮ አስቴር ማሞ ጋር በመሆን አነጋግረው ነበር። በወቅቱ የተማሪዎቹ ጥያቄ ፍትሃዊ እንደሆነ ሲመሰክሩ፣ ይህንኑ ምስክርነታቸውን ለተለያዩ የአገር ውስጥና የውጪ አገር ሚዲያዎች አሳውቀውም ነበር። አያይዘውም ነፍስ ያለ አግባብ ያጠፉ እንደሚጠየቁ ቃል ገቡ።
የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት አባ ዱላ ይህንን ከተናገሩ በኋላ ከፍተኛ ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል። “ረብሻውን ያስነሱት ራሳቸው የኦህዴድ ካድሬዎች ናቸው” ከሚል ድምዳሜ የደረሰው ኢህአዴግ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ሰፊ የስለላ ስራ አከናውኗል። “ጥፋተኞቹን ለህግ እናቀርባለን” በማለት መግለጫ ያወጣው ኢህአዴግ በቀጣይ የሚያስራቸውና የሚከሳቸው ባለስልጣኖች አሉ። ምንጮቹ በተለይ አባዱላና የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑት አቶ ድሪባ ኩማ ላይ ስለሚወሰደው ርምጃ ያሉት ነገር ግን የለም። ክስ ከተመሰረተባቸውና ምርመራው በሰንሰለት ታች ድረስ ከዘለቀ የኦህአዴድ የታችኛው መዋቅር ሊናጋ እንደሚችል ግን ግምታቸውን አኑረዋል። ለምሳሌ ያነሱት ሽፈራው ሽጉጤን ነው። ሽፈራው ሽጉጤ በሙስና እንዲከሰሱ ከተወሰነ በኋላ የታለፉት “የሲዳማ ብሔረሰብ ይነሳል” በሚል እንደሆነ ያወሱት ምንጮች “ክስ ተመስርቶ ምርመራው ቢካሄድባቸው ወ/ሮ አዜብም አሉበት ሲሉ አስቀድመው በምክር ቤት ይፋ በማድረጋቸው ዝምታ ተመርጧል”።
ኦህዴድን ወደ ታች ማዘዝ እንደ ቀድሞው አይቀልም
አዲስ አበባን የሚያሰፋው አዲሱ ማስተር ፕላን ተግባራዊ እንዲሆን ሀሳብ ሲቀርብ ድፍን የኦህዴድ ምክር ቤትና ካቢኔ ተቃውሞ አሰምቷል። በክልሉ ምክር ቤት ደረጃም የተያዘው አቋም ተመሳሳይ ነው። ይህንን እውነት የሚያነሱ ክፍሎች ኢህአዴግ/ህወሃት ስንቱን አስሮና ለፍርድ አቅርቦ ይችለዋል ሲሉ ጥያቄ ይሰነዝራሉ” ቀደም ሲል በምርኮኞች ስብስብ የተቋቋመው ኦህዴድና አሁን ያለው ኦህዴድ የተለያዩ መሆናቸውን ኢህዴግ ችግር ሊገጥመው እንደሚችልም ግምታቸውን ያስቀድማሉ።
አሁን ያለው ኦህአዴድ ከምርኮ አስተሳሰብ የተላቀቀ። አዲስ ትውልድ የተካተተበት፣ በጎሳ አስተሳሰብ የተቃኙ፣ ህወሃት በሚፈልገው መጠን ከመታዘዝ በላይ ወደ ራሳቸው ደምና ጎሳ የተሳቡ፣ ይህንኑ አስተሳሰብ እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ የተከሉ በመሆናቸው የተወሰኑ የበላይ አመራሮችን በማሰር ችገሩ ሊፈታ እንደማይችል ሰፊ አስተያየት እየተሰጠ ነው። ለዚህም ይመስላል ኢህአዴግ በመደብ መተላላቅ መጀመሩ ይፋ እየሆነ የመጣው።
የመጨረሻው መጀመሪያ
ለጊዜው ይፋ ሆኑ መረጃዎች እንደሚያመክቱት አባዱላና አቶ ድሪባ ኩማ ካገር መውጣት አይችሉም። የተጀመረው ግምገማ ተጠናቆ የሚሆነው ሳይታወቅ በቅርብ ክትትል ስር ናቸው። የጎልጉል ምንጮች እንደጠቆሙት የዞንና ወረዳ መዋቅሮች ላይ ርምጃ ለመውሰድ ስጋት አለ። ካድሬው ዘንድም መደናገጥ ተፈጥሯል። ህወሃት ውስጥም የአቋም መለያየት ተከስቷል፡፡ በአንድ ወገን ካድሬው እንዳይሸፍትና በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን አሳልፎ እንዳይሰጠው ርምጃው የተለሳለሰ መሆን አለበት እየተባለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ግለ ሂስ በማካሄድ ነገሩን የማርገብና ምርጫውን የማለፍ ስልታዊ አካሄድ አለ። ይሁን እንጂ ኦህዴድ እየተለማመደ ያለው አካሄድ ሌሎችን ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ካልታረመ ወደ ፊት ችግሩን ያገዝፈዋል የሚል አቋም የሚያራምዱ መኖራቸው ታውቋል። ህወሃት በዚህ ደረጃ አቋም ለመያዝ አለመቻሉና በርዕዮተ ዓለም መከፋፈል መጀመሩ ለዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የዘራው መርዝ መልሶ ራሱን ሊያጠፋው አፉን መክፈቱ የሚጠቁም ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት “ኢህአዴግ በርዕዮተ ዓለም መበላላት መጀመሩ ይፋ እየሆነ ነው” የሚለው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሳ ዓቢይ ጉዳይ ሆኗል፡፡
source: goolgul.com