ለሽያጭ ከሚቀርቡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ግዮን ሆቴል እንዲወጣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ትዕዛዙ የተሰጠው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ግዮን ሆቴልን ከሽያጭ ውጪ አድርጐታል፡፡
የኤጀንሲው ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ግዮን ሆቴል እንዳይሸጥ መመርያ መሰጠቱን ገልጸው፣ ነገር ግን ስለሆቴሉ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አንጋፋውን ግዮን ሆቴል ለመሸጥ ለበርካታ ጊዜያት ጨረታ አውጥቷል፡፡ ከጨረታ በተጨማሪም ሆቴሉን ለመግዛት ፍላጐታቸውን ካሳዩ ኩባንያዎች ጋር ሲደራደር ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ሆቴሉን የሚገዛ በመጥፋቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሽያጭ ሒደቱ እንዲቋረጥ ማድረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የፕራይቬታይዜሽን ምንጮች እንደሚሉት ግዮን ሆቴልን ለመግዛት የተካሄዱት በርካታ ድርድሮች የከሸፉት፣ በዋጋ ውድነትና በተለያዩ መደራደሪያ ነጥቦች ምክንያት ነው፡፡
በ1950 ዓ.ም. የተመሠረተው ግዮን ሆቴል በ123 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ነው፡፡ ሆቴሉ 191 መኝታ ክፍሎች፣ ሰባት የመሰብሰቢያ አዳራሾችና አንድ የመዋኛ ገንዳ አለው፡፡ የተለያዩ ሬስቶራንቶችም አሉት፡፡
የአፄ ኃይለ ሥላሴ ልጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አክሊለ ብርሃን መኰንን 8.3 ቢሊዮን ብር በማቅረብ የሆቴሉን 80 በመቶ ድርሻ ለመያዝ ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ቢፈራረሙም፣ ተግባራዊ መሆን አልቻለም፡፡
ሆቴሉ ያሉት ሕንፃዎች አሮጌ የሚፈርሱ በመሆናቸው ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ያስቀመጠው መነሻ የመሸጫ ዋጋ ከፍተኛ ነው የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡
በመጨረሻ ግን ግዮን ሆቴል የመንግሥት ይዞታ ሆኖ እንዲቀጥል የተወሰነ በመሆኑ፣ መንግሥት ተጨማሪ ወጪ በማውጣት ማሻሻያ ካደረገለት በኋላ ሆቴሉን በአምስት ኮከብ ደረጃ ለማሳደግ ዕቅድ አለው፡፡
ሆቴሉ በአመቺ ቦታ ላይ ሰፊ ይዞታ ያለው በመሆኑ የማሻሻያ ሥራ ከተሠራበት ትልቅ ገቢ የሚያስገባና አትራፊ የመንግሥት የልማት ድርጅት እንደሚሆን ለሆቴል ሥራ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡
Source: Ethiopian Reporter