ከጌታቸው ሽፈራው
የመመረቂያ ጽሁፌን ለመጨረስ ደፋ ቀና እያልኩ ባለሁበት ወቅት ነው አንድ የማላውቀው ስልክ የተደወለልኝ፡፡ ይህ ስልክ አባል ባለመሆኔ ስራ እንደማላገኝ ተስፋ ወደመቁረጥ በተቃረብኩበት ወቅት ለስራ እንደምፈለግ አበሰረኝ፡፡ ስልኩ ከኢመድኤ (INSA) መሆኑ ተነግሮኛል፡፡ ይህን መስሪያ ቤት ስም ፈጽሞ ሰምቼው አላውቅም፡፡ ለጓደኞቼ ሳወራቸው ከእኔ በፊት አብዛኛዎቹ ተደውሎላቸው እንደነበር አጫወቱኝ፡፡ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ የደኢህዴን ልጆች እርስ በእርሳቸው እንደተጠቋቆሙም ወሬ ደረሰኝ፡፡ በስተመጨረሻ እኔም መጠራቴ ነው፡፡ ሌላኛው ግራ የሚያጋባው ወሬ ግን መስሪያ ቤቱ የስለላ ተቋም እንደሆነ መስማቴ ነው፡፡ ሁለት ሆድ ሆንኩ፡፡ የኋላ ኋላ አይቶ መውጣቱ እንደሚሻል ወሰንኩ፡፡ አንድ በጣም የሚቀርበኝ ጓደኛዬ ስለተቋሙ ካጫወተኝ በኋላ እንዲቀጥሩኝ አባል መሆኔን (ሸውጄ) እንድነግራቸው አግባባኝ፡፡ አልፈለኩም፡፡
ለጥያቄ የተቀጠርንበት ቀን ደረሰ፡፡ ለፈተና ቀረብን፡፡ ጥያቄዎቹ ከጠበቅናቸው በላይ ናቸው፡፡ ከጠበቁት በላይ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውልኛል፡፡ ከዚህ መርህ ያፈነግጣሉ የተባሉ ጓደኞቻችን ሳያልፉ ቀርተዋል፡፡ ፈተናውን አልፈን ለስልጠና በገባንበት ወቅት ደግሞ ሌላ ተስፋ ሰጭ ጉዳይ ተከሰተ፡፡ በነጻነት መከራከር ቻልን፡፡ በአንድ ትምህርት ዘርፍ (ፖለቲካል ሳይንስ) ለቅጥር ያለፍነው 12 ወጣቶች ሌሎቹን እንድናስተባብር በየ ውይይት ክበቡ ተሰባጠርን፡፡ ኢንሳን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውን የሚርቁትን ይቀይራሉ ተብለንም ‹‹12ቱ ሐዋሪያት›› የሚል ስም ወጣልን፡፡ በኋላ አንዷ የውጭ አገር እድል አግኝታ ስትወጣ ‹‹ይሁዳዋ!›› ብለን ተሳልቀንባታል፡፡ ይሁዳ ያወቀው ይህኔ ነው፡፡ ነገር ሳይበላሽና ሳይቆስሉ ቦታ መያዝን የመሰለ ነገር የለም፡፡
ስልጠናውን ጨርሰን ለአንድ አመት ያህል በነጻነት ሰራን፡፡ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ አቋም ስራ ላይ ማንጸባረቅ አይፈቀድም ተባልን፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ አሁን አሁን ሳስበው ግን ለኢንሳዎች ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ማለት ኢዴፓ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አንዱ ‹‹አለቃ›› ስለጉዳዩ ተናግሮ ሳይጨርስ ‹‹ይህን ስል ግን የኢዴፓን አቋም እዚህ (ስራ) ላይ ማንጸባረቅ ይቻላል ማለት አይደለም፡፡›› ሲል አስታውላለሁ፡፡
ብቻ ያ ጊዜ ለመስሪያ ቤቱ መልካም አመለካከት የነበረን ጊዜ ነው፡፡ ጅራትና ምንድን ነበር ወደኋላ የሚመጣው? በእርግጥ ከዚህ በፊት ኢንሳ ጠለፋና ሌሎቹንም ነገሮች እንደሚሰራ መስማት ጀመረናል፡፡ ስለ ጉዳዩ እርግጠኛ ባንሆንም የት ነው የምትሰራው ተብሎ ‹‹ኢንሳ!›› ለማለት የሚያኮራ አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ ጓደኞቻችን ‹‹ሰላይ!›› እንመስላቸው ነበር፡፡ የእኛ አገር ችግር ይህ ነው፡፡ ስለላን ገዥዎች አበላሸተውታል፡፡ ህዝቡም ሆነ ሰላይን መልሶ መሰለል የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ዝም ብሎ መራቅ፡፡ ዝም ብሎ ማማት ብቻ ነው፡፡
አሁን ጅራትና ጉድ ጭራሹን እየፈጠጡ መጡ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አትችሉም ተባለ፡፡ መጀመሪያ የነበረን ተስፋ ሁሉ እንደገና ተስፋ አጣ፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ነው፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንደ አንዳች ክፉ ነገር የሚጠሉትና የሚጠየፉት አቶ መለስ ሰንደቅ አላማውን ከላይ ወደታች ገለበጡት፡፡ እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ‹‹ሰውዬው ለምን ሰንደቅ አላማውን ገለበጡት?›› የሚል ጥያቄ አነሳሁ፡፡ ከቀናት በኋላ ይህን ሰንደቅ አላማው ላይ የጻፍኩትን ትንሽዬ ነገር ተከትሎ 12 አስቂኝ ከስሶች ቀረቡብኝ፡፡ አብዛኛዎቹ ህገ መንግስቱን ካለመቀበል፣ የፖለቲካ ቡድኖች (እነማን እንደሆኑ እነሱው ይወቁት) አባል ሆነሃል እና ጽንፈኝነት ጋር የተለነቀጡ ናቸው፡፡ በዝርዝር የአሰብ ወደብን የኢትጵያ ነው ብለሃል፣ ኢትዮጵያ የውጭ ብድር አለባት ብለሃል፣ የጋዳፊን ፎቶ ግራፍ አጋርተሃል (ሸር አደርገሃል)፣ ከጉራፈርዳ ስለተባረሩት አርሶ አደሮች ጽፈሃል፣ ኢህአዴግን ግንባራም ብለሃል……የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በእነዚህ ክሶች መሰረትም ለ2 ወራት ያህል ከስራ ታገድኩ፡፡ በዚህ ወቅትም ለክሶቼ መልስ እንድሰጥ ታዝዣለሁ፡፡ እናም ክሱ እንዲነሳልኝ የክሶቹን ፍሬ ቢስነት ጠቅሼ ተከራከርኩ፡፡ አይ እኔ ሞኙ! ህግ በሌለበት፡፡ በዚህ ክርክር የዲስሊን ኮሚቴ አባል ናቸው የተባሉ የህወሓት አባላት ልክ እንደ ከሳሽ ‹‹እንዴት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ታንቋሽሻለህ›› የሚል ክስ አቅርበው ተከራክረውኛል፡፡ የብአዴን አባላት ደግሞ እነሱን ተከትለው አስተጋብተዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ‹‹በከፍተኛ ወንጀል›› ተባረርኩ፡፡ በዚህ ወቅት አንድ የብአዴን ካድሬ ያለኝ መቼም ሊረሳኝ አይችልም፡፡ የቅርብ አለቃዬ ስለነበር ስለ ነበረኝ ስነምግባር፣ ስለ ስራ አፈጻጸም፣ ክስ የተባሉት የማያስከስሱኝ መሆኑን ገልጬ መባረሬ አግባብ አለመሆኑን አሳወቁት፡፡ እሱም ‹‹ዋናው ታማኝ መሆን ነው፡፡›› ብሎኝ አረፈው፡፡ ኢህአዴግ ብትሆን አትባረርም ነበር ለማለት ነው፡፡ የሚገርመው ይህ ካድሬ ፌስ ቡክ ላይ እራሱን ፈላስፋ አድርጎ ስለነጻነትና ፍትህ ሲዛላብድ የሚውል መሆኑ ነው፡፡
ከተባረርኩ ከሳምንት በኋላ መሰናዘሪያን ተቀላቀልኩ፡፡ ከወራት በኋላ (ጥቅምት 20) ደግሞ አቶ መለስ የማይወዱት ሰንደቅ አላማ በዓል ተከበረ ተባለ፡፡ በእውኑ ግን ተከብረው የዋሉት ሟቹ ሰውዬ ናቸው፡፡ ጥቅምት 21 መሰናዘሪያ በፊት ገጽ አንድ ጽሁፍ (የእኔው ነው) ይዛ ወጣች፡፡ መለስ የገለበጡትን ሰንደቅ አላማ አንግባ ‹‹እውን ኢህአዴግ ሰንደቅ አላማውን ያከብረዋልን?›› የሚል ነው፡፡ መሰናዘሪያ በሳምንቱ አልተመለሰችም፡፡ አታሚው ኢህአዴጎችን ሰንደቅ አላማው ላይ የተጻፈው ጽሁፍ ስላስቆጣቸው እንዳያትም እንደነገሩት አስታወቀን፡፡ በቃ ዳግም ተባረርኩ ማለት ነው፡፡ አሁን ሌላ ስራ መፈለግ ይጠበቅብኛል፡፡ የኢንሳን ልምድ ሳሳይ ደግሞ በርካቶች ይበረግጋሉ፡፡ በግል ሚዲያው ብጽፍም በቋሚነት ለማሰራት አቅም አልነበራቸውም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከገዥው ፓርቲም በላይ ለሚዲያውም ሆነ ለሰራተኛው በዝባዥና ገዳዮች ሆነው አግቻቸዋለሁ፡፡
እንዲህ እንዲህ ስል ለሁለት አመት ያህል ቋሚ ስራ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ አራት አመት ያህል ደግሞ ከቤተሰብ ጋር ተቆራርጫለሁ፡፡ 18 አመት ያህል አስተምራኝ፣ ስራ ይዠያለሁ ያልኳትን እናቴን እንዴት ተባርሬያለሁ ልበላት? በፖለቲካ አቋሜ ተባረርኩ ብላት ደግሞ ከዚህ ሁሉ የባሰ ይሆናል፡፡ እናም ዝም ብዬ ስራ ፍለጋ መኳተኑን ያዝኩት፡፡ መነኩሴዋን እናቴን አይኗን ሳላያት አራት አመት ሞላ፡፡ ዛሬ ነገ እሄዳለሁ ስል ቀኑ ነጎደ፡፡ ከዛሬ ነገ አግይቼ አይኗን አያታለሁ ያልኳት እናቴም እንደሳሳኋት፣ እሷም እንደሳሳች ለወዲያው ላንገናኝ ተለያየን፡፡ እናቴ አለፈች፡፡ ያለ አግባብ የተፈናቀልኩበትን ስራ ልይዝ፣ ከያዥኩ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ‹‹ልረጋጋ!›› ላይ ታች ስል ለረዥም ጊዜ የተለየኋት እናቴ አመለጠችኝ፡፡
በእርግጥ እናቴ ወርቅን በባሌስትራ ከሚቀይሩት ወገን አይደለችም፡፡ መሬት አልሸጠችም፡፡ ህዝብን በጠባብ ማንነት አልከፋፈለችም፡፡ አገር አላስገነጠለችም፡፡ ሰንደቁን አላዋረደችም፣ አልዘቀዘቀችም፡፡ የህዝብ መብት አላፈነችም፡፡ የህዝብ ገንዘብ ወደ ውጭ አላሸሸችም፡፡ ንጹሃንን አልገደለችም፣ አላሰረችም፡፡ አላፈናቀለችም፡፡ እናቴ ንጹህ ነች፡፡ የእሷ ነፍስ የገነት ነፍስ ነች፡፡ ሌሎች ግን የሞት ሞታቸውን ሞተዋል፡፡ ትውልድም አጥንታቸውን እንደረገመ ይኖራል፡፡
እኔም እላለሁ፡፡ ሞት ማለት የሞት ሞት ሲሆን ነው፡፡ ይህን እናቴ አልሞተችውም፡፡ ምስኪኗ ወላጅ እናቴ የክብር ሞቷን ስትሞት አሁን ለእኔ የቀረኝ አንዲት እናት ብቻ ናት፡፡ እናት አገር ኢትዮጵያ! አገር ብትኖር ወላጅ እናቴ ተቀብራበታለች፡፡ እኔም አልቅሸበታለሁ፡፡ አዎ! ወላጅ እናት ባትሞት እጅጉን መልካም ነበር፡፡ ከሞተች ግን ምን ይደረጋል? ብቻ እናት አገር አትሙት!
እናቴ ሆይ! አምባገነኖቹ ፊቴ ላይ የደቀኑብኝን አቀበት ለመውጣት ስጥር አንቺ አምልጠሽኛል፡፡ አሁን ብችል እናት አገርን ለማዳን ከሌሎቹ ጋር ሆኜ ጠጠር ለመጣል፣ ጥረቴ ለዚህ ባይበቃ እንኳ የራሴን መብት ለማስከበር፣ ይህንን ደግሞ ባልችል ሆድ አደር ላለመሆን አቀበቱ ላይ ነኝ፡፡ ሞት አይቀርምና አንድ ቀን እንደምሞት አውቀዋለሁ፡፡ የሞት ሞት መሞት ግን አልፈልግም፡፡ ደግሞም ከአንቺ ጋር ያለያየኝን አቀበቱን ወጥቼ ሜዳው ሳልደርስ ባልከተልሽ ደስ ይለኛል፡፡ በዚህ አንቺም እንደማትቀየሚኝ አውቃለሁ፡፡ እስከዚያው ግን አምላክ ነፍስሽን በገነት ያኑራት!