አቦ የምን መጨነቅ ነው? የምን መጨናነቅ! የምን መተጋተግ! ተነሱ እስቲ አንዴ ከመሐመድ ወርዲ ጋር ዓለማችንን እንቅጭ! ተነሱ እስቲ ከዚህ ጭቅጭቅና ጭንቅንቅ የበዛበት ዓለም ወደ ፍቅር ሐድራ እንሰደድ! ቅዳሜያችንን ከመሐመድ ወርዲ ጋር ቅዳሜ እናስመስል! በ“ገመር ቦባ” ድብርቱን እናባርር! በ“ቲስዓተ ዐሸር ሰና” የህይወት ምርጫንችን እናሳምር! በ“ሱድፋ” እድላችንን እንሞክር! በ“ፉአዲ ሐኒን” ውበታችንን እንለካው! በ“አነ ማ በንሳክ” ቃልኪዳናችንን እናድስ!
በየፌርማታውና በካፍቴሪያው ተደብተህ የተጎለትከው ሆይ! እስቲ ለዛሬዋ ቀን ተከተለኝ፡፡ በሓሳባችን ወደ ውቢቷ “ኻርቱም” በርረን በሐሴት አውድማ ላይ ውበት ሲመላለስ አብረን እናያለን፡፡ የምስራቅ አፍሪቃ ህዝቦች የጋራ ጌጥ የሆነው ሙሐመድ ወርዲ ቅዳሜአችንን ቅዳሜ ሊያስመስለው ተዘጋጅቷል፡፡
——–
በቅድሚያ የቱን ልጋብዝህ/ልጋብዝሽ? ከ“አነ ዐርፈክ ያ ፉአዲ” ብጀምርልህ ይከፋሃል? እንዴት ሆኖ ነው የሚከፋህ ጃል?.. እንዲያውም ዜማውን በደመ-ነፍስህ ጭምር ስለምታውቀው በቅድሚያ እርሱን ብጋብዝህ ነው ቅዳሜያችን የሚያምርልን፡፡…. ምክንያቱም ዜማውን የኛ ውድ የሆነው ጥላሁን ገሠሠ ሲያዜመው ሰምተህዋልና ነው፡፡ ጥላሁን እንዲህ ብሎ ሲዘፍን ሰምተኸው አልነበር?
አንቺ ከቶ ግድ የለሽም
ስለፍቅር አይገባሽም
ሁሉን ነገር እረስተሽው
ችላ ብለሽ ስለተውሽው
ቻልኩት ፍቅር ለብቻዬ
አዎን! እርሱን ነው የምልህ ወዳጄ! ሙሐመድ ወርዲ በዚሁ ዜማ ምን ብሎ ነበር መሰለህ?
“አነ ዐርፋክ ያ ፉአዲ
ጠል ዐዛበክ ዋ ሱሃዲ
ዋ ሽጃያ አነ ዐዛቢ”
ነበር ያለው፡፡ ታዲያ ሙሐመድ ወርዲ የዘፈነውን ጋሽ ጥላሁን እንዲሁ በጋጠወጥነት ወደ አማርኛ የመለሰው እንዳይመስልህ! የወርዲ ቡራኬ አለበት፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመን የካርቱም መንገድ ለኛ የውሃ መንገድ ነበረ፡፡ ለሱዳኖችም ከዋዲ ሃልፋ ይልቅ ሸገር ትቀርባቸው ነበር፡፡ እናም በዚህ ምልልስ መሀል የኛዎቹ አንጋፋዎች (ጥላሁን ገሠሠ፣ ምኒልክ ወስናቸው፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ዓሊ ሸቦ፣ ዓሊ ቢራ ወዘተ..) እና የሱዳኖቹ ገዲም አርቲስቶች (አሕመድ አል-ሙስጠፋ፣ ሰይድ ኸሊፋ፣ ሙሐመድ ወርዲ፣ አብዱልከሪም አል-ካብሊ፣ አብዱል ዓዚዝ አል-ሙባረክ ወዘተ…) የአንድ ቤተሰብ ልጆች ሆነው ነበር፡፡ ሱዳኖቹ ያዜሙትን የኛዎቹ ወደ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ሶማሊኛ እየመለሱ ይጫወቱታል፡፡ የኛንም ዘፈን ሱዳኖች በቋንቋቸው እየተረጎሙ ይዘፍኑታል፡፡ አንዳንዴ ዕድል ሲገጥማቸው ሁለቱም አንዱን ዜማ በአንድ መድረክ ላይ በየቋንቋቸው ይጫወቱታል፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ነው እንግዲህ የሙሐመድ ወርዲ “አነ ዐርፈክ ያ ፉአዲ” ወደ አማርኛ የተመለሰው፡፡ አገኘኸኝ አይደል? እንዲያ ነው ነገሩ ወዳጄ! እነ ጋሽ ጥላሁን እንደ አሁኖቹ ዘፋኞች (አንዳንዶቹን ማለቴ ነው) የሱዳንና የፈረንጅ ዜማን ወደ አማርኛ እየገለበጡ “የራሴ ድርሰት ነው” ብለው ሊያሞኙን አይከጅሉም፡፡ ዋናው አርቲስት ባለበት ጭምር እየዘፈኑ ያሳዩትና “እንዴት ነው! አበላሽቼብህ ይሆን?” በማለት ምክርና እገዛ ይጠይቁታል፡፡ ሱዳናዊው አርቲስትም በሰማው ነገር ላይ የራሱን አስተያየት ይሰጣል፡፡ የኛዎቹም ከሱዳናዊያኑ አርቲስቶች የሚሰጣቸውን አስተያየት ተንተርሰው እጅግ የተሻለ ስራ ይሰሩና ህዝቡን እንካችሁ ይሉታል፡፡ ለዚያም ነበር ስራው የሚዋጣላቸውና ዘመን ተሻጋሪ የሚሆንላቸው፡፡
*****
አዎን ወዳጄ! ኑሮ አይሞላም፡፡ ላይሞላ ነገር ሁልጊዜ “ተዐብ ዘምዛሚ” መሆን አንችልም፡፡ ሁል ጊዜ መነጫነጭ ይገድለናል፡፡ “ራሃ” እና “ፌሽታ” በአቅማችን ማድረግ አለብን! በዛሬዋ ቀን ጭንቀትን ድራሽ አባቱ እናጥፋው፡፡ እናም የወርዲ ግብዣዬን ልቀጥልልህ!
በርካታ የሀገራችን የሙዚቃ ወዳጆች ከመሐመድ ወርዲ ዜማዎች መካከል ለ“ገመር ቦባ” እና ለ“ቲስዐተ ዐሸር ሰና” (ብዙዎች የሚያውቁት “ሰበርታ” በሚለው ስም ነው) ልዩ ፍቅር አላቸው፡፡ እኔ ግን ብዙ ልጠራልህ እችላለሁ፡፡ በተለይም “ሱድፋ”፣ “ቃሲ ቀልበክ”፣ “አልሀወል አወል”፣ “አነ ማ በንሳክ”፣ “አዚብኒ ወተፈነን”፣ “አንናስ አል-ጊያፋ”፣ “ሐረምተ አድ-ዱንያ”፣ “ያ ኑረል ዐይን”፣ “ሸተል ዘማ”፣ “አል-ሙርሳል” የመሳሰሉትን በአንደኛ ደረጃ አሰልፋቸዋለሁ፡፡ ታዲያ ከዚህ ቀጥዬ የትኛውን ልጋብዝህ?… “ሱድፋ”ን ልመርጥልህ ወድጄ ነበር፡፡ ሆኖም ቪዲዮውን ከበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ላገኘው አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ በቅርበት ያገኘሁትንና ሙሐመድ ወርዲ የዛሬ 18 ዓመት ገደማ በኛ ስታዲየም የተጫወተውን “ዐዚብኒ ወተፈነን”ን ልጨምርልህ፡፡ እግረ መንገድህን የኛ ህዝብ ወርዲን ምን ያህል እንደሚወደው ታይበታለህ፡፡
ዐዚብኒ ወዚድ ዐዘባ ዩምኪን ገልቢ ይክሳዚይክ
ዜይመን ሳኒ ገልበክ ዩምኪን ገልቢ ይክሳዚክ፡፡
አዚብኒ ወተፈነን ፊ አልዋን ዐዛቢ
ማ ቲምሳሕ ዲሙዒ ማ ቲርሐም ሸባቢ፡፡
ኸሊኒ ፊሹጁኒ ዩምኪን ገልቢ ይክሳዚይክ
ዜይ መንሳኒ ገልበክ ዩምኪን ገልቢ ይክሳዚይክ፡፡
ቪዲዮውን በሚከተለው ሊንክ ላይ ተመልከተው….
በመሀሉ የዛሬዋ ቅዳሜ ምርጫችን ስላደረግነው ሙሐመድ ወርዲ ታሪከ-ህይወት ጥቂት ሐተታ ካስፈለገህ እነሆ ልበልህ ወዳጄ!
ሙሉ ስሙ ሙሐመድ ዑስማን ሳሊሕ ወርዲ ነው፡፡ እርሱ ግን “ሙሐመድ ወርዲ” ወይንም በአጭሩ በቤተሰቡ ስም “ወርዲ” ተብሎ ነው የሚታወቀው፡፡ የተወለደው እ.ኤ.አ. በ1932 ዋዲ ሀልፋ በተሰኘው ሰሜናዊው የሱዳን ክፍለ ሀገር፣ “ሱወርዳ” በተባለች ትንሽዬ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፡፡ እናቱ የኑቢያ ተወላጅ ስትሆን አባቱ ዐረብ ነው፡፡ ወርዲ የሙት ልጅ ነው፡፡ ሁለቱንም ወላጆቹን በልጅነቱ ነው ያጣው፡፡ በመሆኑም በዘመዶቹ ጥበቃ ስር ሆኖ ነው ያደገው፡፡ ትምህርቱን በዋዲ ሀልፋ እና በካርቱም ተከታትሏል፡፡ የተወለደበትን ሀገር እስከ 1956 በመምህርነት ሙያ ካገለገለ በኋላ በወቅቱ ይሞካክራቸው የነበሩት ዘፈኖች በኦምዱርማን ሬድዮ ጣቢያ ተቀርጸው በመተላለፋቸው በህዝብ ልብ ውስጥ ገባ፡፡ ያገኘው የሞራል ድጋፍ ማነሳሻ ስለሆነው መምህርነቱን ትቶ የአርቲስትነቱን ጎራ ተቀላቀለ፡፡ ከዚያም ሱዳኖች ከሚያፈቅሯቸው ቁንጮ ዘፋኞቻቸው አንዱ ለመሆን በቃ፡፡
ወርዲ በህይወቱ የተረጋጋ ኑሮ አልኖረም፡፡ በሱዳን የተለዋወጡት መንግሥታት በተቃዋሚነት እየፈረጁት አንገላተውታል፡፡ በመሆኑም ለሀያ ዓመታት ያህል በካይሮና በለንደን ነው የኖረው፡፡ በ2002 ግን ወደ ሀገሩ በክብር ተመልሷል፡፡ ወርዲ በሙዚቃው ዕድገት ላደረገው አስተዋጽኦ ከካርቱም ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸልሟል፡፡ ከልዩ ልዩ የአውሮጳ፣ አፍሪቃና እስያ ሀገራትም ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡ ሱዳኖች እ.ኤ.አ. በ2000 ባደረጉት ምርጫ “አል-ገመር ቦባ” የተሰኘው ዘፈኑ የክፍለ ዘመኑ ምርጥ “ነጠላ ዜማ” ተብሎ ተመርጧል፡፡ መሐመድ ወርዲ በመጨረሻዎቹ ዓመታት በደረሰበት የጤና መታወክ ሁለት ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ ሆነው ነበር፡፡ ይኸው የኩላሊት ህመም ፋታ ነስቶት በየካቲት ወር 2012 ከዚህች ዓለም አሰናብቶታል፡፡
መሐመድ ወርዲ ከብዙ በጥቂቱ እንዲያ ነበር፡፡ አሁን በርሱ ዘፈኖች “ራሓ” ማድረጋችንን እንቀጥል፡፡
—-
ታሕሳስ 6/2013