ከሠሎሞን ታምሩ ዓየለ
ክፍል 4
በክፍል 3 መጣጥፌ በዋናነት የአገራችን የተፈጥሮ ሃብቶችና ዓየር ንብረቷም ለተለያዩ አዝርዕቶችና ኦንስሳቶች ልማት ምቹነቱን በመግለጽ ነበር ያቆምኩት። አሁን በሚቀጥለው ደግሞ በክፍል 2ት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያልቻልንባቸውን መሠረታዊ ተግዳርቶች ውስጥ እንደ መንስኤ የቆጠርነው የመንግስትን በተለይም የአምባ ገነንነት ቅርጽ የያዙት የሚከተሉት ያልተስተካከለ የግብርና ፖሊሲ ተወግዶ በምትኩም ትክክለኛውና ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ ምንን ማዕቀፍ ማድረግ እንዳለበት የአቅሜን ያህል ለማሳዬት ነው።
እንዲህ ልጀምር። በፖሊሲ ጥየቄና ዝግጅት የተለየ ትምህርት ወይም ሥልጠና የለኝም። ፖለቲከኞች፤ የመንግስት ሹማምንቶች፤ ኢኮኖሚስቶች፤ ለሎችም የማኀበራዊ ሳይንስ ሰዎችና በስፋትም በትልልቅ ኮርፖሬሽኖችና ካምፓኒዎችም ውስጥ ቃሉ ተደጋግሞ ይደመጣል። እኔም ከጊዜ ብዛት ትንሽ የገባችኝን ያህል ላክልባት። ” መወያየት መልካም” የሚል አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራም እንደ ነበር ትዝ ይለኛልና ያንን መሰረት በማድረግ ልቀጥል። የአገሬ የፖሊሲ ማውጣት ስራዎች እንዴት እንደሚዘጋጁና እንደሚጠናቀቁ፤ ዋነኛ ተቋሞቹ የት የት እንደሚገኙ ግን ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እኔንም ጨምሮ የምናውቀው አይመስለኝም ( ምን አልባት መንግስት ጓዳ ይሆን)። ለመሆኑ ፖሊሲ ምንድነው? ፖሊሲ ሃሳብ፤ መርህ፤ አቅጣጫ፤ ሥርአት፤ መንገድና መመሪያ ነው ብል ትልቅ ስህተት የሰራሁ አይመስለኝም። ባጭሩ ፖሊሲ በህግ፤ በአዋጅ፤ በደንብ ፤ በትዕዛዝ፤ በመመሪያና በአሰራር ተደግፎ ወደ ተግባር ለመለወጥ ይመነዘራል። የፖሊሲ ምንጩ ወይም መነሻው ችግር ነው ቢባልም ማጋነን አይሆንም። የችግሩ አብዛኛውን ጊዜ ሰለባ ወይም ተጠቂ ደግሞ ሕዝብ ነው። ስለዚህ እውነተኛና ሕዝባዊ ፖሊሲ የሕዝብን የልብ ትርታ (አመታት በህክምና ሰዎች ቋንቋ) አዳምጦና ተከትሎ የሚዘጋጅ ሰነድም ነው። ፖሊሲ አንዴ ከተነደፈ ችግር የለውም ማለትም አይደለም። እንደ አፈጻጸሙና አካሄዱ አመቺነት፤ እንደአስከተለው ችግር ቀላልነትና ግዝፈት ይለወጣል፤ በሌላም ይተካል፤ ይዳብራል፤ ይታደሳልም። መሠረቴና መኖሬ ለሕዝብ ነው ብሎ የተነሳ መንግሥት ደግሞ የፖሊሲውን ጥቅም ለሕዝብ አገልግሎት ቅድሚያ ይሰጣል። ፖሊሲው ሲነደፍ ከአሰራር ዝርክርክነት የጸዳና ለሚነሱ ጥያቄዎችም የጠራ መልስ የሚሰጥና ኃላፊነት፤ ተጠያቂነትና በሕዝብ ተአማኒነትና ተቀባይነት አንዲኖረው ያስፈልጋል። ለብዙሃን እንጂ መቆም ያለበት የጥቂቶችን ጥቅም ማስጠበቂያ መሳሪያ መሆን እንደሌለበት ዕሙን ነው። የአንድን አገር መሪ ቃል ብቻ ወይም የአንድን ፖለቲካ ፓርቲ የአቋም መስመር ተከትሎ እንደ መዘውር መንዳት የኋላ የኋላ ገደል ይዞ ይገባል። ባጭሩ ፖሊሲው የሕዝብ ፍላጎት መሆኑን በዚህኛው ወይም በሌላኛው ዘዴ ደህና አድርጎ ማረጋገጥ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። የተዘጋጀው ፖሊሲ ሕዝባዊነት ከሌለው ደግም ተቀባይነቱና ተአማኒነቱ ይቀንሳል፤ ጭራሹንም ይጠፋል። የመንግስት ፖሊሲ ተቀባይነት የሚገመገመውም ለመንግስት ሹመኞችና ለቅርብ ባለስልጣናት በሚሰጠው ደስታና ፌሽታ ሳይሆን በሕዝብ ኑሮ ላይ በሚያመጣው አሉታው ወይም አዎንታዊ ገጹ እየታየ ነው። መንግስትም ይህንን ተገንዝቦ ያለመስማት ወይም ያለማዳመጥ ፖሊሲውን አዲዮስ ማለት አለበት። ምሁራን የሚሰጡትን ገንቢ አስተያዬት አሌ ማለት አይገባም። አንድ ወቅት ላይ በ1984 ዓም መሰለኝ ፕሮፌሰር መስፍን ኃ/ ማሪያም ከመንግስት ሰዎች ጋር እሰጥ እገባ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለይ ጀምረው ሳለ እንዲህ እንዳሁኑ ነጻ ጋዜጦችና ድረ ገጾች ውድ በሆኑበት ጊዜ የሚከተለውን ተናግረው ነበር። “መንግስትና ምሁራን በኢትዮጵያ ሆድና ጀርባ ናቸው” ። በሃሳብም፤ በግብርም አልተገናኙም፤ አልተዋሃዱም ማለት ነው። ልጆች ሳለን ለሙሽሮች የምንዘፍነው ዘፈን ትዝ አለኝ። የሙሹሮችን መግጠምና መዋሃድ ለማብሰር እንዲህ በማለት ገጥመናል። እከሊትና እከሌ ምንና ምን ናቸው፤ የጆሮ ጉትቻ የአንገት ሃብል ናቸው። መንግሥትም ሕዝብ የኔ ነው ያላለውን ፖሊሲ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ሲል ከሕዝብ ጋር ይጋጫል፤ ይቀያየማል፤ የተቃወሙትን በአደባባይ ይደበድባል፤ ያስራል፤ ይከሳልም፤ እስርም ይፈርዳል። ከፍ ካለ ደግም የጠመንጃ ቃታ ስቦ ደም ካፈሰሰ በኋላ በሰራው አስነዋሪ ሥራ ከተጠያቂነት ለማምለጥ በቁጥጥሩ ሥር ባደረጋቸው መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም “አንዳንድ የኅ/ሰቡን ሰላም ለማደፍረስ “ የሚል መግለጫ ይሰጣል፤ ይፎክራል፤ ያቅራራል ፤ ያስፈራራል። አንዳንዴም ሁኔታዎች አስጊ መሰሎ ከታየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል። ይህችን ፓራግራፍ በዚህች ጨዋታ ወይም ቀልድ ልቋጫት። አብሮኝ በአምቦ እርሻ ተቋም የተማረና በኢሉአባቦር ግብርና ተጠሪ ጽ/ ቤት በተለያዩ አውራጃዎችም ተመድበን ስንሰራ የነበረ ጉዋደኛ ነበረኝ። ጉዋደኛዬ ዕድገት በኅብረት (በእብደት ሳቅ!) የሥራና የዕውቀት ዘመቻ ከተሳተፉት ተማሪዎች አንዱ ነው። በምድብ ሸዋ በደንዲ ጣቢያ ያለኝ መሰለኝ። ታዲያ በ1968ንቱ አካባቢ በሱ መስመር ከወሎንኮሚ ጀምሮ እስከ ጌዴዎ ድረስ ያለው የጅባትና ሜጫ አርሶ አደር በሆነ ምክንያት ያምጽና በወቅቱ የሸዋው የደርጉ አንበሳ የነበሩቱ ኮሎኔል ደበላ ዲንሳን (ነፍስ ይማር) አመራር ለመከተል አስቸግሮ ኖሮ፤ ደበላ በላንድሮቨር፤ አጃቢዎቻቸው ደግሞ በፈጣኗ ከፍት ጂፕ ቢ አር መሣሪያቸው ተደቅኖባቸው ከተፍ ካሉ በኋላ፤ በየጣቢያው የሚገኘትን ዘማቾች ሰብስበው ዐመጹን ለማቆም ” ዘማቹ ተሜን “ መላ በሉኝ ብለው ስብሰባውን ለውይይት ይከፍታሉ አሉ። ተሜ ተንኮለኛዋ የምትሰጠው ሃሳቦች ሁሉ ያልተዋጠላቸው ደበላ በመጨረሻ እንዲህ አሉ ይባለል። እኔና ወታደሮቼ በምታይዋቸው ክፍት የጂፕ መኪናዎች ላይ የድምጽ ማጉያ ይዘን ከአዲስ ዓለም ጀምሮ እስከ ጌዴዎ ድረስ ባለው አውራ ጎዳና ላይ (አውራ ጎዳና ከተባለ በዛሬ መለኪያ) ” ሲ ዳጰና “ በአፋን ኦሮሚፋ እንዲሁም “ ላንተ ነው የቆምኩት “ ስለው ዓመጸኛው ሰጥ ለጥ ይላል ብለው አረፉት። አዎን! ሰላምና ሕዝባዊ ፖሊሲ ያለው አመራር ቅንና ደግ ነው። ለጊዜውም ቢሆን ጠመንጃንና ጉልበትን እንደ አማራጭ አልተጠቀሙም። በዚህ አጋጣሚ እኝህ ኢትዮጵያዊ የፖሊስ መኮንን ንግግራቸውና ምክራቸው ጣፋጭ መሆኗን በ1971 ዓም የአምቦ እርሻ ተቌም ምሩቃንን ሲመርቁ በአካል አይቻቸዋለሁኝ። አንዳንዶቹ ሰውዬውን ደህና አድርገው የሚያውቋቸው ደግሞ ቢዘገይም ቀይ ሽብር የተባለው ጸረ ወጣት፤ ጸረ ምሁርና ጸረ ተራማጅ ህይሎች እርምጃ በተለይ በሸዋ ጠ/ግዛት እንዲቆም ካደረጉት ውስጥ በዋናነት ይጠቅሷቸዋል።
በክፍል 2 መጣጥፌ የምግብ ዋስትናችንን ጉዳይ እንዳናረጋግጥ ካደረጉን ምክንያቶች አንዱ የሆነውን ተፈጥሮአዊ መንስኤ ጸባይ እንዳለው ገልጬ ነበር። አንዳንዶቹን ለመከላከልና ለመገደብ ብንሞክርም ሌላውን ግን ፈጣሪያችን ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ሥር የሚያደርግ መሪ እስከሚሰጠን ድረስ በትዕግሥት እንጠብቅ። በሁለተኛው ምክንያት ላይ ግን የመሪዎቻችን መልካም ፍቃድ ለጊዜው ታክሎበት መስራት ይቻላል። ይሄ ነው ጥሩ ፖሊሲ ብሎም አፍን ሞልቶ ለመናገርም ሊቸግር ይችላል። ማውራት ሌላ፤ ስራ ሌላ አይደል። አዎን! መስራት እንደ ማውራት ቀላል አይዶለም። ነገር ግን በቅድሚያ የሚያሰራና የሚያንቀሳቅስ የግብርና ፖሊሲ ለማዘጋጀት ግን ያለንን የተለያየ ዕውቀት፤ ክህሎትና የስራ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በማቀናጀት በሃሳብ ነጻነት እንዲሰሩ ማድረግ የመልካም ግብርና ፖሊሲ የመጀመሪያው ምዕራፍ ፩ ሊሆን ይችላል። የዘመቻ ዓይነት አሠራር አስወግዶ በምትኩም ደህና አድርጎ በማሰብ የተዝጋጀ ፖሊሲ ያስፈልጋል። በሥራ ላይም ችግር ቢገጥመው ወዲያውኑ ሊስተካከል ይችላል። ስለዚህ በዚህ የግብርና ፖሊሲ ውስጥ እንዲካተቱ የምንፈልጋቸው ጉዳዮች በዋናነት የሚከተሉትን መሠረታው ጥያቄዎች ሊመልሱ የሚችሉ መሆን አለበት። ለምን? ማን? እንዴት? እንደምን? ምን? የት? የትኛው? መቼና ሌሎችንም ጥያቄዎች በማንሳት፤ የማይሰሩትን በማስወገድ ሃሳቡ ይጀምራል። በዚሁ ጉዳይ ብዙ አዋቂዎችና ምሁራን ተናግረዋል፤ መክረዋል፤ ዘክረዋል። መስማትና መተግበር ያቃታት ግን ይቺ መንግስት የሚሏት ተቋም ነች። እርሷ የምትፈልገው እኔን ብቻ አድምጡ፤ እኔ የምላችሁን ብቻ ደግፉ ነው። ፖሊሲው በግልጽ መሰረታዊ የሆነውን የመሬት ይዞታ ጥያቄ ካለማወላወል መልስ መስጠት የግድ ይለዋል። መሬት የግል ይዞታ ይሁን! የረዥም ጊዜ ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት። የደንና ዱር እንስሳትን ፤ የአፈርና የውሃ ሃብታችንን አጠቃቀም፤ አጠባባቅና አስተዳደር መፍትሄ ማበጀት አለበት። የመሬትን ዓይነት ምዘናና ምደባ በትክክለኛው፤ አግባብነትና ተቀባይነት ባለው መንገድ መዘጋጀት አለበት። የዘመናዊና ሰፋፊ ኣርሻዎችን ይዞታና የት የት ሥፍራ መሆን እንዳለባቸው በቅድሚያ ጥናት መሰረት አድርጎ መዘጋጀት ተገቢ ነው። የአካባቢ ነዋሪዎችንም ዕውቀት ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። በተለይ በተለይ ደግም ከውጭ በኢንቨስትመንት ስም የሚያገኙትን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ አስልተው የሚመጡትን ባለ ሃብቶች ክፉና በጎውን ለይተን ሳናጠና በችኮላ ፍቃድ መስጠት የኋላ የኋላ አገር ይጎዳል። ግልጽ የሆነና የትኞቹ የሰብልና የእንስሳት ዓይነቶች ቅድሚያ ትኩረትን ተችረው መልማት አለባቸው ተብሎ መጠየቅም አግባብነት አለው። የግጦሽ መሬት አጠቃቀምንና አያያዝን እንዲሻሻሉ መርሃ ድርጊት መንደፍ። የዓሳ ሃብታችንን በሳይንሳዊ ጥናት ላይ በተመረኮዘ አሰራር ማሻሻል። የምርት አያያዝን፤ አቀነባበርን፤ አዘገጃጀትንና ጥራት አጠባበቅን አዋጭውን መንገድ መከተል ። የምርት ዓይነቶች ተገቢውን የገበያ ዋጋ በጊዜና በቦታ እንዲያገኙና ሥርጭታቸውም የተስተካከለ እንዲሆን የአቅምን ያህል ካለ ማቋረጥ መጣር። ለገበያ የቀረቡ ምርቶችም የታክስ ዋጋ የማይጎዳ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። የምርት ግብአቶች ሁሉ በተፈለው ጊዚና መጠን እንዲሁም ዋጋቸው የሚቻልና ተመጣጣኝ እንዲሆን መንግስት በጥናት ላይ የተመሠረት የዋጋ ድጎማ እንዲያደርግ አሠራሩን ማመቻቸትና ማስተካከል። ዋነኛ የሜካናይዝድ እርሻ አገልገሎት መስጫ ጣቢያዎች እንዲስፋፉና እንዲጎለብቱ ማበረታታት። የብድርና የባንክ አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲገኙ አሰራሮችን ማሻሻልና ትኩረት ሰጥቶ መከታተል። የትምህርትና የሥልጠና መርሃ ፕሮግራማችንን በፍላጎትና በችግሮቻችን ዙሪያ በቅድሚያ ማዘጋጀትና መንደፍ፤ የምርምርና የሥርጸት ሥርአቱን ለስራው ምቹነት ባለው አካሄድ ማደራጀት። የልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ መዋቅሮችን ( መንገድ፤ ግድቦች፤ የመስኖ ቦዮች፤ ጎተራዎች፤ የሰው ሰራሽ እንስሳት ማዳቀያ ጣቢያዎችንና የእንሳሳት ህክምና መስጫ ክሊኒኮችን አርሶ አደሩ በቅርብ ርቀት የሚያገኝበትን መንገዶች ካለማቋረጥ ማሰብና መገናኛ መሳሪያዎችና ሌሎችንም ጨምሮ) በአቅም በፈቀደ መጠን ማስፋፋት። በገጠሩ የኃይል አጠቃቀም ሥርዓትን ማጎልበት። የምግብና የምግብ አዘገጃጀት ሥርአታችንን ከጤና ፕሮግራም ጋር ተስተካክሎ እንዲሄድ መላ መሻት። አዳዲስ የሚቋቋሙት የሰፋፊ እርሻ ልማት ፕሮግራሞች የሠራተኛውን ጉልበት አጠቃቀም ከግምት ውስጥ ያስገባ፤ ደህንነትና የጤና እክሎች እንዳይፈጠሩና እንዳይባባሱ ከልብ መስራት። የአዳዲስ የሠፈራና የመንደር ምሥራታ መርሃ ድርጊቶች በቅድሚያ በሕዝብ ሙሉ ፍቃድ ላይ መመስረታቸውን ማረጋገጥ። የአምራቹን ሙሉ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስጠብቁና የሚከራከሩ የተለያዩ ዓይነቶች የህብረት ሥራ ማኀበራት ማቋቋምና ማጠናከር፤ የሴት አርሶ አደሮችን ጥቅም የሚያስጠብቅ አሰራር መፍጠርና እንዲተገበሩ እገዛ ማድረግ፤ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመርን የሚገታ የድርጊት እንቅስቃሴዎችን ማስፋፋትና ሌሎችም በዝርዝሩ ውስጥ ያልተጠቀሱቱ በአግባቡና ከልብ ከተሰራባቸው ችግራችንን የማንቀርፍበት ምክንያት አይታየኝም።
የማንኛቸውም አገር የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዓይነቱ፤ ደረጃው፤ ዕድገቱና ውጤቱ በተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ተግባሮችና እንቅስቃሴዎች ሁሉ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ግብርና በዋናነት በተለይም ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ለየት የሚያደርገው በባህርዩ ከጸሃይ በታች በምትገኘው የተፈጥሮ ጸጋ በሆነችው በምድር ወይም በየብስ ላይ በመከናወኑ ምክንያት በርካታ አካባቢያዊና ሥነ ምህዳራዊ ተጽዕኖዎች ይፈራረቁበታል። በተጨማሪም ማኅበራዊም ሆነ ባህላዊ ተጽዕኖዎችም ለፍጥነቱም ሆነ ለውድቀቱ የማይናቁ ስፍራ አላቸው። ነገር ግን ለኢኮኖሚው መሻሻልና ለውጥ እንዲያሳይ ከተፈለገ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ መንገዶችም እንበለው ስልቶች ወይም ሌላ በአንድነት ተጣጥመው፤ ተዋህደው፤ ተደጋግፈውና አንዱ አንዱን ተከትሎ እንዲተገበሩ ግድ ይላል። እነርሱም በዋናነት መሰረታዊና አፋጣኝ ( አቀጣጣይ / አጋዥ ሃይሎች) ተብለው ይታወቃሉ። የቀድሞው የአምቦ እርሻ ተቋም መምህሬ የሆኑትና የአሁኑ የአምቦ ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚያገለግሉት በቀለ ጣሰው ናቸው ይህችን ደህና አድርገው በግብርና ኤክስቴንሺን ትምህርት ቁጥር 1 ላይ በ1971 ዓም ያስተማሩኝ። ምስጋና ለሁሉም መመህራኖቼ በዚህ አጋጣሚ።
መሰረታዊ በመባል የሚታወቁቱ የሚከተሉት ናቸው። ለግብርናው ምርት ተስማሚና በቂ የገበያ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች፤ ዘመናዊና በየወቅቱ እየተሻሻሉ ወደ ተግባር የሚሸጋገሩና ተመጣጣኝ የሆኑ አሠረሮች ወይም ቴክኖሎጂዎች፤ የምርት ግብዓትና የተግባር መገልገያ መሣሪያዎች አቅርቦትና በሚያስፈሉግበት ጊዜ መገኘት፤ አምራቹን የሚያበረታቱና ለበለጠ ምርትና ምርታማነት የሚያነሳሱ እርምጃዎችን ቶሎ ቶሎ መውሰድና የተለያዮ መዋቅራዊ አገልግሎቶችን ማለትም እንደ ዋናና መጋቢ መንገድ፤ ግድቦችና የመስኖ ቦዮች፤ የጎተራ አገልግሎቶች፤ ማቀናበሪያ፤ ማዘጋጃዎችና ማሸጊያዎች፤ የእንሰሳት ክሊኒኮችና የመድሃኒት ማከፋፈያዎች፤ የኃይል ምንጮችና ሌሎች በፍጥነት ማስፋፋትና ማዳረስ ዋነኞቹ ናቸው። የሚያፋጥኑ ወይም አጋዥ ሃይሎች የተባሉት ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ የሚዘረዘሩት ናቸው። ተከታታይ ትምህርትና ሥልጠናዎች ለሁሉም በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ በዋናነት ሆነ በአጋዥነት ለሚሰሩቱ በሞላ እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠና፤ የብድርና የባንክ አገልግሎት በቀለጠፈና አስተማማኝ በሆነ መልኩ መቅረብ አለበት፤ አምራቾቹ የራሳችውን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የጋራን ችግር በጋራ እንዲቀርፉ የሚያስተባብር ቡድን ወይም ማኅበር መመስረት፤ የመሬት ለምነት የሚያሻሽሉና የሚጨምሩ እርምጃዎችና ተጨማሪ መሬት ለአገልግሎት ማዘጋጀትና ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በዕቅድና በመርሃ ድርጊትና በፕሮጃክቶች መልክ መቅረጽ ናቸው።
እኔን ከሁሉ የሚገርመኝ ግን አብዛዎቻችን ተምረን ሥልጣን ላይ ቂብ ያልን ፍጡራን ሁሉ የአሁኑን ጠቅላያችንን ጨምሮ፤ የክልልና የዞን የወረዳ ባለ ሥልጣናትንም አክሎ የገዥውንም ፓርቲ አባላትን በትግራዊ ቋንቋ ለመጠቀም “ከናይ ጭቁን መደባት” እያሉ ከሚያደነቁሩን ፖለቲከኞቻችን ይዞ መነሻችንና ምንጫችን ከእዚሁ ገበሬ ቤተሰብ እንደሆን ይታወቃል። ይህም በመሆኑ የገበሬውን ኑሮ በቅርብ እርቀት የተመለከትን ይመስለኝ ነበር። በዚሁ ገበሬ ልፋት፤ ድካም፤ ጥረት፤ ጉልበት፤ ዕውቀትና ክህሎት ለአንዳንዶቻችን የተቀናጣና ለግልገሎቹ ደግሞ የተመቸ ኑሮ እንድንኖር ያደረገን ይኽው ግፉአን የተሰበሰቡበት የሕዝብ ክፍል መሆኑ ጭርሹኑ የተረሳን ይመስላል። ለእርሱ እየሰራንለት ሳይሆን እየሰራንበት ነው። እርሱ የሚያመርተውን ምርት ተገቢውን ዋጋውን ሳናጋራው እኛው አራዳውቹ በእርሱ ልፋት ሃብት በሃብት ላይ እንጨምራለን፤ በስራው ላይ ያፈሰሰውን ላቡን ሳንጠርግለት ድካሙን እንጋራዋለን፤ እንቦጠቡጠዋለን፤ እንደ ዋግምት እንመጠዋለን። እንዴት ቡናን ያመረተና ምርቱን ሁልጊዜ ገንዘብ ያላቸው እንደ ጠበል ፉት ሳይሉ ስራን መጀመር የማይሆንላቸው በዓለማችን ሞልተው ያሉ ሕዝቦች እያሉለት የአገሬ የቡና ገበሬ በባዶ እግሩ ገጀራ እየያዘ በማሳው ውስጥ ከቤተሰቡ ጋር ለትንሽ ዋጋ ይለፋል፤ ይማስናል? ልብ በሉ! ከእርሱ ምርቱን እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ ከተረከቡት በኋላ የበለጠ ለማግኝት የሚጣደፉትን አስተውሉ፤ እንዴት ሠራተኞቻቸውን በተሻለ ኑሮ ላይ እንዳስቀመጡ። እንደምን የዓለምን “የፖለቲካ ሰብል” እየተባለ የሚጠራውን ስንዴ አምራች በድህነት ይኖራል? የስንዴ ዱቄት አምራቾቹን የማይቀመስ የፉርኖ ዱቄት ዋጋ ልብ ይበሉ! ምንጩ ይኽው መከረኛ ድሃ እየተባለ የሚጠራው ገበሬ አይደለምን? የቢራ ገብስ አምራች ገበሬን ተመልከቱና መልሳችሁ እራሳችሁን ጠይቁት? የዘይቱም ምርት፤ የዶሮውን ዋጋ፤ የከብት ስጋ ዋጋን፤ የዕንቁላል ዋጋን፤ የዓሳ ስጋን፤ የቅቤውን ዋጋ፤ የማሩን፤ የምግብ እህሉንና የጥራ ጥሬ፤ የቅመማ ቅመም ዋጋን ሌሎችንም እንደዚያው ተመልከቱት። በርግጥ ገበሬው የልፋቱና የድካሙ ተጠቃሚ ነውን ብላችሁ ታስባላችሁን? ስንቱ በዚህ ገበሬ ላብና ድካም የተሻለ ኑሮን እያጣጣመ፤ የራሱ ልጆች መልሰው ይገፉታል፤ ችግርህን አንተ አታውቅም እኛ እናውቅልሃለን ይሉታል። በቅርቡ እንኳን ግምባሩ ታንክ ይመስላል እየተባለ የሚቀለድበት በረከት ስምኦን አቅም ሳይቀር ገበሬውን እንደ ጅል ተመልክቶታል። በረከት የገበሬውን ኑሮ ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋር ያመሳሰለው ይመስላል። የጨዋታው እንቅስቃሴ ሁሉ በዳኛው ፊሻካ ብዛትና ማነስ የሚወሰን መስሎታል። ማነው ስሙ ያ የአማራ ም/ ገዢ እንፈፍ ደግሞ በባዶ እግሩ እየሄደ ብሎ ተሳልቆበታል። ገበሬው ለልፋቱና ለድካሙ ተመጣጣኝ ዋጋ ካገኘ ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑትን ሸቀጦች ተመልሶ መጥቶ ይገዛበታል፤ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ለመስደድ አያቅማማም፤ ጤናውን ለመጠበቅ ወደ ኋላ አይልም፤ የግብአት ብድር ካለበት ለመመለስ ወደ ኋላ አያፈገፍግም፤ በሚቀጥለው ምርት ዘመን ምን? መቼ? ስንት? ለምን? ላምርት የሚለውን መሰረታዊ የስራ ጥያቄ ጠይቆ ይዘጋጅበታል። በአገራችን ተልካሻ አሰራር ገበሬው ሁልጊዜ ተጠቃሚ ሳይሆን ተጠቂ ነው። የኔ ቢጤው ሸማቹም እንደዚያው። ተጠቃሚዎቹ የመንግስት ትልልቅ ሹመኞችና ከእነርሱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩት ብቻ።
ለመሆኑ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሚሰጠው ጥቅም ምንድን ነው? ጠቅለል ባለ አገላለጽ እንዲህ ይጠቀሳል።
1ኛ፡ ከመሠረታዊ የሰው ልጆች ኑሮ አስፈላጊ ናቸው ተብለው በተከታታይ ከሚጠቀሱትና የክቡሩን የሰውን
ልጅ ህልውና ለመጠበቅና የምግብ ፍላጎቱን ለሟሟላት ይረዳ ዘንድ የምግብ አዝርዕቶችን ማምረት፤
ማቅረብና አዘጋጅቶ ማቅነባበር ነው። ባጭሩ የምግብ ምንጭ ነው።
2ተኛ፡ ለሌሎች ማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ ጥሬ ምርቶችን በማቅረብና ተጨማሪ የምርት
ውጤቶችን በማስገኘት ገደብ የሌለውን የሰው ልጆች የሸቀጥ ፍላጎት ለማሟላት።
3ተኛ፡ የኢኮኖሚ ጠቀሜታን የሚሰጡ የአዝርዕት፤ የእንስሳት ምርትና ተዋጽዎኦችን እንዲሁም ደንና ውጤቶ
ቹን ለአገርም ሆነ ለውጭ አገር ገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጭ መሆኑና በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ
አገሮች ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛና መሰብሰቢያ መሆኑ።
4ተኛ፡ ለአብዛኛው የገጠሩም ሆና የከተማ ነዋሪው ዋነኛ የስራ ምንጭ ( ጊዜያዊና ቋሚ ስራ) በመሆኑ፤ የገቢያቸ
ውን መጠን ድርሻና ዓይነት በቀጥታ ሰለሚወስን። ይቺ የሥራ ሃይል ምንጭነቷ እኛ በአገራችን
ግብርና ሲባል ከምናውቃት በላይ ነው። አብዛኛዎቻችን ግብርና ሲባል ያው ገበሬ ማረሻውን ይዞ ከአፈ
ር ጋር መታገሉና በጭቃ መለወሱና አንዳንዴም ከከብቶቹና ዶሮዎቹ ከንብ እርባታው እንቅስቃሴ ጋር
ብቻ የምናቆራኝው አለን። ነገር ግን ዕውነታው ከዚያም ባሻገር ይዘልቃል። ግብርናቸው የሜካናይዝድ
ደረጃ በደረሰባቸው አገሮች ደግሞም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ አገሮችና የሥራቸው መሠረት ይኽው ክፍለ
ኢኮኖሚ የሆኑቱ እንደ የእርሻ መሳሪያዎችና መገልገያ ቁሶችን፤ የመሬት ማዳበሪያና የጸረ_ተባይ ኬሚካል
ማምረቻ፤ የምግብ ማቀናበሪያና ማዘጋጃ ስፍራዎቹ፤ የግብርና
ምርት ውጤቶች ማከፋፈያና መሸጭያዎች ለዓብነት ያህል የዚሁ የግብርናው የሰራ ምንጭነት ውጤት
ናቸው።
5ተኛ፡ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ በቀጥታም ሆነ በኢቀጥታ የተዘጋጁ ፈዋሽነትን በዋናናነት የ
ሚሰጡና ለተጨማሪ አገልግሎት የሚውሉ መድሃኒቶችን ዓይነት በማምረት።
6ተኛ፡ በተለይ ከደን ልማት የምናገኘው ጥቅም በዋናነት የአካባቢን የተፈጥሮ ሚዛን በመጠበቅ፤ ለሙ አፈራች
ን በአፈር መከላት ኃይሎች ተጠርጎ እንዳያልቅና ምድረ በዳንነትን በመከላከል፤ ለብርቅዬ የዱር እንስ
ሳትም መጠለያ በመሆንና የቱሪስት መስህብ እንዲኖረው በማድረግ በዋናነት ይጠቀሳሉ። ይህንን ሁሉ ጠቀሜታውን ስገልጽም ነገ የተስተካከለና የተረጋጋ የግብርና ፖሊሲ ቢኖረንና፤ ገንዘብና ዕውቀት ኖራቸው በዚህ በምግብ ማምረት ስራ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ የአገር ሰዎች እድሉ ምን ያህል ክፍት እንደሆነና አዋጬ እንደሆነ ለመጠቆምም ጭምር ፈልጌ ነው።
በክፍል 5ትና የመጨረሻው ክፍል እስከምንገናኝ ድረስ በቸር እንሰንብት!!!
አሜን!!
↧
ያረጋገጥነው የምግብ ኢዋስትናን (ዋስትና አላልኩም) ነው።
↧