ከመስፍን ደቢ
በዚህ ባለንበት ዘመን አለማችን በሚገርም ፍጥነት ለመከታተል ፋታ በማይሰጥ ሁኔታ የፖለቲካ ለውጦች እየተካሄዱ ነው። ሶቭየት ህብረት ሲፈረካከስ ትልቁ ስባሪ ዩክሬን ነው። ዛሬ ዩክሬን እየተናጠ ነው አለምም አተኩሮበታል ። በቤንዚዌላ ቀውጢ ሆኗል ፤ አብዛኞቹ የአረብ መንግስታት ተፋጠዋል፤ በኢትዮጵያችን ደግሞ የወያኔ የመጨረሻ ምዕራፍ መድረሱ ይተነበያል። ወያኔና ደጋፊዎቹ ሽብር ላይ ናቸው። እንዲህ በምትናወጠው አለማችን የሆነውን በትክክል ማን? የት? መቼ? እንዴት? የሚለውን አንዱም ሳይቀር እንድናውቀው የሚያደርጉን ጋዜጠኞች ናቸው። ለሙያቸው ትልቅ ክብር አላቸው፣እውነተኞች ናቸው፣ ደፋር ናቸው፣ ለህሊናችው ብቻ የሚታዘዙ ናቸው፤ እውነትን ፈልገው ለኛ ሲያቀርቡና እንድናውቅ ሲያደርጉን እነሱ እስራት፣ ድብደባ፣ ስቃይ፣ ሞትም አለባቸው። እነዚህን ቁርጠኛ የእውነት አርበኛ ጋዜጠኞች እላቸዋለሁ። ስለአገራችን ብቻ ብናገር ኢትዮጵያ እንዲህ ባሉ ጋዜጠኞች ታድላለች። ተሰደውላታል፣ ታስረውላታል፣ ሞትንም ቀምሰውላታል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እና በዲያስፖራው ሁለት አይነት ጋዜጥኞች አሉ። አንዱ ክፍል የወያኔ አገልጋይ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ የሆኑ ያሉበት ነው። ሌላው ክፍል ደግሞ ለጋዜጠኝነት ሙያ ተአማኒነቱ የበረታ እውነቱን ማቅረብ ዋጋ ቢያስከፍልም ቆርጠው የሚጋተሩ ያሉበት ነው። እንዲህ ባለ አጠቃላይ ምደባ ብንጠቀም የሚቀር አንድ ክፍል አለ። የስራ ተቋማቸው በሌሎች መንግስታት የተመሰረተ ሆኖ ኢትዮጵያ ተኮር ዜና የሚያቀርቡትን ለማለት ነው። ይህም ቪኦኤ እና የጀርመን ሬዲዮ የመሳሰሉ ናቸው። በተለይ እነዚህ ተቋማት ቪኦኤ የአሜሪካን ጀርመን ሬዲዮ የጀርመን ናቸው። ኢትዮጵያ ተኮር ዜና በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በሱማሊኛ ያቀርባሉ። ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ እና በውጭ እንደ አማራጭ የዜና ምንጭ ይጠቀሙባቸዋል። በእነዚህ የዜና አውታሮች ያሉ ጋዜጠኞች የአሜሪካን ወይም የጀርመን መንግስትን አቋም እንዲያንጸባርቁ ቢገደዱ እንረዳቸዋለን ከዚህ በተረፈ ግን ለተግባራቸው መሪ ህሊናቸው ብቻ ነው ብለን እናምናለን። ለእውነት መቆምን፣ ሚዛናዊ መሆንን ያለውን እንዳለ የሆነውን ያለተጨማሪ አስተያየት ለአድማጩ ማቅረብ ሙያው የግድ ይላል ፡የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የለቀቀውን ውሸት ቢያስተጋባው የምንታዘበው ይሆናል። ቪኦኤ የኢትዮጵያ መንግስታዊ የዜና ተቋም ያለውን ቢያስተጋባ ትዝብት ላይ ይጥለዋል:: ቪኦኤ በዲያስፖራው ካሉ የወያኔ “የዜና” የፕሮፓጋንዳ ጋዜጠኞች መለየት አለበት ። ቅዳሜና እሁድ በመጣ ቁጥር አምባሳደር ኢንተርቪው የሚያደርጉና ስለልማት የሚያወሩ ባዶ ገረወይና የሆኑ አሉ። ቪኦኤ ከነዚህ መለየት አለበት።
ቪኦኤ በሞያቸው የተከበሩ ጋዜጠኞች ያሉበት ተቋም ቢሆንም ደግሞ ደጋግሞ ስህተት የሚፈጽም ረቀቅ ባለ መንገድ የወያኔን አቋምና መልእክት የሚያቀርብ ጋዜጠኛም አለበት። ይህ መሆኑ ደግሞ ያሳዝናል ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላንን አቅጣጫ አስቀይሮ ጄኔቭ እንዲያርፍ አድርጎ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቀው ረዳት አብራሪ ሀይለመድህን አበራ ድርጊቱ በአለም የዜና አውታሮች ሁሉ ቀርቧል። ከሁሉም የዜና አውታሮች ግን ቪኦኤ እና የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቲቪ የዘገቧቸው ይመሳሰላሉ። ሁለቱም ያተኮሩት የሀይለመድህን የአእምሮ ሁኔታ ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ሀይለመድህን አእምሮ ማተኮር የፖለቲካ ብሶቱና በደሉ እንዳይሰማ እና እንዳይተኮርበት ለማድረግ ነው። የቪኦኤውም “ጋዜጠኛ ” ይህን የማድረግ ግዴታ የለበትም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መዘገብ በቻለ ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ የተዋጣለት ወጣት ሙያተኛ ምን ምክንያቶች ላደረገው ድርጊት ጋፋፉት ብሎ ጥያቄውን ወርውሮ ማለፍ ይችል ነበር፤ ግን መልእክቱን ጋዜጠኛው ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር በረድፉ ለማሰለፍ የቆረጠ ስለሚመስል የአእምሮ ሁኔታ ላይ አተኮረ፤ ሁኔታውም ካለማወቅ አይመስልም።
ዛሬ ዘመናችን አማራጭ የዜና ተቋማትን ቴክኖሎጂ ያንበሸበሸን ዘመን ነው። እንደ ዱሮው ቪኦኤ ወይም የጀርመን ሬዲዮ ብቸኞቹ የነበሩበት ግዜ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገር ቤትና በውጭው ይህን እውነታ ያውቃል። ቪኦኤ ለራስህ ብለህ ጣፍጥ ነው መልእክቱ ። ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም እንዲሉ ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉትን ጥቅም ሊያማልላቸው የማይችሉትን የእውነት አርበኛ የሆኑትን ጋዜጠኞች ከፊት ረድፍ ቢያሰልፉ ለቪኦኤ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ቀድሞ እንደተባለው ኢትዮጵያ የጀግኖች እና የእውነተኛ ጋዜጠኞች ባለ ጸጋ ነች፤ ገና ብዙ ታፈራለች።ብዙ ጀግና ጋዜጠኛ የሚወለድበት የለውጥ ማእበል እያስገመገመ ነው። መጥኔ ለቪኦኤ እራሱን ካላረመ፤ ሰሚ ያጣ ጋዜጠኛ ከመሆን ሰውረኝ ነው።
ቪኦኤ አንዱ ጋዜጠኛው አግባብ የሌለውን ተግባር ቢፈጽም እንደ ተቋም መጠየቁ አይቀርም። ሄኖክ ሰማእግዜር ባደረገው ነገር ትዝብት ብቻ ሳይሆን በጣም አዝነናል ቆይቶ ደግሞ ህዝባዊ ቁጣ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው።