Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“የኦነግ ጭፍጨፋ ተብለው ከሚጠቀሱ ትራጄዲዎች መካከል አብዛኛዎቹ በኦነግ የተፈጸሙ አልነበሩም”–ከአፈንዲ ሙተቂ

$
0
0

olf flag
ከአፈንዲ ሙተቂ

——
“ዳውድ ኢብሳ ሲሞት ጥሩኝ” በሚል ርዕስ በለጠፍኩት አነስተኛ ሐተታ ላይ ሁለት ዓይነት ተቃውሞዎች ቀርበውብኛል፡፡ አንደኛው “ኦነግ በአማራው ላይ የሰራውን ሴራ እና ሸፍጥ እያወቅክ ጥብቅና ቆመህለታል” የሚለው ሲሆን ሁለተኛው “የኦፒዲኦን ድርጅታዊ ህልውና አንኳሰስክ፤ አቶ አለማየሁንም ረገጥክ” የሚል ነው፡፡ ስለ ኦፒዲኦ የጻፍኩት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የድርጅቱ አባላት እራሳቸው በየአጋጣሚው የሚናገሩትን ነው በፌስቡክ የደገምኩት፡፡ በተለይ ደግሞ አባላቱ ከስራቸው ሲባረሩ፣ ወይ ደግሞ ከድርጅቱ ከድተው ወደ ውጪ ሀገር ሲኮበልሉ “ኦፒዲኦ የኦሮሞን ህዝብ ለማጭበርበር ሆን ተብሎ የተፈጠረ ድርጅት ነው” የሚል ጩኸት በማሰማት ነው የሚታወቁት፡፡ እነ ዮናታን ዲቢሳ፣ ዱባለ ጃሌ፣ ኢብራሂም መልካ ሲያደርጉት የነበረው ይህንኑ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ የነርሱን ፈለግ በመከተል አይደለም እንዲያ ብዬ የጻፍኩት፡፡ ከነርሱ በፊትም እንደዚያ ስል ነበር፡፡
——
ኦነግን ለመጀመሪያ ጊዜ ካየሁበት ግንቦት 1983 ጀምሮ የድርጅቱን የፖለቲካ መስመር ስደግፍ ቆይቻለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ግን ድርጅቱ በሚያራምደው ርዕዮተ ዓለምና በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ጥያቄዎች ማንሳት ጀመርኩ፡፡ በዋነኛነትም “የመገንጠል ፖለቲካው የኦሮሞን ጥያቄ የትም አያደርሰውም” የሚል ሀሳብ አነሳሁ፡፡ እንዲሁም የሚከተላቸው ስትራቴጂዎቹ ፍጹም ሊዋጡልኝ አልቻሉም፡፡ በዚህም ከኦሮሞ ወንድሞቼ ጋር ብዙ ጊዜ እነታረክ ነበር፡፡ በተለይም በዚያ ጊዜ ኦነግን መተቸት Taboo ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር ከቅርብ ጓደኞቼ ጭምር እስከመጣላት ደርሰናል፡፡ እናም ከ1990 ጀምሮ የድርጅቱ ተቃራኒ እንጂ ደጋፊ አይደለሁም፡፡

እንዲህ በመሆኑ ግን ድርጅቱን በሐሰት መክሰስ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ድርጅቱን በሰራው ጥፋት ብወቅሰው ማለፊያ ነው፡፡ ባልሰራው ወንጀል መክሰስ ግን ለማንም የሚበጅ አይሆንም፡፡ እንደምሳሌም ኦነግ የሚከሰስባቸውን ጭፍጨፋዎች እንመልከት፡፡ በደኖ፣ አርባ ጉጉ፣ ወተር፣ አረካ፣ አሰቦት ገዳም ወዘተ…

እነዚህ ጭፍጨፋዎች መከሰታቸው ሁላችንንም ያሳዝነናል፡፡ አንድ ቀን እውነቱን ፈልፍለን የማውጣት ግዴታም ተጥሎብናል፡፡፡ ነገር ግን በርካታ ሰዎች በሁሉም ጭፍጨፋዎች ኦነግን ተጠያቂ ሲያደርጉ በጣም እገረማለሁ፡፡ በተለይም ዛሬ በህትመት ላይ የሌሉ ሁለት የግል ጋዜጦች ይህንን ፕሮፓጋንዳ እየደጋገሙ ሲያስተጋቡት ሳይ “ስለ የትኛው ሀገር ነው የሚያወሩት” እያልኩ እደነቅባቸው ነበር፡፡ እንዲህ የምለው ጋዜጦቹ የመረጃ እጥረት የነበራቸው መሆኑን በማወቄ ብቻ አይደለም፤ የጂኦግራፊ እውቀትም ያጠራቸው ስለሚመስለኝም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ “አረካ”ን እንውሰድ፡፡ ይህቺ ከተማ የት ነው ያለችው? ኦሮሚያ ውስጥ ነው? ወይስ ሌላ ቦታ?

ይገርማል! አረካ ማለት በደቡብ ክልል በወላይታ አውራጃ ከሶዶ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ያለች ከተማ ናት፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ኦነግ እዚያ ድረስ ሄዶ ሀገር አላስተዳደረም፡፡ “አረካ የኦሮሚያ ግዛት ናት” ብሎ የሚያውቅም አይመስለኝም፡፡ እናም ጂኦግራፊን በትክክል የሚያውቅ ጋዜጠኛ የአረካውን ግጭትና ጭፍጨፋ ለኦነግ አይሰጥም ነበር፡፡ በተጨማሪም የአረካው ግጭት የደረሰው ኦነግ የሽግግር መንግሥቱን ለቆ ከወጣና በእጁ የነበሩት መሬቶች በሙሉ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ከወደቁ በኋላ ነው፡፡

የአረካው ግጭት በሽግግሩ ዘመን ለነበረው የተወካዮች ምክር ቤት የውይይት አጀንዳ ሆኖ እንደቀረበ ይታወሳል፡፡ በከተማዋ ያለቁት የ31 ሰዎች ግድያ በመከላከያ ሰራዊቱ እንደተፈጸመ መንግሥቱ በይፋ አምኗል፡፡ ዳሩ ግን ለግድያው የተሰጠው ምክንያት በጣም አነጋጋሪ ነበር፡፡ መንግሥት ያቀረበው ምክንያት “ሰልፈኞቹ የተገደሉት ቦንብ በመወርወራቸው ሳቢያ የመከላከያ ሰራዊቱ ራሱን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ ነው” የሚል ነው፡፡ ይሁንና ይህንን ምክንያት ብዙዎች አልተቀበሉትም፡፡ ብዙዎች እንደተጠራጠሩት እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቷል፡፡ በነገራችን ላይ በአረካ የሞቱት የቀድሞ መንግሥት ወታደሮች ነበሩ፡፡ እነዚያ ወታደሮች “የጡረታ መብታችን ይከበርልን” በማለት የተቃውሞ ሰልፍ በማድረጋቸው ነው ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር የተጋጩት፡፡
——–
በሚያዚያ ወር 1984 በወተር ከተማ በተካሄደ ጭፍጨፋ የሞቱትም በተመሳሳይ መልኩ በመከላከያ ሰራዊቱ እንደተገደሉ የሽግግር መንግሥቱ በወቅቱ አምኗል፡፡ ይሁን እንጂ በወተር የተገደሉት 230 ሰዎች በሙሉ ኦሮሞዎች እንጂ አማራዎች አልነበሩም፡፡ እነዚያ ሰዎች የተገደሉት ኢህአዴግ ከከተማቸው ወጥቶ ኦነግ ወደ ከተማዋ እንዲመለስ በመጠየቃቸው ነው (ወተር ለአንድ ዓመት ያህል በኦነግ ቁጥጥር ስር ነበረች፤ ኦነግ ከከተማዋ ሲወጣ ኢህአዴግ ገብቶባታል፤ ነዋሪዎቹ “እንደ ቀድሞው ጊዜያችን ኦነግ ወደ ከተማዋ ይመለስ” በማለታቸው ነው ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር የተጋጩት)፡፡ ጋዜጦቹ ግን “ኦነግ አማራዎችን ጨፈጨፈ” እያሉ ነበር የሚዘግቡት፡፡
——-
በ1984 (ወሩን አላስታውሰውም) በአሰቦት ገዳም በተካሄደ ግድያ ሰባት መነኮሳት ሞተዋል፡፡ ይህንን ግድያ የፈጸሙትም በወቅቱ የአሰቦት ከተማን ለትንሽ ጊዜ ተቆጣጥሮ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት እስላማዊ ግንባር (IFLO) ታጣቂዎች ነበሩ፡፡ ግድያው ስር ሳይሰድ በአፋጣኝ ያስቆሙት ደግሞ ኢህአዴግና ኦነግ ነበሩ፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች አንድ ጥምር ኮሚቴ በማቋቋም በወሰኑት ውሳኔ መሰረት IFLO ከከተማው ተባርሮ አካባቢው በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል፡፡
——
በአርባ ጉጉ የተፈጸመው እልቂት በሁለት ተጎራባች መንደሮች መካከል በተካሄደ ግጭት ነበር የተለኮሰው፡፡ እያደር ግን መርቲ ጀጁ እና አሰኮ የሚባሉ የአርባ ጉጉ ወረዳዎችን አዳርሷል፡፡ በግጭቱ የኦሮሞ እና የአማራ ተወላጆች በእኩል ደረጃ ተጎድተዋል፡፡

በአርባ ጉጉ ግጭት የራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የፈለጉ ወገኖች እጃቸውን አስገብተውበታል ይባላል፡፡ በመሆኑም በውጤቱ ከሁሉም ግጭቶች የከፋ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ ግጭት ከሁለቱም ወገን እስከ ስድስት መቶ ያህል ሰዎች መሞታቸው ይነገራል፡፡ ከመቶ ሺህ ያላነሰ ሰው ወደ ሀረርጌና ሸዋ ክፍለ ሀገሮች ተፈናቅሏል፡፡ ሆኖም ኦነግ በዚህ ግጭት ውስጥ እጁን ማስገባቱን የሚያረጋግጥ ፍንጭ እስከ አሁን ድረስ የለም፡፡ ኦነግ በወቅቱ በአርባ ጉጉ አውራጃ ምንም ይዞታ አልነበረውም፡፡ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትም ቢሆን በግጭቱ የከሰሰው ኦህዴድን (OPDO) እንጂ ኦነግን አልነበረም፡፡ በተለይም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የምዕራብ ሸዋ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ የነበረው ኮሎኔል ዲማ ጉርሜሳ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ ስሙ በሰፊው ይነሳ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በዚያን ጊዜ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሐሰን ዓሊ ከእፎይታ መጽሔት ጋር (ግንቦት 1985) ባደረጉት ቃለ-ምልልስ “አቶ ዲማ ጉርሜሳ ንጹሕ ነው” በማለት ከመከላከላቸውም በላይ ለግጭቱ ዋነኛ ተጠያቂ ያደረጉት መአሕድን እንጂ ኦነግን አልነበረም፡፡

የግል ጋዜጦች ግን ነገሩን አራግበው በኦነግ ላይ አላከኩት፡፡ ነገሩን ሳያውቁት ቀርተው የተደረገ አይመስለኝም፡፡ አንዳንድ ጋዜጦች -ተከፍሎአቸው እንዲህ እንደሚያደርጉ በደንብ እናውቃለን፡፡
——–
የበደኖ ጭፍጨፋ! አዎን! ኦነግ ሊጠየቅበት የሚገባው ብቸኛው ትራጄዲ ይህኛው ነው፡፡ በርግጥም እልቂቱ በተፈጸመበት ወቅት በደኖ በኦነግ ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡ የሞቱት ሀምሳ ያህል ሰዎች ለምን እንደተገደሉ ባይታወቅም አድራጎቱ በኦነግ ወታደሮች እንደተፈጸመ ድርጅቱ ራሱ አምኗል፡፡ ኦነግ በወቅቱ በወታደሮቹና በአዛዦቹ ላይ እርምጃ ወስጃለሁ ቢልም የተወሰደውን እርምጃ ምንነት አልገለጸም፡፡ በነገራችን ላይ በዚህኛውም እልቂት ከሞቱት መካከል ግማሽ ያህሉ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡
—–
ከላይ በዝርዝር እንዳስረዳሁት የኦነግ ጭፍጨፋ ተብለው ከሚጠቀሱ ትራጄዲዎች መካከል አብዛኛዎቹ በኦነግ የተፈጸሙ አልነበሩም፡፡ ኦነግ ሊጠየቅበት የሚገባው ብቸኛው ድርጊት በበደኖ የተፈጸመው ነው፡፡ የእውነት ቀን ሲመጣ ያንን ፋይል ማውጣታችንም አይቀሬ ነው፡፡ ይሁንና በኦነግ ያልተፈጸመውን ከርሱ ጋር አያይዞ መጻፍ ጥቅሙ ምን እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም፡፡ እንዲያውም የያኔዎቹ የግል ጋዜጦች የሚያራግቡት ወሬ በተወሰነ መልኩ የኦነግ ጨካኝነትን ከመግለጽ ይልቅ “ኦሮሞ ጨካኝ ነው” የሚል እድምታ ለመፍጠር የታለመ ነበር የሚመስለው፡፡

እርግጥ የኦነግ ወታደሮች በብዙ አጋጣሚዎች ልዩ ልዩ የጭካኔ ተግባራትን ሲፈጽሙ ተስተውለዋል፡፡ እርሱን አንክድም፡፡ የነርሱ ገፈት ቀማሽ ሆኖ የዘለቀው ግን በአብዛኛው ኦሮሞው ነው እንጂ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጅ አልነበረም፡፡ በተለይ አንዳንዶቹ የኦነግ ወታደሮች “ጎበና፤ ቢተምቱ.፤ ወዘተ..” ለሚሏቸው ግለሰቦች ምህረት አልነበራቸውም፡፡ እንዲሁም ተጻራሪ ድርጅት ሊያቋቁሙ ነው በሚል ፍርሃት አባላቶቻቸውን ጭምር እስከ መግደል ይደርሱ ነበር (የኦነግ የሀረር ቢሮ ሃላፊ የነበሩትን አቶ አራርሶ ወዳይን እና በመቻራ ከተማ የተገደለውን የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ካሊድ ሃጂ ኑራን መጥቀሱ ይበቃል)፡፡ ሆኖም ጋዜጦቻችን ድርጅቱ የፈጸመውን ማውራት ይተውና ድርጅቱ ያልፈጸመውን ወንጀል ይነግሩን ነበር! ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ማለት ይህ ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል እኔ ለኦነግ አልተከላከልኩለትም፡፡ አንዳች ጥብቅና አልቆምኩለትም፡፡ የጻፍኩት የማውቀውን ሐቅና የማምንበትን አቋሜን ነው፡፡ ይሁንና ይህ አባባሌ ኦነግን ከመፍራት እንዳይወሰድብኝ አደራ እላለሁ! አስፈላጊ ከሆነ በኦነግም የተፈጸሙ ስህተቶችና ጥፋቶችን አንድ በአንድ መዘርዘር እችላለሁ፡፡

ሰናይ ቀን ይሁንላችሁ!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>