ከማስረሻ መሐመድ
የኩላሊት ጠጠር የሚባሉት አብዛኛውን ጊዜ የካልስየም ክሪስትያል የሚሠሯቸው ድንጋዮች ሲሆኑ በኩላሊት ውስጥ የሽንት መጠራቀሚያ ቦታ ላይ የሚፈጠሩም ናቸው፡፡ ይህ ጠጠር መሠል ባዕድ ነገር ብዙ ጊዜ ባለበት ቦታ ላይ ችግርን የሚፈጥር ሳይሆን ሆኖም ግን የሽንት ቧንቧ ላይና ወደ ሌሎች አካላቶች ላይ መግባት ሲጀምር ችግር እየፈጠረ እንደሚመጣ በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎች ይገልፃሉ፡፡
ኩላሊት ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ በሰውነታችን ውስጥ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከደም እያጣራ በሽንት መልክ ማስወገድ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ አንዳንድ ሚኒራልና ኬሚካሎች ኩላሊት ውስጥ በመቅረት ወደ አሸዋነት ይቀየራሉ፡፡ ከጊዜ በኋላም እነዚህ አሸዋ መሰል ነገሮች ወደ ድንጋይ
በመቀየር አደጋን ያስከትላሉ ማለት ነው፡፡
1ኛ. የኩላሊት ጠጠር ለምን ይከሠታል?
የኩላሊት ጠጠር በአንዳንድ ሰዎች ላይ በምን አማካኝነት ሊከሠት እንደሚችል የተረጋገጠ ነገር የለም በአንዳንዶች ላይ ደግሞ በምን እንደተከሰተ ማወቅ የሚቻልበት ደረጃ እንዳለ ባለሞያዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ከላይ እንደጠቀስነው ኩላሊት ደምን ሲያጣራ በሚቀሩ ሚኒራሎችና ሌሎች
ጠጠር ነገሮች አማካኝነት ሊከሰት እንደሚችል ነው፡፡
2ኛ. የኩላሉት ጠጠር ተጋለጮች እነማን ናቸው?
• ከ8ዐ በመቶ በላይ የሚሆነው የኩላሊት ጠጠር ተጠቂ ወንዶች ናቸው፡፡
• በዘር አማካኝነት ሊተላለፍ እንደሚችልም ይነገራል በተለይ እንደ ሲስታይን፣ኦክስሬት እና ዩሪክ አሲድ የመሳሰሉ ኬሚካሎችን ሜታቦላይዝ ማድረግ ኩላሊት ካልቻለ፡፡
• ሞቃታማ አካባቢ የሚኖሩና ፈሳሽ አዘውትረው የማይወስዱ ሰዎች ላይ ይከሠታል፡፡
• የካልሲየምና የቫይታሚን ዲ ንጥረ ነገሮችን አብዝቶ መጠቀም፡፡
• በብዛት መድኃኒቶችን መጠቀም በተለይ ዲላቲን፣ሴፋትራክሶን እንዲሁም ሲፕሮፋሎ ክሳስሊን የተሰኙ መድኃኒቶችን በበለጠ የኩላሊት ጠጠርን ያመጣሉ፡፡
• በደማቸው ውስጥ የኤች.አይ. ቪ.ቫይረስ ያለባቸው ሰዎችም ተጋላጮች ናቸው፡፡
3ኛ. የኩላሊት ጠጠር ምልክቶች
የኩላሊት ጠጠር በተለይ በኩላሊት ላይ ብቻ ተቀምጦ ከቆየ ምልክቶችን በአብዛኛው አያሳይም ይሁንና ይህ ሁኔታ ለከባድ ኢንፌክሽን ሊዳርግ ይችላል፡፡ ይህ ጠጠር ታዲያ ከኩላሊት ወደ ፊኛ መተላለፍ ከጀመረ ቶሎ ቶሎ መሽናት እና የሽንት ግፊት መጨመር ያስከትላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጎን ውጋት መራቢያ አካላት ላይ ከፍተኛ የማቃጠል ስሜት እንዲሁም ውጋት መሠል ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ በሽንት ላይ ደም መታየት ዋናዎቹ ናቸው፡፡
4ኛ. የኩላሊት ጠጠርን እንዴት ማከም ይቻላል?
የኩላሊት ጠጠር ያለባቸው ህሙማኖችን ለመለየት ሐኪሞቹ በቀላሉ በሚያዩት ምልክት ለይተው ማከም ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ለህክምና የሚውሉ መሣሪያዎች ማለትም እንደ ኮምፒዩተራይዝድ ቴሞ ግራፊ /CT/ እንዲሁም በአልትራሳውንድ አማካኝነት ጠጠሩ እንዳለ ማወቅ ይቻላል፡፡ በአብዛኛው የኩላሊት ጠጠር በራሱ የሚወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህም የሚሆነው አብዝቶ ውኃ ፈሳሽን በመውሰድ ነው፡፡ አንድ የኩላሊት ጠጠር በኩላሊቱ የተገኘበት ሰው በቀን ሁለት ሊትር ውኃ ቢጠጣ ጠጠሩን ጨርሶ ሊያስወግደው ይችላል፡፡ ከዚህ ካለፈ ግን ሌላው አማራጭ ቀላል ቀዶ ጥገና በማድረግ ጠጠሩን የማስወገድ ስራ ነው፡፡ ይህ ታዲያ በህክምና ባለሞያዎች የሚከናወን ነው፡፡
5ኛ. የኩላሊት ጠጠርን መከላከል ይቻላል?
የኩላሊት ጠጠርን ለመከላከል ወይም እንዳይከሰት ለማድረግ በየቀኑ ሁለት ሌትርና ከዛ በላይ ውኃ መጠጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተለይ በመድኃኒት ለሚመጡ የኩላሊት ጠጠሮች አሁንም አብዝቶ ፈሳሾችን በመውሰድ ቶሎ ቶሎ እንዲሸኑ ስለሚያደርግ በዚያም አማካኝነት ጠጠሩን ማውጣት ስለሚቻል ፈሳሹን መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡
እንግዲህ የኩላሊት ጠጠር እኛ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች አለም ላይ ያሉ ህዝቦችን ከአንዱ አንዱን ሳይለይ የሚያጠቃ የበሽታ አይነት ነው፡፡ ሆኖም በሽታውን በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል ከላይ ለማስቀመጥ ሞክረናል፡፡ ስለዚህ ያንን በመጠቀም በሽታውን በቀላሉ መከላከል ነው፡፡ አልያም ደግሞ በአቅራቢያዎ በሚገኙ የህክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ ስለበሽታው መረዳት መልካም ነው እንላለን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡