ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
March 7, 2016 – ትንታኔ
አንድ ማኅበረሰብ ዓይናማ ያወቁ የበቁ የነቁ የጠነቀቁ ልበ ብርሃን ሊቃውንት ያግኝ ይውጡለት እንጅ መላ እሴቶቹን በሙሉ ማለትም ወጉን፣ ባሕሉን፣ አስተሳሰቡን፣ ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ሃይማኖቱን ወዘተረፈ. እንዲፈተሽ፣ እንዲተች የግድ መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ ካልሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ለመፈተሽ ለመተቸት ካልፈቀደ እንዲታይ እንዲገለጥ የማይፈልገውና ቢታይ ቢገለጥ ቢተች የሚያፍርበት የሚሸማቀቅበት አንዳች ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ ዐይናቸውን የገለጡቱ የበራላቸው ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት አለባቸውና እነኝህ ምሁራን ዝም ማለት ስለማይችሉ ስለማይኖርባቸውም የማኅበረሰባቸውን ጠንቀኛ አስተሳሰቦች ለመንቀስ ለመቅረፍ በፈለጉ ጊዜ በልኂቃኑ አቀጣጣይነት ከማኅበረሰቡ ጋር ግጭት የሚፈጠር ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ከጥንት ጀምሮ በመላው ዓለም ልማዳዊና ባሕላዊ አስተሳሰብ ከተጫነው ማኅበረሰብ የወጡ ዓይናሞች ተወግረው እስከ መገደል በእሳት እስከ መቃጠል እስከ መሰቀል ድረስ ደርሰው እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡ የብዙዎቹ አስተሳሰብ ዓለም እየሠለጠነ ሲሔድ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይሄም ሆኖ አሁንም ድረስ ብዙዎቻችን ፍልስፍናን የምንረዳበት መንገድ የተሳሳተ ነው፡፡
በዚህ ወቅት አስቀድሞም በነበረው ትውልድ ተማርኩ የሚሉ በርካታ ወገኖች ምሁርነትና ፈላስፋነት ማለት በእግዚአብሔር አለማመን፣ ሃይማኖትን መቃወም ማረካከስ፣ ማኅበረሰቡ ተቀብሎት ከሚኖረው እውነት፣ ሥነምግባር፣ ግብረግብ፣ የሞራል (የቅስም) እሴቶች ጋር መጋጨትን አለመቀበልን የመማራቸው ማረጋገጫ አድርገው ለማሳየት ይጠቀሙበት ነበር እየተጠቀሙበትም ይገኛሉ፡፡ በእግዚአብሔር ማመንንም ሞኝነት ቂልነት ለማስመሰል ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡
በእግዚአብሔር አለማመን መብት ቢሆንም “እንዴት?” እና “ለምን?” ለሚሉት ጥያቄዎች ግን መልስ መስጠት አመክንዮአዊና ሞራላዊ (ቅስማዊ) ግዴታ መሆኑን፤ ለእነኝህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ሳይችሉ በእግዚአብሔር አላምንም ማለት እጅግ የወረደ ማንነት ወይም ድንቁርና ስለመሆኑ ወይም ይሄ አመለካከታቸው ምን ያህል የተሳሳተና ያልበሰለ እንደሆነ በዚህ ጽሑፍ ላይ በስፋት እናያለን፡፡ ሁሉንም ዓይነት አንባቢ ሊገባው በሚችል መልኩ ግልጽ በሆነና በተብራራ መልኩ በመጻፉ ሁላችሁም ይገባቹሀል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ መልካም ንባብ፡-
ፍልስፍና ማለት ምን ማለት ነው? ለዚህ ጥያቄ ባጭሩ መልስ ስንሰጥ፡- ፍልስፍና ማለት በእግዚአብሔር አለማመን ሃይማኖትን፣ መቃወም፣ ማረካከስ፤ ማኅበረሰቡ ተቀብሎት ከሚኖረው ባሕል፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ እውነት፣ ሥነምግባር፣ ግብረገብ፣ የሞራል (የቅስም) እሴቶች ጋር አለመስማማት መቃወም ማለት ሳይሆን ያልታየን ያልተደረሰበትን እውነት መግለጥ ማሳየት ማለት ነው፡፡
እርግጥ ነው በዓለማችን ጥቂት የማይባሉ ፈላስፎች በእግዚአብሔር መኖር የማያምኑ አሉ፡፡ በእግዚአብሔር የማያምኑ እንዳሉ ሀሉ ደግሞ የሚያምኑም የሚያምኑ ሲባል በጣም የሚያምኑም አሉ፡፡ “የማያምኑቱ የእግዚአብሔርን አለመኖር ስለደረሱበትና እውነት ስለሆነ ነው ወይ የገለጡት የተናገሩት?” ካላቹህኝ አይደለም ነው መልሱ ዝርዝሩን ወደ ኋላ እናየዋለን፡፡
በእግዚአብሔር መኖር ከሚያምኑት ታዋቂና ታላላቅ ፈላስፎች ጥቂቶችን እንጥቀስ ካልን ካንት፣ ሔግል፣ ዲስካርትስ፣ ፊችት፣ ሌይብኒዝ፣ ሩሶው፣ ኪከርጋርድ፣ ማሪቴይን፣ ዊትገንስቲ፣ ዌይል የመሳሰሉት በእግዚአብሔር ላይ ጥልቅና ጥብቅ እምነት ያላቸው በመባል ይጠቀሳሉ፡፡
እንዲሁም ከአንጋፋ ሳይንቲስቶችም እንጥቀስ ከተባለ ቀደምቱና አንጋፋው የሃያኛው ምእት ዓመት መጣቂ (ሳይንቲስት) እ.ኤ.አ. (1879-1955) አልቨርት አንስታይንን በቅድሚያ እናገኛለን፡፡ እሱ እንዲያውም አንድ ተወዳጅ አባባልም አለው “Science without religion is lame, religion without science is blind.” “መጣቅ (ሳይንስ) ያለ ሃይማኖት ሽባ ነው፤ ሃይማኖት ያለ መጣቅ እውር ነው” በማለት የተናገረው አባባል ይጠቀስለታል፡፡
የተቀሩት ደግሞ እነ ማክስ ፕላንክን (1858-1947) ዊሊያም ቶምሰን ከልቪንን (1824-1907) ግሪጎር ሜንደልን (1822-1884) ሚካኤል ፋራዴይን (1791-1867) ሮበርት ቦይልን (1791-1867) ኢሳክ ኒውተንን (1642-1727) ብሌይዝ ፓስካልን (1623-1662) ሬን ዲስካርትስን (1596-1650) ጋሊሊዮ ጋሊሊን (1564-1642) ጆሐንስ ኬፕለርን (1571-1630) ሰር ፍራንሲስ ባኮንን (1561-1627) ኒኮላስ ኮፕርኒከስን (1473-1543) የመሳሰሉትን ታላላቅ ሳይንቲስቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በእውነቱ እኔ ሰው “በእግዚአብሔር አላምንም!” ሲለኝ ለእሌ የሚገባኝ ምን እንደሆነ ታውቃላቹህ? ዓይን አለኝ አላይበትም ጆሮ አለኝ አልሰማበትም ጭንቅላት አለኝ አላስብበትም ያለኝ ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡ መመጻደቄ አይደለም ምን ማለቴ እንደሆነ ወደ ኋላ በደንብ ግልጽ ሆኖ ይገባቹሀል፡፡
አፍንጫችንን ተራራው ላይ አስነክተን በመጠጋት ዓይናችንን የቱንም ያህል ብንበለጥጥ ተራራው ላይ ያለችውን ጠጠር እንጅ ተራራውን አናየውም፡፡ በእግዚአብሔር መኖር አላምንም የሚሉ ሰዎች የተራራው መኖር እርግጥ ሆኖ እያለ የት ሆነው እንዴት ማየት እንዳለባቸው ካለማወቅ ተራራው የለም የሚሉ ናቸው፡፡ ማሰብ ማስተዋል ስለተሳናቸው እግዚአብሔር እንደተራራው የቅርብ እሩቅ ሆኖባቸው ነው እንጅ አእምሮ ልቡና ቢኖራቸው ማሰብ ማስተዋል ቢችሉ የእግዚአብሔርን መኖር እንደመረዳት እንደማወቅ የቀለለ ጥያቄ የለም! ስል ያለ አንዳች ማጋነን ነው፡፡
ሌላው ሁሉ ይቅርና በዙሪያቸው ያለውን ነገር ልብ ብለው ቢመለከቱ ሊመለስላቸው የሚችለውን ነገር ነው ሊያውቁት ያልቻሉት፡፡ እንበል ለምሳሌ ፍጥረታት ሁሉ ማለትም እንስሳት፣ አራዊት፣ አእዋፍ፣ ዓሣት ወዘተረፈ. ያስተማራቸው ያሳያቸው ሳይኖር እንዴት ኑሯቸውን እንደሚገፉ፣ ከሚገጥማቸው ፈተናና ጠላት እንዴት እራሳቸውን መጠበቅ መከላከል እንደሚችሉ አውቀው የኑሮ ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ማን አስቻላቸው? አስቀድሞስ ጠብቀውት የሚኖሩበትን ሥርዓት ማን አበጀላቸው? ጠብቀውት እንዲኖሩስ እንዴት አስቻላቸው? ፍየልን እባብ ከበላች በኋላ መርዙ እንዳይገላት ፈልጋ የምትበላትን ቅጠል የእባብ መርዝ ማርከሻ መድኃኒቱ ያች ቅጠል መሆኗን ማን ነገራት? ማን አስተማራት? እባብ መርዝ እንዳለውና ስትበላው እንደሚገላትስ ማን ነገራት? ሞታ የተነሣች ፍየል ፍየሎችን ሁሉ ሰብስባ ስለነገረቻቸው ነው? ወይስ ገበሬዎቹ እየነገሯቸው? ዶሮን የጣለቻቸው እንቁላሎች ጫጩት ሆነው እንዲፈለፈሉ ሙቀት መስጠት እንዳለባት አውቃ ለሃያ አንድ ቀናት መታቀፍ እንዳለባት አውቃ ያንን የምታደርገው ማን ነግሯት ነው? ገበሬዎቹ ይሆኑ?
ለእኛ ቅርብ የሆኑትን ምሳሌዎች ለመጥቀስ ያህል እንጅ ከእንስሳት ዓለም ስንት ድንቅና ግርም የሚሉ ትንግርቶችን ማንሣት በተቻለ ነበር፡፡ በናሽናል ጂኦግራፊ (በብሔራዊ መልክዓ ምድር) ድርጅት እየተዘጋቹ የሚቀርቡትን ቪዲዮዎችን (ትዕይንተ ኩነቶችን) ብታዩ ብዙ የምትረዱት ነገር ይኖራል፡፡
ፍጥረታቱ ሁሉ የነገራቸውና ያስተማራቸው ሳይኖር እነዚያን ኑሯቸውን የሚገፉባቸውን አስደናቂና አስገራሚ ዕውቀቶችን ያስተማራቸው ከሌለ ይሄንን ዕውቀት ይዘው እንዲፈጠሩ የሚያደርጋቸው ማን ነው? ተፈጥሯዊ ሕጋቸውን ጠብቀው ሳያፈርሱ የሚኖሩበትን ሥርዓት ማን ሠራላቸው? ያበጃጀው ያደራጀው የቀመረው ሳይኖር እራሱ በራሱ ጊዜ ተበጃጀ? ተቀመረ? ተሠራ? ተከወነ? ተወሰነ?
እስኪ ሰውነታቹህን ተመልከቱ ይህ አካላቹህ በተሳካ ሁኔታ እንዲያደርግ የሚጠበቅበትን እንቅስቃሴ ሁሉ እንዲያከናውን የአንጎል፣ የልብ፣ የሳንባ፣ የዓይን፣ የጆሮ ወዘተረፈ የተቀናጀ፣ የተሰናሰለ፣ የተናበበ ሥራን ይጠይቃል፡፡ እንዲህ እጅግ በረቀቀና እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የእያንዳንዳቸውን የሰውነት አካላት የሥራ ክንውናቸውን ለመረዳት ከአእምሮ በላይ በሆነ ችሎቻ አበጃጅቶ፤ የመጨረሻ ቀጭኗን የደም ስርና ጅማት ያለጥቅምና ያለአገልግሎት ሳያስቀምጥ እንዲያ እጅግ በጠወሳሰበ ሁኔታ እያንዳንዳቸውን ፈጥሮ እየተናበቡ ሥራቸውን እንዲሠሩ ቀምሮ ያደራጀው ማን ነው? እንዲህ ያለ የሰውነት አካል አስቦበት የሠራው፣ ያበጃጀው፣ የፈጠረው ሳይኖር እንዲሁ በአጋጣሚ ተፈጥሮ ይገኛል? ወይም ደግሞ እራሱን በራሱ ፈጠረ?
እንሒድ ወደ ላይ ወደ ሕዋው እንውጣ የሕዋ ተመራማሪዎች የአጠቃላዩን ዩኒቨርስ (ፍጥረተ ዓለም) ማለት የፕላኔቶቹን (የዐበይተ ከዋክብትን) ያሉበትን አቀማመጥ ዑደትና ተያይዘው ስላሉ ነገሮች ፍጹም (ፐርፌክት) በሆነ መንገድ በዓላማና በምክንያት እጅግ እጹብ ድንቅ በሆነ መንገድ ስለ መተለማቸው (ዲሳይን ስለ መደረጋቸው) ሲናገሩ አድንቀውና አውርተው አይጠግቡም፡፡ ያሰበበት ያበጃጀው ያደራጀው ሳይኖር በአጋጣሚ እንዲህ ሆኖ የመተለም (ዲሳይን የመደረግ) ዕድሉም ከዜሮ በታች ነው ብለውም ይመሰክራሉ፡፡
እንግዲህ ምን ማለቴ ነው ልብ ያለውና አስተዋይ ለሆነ ሰው እያንዳንዷ በአካባቢያችን ያለች ነገር ሁሉ ልብ ብሎ ለተመለከታት የፈጣሪን መኖር ትመሰክርለታለች፡፡ ደናቁርቱ ግን ይሄንን ማሰብ ማስተዋ መገንዘብ መረዳት ማጤን አይችሉምና ሁሉንም ቦታ አስሰው ፈልገው እንዳጡት ሁሉ አፋቸውን ሞልተው “ፈጣሪ የለም!” ሲሉ ትንሽም አይከብዳቸውም፡፡ የደንቆሮ ነገር ይሄው አይደል! በእነሱ ዘንድ ምንም ነገር ለማለት ድፍረት በሽ ነው፡፡
የተፈጠረ ነገር ሳይኖር “ፈጣሪ የለም!” ቢሉ ምንም ባልገረመኝ ባልደነቀኝ ነበር፡፡ ሰው እንዴት በዓይኑ የሚያየውን፣ በጆሮው የሚሰማውን፣ በእጁ የሚዳስሰውን፣ የተሸከመውን ነገር ዓይቶ አስተውሎ ማወቅ መረዳት መገንዘብ ይሳነዋል? የተፈጠረ፣ የተበጃጀ፣ የተደራጀ፣ የተቀመረ ነገር ካለ ማለት የሚቀለው “ፈጣሪ አለ!” ማለት ነው ወይስ “የለም!” ማለት? ከዚህ የከበደ ድንቁርናስ ምን አለ? አስቂኙና ማስተዋል የጎደለው አባባልስ የትኛው ነው? ለዚህም ነው ታላቁ ሳይንቲስት (መጣቂ) አንስታዩን “ፈጣሪ የለም!” የሚሉትን ሽባ ሲል የገለጻቸው፡፡
ይሄ ያልበሰለ ልጅ በመጽሐፉ በእግዚአብሔር ስላመኑ የዋሀን ሲል የሚጠራቸው ወገኖቻችን እሱ ያላንዳች ሐፍረት “ያወኩ የነቃሁ ነኝ!” የሚለው ሊያስተውለው ሊረዳው ያልቻለውን ከላይ የገለጽኩትን ሁሉ ትንግርት ልብ ብለው በማስተዋል ያለፈጣሪ እንዲህ ተሰካክቶ ሊቀመር ሊበጃጅ እንደማይችል በመረዳታቸው ነው “ፈጣሪ አለ!” ብለው ሳያወላውሉ ሊያምኑ የቻሉት፡፡ ቢያውቀው የዋሁ የማያስተውለውና ደንቆሮው እሱ እንጅ እነሱ አይደሉም፡፡
ሌላኛው የእግዚአብሔርን መኖር ያረጋግጣል የምለው አመክንዮ፡- መቸም ሰው ሆኖ የማይመኝ ሊኖር አይችልም፡፡ የሰው ጭንቅላት በተፈጥሮው እንዲሆን እንዲደረግለት እንዲያገኘው የሚፈልገውን እንዲመኝ ተደርጎ የተፈጠረ ነው፡፡ እኔ ተመኝቸ ፈልጌ አላውቅም የሚል ሰው ቢኖር እራሱን ሐሰተኛ ማድረጉ ነው፡፡ ጭንቅላቴ አያስብም ማለት ነውና፡፡ የሰው ልጅ እሱ ማድረግ ማግኘት ስላልቻለም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚፈልገውን ነገር እንዲሆንለት እንዲያገኝ ይመኛል፡፡
ይሄ ማለት የምንመኘውን ነገር ሊያደርግልን የሚችል ኃይል አለ ማለት ነው፡፡ መቸም ምንም ነገር የሚያደርገው የሚከውነው ሳይኖር በራሱ አይፈጸምም አይሆንምና፡፡ ጭንቅላት ሲፈጠር የሚመኝ ሆኖ የተፈጠረው የሚመኘውን ነገር የሚፈጽም ኃይል ስላለ ነው፡፡ ጭንቅላት የሚመኘው ከምንም ተነሥቶ ሳይሆን የሚያደርገው አካል እንዳለ ስለሚያውቅ ነው የሚመኘው፡፡ ጭንቅላት ጤናማ በሆነ ሁኔታ እስካሰበ ጊዜ ድረስ ሊሆን የማይችልን የሌለን ሊፈጸም የማይችልን ነገር አያስብም አይመኝም፡፡
እናም እኛ በተለያየ ምክንያትና መንገድ በአቅም ውስንነት ተገትተንም ይሁን በሌላ ልናደርገው ልናገኘው ያልቻልነውን እንዲያደርግልን የምንጠብቀው ኃይል ያ ማለት ነው እግዚአብሔር ማለት፡፡ ይሄንን ስል መቸም ያን እንዲደረግልን የፈለግነውን ነገር እሱ እራሱ እግዚአብሔር ወርዶ ያደርገዋል ማለቴ አይደለም፡፡ በሆነ አካል ያድርና ነፍስ ያለውንም ግዑዙንም ነገር በመጠቀም ሁኔታዎችን በማሰካካት የተመኘነውን ነገር እንዲደረግ እንድናገኘው እንዲሆንልን እንዲፈጸምልን ያደርጋል እንጅ፡፡
ምን እያልኳቹህ መሰላቹህ የሰው ልጅ በዚህ መልኩ አቅመ ውሱን ሆኖ መፈጠሩ ይሄንን ክፍተቱን የሚሞላለት ኃይል (ፈጣሪ) መኖሩን ያሳያል፡፡ አቅመ ውሱንነቱ እራሱን በጭንቅ ጊዜ ከጭንቅ፣ በመከራ ጊዜ ከመከራ ለማዳን ለመጠበቅና እራሱን ከአደጋ ሥጋት ፍጹም ነጻ ማድረግ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ከድሮ ጀምሮ የሰው ልጅ እራሱ ለራሱ ይሄንን ማድረግ ካልቻለና ይሄንን የሚያደርግና እያደረገ ያለና የነበረ ኃይል ካለ በቃ! ያ ማለት ነው እግዚአብሔር ማለት፡፡
እናም ከዚህ ከዚህ በመነሣን ነገሩን በአስተውሎት ያየነው እንደሆነ “እግዚአብሔር የለም!” ማለት አለመብሰል መሆኑን መረዳት የሚቸግረን አይመስለኝም፡፡ ከላይ የጠቀስኩላቹህ ዓለም ያከበረቻቸው ታላላቅ ሰዎች በእግዚአብሔር ያመኑት ያሳይቡ ሳይመረምሩ የተረዱት ነገር ሳይኖር አይደለም፡፡
የዛኑ ያህል ደግሞ የእነዚህን የአማኞቹን ያህል ማሰብ መመርመር መረዳት ያልቻሉት ደግሞ ታላላቅ ሰዎች የሚባሉ ቢሆኑም የማያምኑ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህ አባባላቸው ስሜት ላይ እንጅ ዕውቀት ላይ የጠመሠረተ እንዳልሆነ ከላይ ላነሣናቸው አመክንዮዎች ምላሽ መስጠት የማይችሉ መሆናቸው ያረጋግጣል፡፡ ሁሉም ሊባሉ በሚችል ሁኔታ እነዚህ “እግዚአብሔር የለም!” ያሉ ዓለም ታላላቅ የምትላቸው ሰዎች “እግዚአብሔር የለም!” ያሉት ብዙ ሳይበስሉ ሳይመረምሩ ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው ከዕድሜ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ስሜት በመሸነፍ ለሃይማኖታዊ ሕግጋትና ለሞራል (ለቅስም) ድንጋጌዎች ላለመገዛት ላለመታዘዝና ስሜታቸው እንደወደደ መጠን “አጥፍታቹሀል! ኃጢአት ነው!” ሳይባሉ እነሱም “ደካማ ስለሆንኩ ተሸንፌ ሳይሆን በድንጋጌው ስለማላምንበት ነው!” በማለት ደካማ ተብለው ተወቃሽ ተከሳሽ እንዳይሆኑና ስሜታቸው ያዘዛቸውን የፈለጉትን ነገር ያለከልካይ እንዳሻቸው ለማድረግ ሲሉ ነው “እግዚአብሔር የለም!” የሚሉት፡፡
በወጣትነት ብዙ ሳያውቁ ሳይመረምሩ “እግዚአብሔር የለም!” ያሉ ፈላስፎች እድሜያቸው እየጨመረ ሲሔድ ከብዙ አቅጣጫ በሚያገኙት ዕውቀት ትምህርትና አስተውሎት እግዚአብሔር መኖሩን ቢረዱም ቢያውቁም ቢያረጋግጡም ያንን መመስከር አይፈልጉም፡፡ በፊት “የለም!” ብለው ስለነበረ አሁን “አለ!” ቢሉ እንደ አላዋቂና በስሜት እንደሚነዳ ማስተዋልና ኃላፊነት እንደጎደለው ሰው ስለሚያስቆጥራቸው ከጊዜ በኋላ በመጣና ባገኙት ዕውቀትና አስተውሎት ፈጣሪ መኖሩን ቢያውቁም ቢረዱም አለ ብለው አይመሰክሩም፡፡ የለም ብለው እንደደረቁ ይሞታሉ፡፡ እናም ወጣት “ፈላስፎች” አንዴ የያዙትን አቋም እስከመጨረሻው ይዘው የሚቀሩትና የመማር የመለወጥ ዕድል የማይኖራቸው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
“እግዚአብሔርን በአካል ካላየነው በስተቀር አናምንም!” ከሆነ ጥያቄያቸው አዎ! በእርግጥ እግዚአብሔርን ማየት ይቻላል፡፡ የዩኒቨርስን (የፍጥረተ ዓለሙን) ስፋት ጥልቀትና ግዝፈት ተመልክታቹህ የዚህ ሁሉ ትንግርት ፈጣሪ ደግሞ ምን ያህል ሊያይል ሊገዝፍ ወይም ሊረቅ ማለትም ለማየት ከእኛ አቅምና ችሎታ በላይ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ እንደሚገባ ታውቆ ማየት ከተፈለገ ግን እግዚአብሔር ከዚህ ቀደምም ለነቢያቱ ለሐዋርያቱ ለቅዱሳኑ ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ ልትረዱት በምትችሉት መጠንና አምሳል ተገልጦ ሊታያቹህ ይችላል፡፡ ይሁን እንጅ ለማየት ግን ቅድስና ያስፈልጋል፡፡ እንኳንና እግዚአብሔርን ሰይጣንን ለማየት እንኳን ቅድስና ያስፈልጋል፡፡ ሰይጣን ውዳቂ ምናምንቴ ስለሆነ ለሁሉም ዓይታይም፡፡ በእርግጥ ለጠንቋዮች ማለትም ለአገልጋዮቹ ይታያል፡፡ እየጠነቆሉ በሚያደርጉት ነገር እሱን ስለሚያገለግሉት፡፡ ለመገልገል ለማዘዝ እንዲመቸው ለነሱ ይታያቸዋል፡፡
አሁን ወደ በውቀቱ እንለፍ፡፡ አንዴ ከዓመታት በፊት ነው ቆይቷል በውቀቱ ሥዩም በአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ላይ እየተሳለቀ “…የእኛ አባቶች ለተጠማ ወፍ ዓይናቸውን አፍስሶ ውኃ እንዲጠጣ የሚፈቅዱ የዋሀን ናቸው…” በማለት ስላፌዘ ደወልኩለት፡፡ እንደምታውቁት በውቀቱ ፍጹም አመክንዮአዊና ሥርዓት በሌለው፣ ሞያዊ አኪያሔድ ባልጠበቀ መንገድ፣ ሚዛናዊነት የሚባል ዕይታ ጨርሶ በሌለው ዓተያይ በቅዱሳንና በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እሴቶች ላይ እያፌዘና እየቀለደ ያለ፤ በዚህም መታወቅ የሚፈልግና ይሄንን በማድረጉም እንደፈላስፋ ለመቆጠር የሚመኝ የሚጥር ግለሰብ ነው፡፡
እናም ከዓመታት በፊት የገና ዕለት ደወልኩለት፡፡ ከላይ የጠቀስኩትን ቃል አስታወስኩትና በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እንድንነጋገር ፈልጌ እንደደወልኩለት ነገርኩት፡፡ ለመነጋገር ፈቃደኛ እንደሆነ ገለጸልኝና ለረጅም ሰዓታት አወራን፡፡
ቅድሚያ ያነሣነው ጉዳይ የነበረው “እንዲህ ዓይነት ነገሮችን መናገር ፈላስፋነት ይመስልሀል ወይ?” ብየ የጠየኩትን ጉዳይ ነበር፡፡ እሱም ፈላስፋ ለመሆን ሳይሆን የታየውንና ትክክል ነው እውነት ነው ብሎ የማያምንበት ነገር ሐሳብን የመግለጽ ነጻነቱን በመጠቀም እንደገለጸ ነገረኝ፡፡ እኔም “አይ ይሄ እማ ከሆነ እራስህን ወንጀለኛ አድርገሀል ማለት ነዋ! እኔ መስሎኝ የነበረው እራስህን እንደፈላስፋ ቆጥረህ በፈላስፋነት ያለውን ነጻነት ተጠቅመህ ለመተቸት ለመሔስ አስበህ የምትናገር አድርጌ ቆጥሬህ ከተናገርከው አንጻር ፍልስፍና ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመነጋገር ነበር ያሰብኩት፡፡ እንዲህማ ከሆነ የፈላስፋነት ከለላም አይኖርህም ተራ ወንጀለኛ ሆንክ ማለት ነው” ስለው “የተናገርኩት ከፍልስፍና አንጻር ማየት አይቻልም?” ሲል ጠየቀኝ “ከፍልስፍና አንጻር ለማየት አይደለም ስላልክ ከሱ አንጻር ነበር ወንጀለኛ ነሀ ያልኩት፡፡ ምንም ነገርን መተቸት የለብህም” ማለቴ እንዳልሆነ ገልጨለት ሲተች ግን ሞያዊ የትችት ወይም የሒስ አሰጣጥ ዘዴን መከተል እንደሚኖርበት፣ ከዚህ አንጻር ይህ ስለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተናገረው ነገር እንደሌሎቹ በእሴቶቻችን ላይ የሚናገራቸው ነገሮች ስድነት የሚታይባቸው ተራ የጥላቻ ወሬ መሆኑን ይሄም ትዝብትና መገመት ላይ እንደሚጥለው ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡
እሱም ይህ የተናገረው ነገር ሞያዊ የሚሆነው እንዴት ቢሆን እንደነበረ ጠየቀኝ፡፡ እኔም አነጋገሩ የፍልስፍናን የመከራከሪያ አኪያሔድና ስልት የተከተለ የጠበቀ እንዳልሆነ ስነግረው “እንዴት?” ሲል ጠየቀኝ “ጥሩ” በማለት ይሄን ወደ ኋላ እንደምናየው ነግሬው አሁን ግን አንተ “የመናገር ነጻነትን መብት ከመጠቀም አንጻር ነው የተናገርኩት” ብለሀልና ከዚህ አንጻር የተናገርከው ነገር እንዴት ስሕተት እንደሆነ እናውራ አልኩትና በዚሁ ጉዳይ አወራን፡፡
ይሄውልህ በውቀቱ እርግጥ ነው አንተ እንዳልከው አንድ ሰው ሐሳቡን በነጻነት የመግለጥ ተፈጥሯዊ መብትና ነጻነት አለው፡፡ ፖለቲከኞች (እምነተ አሥተዳደራዊያን) ይሄንን መብት ከዲሞክራሲያዊ (ከመስፍነ ሕዝባዊ) መብቶች አንዱ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጅ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር (እንስሳ ላለማለት ነው) እንደመሆኑ ምንም እንኳን ሐሳብን በነጻ የመግለጥ ነጻነት ቢኖረውም ያ የሚናገረው ነገር የሌሎቹን መብት የሚጥስ የሚጋፋ የሚያጠቃ ከሆነ መብት መሆኑ ቀርቶ ወንጀል ይሆናል፡፡ እንደ ማኅበራዊ ፍጡርነታችን ሐሳብን በነጻ የመግለጥ መብት የጋራ ጥቅማችንን ከመጉዳት ከማጥቃት በመለስ ያለ መብት እንጅ ሥርዓትና አግባብነት በሌለው መንገድ እንደፈለግን የሌሎችን መብት ማንነትና ጥቅም ልናጠቃ የምንችልበት መብት አይደለምና፡፡
አልኩትና አቶ ዓለማየሁ ሞገስን (በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወይም መካነ ትምህርት መምህር የነበሩ) ምሳሌ አድርጌ አቀረብኩለት፡፡ አቶ ዓለማየሁ ሞገስ እስላሞች ነቢያችን ናቸው የሚሏቸውን መሐመድን “ለምን አልሰለምኩም” በሚለው መጽሐቸው ለመግለጽ የሚቀፉ ድርጊቶችን እየዘረዘሩ “እንዲህ እንዲህ ያደረገ ነው” እያሉ ክፉኛ አበሻቅጠው አዋርደው ስለነበር እስላሞች ተጠቃን ተደፈርን ተዋረድን ብለው መክሰሳቸውን በማስታወስ ፍርድቤቱም ክሱን ትክክል ነው ብሎ ተቀብሎት እንደነበር፤ አቶ ዓለማየሁ ሞገስም “ለጠቀስኳቸው ነገሮች ሁሉ ማስረጃ ማጣቀሻዎች አሉኝ” ብለው የነ ሳልማን ሩሽኪን (ኢራን እሱን ለገደለ አምስት ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ስትል የሞት አዋጅ ያስነገረችበት ኢንግሊዛዊ ደራሲ) እና ሌሎች መሐመድ ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን በመከላከያ ማስረጃነት አቅርበው ጉዳዩ እየታየ እንዳለ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ክሱ እንደተቋረጠ በማንሣት ቤተክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ሥራውን በአግባቡ የሚሠራ ተቆርቋሪ አካል ስለሌላት እንጅ እሱ የሚናገራቸው ነገሮች ተራና መረጃ የሌለው ስም ማጥፋትና ክብር መዳፈር ስለሆኑ ሊያስከስሱት ይችሉ እንደነበር ገለጽኩለት፡፡
እሱም በሀገራችን ነው እንጅ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ያልተለመደው በሠለጠነው ዓለም ግን እንዲህ ዓይነት ሒሶችና ትችቶች በነጻነት እንደሚሰጡ ተናገረ፡፡ እኔም “ልክ ነህ ግን አንተ በተረዳህበት መንገድ አይደለም” ስል ገልጨ ከላይ ወደ ኋላ እናየዋለን ወዳልኩህ ጉዳይ መግባታችን ነውና ወደዚያው ልግባ ብየ “እርግጥ ነው በሠለጠነው ዓለም እንዲህ ዓይነቱ ነገር የተለመደ ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም ሞያዊ አኪያሔድና አሠራር የተከተሉ አይደሉም ይሄም በመሆኑ ጥቂት የማይባሉ ትችቶች በእምነት ተቋማቱ ክስ እንደመተመሠረተባቸው ከፊሎቹ ደግሞ የአተያው ልዩነት ቢኖርም ሞያዊና በመረጃ የተደገፉ በመሆናቸው የእምነት ተቋማት ባይወዷቸውም ክስ ያልመሠረቱባቸው እንዳሉ ገለጽኩለት፡፡
ከዚህም ጋራ አያይዠ እሱ በአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ላይ የተናገረው ነገር እንዴት ሞያዊ አኪያሔድን የተከተለ እንዳልሆነ ልገልጽለት ሞከርኩ፡፡ እንዲህ በማለት፡- አስቀድሜ “ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” ስል ጠየኩት፡፡ ሃይማኖት እንደሌለውና በእግዚአብሔር እንደማያምን ቀደም ሲል ያልመረመረና አላዋቂ በነበረ ጊዜ ግን ኦርቶዶክስ እንደነበረ ነገረኝ፡፡ እኔም እሽ አስቀድመህም ከፈላስፋ አንጻር ትችቱን እንዳልሰጠህ ነግረኸኝ ነበር ከዚህ አንጻር ለማየት የሚያበቃ ብቃት ስለሌለው ስልህ እንዴት አይችልም ብለኸኝ ነበር እሱን አሁን እነግርሀለሁ፡፡ የተናገርከውን ልብ በል “የእኛ አባቶች ለተጠማ ወፍ ዐይናቸውን አፍስሶ ውኃ እንዲጠጣ የሚፈቅዱ የዋሀን ናቸው…” ነው ያልከው፡፡ “አባባልህ በሙሉ ልቡ ያላመነ የተጠራጣሪ አማኝ አባባል እንጅ የፈለስፋ አይደለም” ስለው “እንዴት?” አለኝ “አባባልህ የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስን ገድል ከፊል አምነህ ተቀብለሀልና፡፡ ለማለት የፈለኩት ገድላቸው ላይ እንዳለው አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ በወፍ ተመስሎ ለመጣው ሰይጣን ውኃ ሳያጣ ሲጠማው ሊጠጣ የሚችልበትን ሐይቁን ትቶ ምን ፈልጎ በምን ምክንያት ውኃ እንደጠየቃቸው ስለሚያውቁ የዓይናቸውን ውኃ እንዲጠጣ ስለመናገራቸው ገድላቸው ላይ የተጻፈውን አምነሀል፡፡ ይሄንን አምነህ የተናገርከውን ከተናገርክ በኋላ እንደገና ደግሞ ከዛ ወጥተህ ድርጊቱን ቂልነት ነው ልትል የምትችልበትን መሠረት ልታገኝ አትችልም፡፡ አባታችን ከዓይናቸው እንድትጠጣ መፍቀዳቸውን ቂልነት ነው ካልክ የወፏን በሰው አንደበት ተናግራ ውኃ አጠጡኝ ማለቷን ልታምን አትችልም፡፡ ስለዚህ በፈላስፋ ቦታ ሆነህ “ለተጠማ ውኃ ዓይናቸውን አፍስሶ እንዲጠጣ የሚፈቅዱ የዋሀን” በማለት ልትሳለቅ አትችልም ማለት ነው፡፡
የፈላስፋን የመተቸት መሠረት ወይም ሞያዊ አኪያሔድ የተከተለ አይደለም ያልኩህም ለዚህ ነው፡፡ ቀሽም ተች የሆንከውም ለዚህ ነው፡፡ ከፊሉን አምነህ ከፊሉን ለመተቸት በመሞከርህ፡፡ ሊሆን አይችልም ካልክ አለቀ በቃ ሊሆን አይችልም ወፏ በሰው አንደበት ተናግራ ውኃ አጠጡኝ ማለቷንም ማመን የለብህም፡፡ ይሄንን ካመንክ ደግሞ እሳቸው ወፏን ያስተናገዱበትን መንገድም ልትተች አትችልም፡፡ ካመንክ እንደ ተአምርነቱ ሁሉንም ማመን ይኖርብሀል ካላመንክም ሁሉንም አለማመን ይኖርብሀል፡፡ አንተ ከሁለቱም የለህም፡፡ በመሆኑም ያቀረብከው ሞያዊ አኪያሔድን የተከተለ ፈላስፋዊ ትችት ሳይሆን ሥነ ምግባር የጎደለው ስድ የደንቆሮ አባባል ነው፡፡ ከሁሉም የሌለ አንተነትህን ማንነትህን ብቻ የሚያሳይ ወንጀለኛ አነጋገር ነው፡፡ ስል መለስኩለት፡፡
በመቀጠል ለምን በእግዚአብሔር ከማመን ወደ አለማመን እንደተሸጋገረ ጠየኩት፡፡ እሱም “አይ! እግዚአብሔር የሚባል ነገር ስለሌለ፤ እግዚአብሔር የሚለውን አካል የፈጠሩት ሰዎች መሆናቸውን ስላወኩና በእግዚአብሔር ማመን ሞኝነት ቂልነት ስለሆነ ነው” አለኝ፡፡ እኔም “ጥሩ እግዚአብሔር አለመኖሩን እንዴት አረጋገጥክ? መሬቱንም ሰማዩንም አጠቃላይ ፍጥረተ ዓለሙን (ዩኒቨርስን) ፈትሸህ ስላጣኸው ነው? እንኳንና አንተ ጠፈርተኞችም እንኳን ገና ከማርስ አላለፉም በመንኮራኩር ጥቁር ጉድጓድን (ብላክ ሆልን) ለመሻገር ብቻ እንኳን በብዙ ሚሊዮን (አእላፋት) ዓመታት እንዲሚያስፈልግ ነው የሚናገሩት፡፡ አንተ ታዲያ ከጎጃምና ከአዲስ አበባ ሳታልፍ መላ ፍጥረተ ዓለሙን አስሰህ እንዳጣኸው ሁሉ እንዴት እግዚአብሔር የለም ትላለህ?” ስል መልሸ ጠየኩት፡፡ ሊመልሰው የቻለው ነገር አልነበረም፡፡
ቀጠልኩና ሲጀመር እንዲያው አባባልህ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ እንድትረዳና እራስህን እንድትታዘበው ይሄንን አልኩህ እንጅ እግዚአብሔር እንደ ዕቃ ተፈልጎ የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ለማየት ወይም መኖሩን ለማረጋገጥ የሚቻለው በእምነት መንገድ ነው እንጅ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አይደለም ማረጋገጥ የሚቻለው፡፡ ስለሆነም የትኛውንም መንገድ ተጠቅመህ ፈትሸህ ሳታረጋግጥ የለም ማለትህ እጅግ ግብዝና አላስተዋይነትህን እንጅ በሳል መርማሪነትህን አይደለም የሚያሳየው ስለው፡፡ እኔ በሱላይ የተጠቀምኩትን አመክንዮ በእኔ ላይ መጠቀም ፈለገና “አንተ በእግዚአብሔር ታምናለህ?” ሲል ጠየቀኝ “አዎ! በሚገባ ነዋ!” ስል መለስኩለት፡፡ ቀጠለና “አንተ በእግዚአብሔር ያመንከው መኖሩን አረጋግጠህ አይተኸው ነው?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ እኔም “አዎ” ስል መለስኩለት፡፡ እሱም “እንዴ! እንዴት ሊሆን ይችላል? ልታረጋግጥልኝ ትችላለህ?” ሲል ጠየቀኝ “በሚገባ” ስለው “አይ! በቃ መቀለድህ ነው መሰለኝ” አለኝ፡፡ እኔም “ኧረ እኔ እውነቴን ነው እንዲህ ባለ ቁምነገር ላይ ቀልድ አለ እንዴ!” ስለው “እና ምን እያለከኝ ነው?” አለ፡፡
እኔም ““ልብ ብለህ አድምጠኝ በውቀቱ፤ ቆይቷል ከዓመታት በፊት እኔም እንዳትተ ክህደት ጠልፎኝ “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድር በምድር ስላሉ ፍጥረታትና ስለሌሎች ዓለማት የሚሰጠው ምንም ዓይነት በቂ መረጃ የለም! እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ቢሆን ኖሮ ስለ እግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ በቂ መረጃ ይሰጥ ነበር በቃ! ይሄ ውሸት ነው…” በማለት የእግዚአብሔርን መኖር ተጠራጥሬ ለመፈጥፈጥ እየወረወርኩ የነበርኩበት ወቅት ላይ ሆኘ ለሥራ ጉዳይ ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ወደ ሆንኩበት ሀገር ሔጀ ነበረ እዚያ ቦታ ላይ የክህደት አስተሳሰቤን እንደጉም አብንኖ እንደጢስ አትንኖ ያጠፋልኝ አንድ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡
ለሥራ በሔድኩበት ሀገር እንዳልኩህ የማውቀው የሚያውቀኝ የሌለበት ቦታ ነው፡፡ እዚያ ሀገር እንደገባሁ በማግስቱ ከአካባቢው ሰው ጋር ሆኘ አካባቢውን ስጎበኝ የጸመል ቦታ ላይ ደረስኩ፡፡ ከጸበሉ ቦታ ላይ ተጸባዮች (ተጠማቂዎች፤ ተጠመቀ የሚለው ቃል በአርባና በሰማንያ የምናገኘውን የእግዚአብሔር ልጅነት ለመግለጽ ስለምንጠቀምበት ለዚህኛው ጉዳይ ተጸበለ የሚለው አማርኛ ተስማሚ ነው) ነበሩ፡፡ ከተለያየ ሕመም ወይም ደዌ ለመፈወስ የሚጸበሉ ነበሩ ካደረባቸው እርኩስ መንፈስ ለመላቀቅ ለመገላገል የሚጸበሉም ነበሩ፡፡
እኛ ከቦታው ስንደርስ ክፉ መንፈስ ካደረባቸውና ሲጸበሉ ያደረባቸው ይሄ ክፉ መንፈስ ይለፈልፍባቸው ከነበሩ ተጸባዮች በአንዷ ላይ የሚለፈልፈው ጋኔን እኔን በስሜ እየጠራ “የኛ ፈላስፋ! እግዚአብሔር የለም አይደል?” እያለ ከልጅነቴ ጀምሮ የተረፍኩባቸውን ለሞት የሚያበቁ አደጋዎችን እያስታወሰ “ከዚህ ከዚህ ያዳነህ ያተረፈህ ያወጣህ ማን ነበረ? አንተ ከሀዲ!” እያለ ይዘልፈኛል፣ እኔ እና እግዚአብሔር ብቻ የምናውቀውን ምሥጢርና የሠራሁትን ኃጢአቴንም ጭምር እየተናገረ ከዚያ ሁሉ ሰው ፊት አዋረደኝ፡፡ መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ በወደድኩ፡፡ እዚያ የጸበል ቦታ ላይ እንዲያ ከመዋረዴ የተነሣ ልገልጸው በማልችለው መልኩ እጅግ ቀልየ ብዙ መቆየት ስላልፈለኩ ወዳረፍኩበት ቤት ወዲያው ነበር የተመለስኩት፡፡ ይህ ሁኔታ እዚያ ሀገር የወሰደኝ የሥራ ጉዳይ የጥቂት ቀናት ቢሆንም ከሚገባው በላይ አሳጥሬ ቶሎ ወደ መኖሪያዬ እንድመለስ ስላስገደደኝ ቶሎ ተመለስኩ፡፡
ይህ አጋጣሚ ነበር አሁን አንተ እንደምትለው ሁሉ ተፈላሰፍኩ ተመራመርኩ ብየ “እግዚአብሔር የለም!” ከሚለው ክህደቴ መልሶ በሃይማኖት እንድጸና ያደረገኝ፡፡ ከዚያ በኋላማ ገዳማት ውስጥ ከተጋድሏቸው የተነሣ ለዚያ ጸጋ ከበቁ ቅዱሳን አባቶች ጋር በመገናኘት የነቢይነትን ጸጋ እንደማግኘታቸው ያሳለፍኩትንና የሚገጥመኝን እየነገሩ በመገሰጽና በማስጠንቀቅ ማወቅ የተፈቀደችልኝን ያህል እየነገሩም ሕይዎቴን አንጸውታል፡፡ ባገኙት ጸጋ ፈጣሪን በእነሱ ውስጥ ዓይቸዋለሁ መኖሩንም በዚህ መልኩ አረጋግጫለሁ፡፡
“መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ስለ እያንዳንዱ ነገር በቂ መረጃ ይሰጠን ነበር” ብየ እራሴ አንሥቸ እራሴ የተሰናከልኩበት ጥያቄም ማንም ሳይመልስልኝ መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ባለበት መልኩ የተጻፈው “ለአዋቂ አንዲት ቃል ትበቃዋለች” እንዲሉ በጥቁምታ ደረጃ እግዚአብሔር የሚባል አምላክ ፈጣሪ መኖሩን ለማሳወቅ ያህል መጻፍ የነበረበትና የተጻፈ ቅዱስ መጽሐፍ እንጅ ስለ አጠቃላይ ፍጥረተ ዓለም (ዩኒቨርስ) ይጻፍ ይዘርዝር ያስረዳ ቢባል ወንጌላዊው ዮሐንስ እንዳለው “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ዮሐ. 21፤25 እንዳለው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ሥራ ብቻ ሳይሆን ስለፈጠረው እያንዳንዱ ነገር ሁሉ ይናገር ቢባል መጽሐፉ መጽሐፍ መሆኑ ቀርቶ ሰማይ ጥግ ድረስ የሚደርስ እጅግ ግዙፍ ተራራ የሚያክል ሊሆን እንደመቻሉ የሚታሰብ ነገር አይደለምና ይሄ ሐሳቤ ትክክለኛ ጥያቄ አለመሆኑን ከእራሴ አመክንዮ ተረድቸ ተሰበሰብኩ እልሀለሁ በውቀቱ፡፡ ስለዚህች ዓለም ጉዳዮች የሚያትቱት የትምህርትና የምርምር ውጤት መጻሕፍት እንኳን ምን ያህል እንደሚበዙ አስብ፤ እኔ እያልኩ የነበርኩት መጽሐፍ ቅዱስ እነሱ የተናገሩትን ሁሉ መያዝ ነበረበት ነው እያልኩ የነበርኩት፡፡ አየህ ምን ያህል ቂል እንደነበርኩ?
በእርግጠኝነት አንተም ጸበል ቦታ ብትሔድ የግድ እኔ ሔጀበት ወደነበርኩበት ቦታ ማለቴ አይደለም የትኛውም ጸበል ቦታ ብትሔድ እግዚአብሔር ለአንተ በሚገባህ አንተ በምትረዳው መልኩ ተመሳሳይ ነገር አድርጎ ህልውናውን ወይም መኖሩን ያረጋግጥልሀልና ጸበል ሒድ፡፡ በሚገርም ሁኔታ የጸበል ቦታዎች እዚያ በሚሠሩ ተአምራቶች የእግዚአብሔር መኖር የሚረጋገጥባቸው (ፕሩፍ የሚደረግባቸው) ቦታዎች ናቸው፡፡ እንኳን የጸበል ቦታ የጠንቋይ ቤት እንኳን እግዚአብሔር መኖሩ የሚታወቅበት ቦታ ነው፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ሰይጣን በጠንቋዩ አድሮ የሚያደርገውን የክፋት ሥራና የሚሠራውን ተአምራት በማየት የማተካካትን (የሰብስቲቲዩሽንን) አመክንዮ በመጠቀም (A=B=C\A=C) በሚለው አካሔድ “ሰይጣን አለ ማለት ተቃራኒው እግዚአብሔር አለ ማለት ነው!” ብሎ በማሰብ የእግዚአብሔርን መኖር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ብየው እሱም በሆነው ነገር ተገርሞ “እሽ እሔዳለሁ!” ብሎኝ ነበር፡፡ ስንለያይም ስምህን አውሰኝ (አስተዋውቀኝ ማለቱ ነው ነገር ግን አውሰኝ የሚባለው ተገልግለንበት ለምንመልሰው ነገር ነውና የቃሉ አጠቃቀም ስሕተት ነው) ብሎኝ ስሜን ነግሬው ተለያየን፡፡
እናም ከዓመታት በፊት የጌታ ልደት በዓል በሚከበርበት ቀን ለበውቀቱ ደውየለት ይሄንን ነበር ያወራነው፡፡ አሁን ከልጁ “ከአሜን ባሻገር” ከሚለው መጽሐፉ እንዳየሁት ግን ምክሬን ሰምቶ እሽ ብሎኝ የነበረውን እንዳልፈጸመ ነው፡፡ ለምን እንዳልፈጸመም አላውቅም ወይም እንግዲህ “እግዚአብሔር የለም!” ማለትንና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እሴቶችን እያዋረደ እየዘረጠጠ መኖርን እንጀራው አድርጎት ይሄንን ማጣት ስላልፈለገም ሊሆን ይችላል ልጁ አሁንም ባለበት የክህደት ዓለም ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለነገሩ ይሄ ክህደቱና ቤተክርስቲያንን የማጥቃት የመዋጋቱን ነገር እያደረገ ያለው ካደረበት ጋኔን የተነሣ ነውና ደኅና ዘመድ ካልወሰደው በስተቀር እንደመከርኩት ሁሉ በራሱ ተነሣሽነት ወደ ጸበል ይሔዳል ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው፡፡ ይሄንን የሚያደርገው ካደረበት ጋኔን የተነሣ ስለሆነም ነው ብቸኛው ማረጋገጫ ነው ማለት ባይቻልም ልጁ አፉን የሚከፍተው በአንዲቷ ቤተክርስቲያን ላይ ብቻ እንጅ በእስላሞችና በመናፍቃን ላይ ትንፍሽ የማይለው፡፡ እንደ ከያኔ የከያኔነት ኃላፊነት ተሰምቶት የሚያየውን የሚያስተውለውን የሚሔስ የሚተች ቢሆን ኖሮ በመናፍቃኑና በእስላሞች ላይ ስንትና ስንት ሊለው የሚችለው ነገር ነበር፡፡
ይሄ ካልሆነ በስተቀር ለዚህች ሀገር ሁለንተናዊ ማንነት ከነጻነቷ እስከ ብርቁና ድንቁ ጥንታዊ ሥልጣኔዋ ድረስ ብቻዋን ስትፈጋ የነበረችን፣ ስንት ተነግረው የማያልቁ ትሩፋቶችን ያበረከተችን ቤተክርስቲያን፣ በመንግሥት አሥተዳደርም የከፋ ሲመጣ አባብላ ጫና ሲመጣባት እያቻቻለች ይህችን ሀገር ከሕዝቧ ጋር የተቻላትን ሁሉ በማድረግ ጠብቃ የኖረችን ቤተክርስቲያን ይሄንን ሁሉ ውለታዋን ገደል ከቶ ጥቃቅን ነገር እየጠቃቀሱ መኮነን፣ ለማዋረድ ዋጋ ለማሳጣት ጥረት ማድረግ ከድንቁርና የመነጨ ወራዳ ተግባር ወይም ለጠላት ቅጥረኛ ሆኖ ሥውር የባንዳነት ተልእኮን መፈጸም ካልሆነ በስተቀር በምንም ተአምር አግባብነት ያለው ተግባር ሊሆን አይችልም፡፡
አለማወቁ ነው እንጅ ይህች ቤተክርስቲያን በፍጹም በፍጹም እሱ በሚያስባት መልኩ የምትከሰስ አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከስድስት መቶ ዓመታት በፊት በአባ ማስያስ ገድል ላይ “ዓለም እንደጋን ድቡልቡል ናት ጠፍጣፋ አይደለችም!” ስትል የምዕራቡ ዓለም ስቆብን አፊዞብን ነበር፡፡ እነሱ ይሄንን እውነታ ለማረጋገጥ ዘመነ ቴክኖሎጂን (ኪነብጀታን) መጠበቅና ወደ ሕዋው መጥቆ ማረጋገጥ ግድ ነበረባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት በርካታ ነገሮች ሳይንስ (መጣቅ) የራሱ ግኝት አድርጎ የሚያወራቸው የቤተክርስቲያን ዕውቀቶች በርካታ አሉ፡፡ በሥነፈለኩ (በሕዋው ምርምር) ሳይንስ (መጣቅ) እስካሁን ከተጠቀመበት የቤተክርስቲያናችን ዕውቀት ይልቅ ገና ያልደረሰበት ይበዛል፡፡
ምዕራባዊያ ሀገራት ከሽህ ዓመታት በፊት ጀምሮ የእኛን የብራና መጻሕፍት የመዝረፍ እሽቅድድምና ሽሚያ ውስጥ የተጠመዱት ያለአንዳች ጥቅም አይደለም፡፡ በየ ዩኒቨርስቲያቸው (መካነ ትምህርታቸው) ዜጎቻቸውን የግእዝ ትምህርትን የሚያስተምሩት ለእኛ ቋንቋ ፍቅር ስላላቸው ሳይሆን እየዘረፉ የወሰዷቸውን መጻሕፍቶቻችን የያዟቸውን ዕውቀትና ጥበቦች ለመቦጥቦጥ ለመበዝበዝ ነው፡፡
የምዕራቡ ዓለም የመድኃኒት ፋብሪካዎች መድኃኒት ማምረትን ሲጀምሩ ብቸኛ የዕውቀት ምንጫቸው የነበረው የእኛ የብራና መጻሕፍቶቻችን መሆናቸውን እራሳቸው ይናገራሉ፡፡ የጀርመኑን ባየር መድኃኒትና ኬሚካል (ምዝ) አምራች ድርጅትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ድርጅት በዓለም በፈዋሽነታቸው ታዋቂ የሆኑ መድኃኒቶችን በማምረት ይታወቃል፡፡ ይህ ድርጅት መጀመሪያ ላይ ያመርታቸው የነበሩትን መድኃኒቶች ያመርት የነበረው ስለ እጽዋትና ጥቅማቸው የሚተነትን ጥንታዊ የግእዝ መጽሐፍ የሰጠውን ዕውቀት በመጠቀም እንደሆነ እራሱ ድርጅቱ መጽሐፉን በድርጅቱ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ላይ በመስታውት ሳጥን ላይ በክብር አስቀምቶ በማስጎብኘት ጭምር የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡
ከምናውቀውና ከማናውቀው ይህች ሀገር ከምትታወቅባቸው ከዚህች ሀገር ወጥቶ ዓለም ከተጠቀመበት የሥልጣኔ ፍሬያችንና ብርቅየ እሴቶቻችን ውስጥ ከእሷ ያልወጣ የእሷ ያልሆነ አንድ ነገር እንኳን መጥቀስ አንችልም፡፡ ይሄንን ያህል ለዓለም ሥልጣኔ የማይተካ ሚና የተጫወተችን ቤተክርስቲያን እንደ ምናምንቴ ቆጥሮ ማዋረድና መዘርጠጥ እንድትናቅም ጥረት ማድረግ ድንቁርና አይደለም ካላቹህ ባንዳነት ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር አይደለም፡፡ ለነገሩ ልዩነት የላቸውም፡፡ ደንቆሮ ሁሉ ባንዳ ነው ባይባልም ባንዳ ሁሉ ግን ደንቆሮ ነው፡፡
ሲጀመር አንድ ሰው አንድን አካል መተቸት ስለተፈለገ ብቻ አይተችም፡፡ ለመተቸት ከመነሣታችን በፊት ማንን እንደምንተች፣ ምን እንደምንተች፣ ለምን እንደምንተች፣ እንዴት እንደምንተች ጠንቅቀን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ አንድ አካል በሁለት መንገድ ይተቻል፡፡ አንደኛው ያ አካል አርአያነት የሌለውና ጎጂ አጥፊ መሆኑን ከማስረዳት ከማረጋገጥና ሕዝብና ሀገርን ከዚህ ጎጂ አካል እንዲጠበቁ እንዲርቁ ለማብቃት ከማሰብ አንጻር ይተቻል፡፡ ይሄንን አካል በዚህ ተግባር ለመፈረጅ ከሠራው ሥራ ያጠፋው ካለማው የሚበልጥ የሚበዛ ወይም ከሞላ ጎደል ሥራው ተግባሩ የጥፋት መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሄኔ ይህ አካል “በውጉዝ ከመ አርዮስ” ቅኝት ይወገዛል ይኮነናል ይጣጣላል ይብጠለጠላል፡፡
ሌላኛው መንገድ ደግሞ ያ አካል ጠቃሚ በጎ የሚበጅ ሥራ የሠራ ሆኖ እያለ መቸም ቢሆን የትም ፍጹም ሆኖ መገኘትና መቶ በመቶ ከእንከን የጸዳ ፍጹም የሆነ ሥራ ሠርቶ መገኘት ከቶውንም አይቻልምና ከዚህ ውስንነት የተነሣ አንዳንድ ጥፋቶች እንከኖች ሲገኙበት እንዲያው “ይህቺ ይህቺ ነገር ባትፈጸም ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር!” ለማለት ለመማሪያ ያህል ትንኝ እንደማጥራት ያለ የመተቸት ተግባር ይሠራል፡፡ ምን እናውራ ከሚል በዚህ የትንኝ ማጥራት ዓይነት ትችት ለመተቸት የሚበቃው አካልም በዚህ ቦታ ወይም መገለጫ ለመፈረጅ ከሠራው ሥራ ያጠፋው ጥቂት መሆንና ያለማው የሚበዛ መሆን ይኖርበታል፡፡
አሁን ታዲያ ይሄ ሰው የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን “በውጉዝ ከመ አርዮስ” ቅኝት እየተቸ፣ እያወገዘ፣ እየተቃወመ፣ እያብጠለጠለ ያለው ቤተክርስቲያኗ ለዚህች ሀገር ሁለንተናዊ ማንነት ካበረከተችው አንጻር ያጠፋችው ካለማችው በዝቶ ይሄ በርካታው ክፉው ሥራዋ ጥቂቱን መልካሙን ሥራ ውጦት ነው ቤተክርስቲያኗን ታጥቆ እያጠቃ ያለው??? ነው ወይስ ማን? እንዴት ባለ መንገድ? ለምን? እንደሚተች እንደሚሔስ ጨርሶ ምንም የሚያውቀው ነገር ስለሌለው ምናልባትም ከአስተዳደጉ ባዳበረው ኢግብረገባዊ ጠባይ በመገፋፋት ነው አፉ እንዳመጣለት ስድና ግብረገብነት በጎደለው መልኩ ሊያዋርዳት ጥረት እያደረገ ያለው?
እርግጥ ነው አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ቤተክርስቲያን ከሐዲስ ኪዳንም ከብሉይ ኪዳንም በፊት ከጥንት ከሕገ ልቡና ጀምራ (በዚያን ጊዜም ቤተክርስቲያን ትባል ነበር ማለቴ አይደለም) ለዚህች ሀገርና ሕዝብ ያደረገችውን ጥረት ድካምና ልፋት አሁን በዚህ ዘመን ላይ ሀገሪቱ ሀብታም (ቁሳዊ በሆነ) ሆና ማየት መገንዘብ እንዳንችልና ውለታዋን እንዳናውቀው ቢያደርገንም መታወቅ ያለበት ነገር ግን ይህች ቤተክርስቲያን ባትኖር ኖሮ እንደጠላቶቻችን ብዛትና እንደሚፈጽሙብን ሸር፣ ሴራ፣ ጥቃት፣ ጥረት ቢሆን ኖሮ ይህች ሀገርና ይሄ ሕዝብ ገና ድሮ ጠፍቶ ዛሬ ላይ ስም አጠራሩ የማይታወቅ ይሆን የነበረ መሆኑ ነው፡፡
ታዲያ ይሄ ልጅ እንዴትና ለምንስ ነው ይህችን የሀገር መሠረት የሆነችን ቤተክርስቲያን ጠምዶ ይዞ እያጠቃ ያለው? ያልን እንደሆነ በሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛውን ከላይ ያነሣሁት ባለጌነቱ ነው፡፡ የቀሩት ሁለቱ ደግሞ ለነገሩ ተያያዥ ስለሆኑ እንደ አንድ መቁጠርም ይቻላል፡፡ አንደኛው ማሰብ ማስተዋል መረዳት የማይችል ደንቆሮ ስለሆነ ሲሆን፡፡ ሌላኛው ደግሞ የዚህች ሀገር ጠላት ሀገራት ቅጥረኛ ባንዳ ስለሆነ ነው፡፡ ሁለቱን እንደ አንድ መቁጠር ይቻላል ያልኩት ባንዳና ቅጥረኛ የሚሆኑት ደናቁርቱ ማሰብ፣ ማስተዋል፣ መገንዘብ፣ መረዳት የማይችሉት እንጅ ብልሆች አስተዋዮች ሀገር ወዳዶች ባለመሆናቸው ነው፡፡
ታስታውሱ እንደሆን ይሄ ሰው ከሦስት ዓመታት በፊት እንግሊዝ ባዘጋጀችው ዓለማቀፋዊ የእስፖርት (የፍን፤ ሲነበብ ን ትጠብቃለች) ዝግጅት ላይ ከዓለም ሀገራት ከተጋበዙት የሥነጽሑፍ ሰዎች አንዱ ሆኖ ተጋብዞ ሔዶ ነበር፡፡ የተጋበዘው ካሉ የሥነ ጽሑፍ ሰዎቻችን የተሻለ ሆኖ ተገኝቶ እንዳልሆነ ሁላቹህም በግልጽ የምትረዱት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ልጁ በወቅቱ ብቅ ብሎ መታየቱ ሌላ ጉዳይ ነው የአጠቃላይ የብቃትና የችሎታ የክንውን ጉዳይ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እናም ስንት ከእሱ የተሻሉና ስንት ያበረከቱ እያሉ ወደ ስር እጃቸውን ሰደው እሱን አወጡትና ጋብዘው ወሰዱት፡፡ ለምን መሰላቹህ? ይሄንን ጉዳይ ገና እጀን ሳወጣ ምን ልል እንደምችል ገምቶ ነው መሰለኝ አቋርጦ ወጥቶ እዛው ባይሰማም ወደ እንግሊዝ ከመሔዱ ከቀናት በፊት እሱ ራሱ በነበረበት አንድ የመጽሐፍ መገምገሚያ መድረክ ላይ አንስቸው ነበር፡፡
በዚያ መድረክ ላይ ብየው የነበረው ነገር ምን መሰላቹህ፡- “በውቀቱ የተጋበዘበት ሰሞን ጋዜጣ ላይ ዐፄ ቴዎድሮስን እያብጠለጠለ እያዋረደ እያበሻቀጠ በተከታታይ ጽፎ ነበር፡፡ እናም አኔ ይሄንን በማስታወስ በውቀቱ የተጋበዘው ባንዳ ስለሆነ በሀገሩ ላይ ክህደት በመፈጸም ዐፄ ቴዎድሮስን በማብጠልጠል የእንግሊዝን ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት ስላደረገ ለዚህ ውለታው ነው የተጋበዘው እንጅ እሱን ለይተው ሊያወጡ የሚችሉበት ምን ጉዳይ አለ?” ብየ ስል ጥግ ላይ የነበሩ ደጋፊዎቹ እየተንጫጩ “ከመወያያ ርእስ ውጭ ነው! ያቁምልን!” በማለታቸውና በመረበሻቸው ስለ እሱ ተጨማሪ ነገር እንዳልናገር አደረጉኝ፡፡
እኔ ግን ከርእስ ውጭ ሆኘ አልነበረም ይሄንን የተናገርኩት፡፡ እየተገመገመ የነበረው “እሳት ወይ አበባ” የሚለው የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን የግጥም ሥራ ነበር፡፡ የመወያያ የጥናት ሐሳብ ያቀረበው ሰው “ቴዎድሮስ” የሚለውን የሎሬቱን ተውኔትም (ቲያትርም) አትቶ ስለነበር እኔም ዕድሉ ተሰጥቶኝ ሐሳቤን በማቀርብበት ጊዜ “የገባው ደራሲ የገባው ባለቅኔ የገባው ከያኔ አስተዋይና ልባም የሥነኪን ሰው እንዲህ የዐፄ ቴዎድሮስን ሰብእናና ማንነት በሚገባ ተረድቶ በድርሰት ሥራዎቹ አቅሙ የፈቀደለትን ያህል በዚህ መልኩ ይገልጸዋል እንደ በውቀቱ ያለ ደንቆሮ ባንዳና ቅጥረኛ ግን ዐፄ ቴዎድሮስን በፍጹም ሊረዳ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ያለ የሌለ እያወራ ዐፄ ቴዎድሮስን የተቻለውን ያህል ለማዋረድ ጥረት ያደረገው…” ስል ያቋረጡኝ፡፡ እናም የሱ ቢጤ የባንዳ ጥርቅም ስለሆኑ እንጅ ከርእስ ወጥቸ እንኳን አልነበረም እዚያ ድረስ እያወራሁ የነበርኩት ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ ነበርና፡፡
እናም ይሄ ሰው ድንቁርናው ለባንዳነት አጋለጠው፡፡ ይሄው እንደምታዩትም የባንዳነት ሥራውን ተያይዞታል ወደፊትም ገና ብዙ ብዙ ያገለግላቸዋል፡፡ ኤምባሲዎች (የመንግሥት እንደራሴ መሥሪያ ቤቶች) የባሕል አታሸዎቻቸውን (ምድብ ሠራተኞቻቸውን) በመጠቀም ሀገራቸው በዚህ ሕዝብ ዕይታ እንዴት ዓይነት ገጽታ እንዳላትና በዚህ ሕዝብ ዘንድ ሀገራቸው የተበላሸ ገጽታ ካላትም የተለያየ መንገድ በመጠቀም ያንን የተበላሸ ገጽታ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ፤ ለእነሱ በጎ አስተሳሰብ ላላቸው የሥነጽሑፍ ሰዎች ድጋፍ በማድረግ ለገጽታ ግንባታና ከዚህም አልፈው የሀገራችንን ጥቅሞች በሚጻረሩ ጉዳዮች ላይ የሀገራቸውን ጥቅሞች ለማስጠበቅ መጠቀሚያ ማድረግ የመሳሰሉትን ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በውቀቱ የተመረጠው ለዚህ የበቃና የተመቸ ጥሩ ባንዳ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡
ባለፈው “በአይሁዶች መርዘኛ ጥርስ የገባች ሀገር ኢትዮጵያ!” በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ ከያኔያኖቻችንን እንዴት አድርገው አሳስተው ከሀገራቸው ጥቅም በተጻራሪ እንዴትና ለምን ዓላማ እንደሚጠቀሙባቸው በዝርዝር ለማስረዳት መሞከሬ ይታወሳል፡፡ ጽሑፉን ጎግል አድርጋቹህ እንድታዩት እየጠቆምኩ የልጁ በዚህ መልኩ መቀረጽ ከዚህ ማንነቱ አኳያ እንደሆነ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ለዚህም ነው ሁሉንም ነገሮች ሲመለከት የሚያይበት መነጽር የጥላቻ ከመሆኑ የተነሣ የሚታየው የሸማው ንጣት ሳይሆን ሸማው ላይ ያለችው ነቁጥ ጥላሽት የሆነው፡፡
በዚህች ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ነገር የለም ካልንና “በውጉዝ ከመ አርዮስ” ቅኝት ልንተቸው የሚገባን ነገር በአብዛኛው ጥፋት የበዛበትን የሠራ አካል መሆን ካለበት በውቀቱ የሚጽፈው ሁሉ 95 ከመቶው ብላሽ ከንቱና ከላይ የገለጽኩት አስተውሎትና ሞያዊ አተያይ ያልተከተለ ነው፡፡ በሌላ ጊዜ “ከአሜን ባሻገር” በሚል ያሳተመውን መጽሐፉን በተመለከተ ትችቴን አቀርባለሁ፡፡ ከላይ ካልኩት አንጻር ሁሉንም ጅልነቱን ልንቀስ ብል፣ ጥልቅ ዕይታ ከማጣቱ የተነሣ የተሳሳተውን ሁሉ ልግለጥ ካልኩ ሌላ መጽሐፍ መጻፍ ሊሆንብኝ ነው፡፡ የቱን ትቸ የቱን እንደማነሣ አላውቅም፡፡
ሌላው ችግሬ ብዙዎቹ ሐሳቦቹ ቆዳቸው ብስል ውስጣቸው ጥሬ ከመሆናቸው የተነሣ እነዚህ የወረዱ አስተሳሰቦች ልተች ስል ለመተቸት የሚበቃ ክብደት የሌላቸው መሆናቸው ነው፡፡ እንዲህ ስል መጽሐፉ ጨርሶ እርባና የሌለው ነው ማለቴ አይደለም ጥቂትም ቢሆን ቁምነገር አይጠፋውም፡፡ ለምሳሌ ያ ነፈዝ ሸአቢያ በልብ ወለድ ድርሰቱ የነዛው የፋሽስት ጣሊያን የአኖሌና የጨለንቆ የጡት መቁረጥ ፈጠራን ፈጠራ መሆኑን ለማረጋገጥ የጻፈው በጣም ጥሩ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ግን እኔ አሩሴ ሔጦሳ ላይ የቆመው የአኖሌ የጥፋት ሀውልት ከመመረቁ አስቀድሜና ከተመረቀም በኋላ በመጽሔቶችና ድረገጾች ላይ አከታትየ ከጻፍኩት የተለየ አልጻፈም እሱኑኑ ነው የቀዳው፡፡
ልዩነት ካለ እኔ በስም ያልጠቀስኳቸውን ባዕዳን ጸሐፍት በስም መጥቀሱ ነው፡፡ እኔ ብየ የነበረው ጉዳዩ ሐሰትና ፈጠራ መሆኑን ካተትኩ በኋላ “…ለኢትዮጵያ ጥላቻ ያላቸውና የራሳቸውን ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ጥቅም ለማስከበር በመጣር በጻፉ ባዕዳን ጸሐፍት እንኳን ይሄ የተባለው ነገር በአንዳቸውም መጽሐፍ ላይ ተጽፎ አልተገኘም፡፡ ካላቸው ዓላማና ጥላቻ የተነሣ ድርጊቱ ቢፈጸም ኖሮ ቢያንስ እነሱ ይጽፉት ነበር” ነው ብየ የነበረው፡፡ ብልጣብልጡ በውቀቱ ይህችን እንዳለች ወሰደና በሰጠሁት መንገድ ሔዶ የእነዚህን ጸሐፍት ስሞችን ከተተና ጻፋት፡፡ ይሄን በማድረጉ ግን አልከፋም ይህ የጥፋት ሐሳብ ሐሰት መሆኑ መናኘቱ ነውና ጥቅሜ ብየ የማስበው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉኝን ሁሉ ልውቀስ ብል መጽሐፍ እያሳተሙ የቦጠቦጡኝን፣ አስፈቅደውም ሳያስፈቅዱም የመመረቂያ ወረቀታቸውን የሠሩትን ሁሉ ዘርዝሬ አልጨርሳቸውምና፡፡ በነገራችን ላይ በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ከጻፍኳቸው ጽሑፎች በመጀመሪያው ጽሑፍ የታቻምናውን የኦሮሞ ተማሪዎች ዐመፅ ቀስቀሷል ብሎ ወያኔ ሁለቴ አስሮኝ ነበር ጉዳዩ እስካሁንም ገና ፍርድ ቤት እያንገላታኝ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለ ሕዝብ ሁሉ አዋቂ አይሆንም ገለባም አለ፣ ድንጋይም አለ፣ እኩይም አለ፣ አረማዊም አለ፣ ምንደኛም አለ፣ ሆዳምም አለ፣ ጭራቅም አለ፣ ቀማኛም አለ፣ አታላይ ጮሌም አለ፣ እራስ ወዳድም አለ፣ አስመሳይም አለ፣ ጭንጋፉም አለ ወዘተረፈ. የሚገርማቹህ የተማረ ነው ከምትሉት ሰው ሁሉ ሳይቀር እነኝህን የሆነ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ገለባውም ድንጋዩም እኩዩም አረማዊውም ምንደኛውም ሆዳሙም ጭራቁም ቀማኛውም አታላይ ጮሌውም እራስ ወዳዱም አስመሳዩም ጭንጋፉም ወዘተረፈውም የዚያን ማኅበረሰብ ሕዝብ የየድርሻቸውን ቢጤ ቢጤያቸውን በመውሰድ አድናቂ የማያጡት የሚያገኙት፡፡ ያለ ጥርጥር የበውቀቱ አድናቂዎች ደጋፊዎች እንደበውቀቱ የሚያስቡ የበውቀቱ አስተሳሰቦች የሚስማሟቸው ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የእነእንትና አድናቂዎችና ደጋፊዎችም እንትኖች ናቸው፡፡
ከዚህ አንጻር በውቀቱ ያገኘውን ያህል ትኩረት ማግኘቱ የሚደንቅ አይሆንም፡፡ በአንድ መንደር ያለ አዋኪ ዋልጌ በድርጊቶቹ የሰፈሩ መነጋገሪያ መሆኑ የማይቀር ነገር ነው፡፡ መልካም የሠሩትን የተለየ አስደናቂ ነገር አድርገው ካልተገኙ በስተቀር የሚያስታውሳቸው የለም፡፡ አዋኪው ዕለት በዕለት መነጋገሪያ ሆነ ማለት በሰፈርተኞቹ ልብ ውስጥ የክብር ቦታ አግኝቷል አለው ማለት አይደለም፡፡ ሰፈርተኞቹ ስለሱ የሚያወሩት ጎሽ የሚሉለትና የሚያበረታቱለትን ምግባር ስላገኙበት በአድናቆት ክብር ሰጥተውት ሳይሆን ትኩረት የሰጡት በእሱ ምክንያት በመታወካቸው፣ ሴት ልጆቻቸው ስለተደፈሩባቸው፣ ወንድ ልጆቻቸው ስለተጠቁባቸው፣ ንብረታቸው ስለተዘረፉባቸው፣ በእሱ ምክንያት ስለታመሱ ሰላም ስላጡ ነው ሳይወዱ በግድ ስለሱ የሚያወሩት፡፡
አደጋው እንግዲህ ይሄ ዱርየ በመላ ሰፈርተኛው ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው በክፉ ሥራዎቹ መሆኑን መገንዘብ ተስኖት መነጋገሪያ መሆኑን እንደ ጀብድ ክብር የቆጠረው እንደሆነ ነው፡፡ እንዲህ ማሰቡ እሱ እስካለ ጊዜ ድረስ ያች ሰፈር ስትታመስ መኖሯ ነው ማለት ነው፡፡ ምንም ያድርግ ምን ለሱ ምኑም አይደለም፡፡ እሱ የሚፈልገው መነጋገሪያ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ በውቀቱ ማለት እንዲህ ነው፡፡ ለዚህም ነው ማንን ምን ብሎ እንዴት መተቸት የማያውቀው ግብረገብ የጎደለው የሆነው፡፡
የገረመኝ ነገር “ምን ብየ ልጻፍና መነጋገሪያ ልሁን?” ብሎ መነሣቱ ነው፡፡ አንድ ጸሐፊ ነኝ የሚል ሰው እንዲህ ብሎ ከተነሣ ፀሐፊ አይደለም፡፡ ብስለትና ጥራት ያለውን ነገር ሊጽፍም አይችልም፡፡ በውቀቱ እንዲህ ብሎ በመነሣቱ በርካታ እጅግ ትዝብት ላይ የሚጥሉት ብላሽና ተራ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማለት ተገዷል፡፡ ሰው እንዴት “ምን ብየ መነጋገሪያ ልሁን?” ብሎ ይጽፋል? በዚህ አጋጣሚ ለበውቀቱ ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት ቢኖር ሳትዘገይ ወደ ጸበሉ ሒድ፡፡ እስክትበስል ድረስ ብታረጅም እንኳን ምንም ነገር አትጻፍ፡፡ ሀገርንና ሕዝብን ይቅርታ ጠይቅና ባንዳነትህን አውለልቀህ ጣል፡፡ ቢቸግርህም ከኅሊና ሰላም ጋር ያለ ድህነት ይሻላልና፡፡
እንዲሁም ለሱ ሽፋን እየሰጡ መነጋገሪያ እንዲሆን በአርዓያነት እንዲወሰድ ዕድል በሰጡት የብዙኃን መገናኛዎችም እጅግ ማዘኔን መግለጥ እወዳለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች የብዙኃን መገናኛ ከባድ ኃላፊነት የተሸከመና እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ተቋም መሆኑን ቢያስቡ መልካም ነው እላለሁ፡፡ የግል ፍላጎታቸውና ስሜታቸው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ኃላፊነት ይዘው ሕዝብን ለማገልገል በተቀመጡበት ወንበር ላይ የግል ስሜትና ፍላጎታቸውን በማስተናገድ እንዲህ ዓይነት ስሕተት እየፈጸሙ በእሴቶቻችን በማንነታችን ላይ እያሴሩ ጠላቶቻችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ከሆነ ግን ይዋል ይደር እንጅ ከሕዝብና ከኅሊና ፍርድ ነጻ እንደማይሆኑ ሊያውቁት ይገባል፡፡ በውቀቱን በአርአያነት በሚያዩት፣ በሚያደንቁትና ደጋፊዎቹ በሆኑትም እጅግ ማፈሬን መግለጥ እወዳለሁ፡፡ በተለይ ተምረናል በሚሉት፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com