ከሥርጉተ ሥላሴ 23.01.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)
በነፃነት ያላደገ ማህበረሰብ ውስጡ ቀለም የለሽ ብዕር ነው ….
መነሻ ሲኖርህ ዛሬን ታውቃለህ። ዛሬን ካወቅህ ነገን ታያለህ። ነገን የማዬት ውስጥህ ሙሉዑ ሰው የመሆንህን ሚስጢር ይገልጽልኃል። በአንተ ውስጥ የሆነ፣ አንተን የሆነ፣ አንተን ያገኘ ረቂቅ ነባቢታዊ ህዋስ ማንነትህ መሆኑኑን ልብ ልትለው ይገባል። ማንነትህ „ማንነት“ ስላለው አንተን እንደራስህ የቀመረህ ቅኔው ነው። የቅኔው ወርቅ ሲገለጥ የነፃነት ትርጓሜ ይበራልኃል። የብርኃኑ ምንጩንና ማሰረቱን በፍላጎትህ መሃልና በአንተ ማሃል ያለውን፤ አንተ የማያታዬውን ግን የሚያበራራልህን ረቂቅ የደም ዋጋ አሳምሮ ያመሳጥርልኃል። ሚስጢሩ አንተን ለባዕድ ስሜት ወይንም ለተለጠፈ ልስን ቅርጽንት ሳይዳርግ ወይንም ከዲቃላነት አድኖ ወጥነትህን በችሎት ያጎናጽፍኃል። ታድለኃልና ለጥ ብለህ ሰግደህ ሁነው!
ወጥነት አንገትን ቀና አድርጎ ከእንሰሳ በላይ ብቻ ሳይሆን ቅኝ ካላሆነ ማንነት በላይ ሰለሆነ መንፈስህ ቅልውጥ ሳይማሳን የበታችነትን ገድሎ የእንደራሴ ውስጥነትን አብቅሎ አሳምሮ ይሸልምኃል። በሙሉ ሰው ሰውነት ቀጥ አድርጎ በማቆም እንደ ስው የማሰብ፤ የመኖር ሰማያዊ እኩል ጸጋህን ታፍስ ዘንድ በአክብሮትና በልግስና ይሰጥኃል። ግን ካልተላለፈክው ወይንም ካልረገጠከው ወይንም ካልጠቀጠከው ብቻ ….። ይህ ማለት አንደ እንሰሳ ከመሸጥና ከመለወጥ ድነህ፤ እንደ እቃ ለአግልግሎት ብቻ ከመመረጥና ከመታዬት ሳትደርስ የሰው ሰው መሆንህን፤ መተርጎም ትችል ዘንድ ይገልጥልኃል። ውስጥን የማንበብ መክሊትህ የሚመተረው ከዚህ ላይ ነው። በአፍንጫህ ዓይን ሳይሆን በህሊና ዓይንህ ማስተዋል ከተሰጠህ አስኳሉ አንተ ነህ።
ተርጓሚ ሲገኝ ነፃነት ቅኔ ነው። ነፃነት ረቂቅ ጥልቅ የተባረከ የመንፈስ ውስጥ ፍላጎት ነው። ዛሬ ነፃነት የሰለጠነ ህዝብ ብቸኛ የግናዛቤ መለኪያ ሆኗል። ነፃነት ሰፊ የሰብዕዊነት ማሳ ሀኖም ይታያል። ነፃነት የነበረ፤ የሚኖር የዕምነት መሰረታዊ ዶግማ ወይንም ልዕለ ቃል ነው። ነፃነት በጥሬው ብቻ ሊተረጎም የማይችል ውስጥን በራስነት የማነፅ ሥልጡን ክስተት ነው።
ነፃነት ዛሬ የዓለማችን ጉልተ – አጀንዳ ነው – አንጎልም። ነፃነት ዛሬ የዓለምን መንፈስ በአንድ ሃዲድ ያገናኘ ቅዱስ አምክንዮ ነው። ነፃነት ህይወት ላላቸው ብቻ ሳይሆን ለግዑዛን ሳይቀር ተቆርቋሪ ጠበቃ ነው። ይህችን ትንሽ ዘርዘር ባደርጋት መልካም ይመስለኛል፤ ከተጠቀለለች እንዳትጠጥር … በመጠኑ
ስለምን? ነፃነት ለግዑዛን አስትንፋስ ሆነ? ምክንያቱም ግዑዛኑም ቢሆኖ በሰው ልጅ ታሪካዊ ሂደቶች ብቁ ታዳሚ ከመሆናቸው በላይ ትናንትን ለዛሬ – ዛሬን – ለነገ፤ ነገን – ለነገ ተወዲያ ያቀባብላሉ፤ ያሰብላሉም። ባለውለታዎቻችን ናቸውና፤ አሁን የዋሻ ዘመናት ታሪክ በድንጋይ ላይ ተቀርጸው ይገኛሉ። ብዙም ይናገራሉ፤ መሬት በከርሷ እፍን ሽክፍ አድርጋ ያያዘቻቸው ቅሬተ – አካላት ትናትን አበክረው ያውጃሉ፤ ከመነሻም ይገነባሉ። ለዝንተ ዓለም ዝክረ ንዑዳን ናቸው። ለዛሬ ሥልጣኔም የምርምር ማዕከል እኮ የትናንት ትንግርት ክንውን ነው። ክንውኑ በምስል በቅርፃ ቅርጽ ወይ በፁሑፍ ሊሆን ይችላል። በባዕድ ተገዝቶ ውስጡ እርሾ አልባ ሆኖ ላልተሟጠጠ ማህበረሰብ ግዑዛኑ ያስቀሩት ታሪክ መስታውት ነው።
… አሁን በድንጋይ ግጭት የእሳት መገኘት በራሱ የሰው ልጅ ብርኃንን በእጁ የመፍጠር አቅሙን ጠቋሚ አድርጎታል። ሳይንሳዊ በሆነ መልኩም ለፊዚክስንና ለኬሚስትሪም መቅኖ ሆኖለታል። የሰው ልጅ ሥልጣኔ እንደ ገና መወለድን /ዬሪናይሰንስንም/ ዓላማ አሳክቷል። የሰው ልጅ የአንኗኗር ዘይቤ፤ አምልኮዊ ሆነ ዕምነታዊ ሂደት ሁሉ በስዕል ሆነ በመጸሐፍት ቅጅ ሳይሆኑ ከነተፍጥሯቸው ከሥረ መሰረታቸው ይገኛሉ። በጦርነት ሆነ በመስፋፋት ከወደሙት የተረፉት። ብቻ እነዚህ ሁሉ በነፃነት ማዕቀፍ ውስጥ ሲካተቱ የነፃነትን ሊቅነትን ቅኔነትን ያናግራሉ። ትውፊት የመሆን ዕድላቸውም የነፃነት ልዩ አቀም ያለው ሥጦታ ነው። አቅማቸው የመናገር ብቻ ሳይሆን የግኝትና የምርምር ማዕከላዊ ዝክረ ነገሮች ናቸው አዲስ የዕውቀት የሥራ መስክም ናቸው።።
የነፃነትን ድርሻ መጠነ ሰፊ ነው። አሁን ዩኒስኮ የተቋቋመበት መሰረታዊ ዓላማ የግዑዛንን መብት ለማስጠበቅ በጥብቅና ለመቆምም ጭምር ነው። እግዚአብሄር ይመስገን እሰከ 2012 ድረስ የእኛ ሰባት የነበረው በ2013 መጨረሻ ላይ ወደ ስምንት አድጓል። ይቀጥላልም። ያው ጠንክረን ከሰራን አደጉ ተመነደጉ የተባሉት ሀገሮች የሌላቸው እኛ ግን ያለን ብዙ የቅርስና የውርስን ጥበቃ በአለም ዓቀፍ ደረጃ የሚያስፈልጋቸው ሃብታት አሉንና … ይህ የማንነት ምንጭ አክባሪ ሲያጣ ግን እጅግ ያማል …. ውስጥንም ይመራል። ለማንኛውም ይህ በራሱ የሚያሳዬን የነፃነት ደንበርየለሽ፤ የአብሮነትን ስክነት – አመክንዮነት ዓለምን በሙሉ ባኃቲ መንፈስ ታዳሚ ማድረጉን ነው። የነፃነት ቤተኝነት ድንበር የለሽ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የተረጋጉ ራሳቸውን ያወቁ፤ ዕውቅናቸውንም ያጸደቁ የነፃነት ውጤቶቸን ጥልቅነትን ያሳያል።
ከሁሉም ነገር በላይ ፍቅር በመተርጎም ሂደት ነፃነት ልዩ ልብ አለው። ነፃነት ሁሉንም በፍቅር አክብሮ የሚያወራርሰው የመንፈሳችን ልዑቅ ምኞት ነው። ምኞቱ እጅግ ተናፋቂ የሚየደርገው ከነፃነት መልስ የሰው ልጅ ደም መፋሰሱን፣ እረዳው … አቃጥለው … አንድድው የሚለውን ጠናና አመለካካትን ገርቶ ምህርትን አውጆ ከናፈቀው ሳላም ጋር የሚተቃቀፍ፤ ተግባራዊ ለማደረግም የሚተጋ ብቁ ሐዋርያ ስለሆነ ነው። ነገ መምጣት ወይንም መገኘት የሚችለው …. ዛሬን ሳናጠፋው ከቀረን፤ ዛሬን በላፒስ ካለሰረዝነው ብቻ ነው። ነፃነት ለትናንት ሰፊ አክብሮትና ምስጋና አለው፤ ለዛሬም ልዩ ዕውቅና ሰጥቶ ትርጉም አለው። ለነገም ዋቢነቱና ቋሚነቱ በሥነ – ጥብብ ነው። ስለዚህ የነፃነት ተፈጥሮ ቅድመ – ማዕክላዊና – ድህረ ሂደት በማስማማት እኩልነትን በገፍ ይሸልማል። መደማመጥን ይሞሽራል። መቻቻልን ያነግሳል። ይህ የነፃነት በኸረ አምክንዮ ህሊና ነው። ነፃነት የህብረት ጥረት ሰብል ነው።
የነፃነት መርህም፣ ህግግታም ጥብቅናም ሁሉንም ለመተግበር የመጀመሪያ ጥያቄ አለው። እሱ እራሱ ነፃ መውጣትን ይሻል። ማለት ተተርጓሚነት፤ ተጠባቂነት፤ ለጋስነት – በፈጻሚነት።
ሀ. ተተርጓሚነት ሲባል ነፃነት ያሰገኛቸው ፋይዳዎች መሪዎች እንዲሆኑ መፍቀድን፤
ለ. ተጠባቂነት ሲባልም ነፃነት ባስገኛቸው ውጤቶች ዙሪያ የማህበረሰቡ ወይንም የህብረ – ሃብት የሆኑ መስዋዕትነቶችና ውጤቶቻቸው ጣባቂ ባለቤቱ ተጠቃሚውና አስገኙ ህዝቡ እንዲሆን መሻትን።
ሐ. ለጋስነት በፈጻሚነት፤ ነፃነት ፈላጊው አካል ነጻነቱን ሲያገኝ ለጋስነቱን የማረጋገጥ ብቃትን። ለነፃነት ነፃነት መስጠት፤
እኔ ሥርጉተ … ከሩቆቹ ጋር ሳይሆን የጥቁር ህዝብ የነፃነት ታሪክ መሰረት ከሆነችው እናት ሀገረችን ኢትዮጵያ ላይ መነሳቱ እኛን አዙረን በማዬት ወደ ልቦናችን ቢመልሰን ሁለመናችን መነሳት ያለበት ከኢትዮጵያዊነት መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። የእኛ ማንነት እኛን ሳይቀይጥ የሰጠን በነፃነታችን በመኖራችን ብቻ ነው። ነፃነታችን ብቃትን በብልህነት ያስዋበ መሪ ነበረው። ተመሪውም ለነፃነቱ ቀናዕይና ዓለምን በተመክሮ ያሰተማረ፤ የእፍሪካን ነፃነት አስተምህሮ ዶክተሪን የቀረጸ ፤ አደራጅቶ፤ ረድቶ፤ በተግባር ያጡትን ነፃነት ያስመለሰ፤ የጥቁር ህዝቦች ቀንዲል ነውና። እኔ የማምነው ለማናቸውም ቀደምት ጉዳይ „በእጅ የያዙት ወርቅ“ ሆኖ እንጂ ከቅርባችን መነሳቱን ነው። ራስን የመተርጎም፤ የማድመጥና የመመርምር ብቁ ሥልጡን መንገድ ብዬ የማምነው እራስን ማዬትን ነው። እናት ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለነፃነት ለራሱ ማገናዘቢያ ሆነ ማውጫ መሆን የምትችል ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር ናትና። ትውስት አይደለም የኢትዮጵያ ሥነ – ተፍጥሮ ያበቀለው። ስለሆነም መነሻዬ ከዚህ እንዲሆን እፈቅዳለሁ ትንሽ ዘርዘር አድርጌ ልሂድበት …..
ሀ. ተተርጓሚነት
በትርጉም ሊቃኑ የማይችሉ ፈላሲ ስሜቶችን ዘልዬ፤ መሬት ላይ ባሉት ባተኩር ይሻላል። ይህ በረቀቀ መልኩ ሊታይ የሚችል ነገር ነውና። በቀላሉ አገላለጽ ለንጽጽር በነፃነት ያደጉና በቅኝ ግዛት ኩርኩም አስተዳደግ ምክንያት በኮድኳዳ ወይንም በጎድጓዳ ዘመን እድገታቸውን ያሳለፉ ብናሰላው ፍቺውን ማግኘት በቀላሉ የሚቻል ይመስለኛል። ሩቅ አትሂዱ ይህን ዘመን በዚህ ልኬታ ፈትሹት ከጓዳችሁ ተነስታችሁ። … ስደት ላይ እኛ አዋቂዎች ኢትዮጵያውያን እና አንድ ኬኒያውያን ስደተኛ እኩል የመንፈስ አቅም ልኬታ አይኖረነም። እንዲያውም አይገናኝም። እኛ ብቁና ንቁ፤ ያልጎበጠ የፃነት ጸጋ የተገለጠልን የኖርነብትም ስለሆነ ቀና ያለ ሰብዕና፤ በራስ የመተማመን ሙሉዑነት አለን። የውስጣዊነት ርትህ ድባበቡ ለእኛ የሚሰጠን ወዛማ ነው። መንፈሳችን ተፈሪነት፤ የማይደፈር፤ መብቱንና ግዴታውን ጠንቅቆ የተገነዘበ የማያጎነብስ ወይንም ለማጣ ያልሆነ ተፈጥሮ ነው ያለን። የእነሱ ደግሞ አድርባይና የተሸበሸበ ከመሆን አልፎ ፍርኃት የከተመበት፤ ያልተቀዬጠ እንደ ራሳቸው የሆነ ነገር ውስጣቸው የራስነት ጥሪት የሌለው — ሰላላና ዝበት የዘፈነበት ዕይታና አቀረረብ ነው ያላቸው። ስለ ራሳቸውም ለመግለጽ ብናኝ ድፈረት እንኳን የላቸውም። ፍላጎታቸው የተቀረቀረ ነው ስልብ ነገር።
…. እራህብን የሚያውቀው የተራበው ብቻ ነው። ራህብን የማያውቀው ሰው ቢጠዬቅ „ራህብ ምንድን ነው ብሎ ይጠይቃችኋል።“ አያውቀውምና፤ በባዕድ ቅኝ ተገዝቶ የነበረ አንድ የአፍሪካ ሀገር ሰውና እኛ ስለ ቅኝ ግዛት አስከፊነት ብንጠዬቅ እሱ ይመልሰዋል። እኛ ግን ፈተናውን እንወድቃለን። ስለምን? አናውቀውም …. አልተገዛነም። የሚያሳዝነው ነገር በባዕድ ባለመገዛታችን ምክንያት የእኛነታችን መግለጫዎች ሁሉ ከእነሙሉ አካላቸው ሳይቀዬጡ እንደ ተፈጥሯቸው አሉን። ፈታተን ብናዬው ስሜታችንም፣ ፍላጎታችንም መነሻው ሆነ መደረሻው ከዛ ላይ ነው። እንጀራን ስታስቡት ሰፍ ብለን እንወደዋለን። ሆዳችን ሞልቶ እንኳን እንጀራ አለ ከተባለ ማዕደኛ እንሆናለን። ተገዘተን ቢሆንስ? ዕውነታውን ሳንርቅ አቅርበን እናወያዬው …. እባካችሁ ናፍቆቶቼ።
የዕምነት ተቋማትን ሥርዐትና ክንውን፤ ቋንቋውን ብትመለከቱት ቀበልኛው ብቻ ዬት እዬለሌ ነው፤ አለባበሱን ብታዩት ቀለማም፤ አመጋገቡን ብታዩት የማይጠገብ፤ የግብይት ሥርዓቱን ብትመለከቱት ወዝ ያለው፤ የማህበራዊ ኑሮ ትውፊቶቻችን ዘርዘር አድርገን ብንመለከታቸው ጠረናቸው የእኛ ብቻ የሆኑ በፍጹም ሁኔታ ያልተዳቀሉ። የአንኗኗር ሥርዓታችን የተደራጀና ያተወቀበት፣ የታቀደና የተዋበ ነው። የትም ቦታ በዬትም ሁኔታ ኢትዮጵውያን እንታወቃለን። ስለፊደል ገበታችን ሌላ ጊዜ ብመለስበትም እሱ በእራሱ ውበታችነን ያነጥረዋል። „የተወሶ ይሄዳል ተመልሶ“ አይደለም። በዛ ዘመን ፊደላችን የመቅረጽ ሥነ -ጥበብ በማስተዋል ስታሰሉት የአባቶቻችን የበራ፤ በቅኝ ያለተወረረ ሥልጡን አዕምሮን ብርኃንነት ይግልጥላችኋል። በነገራችን ላይ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጋዜጣ ሥሙ „አዕምሮ“ ነበር። በ80ዎቹም መግቢያ ይህን ሥም ይዞ የተንቀሳቀሰ የግል መጽሔትና ጋዜጣ ነበር … ትውፊት መጠበቅ የትውልዱ ድርሻ ነውና!
ወደ ቀደመው … ከሁሉ በላይ የትም ቦታ በራስ የመተማመን መንፈሳችን ያልተቀማን በመሆናችን እርግጠኝነት በውስጣችን ስላላ ተሰደን እንኳን የበታችነት ስሜት ፈጽሞ የምይጨፍርብን አንቱዎች ነን። ስለምን? ማንነት ያለው ሙሉዑ ሰብእና ስላለን። ይህን ወርቅ ንጥር ተፈጥሯችን ውስጣችን ለማድረግ ከተሳነን፤ እኛና እኛ ሳንተዋወቅ ተዳብለን ነው የምኖረው ማለት ነው። በርጉማን ይህ የነፃነት ታላቁ ዕሴት ተዘሎ ነፃነቱን ለማስገኘት በተደረጉ ሂደቶች የተፈጠሩ ሳቢያዎች ላይ ብቻ ማተከሩ እራስን በራስ የማጥፋት ያህል ነው – ለእኔ።
የመኖራችን ምክንያታዊ ጭብጥ ኣናቱ ያለው እራሳችን የሰጠን የአባቶቻችን የተጋድሎ ጉልህ ዕንቁ ታሪክ ነበር። የመሪነት ብቃት፤ እንዲሁም የህዝቡ ለቅኝ- ግዛት ምኞት አልነበረከክም ብሎ የከፈለው የደምና የአጥንት ዋጋ ማመሳጠር ለምን እንደገደደን አይገባኝም። እኛ የሚገባን ቂመኞች የሚለጥፉልነን ቅርፊት ማተባችን አድርገን አንገት ደፊነትን በመቀበል አጽድቀን ከመንበራችን በፈቃዳችን መውረድ። ዙፋኑ …. ማማው የእኛ ሆኖ ትቢያ ያሰኘናል። ለምን እንደ ሆን አሁንም አይገባኝም? እነሱ ይባትሉ ትናንት ስላልተሳካላቸው ዛሬም ይማስኑ እኛ ግን መብለጣችን እንዲያስተምራቸው መንፈሳቸውን በድርጊት መቅጣት ይገባናል።
አውሮፓውያኑ አይተኙም፤ ለቀደምቷ የነፃነት ፋና ወጊ ሀገር ለኢትዮጵያ። … አሁንማ ቀንቷቸዋል አስፈጻሚ ባንዳ ሥልጣነ መንበሩን ላይ ሀገር ሻይጩ ወያኔ ስለያዘላቸው። …. ለዚህም ነው በመሰሪ የደህንነት ተቋመቸው ረዳትነት ለሥልጣን ያበቁት …. ትናንትን ለማጥፋት – ለማፍለስ፤ ዛሬን ለመፋቅ ነገን ከመምጣቱ ቀድሞ ለማድረቅ የተሴረው … ይህ እንዴት አይገባንም? እነሱ እኮ እንደ ጥንቸል ሁልጊዜ መሞከሪያ ጣቢያ እኛን ለማደረግ ነው ታጥቀው የተነሱት። የሚበልጥን መንፈስ ማን ይወድ – ማንስ ያደንቅው – ማንስ ዕውቅና ይሰጠው ይመስላችኋል – ወገኖቼ?! የውጭ ፖሊሲያቸው ሁሉ መክኖ እንኩትኩት ብሎ የቀረባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ስለሆነች አሁንም ህዝቧን በማከፋፈል በማጋጨት ለመበተን አይተኙም።
እኮ ስለምን መተላላፍ መጣ ሲባል … ? ነፃነትን መተርጎም ስለቃተን። ነፃነት ለራሱ ከሚፈልገው ነፃነት ላይ እንኳን ለመነሳት አቅማችን የሳሳ – ሰላላ በመሆኑ ምክንያት። አይደለም በቅኝ ግዛት ያለውን ባርነት ዘመን ከእንሳሳ አንሶ መኖር ቀርቶ ተሰደን እንኳን መኖሪያ ፈቃድ አጥተን ስንገላታ የሚደርሰው ሰቆቀቃ ሁሉ ብንፈትሸው ዋናውን አናቱን ነገር የነፃነትን ብሌን ማግኘት ይቻላል። አፈር ያለው ህዝብ ክብር ድንቅ እኮ ነው። በነገራችን ላይ ነፃነት ያላቸው ዜጎች ስደት አይጠይቁም። የሁለተኛ ደራጃ ዝቅተኛ ኑሮ አይናፍቃቸውምና። ለዚህ ነበር በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ከተማሩ፤ ውጭ ሀገር ዕውቀት ከቀሰሙ በኋላ ሙሑራን ወደ ሀገራቸው በደስታ የሚመለሱት። መሰደድ ውርዴት ነበር በዛ ዘመን። የዚህ ዋጋው የሚላካው በመንፈስ ስሌት ነው። ነፃነት ትክክለኛ መኖር ነው። መኖሩ ጣዕሙ በራሱ ይዘትና ቅርጽ የሚዋቀረው በነፃነት ብቻ ነው። የዛሬን የዘመነ ዬወያኔን ተውት … አድርጉት። በዬደቂቃው ወያኔ አሜኬላ ችግኝ ያፈላል፤ ተንከባክቦ ያጸድቃል ተዋጊ አድርጎ የፋልማል …. የተፋለሰ አረም …. ለማንኛውም ነፃነት አብዝቶ ሁሉም የተሰጠው ግን ተርጓሚ አጥብቆ የሚሻ ቅኔ ነው።
ለ. ተጠበቂነት
የነፃነት ግኝቱ ከሰማይ በታች በሰዎች መስዋዕትነት የቀለመ ነው። ይህ ቀለማም ጥሪት ቅርስና ውርስ ደግሞ የእኛ ሁለንትናዊ ሀብት እንጂ የአንድ ጎሳ ወይንም የአንድ ኢሊት አይደለም። ሃብትነቱ ውድ ህይወት ተከፍሎለት ስለሆነ የተከበረ ስጦታ ነው። የአደዋ – የማይጨው – የመቅደላ – የመተማ የዶጋሌ – የአንባለጌ ሚስጢር። ይህን ታላቅ ስጦታ ጠብቆ ለልጅ ልጅ ለማቆዬት ብቁና የሰለጠነ፤ የብሄራዊ ስሜት የሚያንገበግበው፤ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ግዴታ ነው። ምክንያቱም ሃብትነቱ የህዝብ ነውና። ይህንን ሃብትነት የመጠበቅ የማሰጠበቅ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነበር …. ዛሬ በሃገራችን ሳንክ ቢገጥመውም የነፃነት ጥበቃ በኽረና በትረ አብይ ጉዳይ። ነገ ግን ኃላፊነት ያለው ሥርዓት ሲዘረጋ መዘከሩ አይቀሬ ነው ….. እርግጥ አሁንም ከእኛ አልፎ እነ ተፈሪውያን፤ የተከበሩ ቤተሰበ – ኔልሰን ማንዴላ …. መላ አፍሪካውያን የሚዘምሩለት የመንፈሳቸው ጣዕማዊ ዜማ ነው።
የፓን አፍሪካ ቀደምቶች፤ የአፍሪካ ድርጅት ያሁን ህብረት ይሁኑ የዛሬዎቹ አቀንቃኞች ሁሉ በክብር ያከበሩት በመንፈሳቸው አጉልተው የጻፉት ታላቅ መጽሐፋቸው ነው ኢትዮጵያዊነት። በመላ ዓለም ትውልድ ቢለዋዋጠም ዋጋው ሳይቀንስ እንዲዘልቅ የሚተጉ ቀለሞቻችን አሉ። ህያውም ናቸው። ተመስገን! ነፃነትን የተማሩበት ተቋማቸው – እነሱን እንደ ራሳቸው ወደ ራሳቸው የመለሳቸው፤ እነሱነታቸውን ከብክቦ የሰጣቸው ቅዱስ አንደበተ – ተግባር፤ ሁልአቀፍ ሚስጢር ነው ኢትዮጵያዊነት፤ ስለሆነም የጥቁር ህዝብ የነፃነት ታሪክ ጥበቃ ከእኛም አልፎ የተደራጀ ተግባር ከፈጸምን አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የነፃነት ዓላማ አራማጆች ሰብዕዊ ድርጅቶች ሁሉ የሚጋሩት ይሆናል። ይህን መፋቅ ከቶውንም አይቻልም። ማሸለበም አይቻልም – ፈጽሞ።
አብሶ የነፃነት አቀንቃኝ ሁሉ ፍሰቱ የነፃነት ፍላጎትና ተፈጥሮ ተጋፍቶ ወይንም ገፍትሮ መሆን አይገባውም። ውስጥን አስቀድሞ መርምሮ መፈወስ ያስፈልጋል …. ወደ ኋላ ተኑሮ አይታወቅም – በፍጹም። ለዘመኑ የተመቹ ገጠመኞች ሁሉ ውስጥ ሊያበቅላቸው የሚገቡ ጭብጦች መሰረት ብቁ ድልዳል አላቸው። በስተቀር የነፃነትን ሥነ – ተፈጥሮ ጋር ተጣልተናል። ትናንት ያለተሳካላቸው ኃያላን በመቁንን በሚሰጡን ልጣፊ ሳንሸበብ ምኞታቸውን በማምከን እኔ የታሪኬ ባለቤት፤ ታሪኬም የእኔነት መግለጫ በማለት በሙሉ ልብነት ቅስማቸውን ሰብሮ ሴራቸውን አንኩቶ ማደረግ ይጠይቃል። ወደ ራስ መመለስ የወቅቱ ዓራት ኣይናማው መንገዳችን ሊሆንም ይገባል። ነገንም የማይሸጥ የማይለወጥ መሆን አለበት። ለጨረታና ለድርድር የማያቀርብ ትሩፋታችን መጠበቅ ግዴታችንም ነው። መጠሪያችን እራሱ እኮ አዲስ ነው ለዓለም ቅጂ አይደለማ። ለዚህ ነው ለመጥራት ሆነ ለመጻፍ የሚቸገሩት ነጮች። ያልተለመደ — የሚያሰከብር። ትርጉሙን እራሱ ይጠይቃሉ። አያውቁትማ! ማንነት መተርጎም ከተሰጠን … ጆሴፍ፤ ካሎሪን፤ ክርስቲና፤ ወልፍ፤ ስሚዝ፤ አንባልም እኛ … አበበ ፈለቀ ጃርሶ ኬሮድ አምርቲ ሃይሌ ዘለቀ …. ፋና ታዬ ሲራጅ ወዘተ
ሐ. ለጋስነት- በፈጻሚነት።
ነፃነት ከቤት ጀምሮ ተወዳጅ ጉዳይ ነው። ነፃነት ለዕድገት፤ ለሥልጣኔ ለፈጠራ ለሁሉም መንገድ ጠራጊ ነው። የነፃነት ፈላጊው ብዛት ህልቆ መሳፍርት ነው። ነፃነት የማደረግ የመንፈስ መብት ፈቃድ ሰጪ ድርጊት ገዢ ሳይኖርበት ማለት ነው። የመንፈስ ውጤት ተጠቃሚነትና ዲተናት ማለት ነው። ዲታነት በለጋሥነት ከሆነ ውስጥን ፏ አድርጎ ያበራል።
ነፃነት ፈፃሚነት ብቃትን ይጠይቃል። ብልህነትን ይፈልጋል። ማስተዋልን ይሻል። በስተቀር ምድረበዳ የበቀለ ለምልም ይሆንና ዕድሜ ሳይኖረው ጠውልጎ ይሞታል።
ነፃነት በፍላጎት መኖር ማለት ሲሆን፤ ፍላጎትን ፈልጎ ማወቅ የሚቻለው ግን ሥልጡን መንፈስና ተለዋዋጭ ያልሆነ ቋሚ እወቀት ሲኖር ብቻ ነው። አዋቂነት ከተፈጥሮ የተሰጠ ጸጋ ነው። የግድ ፊደል መቁጠር አያስፈልግም። የቀደመችው ኢትዮጵያ የነፃነትን ትርጉም ያወቀቸው እናት ሀገር ከመፈጠሯ በፊት ነበር የነፃነት ፊደልን ቆጥራ የተወለደቸው። ዘመናዊ ትምህርትም ሳይኖር። ይህ ጸጋዋ ነው። ልጇቿን ያሳደገቸውም በዚህ ወተት ነው። ከእቅፋ ወጥተው ሲሄዱ ብቻ ወተቱ ፈሶ መርዝ ይታከበታል። መርዝ አብቃዮች የተፈጠሩበት ዶክትሪን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነውና። ስለምን ኃያልነቷ ያስፈራቸዋል። ያርበደብዳቸዋል። በእፍሪካ ቀንድ አካባቢ የነበራትን የባላቤትነት መብት ተጋፍተዋት እንኳን ባድመ ላይ በዕውናቸው ታላቁ ሚስጢር ተርጎሞላቸዋል ማንነቷን። ሳውዲ አረብያ ላይ ሀገሬው ያልሞከረውን ነፃነት በድፈርት ወጥተው ውስጣቸውን የገለጹት የሚስጢር ልጆች ብቻ ናቸው። መዳፈር ሲመጣም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው በዬትኛውም ዓለም የሚኖሩ ልጆቿ አሳይተዋል። ከውስጥ የሚንቀለቀል፤ ሊያዳፍኑት የማይችሉት የሚንቀለቀል ባለላንቃ የተፈሪነት በረከት ነው ኢትዮጵያዊነት። ስለሆነም ቀደምት ጠላቶቻችን በቀዳዳው ሁሉ ተግተው የጥፋት ተግባራቸውን መከወናቸው አይቀርም።
ስለዚህም ልጆቿ ልብ ሊሉት የሚገባው ፍሬ ዘር እራሳቸውን በለጋስነት ለነጻነታችው ትርጉም ከመስጠቱ ላይ ሊሆን ይገባል። የእኔ የነፃነት ዓርማ! የእኔ እናት! የእኔ መኩሪያ! እኔ እያለሁ ማንም አይነካሽም! እኔ ያንቺ አንቺም የእኔ፤ አንቺ የተገኘሽው በ እኔ ውስጥ እኔም የተገኘሁት በአንቺ ውስጥ። ከአንቺ የሚለዬኝ ማንም የለም። በማለት ሴራዎችን ሁሉ ብን ማደረግ ከቻሉ የነፃነት ወተት ፈውስና ድህነት ሆኖ ሙሉዑ ብቁ ባለቤት ያደርጋቸዋል። ከዚህ ከተላላፉፍን ግን የበታችነት ስሜት ይዳንስብናል። ማህከነ! ዛሬ የምንታገልለት ነፃነት ትርጉም የሚኖረው ትናንት ያገኘነውን ነፃነት በብቃት የመተርጎም አቅምና ችሎታ ከኖረን ብቻ ነው። ሥልጡንነት ማለትም ነፃነትን መተርጎም መቻል፤ በራስ ውስጥ ፈቅደን ተፋጻሚ ለማድረግ መቁረጥና መወሰን ነው ፋይዳው ሆነ እሴቱ።
ይቋጭ መሰል …
ትናንት — የሀገሪዊነትን ባላቤትነት የፈጠረ ማንነት፤ ባዕድነትን ገፍትሮ ድልን በደሙ ያቀለመ ማንነት፤ የመንፈስ ሆነ የአካል ወረራ በትውልዱ – በዘሩ – በሐረጉ – በማንነቱ ላይ ያልነበረ ኩሩ ዜጋ ዛሬ ላይ ሆኖ እንዴት ባዕዳዊ ወራራን ለማስተናገድ ይፈቅዳል? ከፈቀደ ግን – የተጣበቀ ገጠመኝ። የተቀረቀረ ዕሳቤ። አድነን በሉ!
ወዶቼ! ሳላውቀው መጪ አልኩኝ – ብዙ። ውስጤን ፈትሾ ልዩ ሐሤት በሚሰጠኝ እርእሰ ጉዳይ ላይ ስዘናከት እናንተንም በመንፈሴ ሰንቄ ነበር። ብርታቴና ጥጌ ናችሁና። ለነበረን የመደማመጥ ብቁ ቆይታ ፍቅሬን በልግስና ሰጥቻችሁ ልሰነበታችሁ። ደህና ሁኑልኝ – የእኔዎቹ!
ነፃነት ማለት ኢትዮጵያዊነት ማለት ነው።
የነፃነት ቀደምት መምህርት ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ!
የመስዋዕትነት ዕንቁዊ የትውልድ ሽልማት ነፃነት ነው።
እግዚአብሄር ለአፈራችን መሬት ያብቃን! አሜን!
ነፃነት ተግባራዊ በማደረግ እረግድ በአደጉ ሀገሮች አንፃራዊ በሆነ ወይንም ልቅ በሆነ ወይንም መጠራቅቅ ባላው ሁኔታ የተረጎሙት ሀገሮች አሉ። ይህ ወደ እኛ ስንመጣ እንደ ቀደምት መምህርነታችን ለነፃነት የቆመ አካል፤ ድርጅት ተቋም ነፃነት መስጠትን ወይንም ማግኘትን ራህብተኛ የመሆኑን ያህል በነፃነት ዙሪያ ያሉ ነፃነት የሚለግሳቸው አምክንዮችን በመተርጎም እረገድ ገና አልጀመርነውም። ፊደልም ያልቆጠርነበት ጉዳይ ይመስለኛል።
ዛሬ ማታ ነፃነታችን በእጃችን ቢገባ በአግባቡ አስተዳድረን የሚመቸንና የማይመቸንን ፍላጎቶች አስማምተን የነፃነትን ሥነ – ምግባር ካለ መጠራቅቅ እንፈጽማለን ወይ? ዝግጁ ነን ወይ? ስንዱ ነን ወይ? የዕውነት አይደለነም። ሃቁ ይህ ነው። ከእኛ ፍላጎት ትንሽ ፈቀቅ ያለ ነገር ቀርቶ ተመሳሳዩን ሃሳብ የሚደግፍ ግን የተሻለ ሃሳብን፤ የዳበረ ዕይታን፤ የተደራጀን ፈጠራን፤ የበለጠን አመለካከትን፤ የቀደመን መንፈስን ለማስናገድ እንኳን የፍርፋሪ ትዕግስት የለም። አልፍ ሲልም ጦርነት ይተወጅበታል። በዛው በእኔ ፍላጎት ዙሪያ እያለ ጦር ይመዘዝበታል። ስለዚህ አንዱ ለሌላው በ እጁ ያለውን ነፃነት ለመስጠት ገንፉግ ነው።
ይህ የሃሳብ ልዩነት መዋዋጥ መደማመጣ በጓዳ ይቀመጥና፤ በመስመራችን ላለውን እንኳን ከእኛ መንፈስ ወይንም ብቃት በታች መሆኑ ካልተረጋጋጠ ያዳልጠናል …. ስለዚህ በጠራ ቋምቋ ነፃነት በእጃችን ቢገባ ለሌላው ለመስጠት የወጣልን የንፉግነት ተዋናዮች ወይን አጋፋሪዎች ነን። ይህ ሲሰላ ሲመነዘር ስለ ነፃነት ብለን ከፈልን የምንለው መስዋዕትነት የውርንጫ ድካም ሆኖ ቁጭ ይላል። ተቆርቋሪነቱም ባዶ ቀረርቶ ብቻ ….
ንፉጎች። ዛሬ ነፃነት ከራበኝ ባገኘው እኔ እራሴ ሐዋርያ ሆኜ እራሴን ውስጤን መንፈሴ ለድምጽ ብልጫው ካላስገዛሁ ከንቱ ነው። ትግሉ በሉት፣ ልፋቱ በሉት፣ መስዋዕትነቱ በሉት፤ እኔ እጅግ ቁርጥምጥም የሚያደርገኝ ምን እንደሆን ታውቃላችሁ? ነፃነት ታጋይ ከመባላችን በፊት አመኑ በፈቀደው መጠን ስለ ነፃነት ተፈጥሮ ሆነ ሥነ – ምግባር የምናውቀው ምንም ነገር የሌላ መሆኑን ነው። ከዚህ ጋር ትናንት ነፃነታችን ያላስነጠቁትን ጀግኖችንም ከሳሾች መሆናችን።
ዚህ ባለፈ የመንፈሴ ሰሌዳ የማገድናቸው … ለበለኃሰብ አሳልፈን የሰጠናቸው ነፃነት፤ እኩልነት፤ የመጻፍ የመሰብሰብ የመደራጀት የመናገር ነፃነት እያዩሉ በዬዘመኑ በባሩድ የነደዱት፤ ዛሬም ሚሰውት፤ እስር ላይ የሚማቅቁት ወገኖቼን አብዛኞቹ ደግሞ መኖርን ያልጀመሩት ወጣቶች ናቸው እዬተጠፉ ያለቁት ወይንም በፋሽስት በቀል የሚሰለቁት። ይህን ሳስብ ውስጤ ይርመጠመጣል። ፈፃሚነታችን በ እጃችን ሲገባ ስለምነዘለው። ካለ ዘመኑ ካለ ብቃታችን የተፈጠሩ የበለለጡ ጀግኖች የሚከፍሉትን መስዋዕትንት ማድመጥ አለመቻለችን …. ሰቀቀን ነው። እሳት ነው ረመጥ። በተመሳሳይ ፍለጎትና ዓላማ ዙሪያ በተለያየ ሥም ስሜታችነን ከዘንነ የ እኔ ካልሆነ የ አስሱ ይገረብጠኛል … የምሽጉ ፍልሚያ ይህ ነው …. በቃ … ስለምን? ….
አንድ ለነፃነት የሚታገል ድርጅት፤ ግለሰብ፤ ቡድን ለሌላው ነፃነት ተቆርቋሪ መሆን አለበት። ለምሳሌ ሥነ – ጥበብን ልውሰድ። ሥነ ጥብብ ስለፈለግነው ብቻ ተስጥዖው ሊገኝ አይችልም። የሰማይ ሥጦታ ነው። ትግባባኢን ውዶቼ …. ለዚህ የሰማይ ሥጦታ እንኳን የምንፈጥረው ማጠበቂያ፤ የሚጣለው ተዕቅቦ በጣም ድልዝ የሆነ የነፃነት ፈላጊነታችን በእጅጉ የሚያሳርረው የተጋጠ ገጠመኝ ነው። ትናንት ልንሳሳት እንችላላን። ዛሬ ግን አለፍንበትን ገምግምን ሁሉንም በ አውንታዊና በቅንነት መተርጎም ይጋባል። ውስት ፈቅዶ ማረም ይገባል። ዕድሜም ቁጥር መማርም ቁትር መሆኑ እራሳችን አብሶም ህሊናችን እረፍት የማይሰጠን የትውለድ ዕዳ ተሸከምንን ሳናካፍል ማለፍ አለመፈጠር ይሻላል። የቀደምቱ ነብይ ጸሐፊ „የአልወለድም“ ሚስጢር ተዚህ ላይ ተገኘ። የነፃነት ታጋይ ነፃነትን ለመስጠት ስስታም ሳኢሆን ውስጡ በፈፃሚነት መዳሰስ አለበት … በስተቀር ውሃ ወቀጣ ነው …..
አንድ ሰው ሲጽፍ፤ ሲተውን፤ ሲዘፍን፤ ሲስል ሌላ ዓለም ውስጥ ሆኖ ነው። ለነገሩ በዚህ ልዩ ዓለም ለመኖር ላልታደሉት ምንም ሊመስል ይችላል ይሆናል። በሥነ ጥበብ ዓለም ሲኖር ጨለማ ውስጥ ሆናችሁ ብርኃን ይታያችኋል፡ ደማናማ ቀኖች የጸደይ አባባዎች ሆነው ፈክተው ይታያችኋል። ረግረግ ላይ ሆናችሁ መሰላሉን ያቀበላችኋል፤ እጅግ ጉድጓድ ወስጥ ሆናችሁ ካለ መሰናክል የምትወጡበት ደረጃ የሰራላችሁ። ወንዝ ሞልቶባችሁ መሻገሪያ ድልድይ ወይ ታንኳ ያቀርብላችኋል። በጣም ውስብስብ ያለ ፈተና እያሳሁ ወይ እንደ ጠፍር* መየመፍትሄ ጭላንጭል እነደሌለው እአያችሁት ግን ብቃትን – ጥንካሬን – ጽናትን – ተስፋን ያቀብላችኋል። ሥነ – ጥብብ አዲስ ፕላኔት ነው። በተለይ በተኛው በውስጡ ሆኖ ሲዋንበት። ታዳሚው ሲታከልበት ደግሞ ዳግሚያ ትንሳዓ ነው። መከራው፤ ፈተናው፤ ሳንኩ ሁሉ የጥቡ ዕድገት ወተቶች ናቸው። ስተወጡት ማደጋችሁን ታዩበታለችሁ። ይህንን የሰማይ መክሊት እንኳን እንገድባለን በማለት የነፃነትን ጅረት ለመገደብ ማሰብ ቀንና ሌሊትን የማቆምአህል ስለመሆኑ ማስተዋል የከሰለበት እርምጃ ኢሰዳል። ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ „ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ ኢላል“ በዬትኛውም ዕምነት ወይንም ሃይማኖት ህግ ላይ ድርድር የለም ታዲያ የሰማይ ሥጦታን መዳፈር መተላላፍ አይሆንም …. የነፃነት ፈላጊነታችን ትርጉምስ የት ላይ ይረፍ?
መከወኛ?
አሁን ትግሉ ነፃነት ወይንስ ባርነት? ነፃነት ከሆነ አንተለላፈው። ነፃነት ተወዳጅ ሥነ ተፈትሮ አላው ግብታዊ ስሜቶቻችን ሁሉ መለስ ብለን ፈታታሸን …. ፍላጎታችን ነፃነት ስለመሆኑ ተግባር ላይ እንገኝ። ቅልሞሹ ገበጣ ጨዋታው እነድርቺ እንድርቺው ልልጆቻችን የልጅነት ህይወት እንዳይሾልክባቸው በዘመናቸው ይዝናኑበት በዚህ ውስጥም ኢለፉ። እኛ ግን እንደ ዕድሜያችን፤ እንደ ትምህርት ደረጃችን፤ እንደ ተመክሮችን ለመሆን ውስታችን እናሸንፈው፤ ግብታዊ ስሜቶቻኢነን እንግራቸው፤ ቅኑ እንሁን ….. አባቶቻችን አላፉበትን ቅኝ ተገዢነት ናፋቂ አንሁን። ኢልቅ ባለ አደራ ነንና ፍቅርን በፍቅር አባዝተን ከብረን እናስከብረው። ሁሉ ያላት ታላቅ ሀገር አለችናና እሷን ከፍ አድርገን ለማቆዬት ተግተን ለነፃነታችን እነሥራ።
እጅግ የማከብራችሁ የጹሑፌ ታዳሚዎች ስለፈቀዳችሁልኝ መልካም ጊዜ አትዮጵያዊ አክበሩት በ ያላችሁበት አንሆ ላኩኝ።
አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሄር የሰጠንን መስተዋል እንተረጎምው ዘንድ ወደ ልቦናችን ኢመልሰን። አሜን
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
እሜቴ ነፃነት እንድምን ይዞሻል?
እንዴትስ ከርመሻል?
ከእመናው ሸክማ ሸክምሽ ዘንድሮስ ከብዶሻል
እልፈት የለው ኑሮሽ እንዲህ ይፈትልሻል።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10703/
https://www.zehabesha.com/amharic/archives/11816