አቶ ክንፈ ሓደራ በትግራይ ክለተ ዓዉሎ አዉራጃ ጉድ ወረዳ ከአባቱ ፊታዉራሪ ሓደራ ገብረእግዚአብሔርና ከእናቱ ወይዘሮ ብልሃቱ ተላ በታኅሣስ 13 ቀን 1945 ዓ.ም ተወለደ። የ1ኛ ደረጃ ትምሕርቱን በዉቅሮ ከተማ ከተከታተለ በኋላ ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምሕርቱን መቐለ በዓጼ ዮሐንስ ት/ቤት አጠናቋል።
አቶ ክንፈ ሓደራ በስደት ወደ ሱዳን ሔዶ ረጅም ጊዜ በትግል ካሳለፈ በኋላ ወደካናዳ በመምጣት፣ ከባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ጋር በኦታዋ ከተማ ሲኖር በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ሕይወቱ አልፎ አስከሬኑ በተወለደባት፣በሚወዳትና በታገለላት አገሩ ኢትዮጵያ ዉስጥ አርፏል። በኦታዋ የኢቲዮ ካናዳዉያን የዴሞክራሲ መድረክም፣ በትጋቱ፣ በመልካም ሥነ ምግባሩና በረጅም ጊዜ ታጋይነቱ፣ በተለይም በኢትዮጵያ አንድነትና በሕዝቦቿ እኩልነት ላይ በጽኑ እምነቱ የሚታወቀዉን አቶ ክንፈ ሓደራን፣ በኦታዋ ከተማ፣ በኖቬምበር 13 ቀን 2013 ዓ.ም አስቦትና አክብሮት ዉሏል። በዚህ በብሮንሰን ማዕከል ውስጥ በተደረገው ታላቅ ዝግጅት ላይ፣ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች፣ ጓደኞቹ እንዲሁም የመድረኩ አባላትና ቤተሰቦቻቸዉ ተገኝተዋል። በዝግጅቱ ላይም፣ የመድረኩ ተወካዮች ለአቶ ክንፈ ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት ገልጸዋል።በተጨማሪም፣ ዶክተር አረጋዊ በርሄና አቶ መኰንን ዘለለዉ በእስካይፕ ቀርበው ስለአቶ ክንፈ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከዚያም፣ መድረኩ ለዚያ ቅንና እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጅ ክብር ለቤተሰቡ ያዘጋጀውን ስጦታ ለተወካዩ አበርክቷል።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ፣ የአቶ ክንፈ ሓደራ አጭር የትግል ታሪክ ቀርቧል።
የታጋይ ክንፈ አርአያነት
ሞት ለሁሉም ፍጡር የሚዳረስ የተፈጥሮ ሕግጋት ቢሆንም የታጋይ ወንድማችን ኣቶ ክንፈ ሓደራን በድንገተኛ ሞት ምክንያት ከኛ መለየቱ ስንዘክር ጥልቅ ሓዘን ይሰማናል። ይሁን እንጂ አቶ ክንፈ ትቶልን የሄደው ትልቅ የትግል አሻራና በሳል ሰብአዊ ስነ‐ምግባር አሁንም ወደፊትም ከኛ ጋር ስለሚኖር ሞቱ የአካል እንጂ የመንፈስ ሊሆን አይችልም። ኣቶ ክንፈ ሓደራ ገና ከወጣት ዕድሜው ጀምሮ ከተበደለ ህዝብ ጎን በመቆም ለፍትህ፤ ለእኩልነትና ለዘላቂ ሰላም መታገል ዓላማዬ ብሎ የሚኖር ሰው ነበረ። ይህ ዓላማው ነበር ወደ ምድረ ሱዳን ኮብልሎ ትግሉን እንዲገፋበት ያስገደደው። እየታገለም ኖረ፣እየታገለም ዘለቀ። ጠልቀን ካየነው፣ እንደ ታጋይ ክንፈ ለክቡር ዓላማ የሚኖር ሰው ካለ በጣም ጥቂትና የታደለም ነው።
ህወሓት ተመስርቶ የትጥቅ ትግል እንደጀመረ ‐ ከ38 ዓመታት በፊት መሆኑ ነው ‐ ኣቶ ክንፈ ሱዳን አገር በስደት ላይ እያለ ለስደት ያበቃውን ጭቆና ለመታገል ሲል ህወሓትን ተቀላቀለ። በዚያው ጊዜ ህወሓት ገና ትግል ጀማሪ ሆኖ በሱዳን መንግስት እውቅና ያላገኘበትና ተደብቆ የሚታገልበት ወቅት በመኖሩ ኣቶ ክንፈም በህቡእ ትግሉ ተሰማርቶ ድርጅቱ የጠየቀውን ከባድ ሃላፊነት፤ በተለይ ደግሞ ስደተኛው ህዝብን የማደራጀት ውስብስብ ስራ ለማከናወን ተሰማርተዋል፣ ስራውንም በሚገባ ተወጥቶታል።
በዛን ወቅት ትግሉ የሚጠይቀው መስዋእትነት እየከፈለ በነበረበት ጊዜ፣ በኣመራር ደረጃ የነበሩ የድርጅቱ ወኪሎች በምግባረ‐ብልሹነት ይዘፈቁ ስለ ነበር፤ ይህንን በመቃወምና መፍትሄ ለመሻት ባደረገው ጥረት ለፍትህ የቆመው ኣቶ ክንፈ ነጋ ጠባ ከኣመራር ኣባላቱ ጋር መጋጨቱ ኣልቀረም። ግጭቱ ግን መለስተኛ ቅራኔ ነው ከሚል አመልካከቱ የተነሳ በድርጅቱ ውስጥ ሆኖ ሊፈታው ያላሰለሰ በሳል ትግል አድርገዋል። ይህ በዚህ እንዳለ ህወሓት የመገንጠልን ዓላማ የሚያቀነቅነው ማኒፌስቶ‐68 ኣንግቦ ድንገት ብቅ በማለቱ በኢትዮጵያ ኣንድነት ልባዊ እምነት ያለው ኣቶ ክንፈ ከህወሓት ጋር የነበረው ግንኙነት ከተራ ቅራኔነት አልፎ ጭራሽኑ እንዲያቃርጠው ተገደደ።
ትግሉም በሌላ መልክ መቀጠል አስፈላጊ ሆነበት።
በተመሳሳይ እምነት ህወሓትን ተቃውመው ከወጡት ከነ ዶክተር ሃይለ ኣፅብሃ ጋር በመሆን ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ (ዴምህት) የተባለውን ንቅናቄ በመመስረት በኢትዮጵያ እኩልነታዊ ኣንድነት እውን ለማድረግ ትግሉን ቀጠለ። ሁሉጊዜ “ትግራይ ኢትዮጵያ ካልሆነ ሌላ ማን ሊሆን ነው” በማለት ህወሓት በወቅቱ ያራገበውን የመገንጠል ኣባዜ በልበ‐ሙሉነት ፊት ለፊት መቃወም ጀመረ።
ቆየት ብሎም ህወሓት ከውስጥም ከውጭም በደረሰበት ተቃውሞ የመገንጠል ማኒፌስቶውን ውድቅ ኣድርጌዋለሁ ቢልም ኣቶ ክንፈ ኣላመነውም፤ አልተቀበለውም። የህወሓት አስመሳይ ለውጥ ኣለማመኑና አለመቀበሉ፣ ያድርጅት አሁን ድረስ ከሚያራግበው ከፋፋይ አባዜ ጋር አያይዘን ስናገናዝበው የኣቶ ክንፈ ኣርቆ ተመልካችነቱና የዓላማው ጥልቀትነቱ የሚያንፀባርቅ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ በሳል ኣቁዋሙ በህወሓት ኣመራር ስላልተወደደለት፤ ይባስ ብሎም እንደጠላት ተቆጥሮ በሱዳን ሃገር እያል ብዙ ወከባና እንግልት ደርሶበታል።
ታጋይ ኣቶ ክንፈ የመገንጠል ጀብደኞችን ብቻ ሳይሆን የተቃወመው፣ ኢትዮጵያ ሃገራችንን ለኣያሌ ቀውሰ የዳረጋት ጭፍንና የተወላገደ ኣንድነት አራማጆችንም በመቃወም ከብዙ የኣድህሮት ሃይሎቸ ጋርም ተላትመዋል። በሳልና ፍትሃዊ ዓላማው ከተለያዩ ተቃዋሚ ግንባሮች ዓላማ ጋር ቢያጋፍጠውም፣ ኣቶ ክንፈ ከኢትዮጵያዊ መስመሩ ስንዝርም ይሁን ፍንክች ሳይል በፅናት መታገል የቻለ ትልቅ ኣርኣያ ነው።
ከብዙ ኣቅጣጫም ግፊት የነበረበት ታጋይ ኣቶ ክንፈ፣ ቀደም ብሎ እንደማንኛው ከሱዳን የተሰደደው ኢትዮጵያዊ ራቅ ወዳለ የስደት ሃገር መውጣት ይችል ነበር። ነገር ግን ለግል ህይወቱ ቅድሚያ ባለመስጠትና ብዙ ኣመታት ያስቆጠረ በውስጡ የታመቀው ልባዊ የፍትህ ፍላጎት እዛው በሱዳን ሃገሩ ድንበር ላይ ቆይቶ እንዲታገል ኣስገድዶታል። ሆኖም የህወሓት ቂመኛና የአፈና እጅ በምድረ ሱዳን እያንሰራራ በመምጣቱ፣ ከሌሎቹ የዴምህት ኣባላት ጋር ሆኖ ሱዳንን ለቆ መውጣትና ራቅ ብሎ መታገል ግድ ሆነበት። ለዚህ ነበር ካናዳ ድረስ የመጣው።
ኣቶ ክንፈ እዚህ ካናዳ ድረስ መጥቶም ኣርቆ ኣሳቢነቱና ለወገኑ ፍትህ ፈላጊነቱ የሚያንፀባርቅው ትግሉ ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ጋር በመሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በጥልቀት ቀጥሎበታል። በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያዊያን መካከል ያሉት ተቃራኒ ኣመለካከቶች የፈጠሩት ስሜታዊ ትርምስ ምንም ሳይበግረው ድሮውን ለተለመው ዘላቂ‐ፍትሃዊና እኩልነታዊ ኣንድነት በየመድረኩ ሲታገል ኖሮዋል።
በቅርቡ እንደዚሁ በኢትዮጵያ የጋራ ትግል ሸንጎ ስር ከተደራጁት ወገኖቹ ጋር ሆኖ ህይወቱ በድንገት እስካለፈችበት ድረስ ኣበክሮ ሲታገል የነበረ ጀግና ታጋይ ነው።
ኣቶ ክንፈ ሃደራ በድንገት ቢለየንም መልካም ስነ‐ምግባሩ፣ የዓላማ ፅናትና ታጋይነቱ እንዲሁም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍትህ ፈላጊነቱ ለሁላችን ኣርኣያ በመሆን ለዘለኣለሙ ይዘልቃል፣ እያልን ለመላው ቤተሰቡና ለትግል አጋሮቹ አርአያነቱን እንዲጎናጸፉ እንመኛለን።