Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: በኢትዮጵያ የዲያሌስስ (የኩላሊት እጥበት) ህክምና ፈተና ገጥሞታል

$
0
0

ከአስመረት ብስራት / በመንግስት ሚዲያዎች የቀረበ ጽሑፍ

በድሬዳዋ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርታ ትሰራ የነበረችው ወይዘሪት ሰላማዊት ወንድሙ የኩላሊት ችግር ስለገጠማት ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥታ በቅዱስ ዻውሎስ ሆስፒታል ክትትል ከጀመረች ወራትን አስቆጥራለች። ከወራት የህክምና ክትትል በኋላ ኩላሊቷ ስራ ማቆሙን የተረዱት ሀኪሞች የዲያሌስስ (የኩላሊት እጥበት) ህክምና እንዲትከታተል ያደርጋሉ። ሆኖም ለዲያሌስስ ህክምናም ሆነ በየእለቱ ለሚታዘዙ ውድ መድሃኒቶች የሚያወጡት ወጪ ከአቅማቸው በላይ ሆኗል።

(ወ/ሮ ሰላማዊት ወንድሙ)

(ወ/ሮ ሰላማዊት ወንድሙ)


ጥሪታቸውን አሟጠው የእህታቸውን ህይወት ለመታደግ የሚጥሩት የሰላም እህትና ወንድሞች የዲያሌስስ ህክምና ለማግኘት ከቀበሌ የሚሰጥ የነፃ ህክምና ወረቀት እንኳን እንደማያገለግል ነው የሚናገሩት። ሌሎች ከፍተኛ ቀዶ ህክምና የሚፈልጉና ውድ የሚባሉት ህክምናዎች የገንዘብ አቅም ለሌላቸው በነጻ የሚሰጥ ቢሆንም ለዲያሌስስ ህክምና ይህ እድል ያለመሰጠቱን ምክንያት አልተረዳነውም ይላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ለበሽታው የሚታዘዙ መድሃኒቶች በሀገር ውስጥ አይገኙም። ከተገኙም በኮንትሮባንድና በሌሎች ህገወጥ መንገዶች የገቡ በመሆናቸው ከአንድ እስከ ሁለት ሺ ብር ድረስ ማውጣትን ይጠይቃሉ፡፡ ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭና የመኖር ተስፋን የሚያጨልም መሆኑን የምትናገረው ሰላማዊት ቀሪውን ቤተሰብ ችግር ውስጥ ላለመክተት «ምናለ ሞቴን ባፋጠነው» እያለች እንደምትፀልይ ነው የገለፀችው።

ለመዳን ተስፋ አድርጎ ጥሪትን ሟሟጠጥ፤ ከዚያም ተስፋ መቁረጥና ለቋሚው በመጨነቅ እረፍት የሚያሳጣ ችግር ውስጥ መውደቅን የሚያመጣው የኩላሊት ስራ ማቆም ችግር የብዙዎች ፈተና እየሆነ ነው። በህክምናው ውድነት ሳቢያም የበርካቶች ህይወት እያለፈ እንደሆነ በሰፊው ይነገራል።
ሰላማዊትና እሷን መሰሎች ከግሉ የህክምና ተቋም ቢቀንስ ብለው በብቸኝነት የዲያሌስስ ህክምና ወደሚሰጥበት ቅዱስ ዻውሎስ ሆስፒታል መጥተዋል። ቶሎ የመዳን ተስፋ ኖሯቸው ህክምናውን ከጀመሩ በኋላ እጅ ሲያጥር ጭንቅ ሆኗል፡፡

ሌላዋ ከወንጪ አካባቢ የመጣችው ታደሉ ናታ የሀያ አመት ወጣት ናት። ይህች ወጣት ከማህፀን ውጪ ያለ እርግዝና ገጥሟት ወደ ወሊሶ ሆስፒታል ትሄዳለች። እዚያ የቀዶ ህክምና ተደርጎላት ከስቃይዋ ብዙም ሳታገግም ድንገተኛ የኩላሊት ስራ ማቆም ችግር ይገጥማትና በአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ካላገኘች ህይወቷ ሊያልፍ እንደሚችል ተነገሯት ወደ ሆስፒታሉ ከመጣች በኋላ ትንፋሽ አግኝታለች።

ይህች ወጣት ከጭንቅ ብትገላገልም በርካታ እሷን መሰል ዜጎች በድንገተኛ የኩላሊት ስራ ማቆም ችግር እየተጠቁ በገንዘብ አቅም ማጣት የተነሳ እርዳታ ሳያገኙ ቤታቸው ሄደው ይሞታሉ፡፡ በግል ሆስፒታሎች በከፍተኛ ገንዘብ የሚታከሙትም ቢሆኑ ቤትና ንብረታቸውን ሸጠው ገንዘቡ ሲያልቅ ህክምናቸውን ያቋርጣሉ ወደማይቀረው ሞትም ይሄዳሉ። ቀሪው ቤተሰብም በድህነት ይማቅቃል።

ለመሆኑ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እየተሰጠ የሚገኘው የዲያሊስስ ህክምና ምን ይመስላል? በህክምና ወጪው ላይስ ምን አስተያየት አለ? ስንል በሆስፒታሉ የኩላሊት ህክምናና የዲያሌስስ ክፍል ሃላፊ የውስጥ ደዌና የኩላሊት አስፔሻሊስት ዶክተር ሞሚና መሃመድን አናግረናል፡፡
ዲያሌስስ ማለት በከፊል የኩላሊትን ስራ ተክቶ የሚሰራ ህክምና ነው። በዲያሌስስ የሰውነትን ቆሻሻ የማጣራት፤ በሰውነት ውስጥ ያለን ውሃ የመመጠን፤ የኩላሊትን አቅም ማሳደግና ኤሌክትሮ ላይት የመመጠን ሥራ ይሰራል ይላሉ ዶክተር ሞሚና።

ወጣት ታደሉ ናታ

ወጣት ታደሉ ናታ


ሆስፒታሉ ብቸኛው የመንግስት ተቋም በመሆን ይህንን አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከግብፅ መንግስት በተገኘ እርዳታ ከ5 ወራት በፊት ነው። ማሽኖቹም ሆነ አላቂ እቃዎች በእርዳታው የተገኙ ናቸው። በመሆኑም ካለው የአቅም ውስንነት የተነሳ በአሁኑ ወቅት ህክምና የሚሰጠው አጣዳፊ የኩላሊት ችግር ማለትም መዳን የሚችለውን የኩላሊት በሽታ ያጋጠማቸውን ብቻ ነው። ይህም በመሆኑ ሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚያስፈልግ ደረጃ ላይ የደረሱትን ህሙማን ለመርዳት አይችልም።

ዶክተር ሞሚና እንደሚሉት እስካሁን በዚህ አገልግሎት ከስልሳ በላይ ታካሚዎች እፎይታ አግኝተው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል። በብዛት አገልግሎቱን የሚያገኙት ደግሞ ታካሚዎች በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት ችግር የገጠማቸው እናቶች ናቸው።
ህክምናውን ካገኙ በኋላ በርካቶች ወደ ቀድሞ ጤናቸው ቢመለሱም አገልግሎት ሳያገኙ ተመልሰው ህይወታቸው ያጡ ሰዎች መኖራቸውንም ይናገራሉ። እናም ሁሉም የኩላሊት ህሙማን እርዳታ የሚያገኙበት መንገድ መመቸቻት እንደሚኖርበት አስምረውበታል —ዶክተሯ፡፡ ህመሙ በየጊዜው እየጨመረ እንደመሄዱ መጠን ህክምናው የጠብታ ያህል ከመሆን ያለፈ ከችግሩ አንፃር ይህ ነው የሚባልና የሚጠቀስ እንዳልሆነም ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት ለኩላሊት ስራ ማቆም ምክንያት የሆኑት ስኳርና የደም ግፊት ወረርሽኝ በሚመስል መልኩ እየተከሰቱ ከመሆኑ አንፃር ይህ በሽታ በስፋት እየተከሰተ የሚሄድ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሞሚና በርካታ ሰዎች የበሽታው ሰለባ ሆነው በሳምንት ሶስቴ ኩላሊታቸው እንዲያጣረ በሚያግዝ መሳሪያ በከፍተኛ ክፍያ እየታከሙ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

በሆስፒታሉ የኩላሊት የንቅለ ተከላ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ህሙማንን እንደማያስተናግድ ያነሱት ዶክተሯ ይህም በመሆኑ በርካቶች በሆስፒታሉም ሆነ በግል ሲታከሙ ይቆዩና ገንዘባቸው ሲያልቅ ንቅለ ተከላውም ሳይደረግላቸው ህይወታቸው ያልፋል ይላሉ። እሳቸውም በዚህ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ስሜታቸው እንደሚነካ ይናገራሉ «አንዳንዴ…» ይላሉ ዶክተር ሞሚና «አንዳንዴ ይህ ህክምና ባይኖርስ! ብዬ አስባለሁ። ጥሪት ጨርሶ በጭንቀት ከመሞት በሰላም ማሸለብ ይሻላል እላለሁ» ብለዋል።
ይህ ችግር ከመከሰቱ በፊት ህብረተሰቡ በቅድመ መከላከል ስራ ላይ ቢያተኩር የሚሻል መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ሞሚና የበሽታው መነሻ ከሆኑት ዋናዎቹ ምክንያቶች የስኳር በሽታ በአለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ሲሆን ሁለተኛው የደም ግፊት፤ ሶስተኛው ደግሞ ከበድ ባሉ ኢንፈክሽኖች መነሻነት የሚጀምር እንደመሆኑ ህብረተሰቡ እነዚህ ችግሮች እንዳይኖሩ በማድረግ መከላከል ይኖርበታል ሲሉ ይመክራሉ።

ባለሙያዋ እንደሚሉት በሽታው በአብዛኛው ምልክት አያሳይም። ምልክት የሚያሳየው መጨረሻ ላይ ማለትም ኩላሊት ስራውን አቁሞ ከባድ እርዳታ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ ችግሩ ተከስቶ ከማይወጡበት ኢኮኖሚያዊም ሆነ አካላዊ ችግር ከመዳረግ በፊት በአመጋገብ በማስተካከል ራስን ማዳንም ማቆየትም እንደሚቻል ሙያዊ ሃሳባቸውን ያጋራሉ።

ማንኛውም ሰው ጤናማ አኗኗር ሥርዓትን በመከተል ማለትም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በማድረግ፣ አትክልት በመመገብ ግፊት ሰኳርና ሌሎች በሽታዎችን በመከላከል በተጓዳኝ ከሚመጡ ችግሮች ራሱን መከላከል ይችላል፡፡
በሆስፒታሉ ሊድን የሚችለውን የኩላሊት በሽታ ህክምና መስጠት መጀመሩ ካልቀረ የተወሰነውን ህብረተሰብ ማገልግል የሚቻልበት አቅም እንዲፈጠር ማድረግ ይገባል የሚል እምነት አላቸው ዶክተር ሞሚና። በተጨማሪም ሆስፒታሉ ባለው አቅም በነፃ ህክምና ለሚገባቸው ሰዎች አገልግሎት ቢሰጥ የተሻለ እንደሚሆንም ይናገራሉ። በሌላ በኩልም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታውን አሳሳቢነት በመረዳት ተኩረት ቢሰጥ መልካም ነው የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡

የሆስፒታሉ ፕሮቮስት ዶክተር መሰፍን አርአያ በበኩላቸው በሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት ህክምና ተጀምሮ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወራትን እንዳስቆጠረና ለአንድ ጊዜ አገልግሎትም አንድ ሺ ብር እንደሚከፈል ተናግረዋል። ይህም በእርዳታ በተገኙትና ለዓመት በሚያገለግሉት ስድስት የማጣሪያ መሳሪያዎችና ሌሎች ግብአቶች እንደተጀመረ ገልጸው እንዴት መጠቀም እንደሚገባ በሆስፒታል ደረጃ ተነጋግረው መወሰናቸውን ያመለክታሉ። በዚህም በርካታ ተከታታይ ህክምና ያላቸው ህሙማን እንዳሉ ቢታወቅም ያለውን ለድንገተኛና ለአጣዳፊ የኩላሊት ስራ ማቆም ችግር ለማዋል ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

ለአጣዳፊው ህመም የህወይት አድን አገልግሎት መስጠት የተጀመረ ሲሆን ይህም በግል የህክምና ጣቢያዎች ከሚከፈለው ባነሰ ክፍያ የሚሰራ ነው። ይህም አገልግሎቱ ቀጣይ እንዲሆን ለግብዓት ማሟያ እንዲሆን ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ ስራው ከተጀመረ በኋላ አጥጋቢም ባይባል ውጤታማ አገልግሎት መሰጠቱን የተናገሩት ዶክተሩ ችግሩ በነፍሰ ጡር እናቶችና ህፃናት ላይ በሚያጋጥም ወቅት ገንዘብ ኖራቸውም አልኖራቸው አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ያብራራሉ። በመሆኑም በተደረገላቸው ህክምና የተነሳ በርካታ ነፍሰጡር እናቶችና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር የገጠማቸው ሴቶች ዳግም ኩላሊታቸው አንሰራርቶ እፎይታ አግኝተዋል።

«አቅም የሌላቸውን ሰዎች በምን መልኩ እናስተናገዳቸው? ለሚለው ጥያቄ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን በቀጣይ አገልግሎቱ በጣም በአነስተኛ ክፍያ እንዲሰጥ፤ ያንንም መክፈል ለማይችሉ ደግሞ በነፃ ተሰጥቶ በየጊዜው ሪፖርት እየተደረገ እንደሚወራረድ ቃል ተገብቶ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ነን» ሲሉ የህክምናው ውድነት የፈጠረውን ችግር ለመፍታት መፍትሄ መቀመጡን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ህክምናው ወድ ከመሆኑ የተነሳ አቅም ያለውም ሆነ የሌለው የነፃ ህክምና ወረቀቱን በተለያየ መልኩ በማውጣት አገልግሎት ለማግኘት እንደሚጥር ተናግረው ይህንን ማጣራት ካልተቻለና ትክክለኛው ችግረኛ ሰው ካልታወቀ ከዚህ በፊት ስራውን ሞከረውት በገንዘብ ማጣት ምክንያት እንደተዘጉት ሆስፒታሎች አይነት እጣ ፋንታ ሊገጥም እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል ።

ችግሩ ሰፊና አሳሳቢ እንደመሆኑ ሊያግዙ የሚችሉ ድርጅቶችን (ስፖንሰሮችን) በማፈላለግና አቅሙ ያለው ሰውም ተገቢውን ክፍያ እንዲከፍል በማድረግ የህይወት አድን ስራው እንደሚቀጥል ተናግረው ዲያልስሱ ለእድሜ ልክ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ነው ያሉት በረጅም ጊዜ እቅድም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና እንደሚጀመር በመጠቆም።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>