(ዘ-ሐበሻ) በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ጃርሶ ከ2 ሳምንት በፊት ባጋጠማቸው ከባድ የመኪና አደጋ የተነሳ እስካሁን በህክምና ላይ እንደሚገኙ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለጹ።
ከ2 ሳምንታት በፊት በደቡብ ኦሞ አካባቢ እየተገነባ የሚገኝን የስኳር ፕሮጀክትን ለመጎብኘት ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ወደ ዛው አምርተው እንደነበር የገለጹት ምንጮች በአቶ ሽፈራው ጃርሶ መኪና ላይ በደረሰ አደጋ ባለስልጣኑ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።
አቶ ሽፈራው ላይ አደጋው የደረሰው በወላይታ አካባቢ እንደሆነ ያስታወቁት ምንጮቹ እንደ አደጋው አሰቃቂነት ሕይወታቸው መትረፉ በራሱ ትልቅ እድል ነው። በአካባቢው ሄሊኮፕተር ተልኮ ወዲያውኑ ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል እንደመጡና ህክምናቸውን በዛው እየተከታተሉ እንደሚገኙ ምንጮቹ ጠቅሰው ባለስልጣኑ እስካለፉት 2 ቀናት ድረስ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ካለፉት 2 ቀናት ወዲህ ያለውን የአቶ ሽፈራው ጃርሶን ሁኔታ ዘ-ሐበሻ ለማጣራት ሞክራ አልተሳካላትም።
ዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ የሚከተለው ግጥም የዋልድባ የመታረስ ዜና የተዘገበ ሰሞን ወጥቶ ነበር። ግጥሙን ከትውስታ እዚህ አምጥተነዋል።
ስኳር ገዳም ገባ
እያንገራገረ ህዝቡ እያባባ
አበው እያዘኑ ወጣት እያነባ
እየተቃወሙ እየጮሁ እነ አባ
ዜናው በዓለም ዓቀፍ እየተስተጋባ
ድንገት ሳይታሰብ ስኳር ገዳም ገባ
ከፍ ከፍ ብሎ ለዚያውም ዋልድባ
ሲጠፋ ሲሰወር ሲደበቅ ቆይቶ
በአቋሙ ጠንክሮ በአቋሙ ጸንቶ
አመክሮ ሳይዝ ድንገት ገዳም ገብቶ
ጣፋጭ የነበረው ሊመር ነው ከቶ
ለሱ የሚስማማ ስንት ቦታ ሞልቶ
ስኳር እሳት ሆኖ ከገበያ ጠፍቶ
ሊቀመጥ ነው አሉ መቃብር ቤት ገብቶ
ምን ይውጥሽ ይሆን ከእንግዲህ መርካቶ
አባቶ ች ምን አሉ በዋልድባ ያሉ
በአባቶች አጽም ላይ ሸንኮራን ሲተክሉ
ከተቀበረበት እየፈነቀሉ
በደም የበቀለ ሸንኮራ ሊበሉ
በውሳኔ ጸንቶ
ኸረ እግዚኦ በሉ!
ይሄስ ጥሩ አይደለም
ከአቅም በላይ ሆኖ ህዝቡ ቢበደለም
አባቶች ዝም በሉ ይረሱት ግድ የለም
ዋልድባ በጾሙ ምነው ተፈተነ
በገዳሙ ልማድ ትንሽ ከታዘነ
ጸሎቱ እንደወጉ ከተከናወነ
ውሎ አድሮ ይሟሟል ስኳር ስለሆነ
4/3/12 voa radio
ከአዜብ ሮባ