ኢሳት ቲቪ በዛሬ ስርጭቱ እንደዘገበው በሞያሌ ከተማ የኦነግ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ ከተማዋ በመከላከያ ሰራዊት ስትታመስ ዋለች። ባለፈው ረቡእ ታጣቂዎቹ ከቀኑ 10 ሰአት ገደማ ወደ ከተማዋ በመግባት 3 ጠባቂዎችን በመግደልና አንደኛውን ታጣቂ መሳሪያውን በመቀማትና ልብሱን በማስወለቅ ” ሂድና ለአለቆችህ ንገር” በማለት ጉዳት ሳያደርሱበት መልቀቃቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ አንድ ድግን መትረጊስ፣ አንድ ላውንቸርና አንድ ባዙቃ ማርከው ወስደዋል። ይህንን ተከትሎ በአካባቢው የደረሱት የመከላከያ ሰራዊት አባላት አንዳንድ የከተማ ነዋሪዎችን እየደበደቡ ሲያሰቃዩ መቆየታቸውን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
አንድ ሹፌር ለኢሳት እንደገለጹት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተሳፋሪዎችን ከመኪና ላይ በማስወረድ ድብደባ እንደፈጸሙባቸውና እርሳቸውም በጥፊ እንደተመቱ ተናግረዋል
“እኛ ለምን እንደተደበደብን አልገባንም” የሚሉት ነዋሪዎች፣ ሁኔታው እስከትናንት ድረስ ውጥረት የነበረበት እንደነበርና ፍተሻው በእየጫካው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ በነዋሪዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለማድረሳቸውም ተገልጿል። በጉዳዩ ዙሪያ የሞያሌን አስተዳደር ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም። መንግስትም በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።
ኦነግ ገዢውን ሀይል በትጥቅ ትግል ለማስወገድ ከሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግስት ታጣቂዎች በኦጋዴን ውስጥ በሚኖሩ ዜጎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ኦጋዴን ፕሬስ ዘግቧል።
ልዩ ሚሊሺያ የሚባሉት ሀይሎች ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በወሰዱት እርምጃ ፍሪህ ደሃግ አዳር የተባለው ሰው ሲገደል ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል።