ቀን፡ 03/01/2014
በክህነት ካባ ተሸፍኖ እግዚአብሔን ሳይፈሩና ሰውን ሳያፍሩ የሃሰተ መአትን በሕዝበ ክርስቲያን ውስጥ በመርጨት እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚጥሩ ካህናትን አሁንም ማርያም እያጋለጠቻቸው ትገኛለች።
አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ።እንደነዚህ ካሉት ራቅ።1ኛ ጤሞቲ.6፤4-6።
የቤተ ክርስቲያን አባላት፤ ካህናቱንና ምእመናኑን ወክለው ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን በበላይነት እንዲያስተዳድሩ ሕዝብ መርጦ ሰይሟቸው የነበሩት 3 ካህናት፤ 4 ምእመናንና 1 የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች የአገልግሎት ጊዜአቸውን ጨርሰው ለረጅም ጊዜ በኃላፊነት ላይ በመቆየታቸውና ከዛም ጋር ተያይዞ ብዙ የአስተዳደር ችግሮች በመከሰታቸው ምክንያት በ23 September 2012 ሁላችንም በገዛ ፍቃዳችን ከሥልጣናችን ለቀናል በማለት ለሕዝብ ይፋ አደረጉ።
ከዛም በመቀጠል አዲስ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ምርጫ ይካሄዳል ሲባል የካህናቱ ተወካዮች በተለይም አባ ግርማ ከበደ ሥላጣናቸውን ዘለዓለማዊ ለማድረግ ሲሉ አዲስ ምርጫ የሚካሄደው በሕዝቡ ፍላጎትና ውሳኔ ሳይሆን እኛ ባልነውና በሚመቸን መንገድ ብቻ ነው በማለታቸው ከፍተኛ ሁከት ተፈጠረ።
በዚህ ጊዜ ይህንን ሁከትና መከፋፈል መቋቋም ያቃታቸው 4ቱ የምእመናን ተወካዮች ቃላቸውን በመጠበቅ ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ አቆመው እቤታቸው ቀሩ።
ይህ በሆነበት ወቅት አባ ግርማን ጨምሮ ሦስቱ ካህናት በምእመኑ መልቀቅ ተደስተው ሥልጣኑን ሁሉ የግላቸው በማድረግ የማይፈልጓቸውን የቤተ ክርስቲያኑን አባላት ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳትደርሱ በማለት በደብዳቤ ማገድና ማባረር በመጀመራቸው ቤተ ክርስቲያንን እስከማዘጋት የሚደርስ ሁከትና ረብሻ አስነሱ።
ከዛም በመቀጠል የቤተ ክርስቲያኑ መሰሶ፤ ጣሪያና ግድግዳ የሆኑትን አባላቱን ለማሸነፍ የሚችሉበትን ኃይል ለማግኘት ሲሉ የመረጣቸውንና የወከላቸውን ሕዝብ ከድተው ቤተ ክርስቲያኗ የሃገረ ስብከቱ ናት፤ ንብረቷም የቅዱስ ሲኖዶስ ነው የሚል ማጭበርበሪያን በመጠቀም የመንግሥት ተወካይ የሆኑ ጳጳሳትንና የኤምባሲ ባለሥልጣናትን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያኗን ከአባላቷ ነጥቀው በመውሰድ እጅ መንሺያና መሾሚያ መሸለሚያ ሊያደርጓት ጣሩ፤ ሆኖም ግን አባላት ባደረጉት ጠንካራ ትግልና በእግዚአብሔር ተራዳኢነት አንዱም ተንኮላቸውና ክህደታቸው ውጤት ሳያስገኝላቸው መክኖ ቀረ።
ከዛም በመቀጠል ቤተ ክርስቲያኗ የምትገኝበትን ሃገር አጠቃላይ ሕግና በተለይም ቤተ ክርስቲያኗ የተመዘገበችበትን የቻሪ ሕግ መከተልን አሻፈረኝ በማለት በማታለልና በመዋሸት የቤተ ክርስቲያንን ንብረት ከአባላቷ መንጠቅ እንችላለን በማለት የሃገርንም ሆነ የሕዝብ ንብረትን ሲዘርፉ ይሉኝታም ሆነ ሃፍረት ካልፈጠረባቸው የዘመናችን የቀን ጅቦች ጋር በመመሳጠር በቤተ ክርስቲያኑ አባላት ላይ የጥቃት ዘመቻ ከፍተው አሁንም በአባላቱ ጥንካሬና በእግዚአብሔር ተራዳኢነት የተኮል መረባቸው ሁሉ እንዳይሰራ ተደረገ፡፡
በመጨረሻ የቻሪቲ ኮሚሽን ጉዳዩን በመረዳት ምንም እንኳ ከሥልጣን አንለቅም ብለው ሥልጣንን የሙጥኝ ብለው ሕዝብንና ቤተ ክርስቲያንን የሁከት መድረክ ያደረጉት 4 የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባላት (Trustees) ውስጥ አንድም ሥለ ምእመኑ የሚከራከርና ምእመኑን የሚወክል አባል ባይኖርም ከዚህ እነሱ የሙጥኝ ካሉት ሥልጣን እንደ ሰንኮፍ አውጥቶ በመጣል ቤተ ክርስቲያኗን እና አባላቷን ከፈጠሩባት ሕመም ለማዳን ያለው አማራጭ አዲስ ምርጫ ማካሄድ መሆኑን በመረዳት ባለ አደራዎች (Trustees) ነን ብላችሁ ከሆነ የምትንገታገቱት ኃላፊነት የሚሰማው ሥራ መሥራት አለባቸሁ በሚል በንፈስ መብታቸውን ለማስከበርና ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ለማኖር ሕጋዊ መንገድ ይዘው ከሚታገሉ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ተወካዮችና የሕግ ጠበቃቸው ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከቤተ ክርስቲያን መከፈት ጀምሮ አዲስ ምርጫ ስለሚካሄድበት ሁኔታ ታዛቢ ባለበትና፤ በፊርማ በሚረጋገጥ የውል ሰነድ መሰረት ስምምነትና መግባባት ላይ እንዲደርሱ ቀነ ገደብ ወስኖ መመሪያ ሰጣቸው።
ቻሪቲ ኮሚሽን ይህንን መመሪያ ሲያወጣ ግን እነሱ ብቻ ናቸው ትረስቲዎች ብሎ መወሰኑ ሳይሆን ማን ትረስቲ እንደሆነ የሚወስነው ፍርድ ቤት ነው በማለት ከችግሩ ለመውጣት ግን መፍትሔው ሁሉም ወገን የተስማማበት ምርጫ ማካሄድ ነው የሚለውን አበክሮ በመግለጽ ነበር።
ይህንንም ቻሪቲ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ በተራ ቁጥር 5 ላይ እንደሚከተለው በማለት ያብራራዋል።
“As part of our regulatory case we considered the question of who are the validly appointed trustees of the charity. This is a matter to which only the Courts can provide a definitive answer because the question centers on interpreting the governing document of the charity, which is under the jurisdiction of the Courts.”
ይህንን የመሰለ መመሪያና ማብራሪያ ቻሪቲ ኮሚሽን ለሁለቱም ወገን የሕግ ጠበቆች ልኮ እያለ የእውነትና የፍትሕ መንገድ ሁሉ ጨለማ መስሎ የሚታያቸው አባ ግርማና ተከታዮቻቸው ግን በተለመደው የቅጥፈት ተግባራቸው መሠረት ከመመሪያው ውስጥ ቻሪቲ ኮሚሽን ትረስቲዎች ናችሁ ብሎ ተቀብሎናል የሚል የተሳሳተ ትርጉም በማውጣት ከአሁን በኋላ የምንፈልገውን የፈላጭ ቆራጭነት ድርጊት ሁሉ የመፈጸም መብት ተሰጥቶናል የሚል አዋጅ አሰሙ።
ከዛም በመቀጠል
1. ረብሻና ሁከት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተከሰተ በHealth & Safety ችግር ምክንያት ተዘጋ ብለው ለ9 ወር ያሸጉትን ቤተ ክርስቲያን የኛ ሥልጣን ተረጋግጦልናልና የቤተ ክርስቲያን አባላት ቢፈልጉ ገብተው ይጫረሱ በሚል የአረመኔነት መንፈስ ቤተ ክርስቲያኑ በ29/12/2013 እንከፍታለን የሚል ማስታወቂያ አሰራጩ።
3. ከቄሱ የጳጳሱ እንዲሉ አቡነ እንጦስ የሚባሉ በኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ ፓስፖርት የሚንቀሳቀሱና መንበራቸው በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሆነ፡ ራሷን ችላ ስትተድደር ከኖረችው ከንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው በሥላሴ ቤተ ክርስቲያንና በገብረኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ቤተ ክርስቲያኑን እንድከፍት ቻሪቲ ኮሚሽን ስለፈቀደልኝና ከቅዱስ ሲኖዶስም ስለታዘዝሁ እኔ አቅመ ደካማ ነኝና በ29/12/13 እሑድ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ድረሥ ሁላችሁም መጥታችሁ እንድትረዱኝ በማለት ስብከት፤ ቅስቀሳና ጥሪ አደረጉ። ከዛም በማያያዝ ከለንደን ውጪ ያሉ ተንቀሳቃሽ አብያተ ክርስቲያናት የመጓጓዣ ኮች ተልኮላቸው በነጻ በመጓጓዝ ማርያም ቤተ ክርስቲያን መጥተው የእነ አባ እንጦስ ሠራዊት ሆነው እንዲዘምቱ መርሃ ግብር ተዘጋጀ።
አቡነ እንጦስ ከአሁን በፊትም እንኳንስ ብጹዕ ከተባለ ጳጳስ ቀርቶ ከማንኛውም የእግዚአብሔር አማኝ ሰው በማይጠበቅ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት የሚጸልዩበት ቦታ ድረሥ በመምጣት ሰላም አወርዳለሁ በማለት እኔ የሁለታችሁም አባት ነኝ፤ ለአንዳችሁም አላደላም በማለት እውነተኛ አባት መንፈሳዊ አባት መሆናቸውን ለማሳየት ጥረው ነበር። የሚገርመው ግን ይህንን የቅጥፈት ቃል የሚናገሩት በሌላ በኩል ከቤተ ክርስቲያኗ አባላት ጋር ለውነት ቆመው የእውነት ሥራን በመስራት ላይ ያሉትን ቄስ ብርሃኑን ከቤተ ክርስቲያኑ አባላት ጎራ ወጥተህ ከኔ ጎን ተሰልፈህ አባላቱ እንዲበተኑ ካላደረግህ አሳርህን አሳይሃለሁ በማለት በስማቸው እየፈረሙ የሚልኩትን ከአንድም ሁለት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤና ከአባ ግርማ ጎን ቆመው ቀን ከሌሊት እንደሚሰሩ እግዚአብሔር ቀርቶ አባላትም የሚያቁት የአደባባይ ምሥጢር ስለነበር እኝህ ጳጳስ እንኳንስ ሰውን እግዚአብሔርንም አታልላለው ብለው በማሰብ የሚያደርጉት ጥረት በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያሳዝን ነበር።
ይህ አልበቃ ብሏቸው ነው ዛሬ ደግሞ ሌላ በሬ ወለደ ሃሰት ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሚነግሩት። አቡነ እንጦስ ቻሪቲ ኮሚሽን ቤተ ክርስቲያን እንድከፍት ፈቅዶልኛል ያሉት ቻሪቲ ኮሚሽን ግን የእሳቸው ጣልቃ መግባት ተገቢ ያልሆነ መሰናክል ነው በማለት የገለጸው ባጭሩ እንደሚከተለው ነበር።
“We have pointed out that a role of the Archbishop of the Diocese of North West Europe is neither appropriate nor desirable for the trustees to create unnecessary barriers to an inclusive election process.”
በሌላ በኩል ደግሞ አቡነ እንጦስ ይህንን የሃሰት መረጃ መሠረት በማድረግ ለጸሎትና ለቅዳሴ የተሰበሰበውን ሕዝበ ክርስቲያን እኔ አቅመ ደካማ ነኝና መጥታችሁ እርዱኝ ማለታቸው የቤተ ክርስቲያኑን በር ለመክፈት የሚፈነቅል ድንጋይና የሚጎተት ገመድ ኖሮ ጉልበት አስፈልጎ ሳይሆን በብዛት መጥታችሁ በቤተ ክርስቲያኑ አባላት ላይ በመዝመት ቤተ ክርስቲያኗን እንድወርስ እርዱኝ ማለታቸው ነበር።
በዚህ ድርጊታቸው እኚህ ጳጳስ ምን ያህል እግዚአብሔርን ሳይፈሩና ሰውን ሳያፍሩ ውሸትን ከመንዛት አልፈው ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ አንዱን ክርስቲያን በሌላው ላይ አዝምቶ ማፋጀት የማያሳስባቸውና የማይጸጽታቸው ሰው እንደሆኑ መረዳት ይቻላል።
4. ከዚሁ ጋራ አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው፤ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሥልጣናት፤ የወያኔ የደህንነት ሰዎች፤ የሃገረ ስብከቱና የሥላሴ ሹማምንቶች ጋር በመሆን ለአካባቢው ፖሊስ ሥለ ቤተ ክርስቲያኑ አባላት የሃሰት መረጃንና ማስፈራሪያ በማቅረብ የፖሊስ ኃይል በተጋነነው መረጃ ላይ በመመርኮዝ ከፍተኛ የደም መፋሰስና መበጣበጥ ሊመጣ ነው ብሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲያሰማራ አስደረጉ።
5. አባ ግርማና ተከታዮቻቸው የሚደገፉት እጅግ ጥቂት በሆኑ አባላት በመሆኑና 90% የሚሆነው የቤተ ክርስቲያኑ አባላት አንባ ገነናዊና ክርስቲያናዊ ያልሆነውን ድርጊታቸውን የሚቃወምና የሚኮንን በመሆኑ፤ ቤተ ክርስቲያኑ ሲከፈት የወያኔ መንግሥት ደጋፊ የሆኑ የሥላሴና የገብረኤል ቤተ ክርስቲያን አባላት በተለይም የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አባላት ከነካህናቱና የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባላት (Trustees) ሳይቀሩ በዘመቻ መልክ መጥተው የቤተ ክርስቲያኑን አባላት በቁጥር በመብለጥ እንዲያጠቁላቸውና እንዲያባርሩላቸው በማሰብ የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ አገልግሎት በመጨረስ ተጓጉዘው እስኪደርሱላቸው ጊዜ እንደሚወስድ በማሰብ የቤተ ክርስቲያኑን መከፈቻ ሰዓት ከጠዋቱ 5 ሰዓት (1100) እንዲሆን አደረጉ።
የቤተ ክርስቲያኑ በሕገወጥ መንገድ መከፈት ከተረጋገጠ በኋላ የተፈጠሩ ክስተቶች።
1. የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ቤተ ክርስቲያናቸው ከተዘጋችባቸው ጀምሮ ላለፉት 9 ወራት በብርድ፤ በዝናብና በቸነፈር ጸሎታቸውንና ልመናቸውን ሳያስተጓጉሉ በየዕለተ ሰንበቱ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናቸው በመድረስ በቅጥር ግቢ ውስጥ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ጸሎትም ሆነ ሥርዓተ ቅዳሴ ያካሂዱ ሥለ ነበር በ29/12/13 በዛው መሠረት እቤተ ክርስቲያናቸው ቅጥር ግቢ ሲደርሱ አባ ግርማ ከበደና ተከታዮቻቸው ከወያኔ ወኪሎችና ደጋፊዎች በሚያገኙት የገንዘብ ፈሰስ በመጠቀም ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁ ከ10 ያላነሱ Private Security ቀጥረው በማቆም አባላቱ ወደ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገቡባቸውን በሮች በሰንሰለት በመቆለፉ እንዲከለከሉ አደረጉ። ይህ የተደረገበት ምክንያትም አባላቱ የሌሎች ቤተ ክርስቲያን አባላት የራሳቸውን አገልግሎት ጨርሰው ተጓጉዘው ማርያም ቤተ ክርስቲያን እስኪደርሱና የአባ ግርማ ጎራ በሰው ኃይል እስኪጠናከር ጊዜ ለመግዛትና ከዚህም በተጨማሪ አባላቱ ለምን ማምለኪያና መጸለያ ቦታችንን እንከለከላለን ብለው አንባ ጓሮ እንዲፈጥሩና ይህ ሁኔታ ሲፈጠርም ፖሊስ ጠርቶ አባላትን ለማስያዝና ለማስወንጀል ነበር።
2. በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗን ከመመሥረት ጀምሮ ለደረሰችበት ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ለማብቃት ላለፉት 40 ዓመታት በጽናት ቆመው ሃብትና ጉልበታቸውን በማፍሰስ፤ የለፉ የደከሙና ያገለገሉ ካህናትና ምእመናን ከ1 ዓመት ህፃን ጀምሮ እስከ 80 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አዛውንቶች፤ አቅመ ደካሞችና ህመምተኞች ሳይቀሩ በከፋው የክረምት ብርድና ቁር እየተጠበሱ አውራ ጎዳና አስፋልት ጫፍ ላይ በመኮልኮል ከሦስት ሰዓታት የበለጠ ቢሰቃዩም የደረሰባቸውን በደል ሁሉ በጽናትና በትዕግሥት በማለፍ ከፓሊስ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር በመጨረሻ በፖሊስ ውሳኔና መመሪያ መሠረት የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በር ተከፍቶላቸው ሊገቡ ችለዋል።
3. እነዚህ በቁጥር ከ320 በላይ የሚሆኑ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ካህናትና ምእመናን ወደ ቅጥር ግቢው ሲገቡ አባ ግርማና ተከታዮቻቸው ተቻኩለው የቤተ ክርስቲያኑን ዋናና ትልቅ በር ብርግድ አድርገው ቢከፍቱም አባላቱ ግን የተከፈተው ቤተ ክርስቲያን መዝጊያ በር እንጂ የሰዎች በር እንደተዘጋና እንደተቆለፈ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን አባላት ላይ ቂምን ቋጥረው፤ ክርስቲያኑን ህብረተሰብ እርስ በእርሱ አጋጭተው በዛ መሃል ለመኖር ቀንና ሌሊት የዲያብሎስን ሥራ ከሚሰሩ ካህናት ጋር ሆዶ ሻክሮ ጥላቻን አዝሎ እርቅ ሳይወርድና ሰላም ሳይሰፍን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ መቀደስም ሆነ ማስቀደስ በእግዚአብሔር ማላገጥ ነው በሚል ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መግባትን ትተው ወደ ተለመደው የመቀደሻ ሥፍራቸው እየተዥጎደጎዱ ገቡ። ከዛም በመቀጥል ምንም ምንም ሳይሉ የዕለቱን ጸሎታቸውንና ሥርዓተ ቅዳሴ ማካሄድ ጀመሩ።
4. አባ ግርማና ተከታዮቻቸው፤ ከሥላሴ ቤተ ክርስቲያንና ከወያኔ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ከሌላ ቤተ ክርስቲያናትና ከለንደን ውጪ ያስመጧቸውን የወያኔ ደጋፊዎች በማግተለትል ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲገቡ አደረጉ፤ እነዚህ አዋጅ ተነግሮና ነጋሪት ተጎስሞ የመጡ የወያኔ ደጋፊዎች ግን ሲበዙ ቢውሉ በቁጥር ከ120 የሚበልጡ አልነበሩም።
5. አቡነ እንጦስና የሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የተባለው መጋቢ ተወልደና ሌሎች የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ሹማምንቶች የቤተ ክርስቲያኗ አባላት በአንጡራ ገንዛባቸው ገዝተው ባቆሙት የቪካሬጅ ህንፃ ውስጥ ሌሊቱን ተደብቀው በማንጋት በጓሮ በር አድርገው ከሕዝብ ተሸሽገው እንደ ሌባ በጓሮ በር ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገቡ።
6. አባ ግርማና ተከታዮቻቸው ከቤተ ክርስቲያኑ መከፈት ጋር ያቀዱት ዕቅድና ያዘጋጁት ነገር ቢኖር በተቀደሰው የእግዚአብሔር ቤት፤ በጽላት ፊት ሕዝበ ክርስቲያንን ለማጋጨትና በሚነሳው ሁከት የቤተ ክርስቲያኑ አባላትን ወንጀለኛ አድርጎ በፓሊስ ለማስያዝ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየ ጥጉ ካሜራና የድምጽ መቅጃ መሣሪያ አዘጋጅተው ልክ ወጥመድ ውስጥ እንደሚገባ አውሬ አባላትን መጠበቅ ነበር። እነሱ አባላትን ለማጥቃት ወጥመድ ቢያዘጋጁም በዛ ወጥመድ ውስጥ የሚገቡት ግን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተጠርተው በማያገባቸው የሌላ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ የተደረጉት ክርስቲያኖች ጭምር ሊሆኑ እንደሚችሉ ግን የእነ አባ ግርማ ጭንቅላት ታሳቢ እንደማያደርገው የታወቀ ነበር፤ ለዚህም ማረጋገጫው ከአሁን በፊት ወጣቶችን ከየቦታው ሰብስበው አባላትን ለጸብ እንዲያነሳሱና እንዲያስወነጅሉ፤ በመስደብና በድብቅ በመማታት እነሱ መልሰው እንዲመቷችሁ አድርጉ ብለው አሰማርተዋቸው አምስት ወጣቶች ሲታሰሩና ሲወነጀሉ እነ አባ ግርማን የተሰማቸው አንዳችም ፀፀት አልነበረም።
ይህንን ሁሉ ያገናዘቡትና አርቀው ያዩት የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ቻሪቲ ኮሚሽን የሰጠው ሕጋዊና መመሪያ ተጥሶ ከአባላት ተወካዮችና ጠበቆች ጋር ፍጠሩ የተባሉትን line of communication ተግባራዊ ሳያደርጉ እነ አባ ግርማ ለሚፈጽሙት ሕገ ወጥ የተንኮል ተግባር ሰለባ ላለመሆንና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በራሳቸውም ላይ ሆነ በሌሎች ክርስቲያን ወገኖቻቸው ላይ የሚደርሰውን ያልተገባ ነበር ለማስቀረት ሲሉ እነሱ እውጪ በብርድ እየተጠበሱ የሌላ ቤተ ክርስቲያን አባላት ቤተ ክርስቲያናቸውን ወረው ሲይዙ እያዩ ያቺን ቀን በታላቅ ትዕግሥትና ብልህነት አሳልፈዋታል፤ ነገም ቀን አለና የነገው ቀን ደግሞ ምን እንደሚሆን የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው።
በመጨረሻም አባ ግርማ ከበደም ሆኑ ቄስ ዳዊት አበበና ቄስ አባተ ጎበና ሕዝብ አምኖና መርጦ የሰጣቸውን ጊዚያዊ ኃላፊነት ዘለዓለማዊ ለማድረግ ሲሉና የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ሲሉ አንድ ሆኖ በኖረው ሕዝበ ክርስቲያን መካከል የሃሰት ክምር በመሥራት ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲከፋፈልና በጥላቻ እንዲተያይ ከማድረግ አልፈው የቤተ ክርስቲያኑን ውስጣዊ የአስተዳደር ችግር ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በማዛመት በሚያገኙት ድጋፍ የአባላትን መብት ለመጣስ የሚያደርጉት ጥረት በመጨረሻ በሕግ የሚያስጠይቃቸውና ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ፍርዳቸውን ከማግኘት እንደማይድኑ ማመንና መረዳት ያስፈልጋል።
ውድ የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላትና መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮችና በ29/12/2013 በቤተ ክርስቲያናችሁ በመገኘት ቤተ ክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ለመጠበቅና መብታችሁን ለማስከበር በታላቅ ትዕግሥትና ችሎታ ዕለተ ቀኑ በሰላም እንዲያልፍ በማደረጋችሁ እግዚአብሔርም የሚወደው ሰላምና ትዕግሥትን ነውና የማያልቅበት አምላክ በረከቱን አብዝቶ ይሰጣችሁ! ያሰባችሁትን ሁሉ ያሳካላችሁ!!
ወደ ፊትም እንዲሁ በየ ዕለተ እሑዱና በአስፈላጊው ጊዜ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያናችሁ በመምጣት በዚህ የሕግ የበላይነት በሰፈነበትና የሰው ልጅ ነጻነት በተረጋገጠበት ሃገር የሃሰት ተግባርን፤ ተንኮልንና አንባ ገነንነትን በሕጋዊ መንገድ በመዋጋት ለቤተ ክርስቲያናችሁ፤ ለሃይማኖታችሁና ለመብታችሁ መከበር በጽናት በመቆም ሃሰትን በእውነት በማሸነፍ ሃይማኖታችሁንና ቤተ ክርስቲያናችሁን በመጠበቅ ለትውልድ የሚተላለፍ ስራ ታከናውኑ ዘንድ የእውነት አምላክና የእውነት መንገድ በሆነው በጌታችን በመድሐኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ሥም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!!
ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂዎች እናድን!!