Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ልጓሙን የበጠሰው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የስድብ ፈረስ ዳኛቸው ቢያድግልኝ

$
0
0

በ ዳኛቸው ቢያድግልኝ

ፕሮፌሰሩ በጽሁፎቻቸው እንዲህ ብለውናል

“…በዓለም ሕዝቦች መሀከል ውድድር ቢደረግ ያለጥርጥር አበሻ አንደኛ ከሚወጣባቸው ነገሮች አንዱ ልመና ሳይሆን አይቀርም፤ ለአበሻ፣ ልመና የኑሮ ዘዴ ነው……” http://www.goolgule.com/abesha-and-begging-1/

“…አዳም አበሻ ሳይሆን አይቀርም፤ ሁሉንም ነገር ብላ ከተከለከለው በቀር ብሎ ያስቀመጠው ይመስላል፤ በላባችሁ ወዝ ብሉ ተብለው አዳምና ሔዋን መረገማቸውን አበሻ ገና አልሰማም፤ አበሻ የተፈጠረው ገነት ውስጥ ቁጭ ብለህ ያለውን ሁሉ ብላ በተባለበት ጊዜ ነው፤ እግዚአብሄር አበሻን ሁሉንም ብላ ሲለው ምናልባትም በጆሮው ጭራሽ አታስብ ብሎት ይሆናል …….” (ሰረዝ የተጨመረ)

እስከናካቴው “ሆድ” የሚባል ቃል ከአበሻ ቋንቋ ፈጽሞ ቢሰረዝ ቋንቋው ብቻ ሳይሆን አበሻም ጉድ ይፈላበታል። አዕምሮ ፣ ሕሊና የሚባሉትን ቃላት አበሻ አያውቃቸውም፤ ተግባራቸውንም ሁሉ ለሆድ ሰጥቶታል። (ሰረዝ የተጨመረ) http://www.zehabesha.com/amharic/archives/9015

 

ልጻፍ ልተው… ምናልባት… እንዲያው ምናልባት በዚሁ የሚያበቁ ከሆኑ አይቶ እንዳላየ ማለፍ ይሻል ይሆናል ስል ልጓሙን የበጠሰው የስድብ ፈረሳቸው በማንአለብኝነት ጋለበብን። ባእዳን አበሽ እያሉና እየሰደቡ ይገድሉናል። የራሳቸው ታሪክ በረሀብ ቸነፈርና ስደት የተሞላ እንዳልሆነ ሁሉ በመዝገበቃላታቸው ውስጥ ኢትዮጵያን የረሀብ ምልክት አድረገው የሚያዋርዱን በርካታዎች ናቸው። ፕሮፌሰሩ በአንድ ወቅት ሲሉ እንደሰማሁዋቸው ወያኔዎች ከዱር ወደከተማ ሲገቡ ህዝቡን ፈሪ ለማድረግና የሚያከብረው ምልክት ለማሳጣት በየቀዬው በህብረተሰቡ ዘንድ የሚከበሩትን እያፈላለጉ በአደባባይ ፂማቸውን ይዘው በመጎተት ያዋርዱዋቸው ነበር። ይህን መሰሉ የወያኔዎች ተግባር በሚያሳዝን ሁኔታ በፕሮፌሰሩም ላይ በተደጋጋሚ ደርሶባቸዋል። የወያኔዎች ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን የማዋረድ ዘመቻ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። ታዲያ ይህ ባለበት ሁኔታ የእውቀት ጣርያ ላይ ደርሰዋል የሚባሉት አዛውንቱ ፕሮፌሰር መስፍንም በአሮጌና ያለአግባብ በተደረደረ ምሳሌ ይህን መከራ የበዛበትን ህዝባችንን በሚሸነቁጥ የጅምላ ስድብ መቀጥቀጣቸው ግር የሚያሰኝ ሆነብኝ። ይህ ወቅትና ሁኔታን ያላገናዘበ መፍትሄ የመጠቆም፣ የማስተማር አቅምም የሌለው ኢትዮጵያዊነትን የሚያዋርድ ጅምላ ስድብና ሽሙጥ በተከታታይ ሲወርድብን አይቶ እንዳላየ ማለፉ ክብራችንን ለማጉደፍና ለማዋረድ ኢትዮጵያችንን ለማንቋሸሽ ለሚተጉት ዱላ ማቀበል ይሆናል። እናም ይህ ጥያቄ ይከነክነኝ ገባ። እውን አበሻ ሥራ ጠል፣ ለማኝና ሆዳም ነውን? በምን ጥናት በማንስ ትንታኔ?

 
እድሜአቸውን ሙሉ ሀገራችንን አገልግለዋል ሲባል መስማቴ ብቻ ሳይሆን በባህላችን አዛውንት ይከበራልና ክብራቸውን የሚያጎድፍ ትችት ማቅረብ አልፈልግም። ቢሆንም ታድያ የሰሞኑ ማቆሚያ ያጣው የስድብ ጅራፍ ዘላቂ ጉዳቱ ከፍተኛ ነውና አክብሮቴን ሳላጎድል እባክዎን የስድብ ፈረስዎን ልጓም ያዝ አድርጉልን እላለሁ።
በሀገራችን አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች ከነሱ የተለየ ሃሳብ ይዞ የሚመጣን ተወያይቶ የተሻለውን ሃሳብ ከመደገፍ ይልቅ ለየት ያለ ሃሳብ ያቀረበውን አንገት የሚያስደፋ የስድብ ናዳ ማውረድ ይቀላቸዋል። ይህንን በመፍራት አዋቂዎቹ ግዙፍ ስህተት ሲፈጽሙ በዝምታ ማለፍ ለሌላ ስህተት በር መክፈት ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ጽሁፍን በይዞታው ሳይሆን በጸሃፊው ማንነት እየመዘኑ ጸሀፊው በግልጽ ያስቀመጠውን ሃሳብ ወደጎን ትተው ያልተባለውን መልካም ሃሳብ ፍለጋ እየማሰኑ የራሳቸውን ትርጓሜ ይሰጣሉ። ሰአሊ በስህተት የረጨውን ቀለም “አብስትራክት” ነው ብለው በምናባቸው ውብ ስዕል እንደሚሰሩት አይነት ከስድብ ጀርባ ሙገሳ መፈለጉ ከንቱ ነው።

 
የፕሮፌሰር ተከታታይ ጽሁፎች የተጻፉት ኢትዮጵያን በስፋት በማያውቅ ሰው፣ ሀሳብን ለህዝብ ለማቅረብ ምን አይነት ጥንቃቄ የተመላበት የምርምር ጥበብ አስፈላጊ እንደሆነ በማያውቅ ሰው ቢሆን፣ ሀሳብን የማስፈር ዓላማና ግብን መረዳት በማይችል የእውቀት አድማሱ ያልሰፋ፣ በሌሎች ሀገራት የሚኖሩ ሰዎችን አኗኗር በተመለከተ ምንም ግንዛቤ በሌለው ሰው ወይም እንዲያው ለፌዘኛ የመሸታ ቤት ቀልድ ሲባል ለተወሰኑ ታዳሚዎች የቀረበ ቢሆን ምንም ትኩረት መስጠት ባላስፈለገ ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ግን አለምን ተዘዋውረው የጎበኙና ያልኖሩበትን ዘመንና ያልጎበኙትን አገር ህዝብ አኗኗር በምርምርና በንባብ ጠንቅቀው የተረዱ እድሜ የጠገቡ ምሁር ናቸውና በምንም ጥናታዊ መረጃ ባልተደገፈ መንገድ የአንድን ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር ሕዝብ በዚህ መልኩ ማሳነስና ከሌላ ፕላኔት የመጣ ሰንካላ ፍጡር ማስመሰል እድሜያቸውንና እውቀታቸውን አይመጥነውም። የአንድ ሀገር 90 ሚሊየን ሕዝብ በአንድ ቅንፍ ውስጥ “አበሻ” ብለው ከተው እንኳን የሰው ልጅ ቀርቶ ማንኛውም ማህበራዊ እንስሳ የሚያደርገውን ተሳስቦ፣ ተዛዝኖ፣ ተካፍሎ መኖርን በዚህ መልክ አሳንሶ ኢትዮጵያዊነትን ማዋረድ ታላቅ ስህተት ነው።

 

ኢትዮጵያዊነትን እያዋረዱ አገር አልባ ሊያደርጉን አዲስ ታሪክ ሊጽፉልን ያሰፈሰፉ ጠላቶች አራት ኪሎ በተቀመጡበት ሰዓት፤ ከልመና ግርድና ይሻላል ብለው የፕሮፌሰሩ የልጅ ልጆች በመላው አለም ተበትነው ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ቢያልፍልን ብለው በሰው ሀገር እየተደፈሩ፣ እየተዋረዱ በሚዳክሩበት በዚህ ዘመን፣ በርካታ እናቶች አራስ ልጆቻቸውን ታቅፈው ትንሽ ሳንቲም ለማግኘት በየመንገዱ ዳር ጥቂት የተቀቀለ ድንችና ንፍሮ ለመሸጥ ጸሀይና ብርድ ሲፈራረቅባቸው ውሎ በሚመሽበት ዘመን፣ ደካማ እናቶች ወገባቸው እስኪጎብጥ ቅጠልና ጭራጭሮ ተሸክመው የእለት ጉርሳቸውን በሚያገኙበት ሀገር፣ ተራራ የሚያክል ሸቀጥ በጭንቅላታቸው ተሸክመው የሚሮጡ ወገኖች በሚርመሰመሱበት ሀገር፣ ህጻን አዛውንቱ ትንሽ ባገኝ ብሎ ሊስትሮና ማስቲካ ነጋዴ በሆነበት ሀገር ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያውያን ሥራ-ጠል ሆዳምና ለማኝ መሆናችንን አስረግጠው ሲነግሩን መስማት እጅጉን ያማል።
 

ሀገር በሞታቸው ያቆዩልን ተዋርደው አጽማቸው ከመቃብር ሀውልታቸው ከቆመበት እየፈረሰ ባለበት፣ የኢትዮጵያን ገጽታ ማቆሸሽ የመንግስት ፖሊሲ በሆነበትና ግፈኞችና ጎጠኞች ሰው በሀገሩ ሰርቶ ሰው መሆን እንዳይችል በየማዕዘናቱ እየበተኑት ባሉበት የመከራ ጊዜ የኛው የተማሩ አዛውንት ዋናው ተሳዳቢ መሆናቸው ያሳዝናል። አብረን ስለበላን ሆዳም፣ ተቸግሬአለሁ ብሎ ድጋፍ ለጠየቀ ወገን ስለለገስን ኅሊና ቢሶች አሉን። ሰውን ከመዝረፍ መለመንን ስለመረጠ ፈሪና ጅል፣ ስላመነ ሞኝና ተላላ አድርጎ መመልከት ነውር ነው። ይህ መተዛዘንና ተካፍሎ መብላት ቀለም ያልቆጠረው ኢትዮጵያዊ ያቆመውን መሰረትና ያቆየውን ባህላዊ እሴት ልናከብረውና ልንከባከበው ይገባል። በተከታታይ በፕሮፌሰሩ የተጻፉት ጽሁፎች የሚደመድሙት አበሻ ስራ ጠል መሆኑን፣ ሆዳምነቱንና፣ ለማኝነቱን ነው። በሚቀጥለው ጽሁፋቸው ደግሞ ሌላም ሊያስከብሩን የሚገባቸውን ባህሪያችንን ልናፍርባቸው የሚገቡ አጉል ገጽታዎች አድርገው ይጽፉልን ይሆናል። ይህ ወይ እራስን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሌላውን ዝቅ ዝቅ ማድረግ በመፈለግ አለዚያም ተስፋ የቆረጠ ሰው አገርን በጅምላው ሊያስነውር የሚያደርገው ድርጊት ይመስላል።
 

ለመሆኑ ፕሮፌሰሩ ሆድ መውደድን እንዴት ይገልጹታል? ምግብ መውደድ፣ መውደድ ብቻ አይደለም አጣፍጦና አስውቦ መብላት አንደምንስ ያስወቅሳል? በውጪው አለም የምግብ ስራ ጥበብ ምንኛ የተከበረ ሙያ መሆኑን፣ ቴሌቪዥኑ በሙሉ በምግብ ስራ ፕሮግራም መጨናነቁንና የምግብ ስራ ጥበብ መጻህፍት ጸሀፊዎች ምንኛ የተከበሩ መሆናቸውን እንዴት ዘነጉት? ምግብ እኮ የህልውና መሰረት ነው በአካል ለመዳበር፣ አእምሮን ለማጎልበት፣ የማስታወስና የማሰብ አቅምን ከፍ ለማድረግ የታመቀውን የተፈጥሮ አቅም ለማውጣት የሚያግዝ ነው። በጣም የሚገርመው ደግሞ ቢወደውም ጥቅሙን ቢረዳውም እንኳ አልሚ ምግብ አግኝቶ ሳይሆን በተገኘው ምግብ ሆዱን ሞልቶ የሚያድር እንኳን በሌለበት ሀገር ውስጥ ለሚገኝ ሕዝብ በረሀቡ ላይ ሆዳም የሚል የስድብ ምርቃት ማከሉ አሳዛኝ ነገር ነው። ምክርም ይሁን ግልጽ ዓላማ የሌላቸው ጽሁፎች መጻፉ ግቡ ኢትዮጵያን ለሚያዋርዱት ‘ምሁራዊ’ ድጋፍ መስጠት ብቻ ይመስለኛል።

 
በምግብ አብዝቶ መብላትና ሲያመነዥጉ በመዋል የሚታወቁት የሌሎች አገሮች ዜጎች ናቸው። ይህንን የማያውቅ ከመንደሩ አለፍ ብሎ የማየት እድል ያልገጠመው ሰው እንጂ እንደ ፕሮፌሰር አውሮፓ ኤዥያና ሰሜን አሜሪካን ያሰሰ ሊሆን አይችልም። ለዚያውም ባንድ ወገን ሆዳምና አይነቱና ብዛቱ ወደር የማይገኝለት ምግብ ስለመብላቱ የሚነገርለት ሕዝብ በሌላው የፕሮፌሰሩ ፅሁፍ ለማኝነቱንና አምላክ ደድብ ያለው ሥራ-ጠልነቱ ይበሰርለታል። አንዱን ፅሁፋቸውን ከሌላኛው ማገናኛ ድልድዩ ምን ይሆን ያሰኛል። ለማኝ እኮ አጣጥሞና አማርጦ ለመብላት ያልታደለ ምርጫ አጥ ነው። ሥራ ጠልቶና ለምኖ አማርጦ መብላት ከተቻለማ ኢትዮጵያችን መና ከሰማይ የሚዘንብባት ሁናለች ማለት ነው።

 
ኢትዮጵያዊም ሆነ ሌላው በገበታ ዙሪያ የሚሰባሰበው ለመብላት ምክንያት በመፈለግ አይደለም፤ ምግቡ የመገናኛው ማጣፈጫ እንጂ። ሰርግም ሆነ መልስ፣ ልደትም ሆነ ተዝካር፣ ፋሲካም ሆነ እንቁጣጣሽ በጋራ ገበታ መቀመጥ መሰረታዊ ምክንያቶቹ ማህበራዊ ግንኙነቶች ናቸው። የሰው ልጅ ማህበራዊ እንስሳ ነው። አብሮነቱን ካላዳበረ ተነጣጥሎ ይሞታልና የትኛውም ማህበረሰብ በየትኛውም የዓለም ጫፍ ቢኖር በራሱ መንገድ ይሰባሰባል። አብሮ ያድናል፣ ተጋግዞ ያርሳል፣ ፈረቃ ገብቶ ያመርታል። ያንን ውበት ለመስጠትና አብሮነቱን ለማሳመር ደግሞ በጋራ ገበታ ይቁዋደሳል። ታዲያ ለምንድን ነው ኢትዮጵያውያን አብረው መብላታቸው ልዩ እንከን ተደርጎ የሚቀርበው? እንዲያውም ኢትዮጵያውያንን ሰብስቦ የያዘው ጠንካራ ድር ቢኖር እንዲህ ያለው በደስታና በሀዘን አብሮ መሆኑ ነው። አብሮ ያቆመን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ባህላዊ እሴት እንደ ሁዋላ ቀርነትና ሆዳምነት ሲቆጠር ስቆ ማለፉ የሚያስከትለውን እራስን የማዋረድን ጣጣ ልብ ያለማለት ነው። ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆዩ በአብዛኛው ከሀይማኖት ጋር የተገናኙ አሰባሳቢና አገናኝ በዐላት አሏቸው። በለጸጉ የሚባሉት አገሮች ደግሞ ከሀይማኖታዊ በአላት በተጨማሪ ለንግድ የሚመቹ አዳዲስ በዐላት እየፈጠሩ አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበትን መንገድ ፈጥረዋል። የእናት ቀን፣ የአባት ቀን፣ የፍቅር ቀን፣ የምስጋና ቀን እያሉ አብረው ይበላሉ ይጠጣሉ። ስለዚህም ኢትዮጵያውያንን አብረው በመብላታቸው ሆዳም የሚላቸው በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ትንሽም ቢሆን ጥናት ያላደረገ ብቻ ነው።

 

ከዚህ ቀደም እንደ ጻፍኩት ኢትዮጵያውያንን ‘አበሻ’ ባልል እመርጣለሁ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለማሳነስ በርካቶች አበሻ የሚል ስያሜ ላይ በመንጠልጠል መጥፎና ደካማ የሆነውን ነገር ሲያጎሉ ማየት እየበዛ ነው። ‘አበሽ’ የሚለውን የንቀት መሰል አጠራር የሚጠቀሙትም እነማን እንደሆኑ እናውቃለንና ኢትዮጵያ እያልኩ እቀጥላለሁ። እናም ክቡር ፕሮፌሰር የአለም ሕዝብ ከእንቅልፉ ተነስቶ ማዛጋት ሲጀምር ነቃ የሚያደርገውን ቡና…. ፓስታና ማኮሮኒ እያማረጠ የሚበላበትን ስንዴ…. ‘ግሉቲን’ ሆዱን እየነፋው ፊቱን እያዠጎረጎረ የሚያስቸግረውን ሕዝብ ጤናማ የሆነ እሹኝ ፈትጉኝ የማይለውን ጤፍ ጠገብ ሲል ደግሞ የበላውን የሚያወራርድበትን ጥሙን የሚያስታግስበትን ገብስ ለአለም ያበረከተው “ሰነፍ፣ ሆዳምና ለማኝ” እየተባለ የሚዘለፈው የኢትዮጵያ ገበሬ ነው። የሀገሬ ገበሬ ጀምበር ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ የሚተጋ ጠዋት ያሟሸውን አፉን ማታ ባገኛት እፍኝ እህል እየዘጋ የሚኖር ነው። ይህ ደግሞ ከሰማንያ በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያንን ይወክላል። ይህ ወገንዎ ክብር እንጂ ስድብ፣ ሙገሳ እንጂ ውርደት አይገባውም። በምንም መልኩ ኢትዮጵያውያንን እርሶንም ጨምሮ እግዜር በጆሮአችንን አታስቡ ብሎ መርጦ አላደደበንም። ያንን ስድብ ተቀብለው የሚኖሩ ደደቦች ካሉ ምህረቱን ያውርድላቸው። ሀገራችንን ለማጥፋት የሚያዋርዱን በቂ ጠላቶች አሉንና እራሳችንን በማዋረድ ለጠላት ስራውን አናቅልለት።

 
ኢትዮጵያውያንን ከሀገራቸው ውጪ የሚያሳዩትን የስራ ፍላጎትና መነሳሳት ለመመልከት እድል ላገኙ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ሀገሬውንም ሆነ ሌሎቹን መጤዎች በልጠው ሲተጉና ውጤትም ሲያመጡ እንጂ ሰነፍ በመሆን ከሌላው አንሰው አያዩም። ስለዚህ በጅምላ ኢትዮጵያውያንን ስራጠል ሰነፍ አድርጎ መኮነኑ ውሃ አያነሳም። ኢትዮጵያውያን ስራጠል ከሆኑ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ስለምን ወደ አረብ አገር ሊሄዱ ቻሉ? ለልመና ነበር? ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን በተሰደዱባቸው ሀገራት በአውሮፓና አሜሪካ በአፍሪካ ሀገራትም እንኳን የሚታወቁት በስራ አይደለምን? ባዶ እጃቸውን ከሀገር ወጥተው አዲስ ሀገር ውስጥ ኑሮ መስርተው ከብረው ለመኖር የቻሉት በአስማት ነውን? ስለዚህ ፕሮፌሰሩ እነዚህ በአንዲት ጀንበር ዘርፈው የከበሩ ነጣቂዎችን መንግስት ብለው መንግስት አንደተቀበለው ቻይና እንዳረጋገጠው ብለው ስንፍናችንን ሲደመድሙ የፌዘኛ እንጂ ምሁራዊ ትችት አይመስልም። አንድን በይሉኝታና በፈሪሃ እግዚአብሄር (አምላክ) የሚኖርን ሕዝብ አዕምሮና ሕሊና ቢስ የሚል ሰው እውን ሕሊናና አእምሮ አለው ብሎ መገመትስ ይቻላልን?
ኢትዮጵያውያንስ እንዴት ሁኖ ነው በሆዳቸው ነው የሚታወቁት የተባለው? ኢትዮጵያውያን ተጋብዘው ድግስ እንኳን ሲሄዱ “ቤታቸው ምግብ የለም እንዴ” ላለመባል እቤታቸው በልተው የሚሄዱ ናቸው። ነፃ ምግብ አለ ሲባሉ ለሳምንት የሚበቃ ቀለብ በሆዳቸው ለመጫን የሚዳዳቸው ሌሎች አንጂ ኢትዮጵያውያን አይደሉም። ኢትዮጵያዊውማ ከሆዴ ይልቅ ክብሬ በማለት እርቦትም አሁን በላሁ ነው የሚለው።

 
ሰዎች ይህንን ስራ ከምሰራ ለምኜ እበላለሁ የሚሉበት ዘመንም ከነበረ በትንሹ ግማሽ ምዕተ አመትን አሳልፏል። ይህም ክስ እውነት እንኩዋን ቢሆን ኢትዮጵያውያንን ለይቶ ከንቱና ርካሽ የሚያደርግበት ምንም ሚዛን የለም። በየትኛውም የአለም ክፍል ቢሆን በአንድ ወቅት የተናቀ ስራ ነበር። ዛሬም ቢሆን ይህን ከምሰራ ዌልፌር ምን አለኝ ብሎ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ ስንት ፈረንጅ በየሀገሩ አለ። ሌላም አንድ እውነት አለ፣ ሰዎች ከልምዳቸው ውጪ የሚመጣን ነገር የመቀበል ፍላጎታቸው ውሱን ነው። ለምሳሌ ከብት አርቢዎች እርሻን በንቀት ይመለከታሉ። አንዳንድ ከብት አርቢዎች ለምን እነደዚህ ያለ ስራ አትሰሩም የሚባል ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሲቀርብላቸው የኛ ዘሮች ይህንን አይሰሩም ይህን የሚሰሩት ሌሎች ናቸው ይላሉ። አንጥረኞች፣ አዝማሪዎች፣ ነጋዴዎች ሁሉም የለመደውን ስራ አጥብቆ መያዝ የኢትዮጵያውያን ብቻ ባህሪይ አይደለም። እንዲያም ሆኖ ኢንጅነሮች፣ የሙዚቃ ጠበብቶች፣ ዶክተሮች የመንግስት ተጡዋሪ ላለመሆንና ለቤተሰባቸው የተሻለ ህይወት ለመስጠት ስራ ሳይንቁ ከጠዋት እስከማታ መኪና በመጠበቅ፣ ታክሲ በመንዳት፣ ዘበኛ በመሆን፣ ጽዳት ሰራተኛ በመሆን ይዳክራሉ። እንዴት ነው ይህን ህዝብ ስራጠል አድርጎ መኮነን የተቻለው?

 
በሀገራችን ያለጥናትና በቂ መረጃ በምሁሩ ምክር የሰው ንብረት መውረስና ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥፋት በስመ ሶሻሊዝም በተፈጸመበት ጊዜ የተመለከትነው አንድ እውነት አለ። ሁለት ስራ መስራት አድሃሪነት ነበር ገንዘብ መያዝና ፈጠራ ወንጀል ነበር። ሶሻሊዝምን ያመጣውና መስራትንና መክበርን ወንጀል ያደረገው ተማርኩ ያለው ወገን የመረጠው የሶሻሊዝም መንገድ ነበር። እንዲያም ሆኖ በአዋጅ ሰዎች ድህነትን እንዲቀበሉ በተደረገበት ጊዜ እንደ አቅምቲ ከበርቴ ተብለው ሀብት ንብረታቸው እየተዘረፈ ሰዎች ወደ እስርቤት በተጋዙበት ጊዜ አዲስ አበባ የተከፈቱ ምግብ ቤቶች (ኢድዩ ቤቶች)፣ ባልትና ቤቶች ሁሉ ሕዝባችን ችግሩን ለማሸነፍ ምን ያህል የሚፍጨረጨር እንደነበረ የሚያስመሰክር ታሪካዊ ወቅት ነበር። እነዚያ “እመቤቶችና ወይዛዝርቶች” ሆቴል ቤት ከፍቼ ለማንም ከማስተናግድ ልመና እመርጣለሁ አላሉም።

 
ኢትዮጵያውያኖች ለማኞች መሆናችንን ፕሮፌሰር በተለያየ ምሳሌም አስቀምጠዋል። መንግስትን መጠየቅን፣ ሰውን መማለድን (ድርድርን)፣ ትህትናንና ሰላማዊነትን ፕሮፌሰር በልመናነት መድበውታል። እውነታው ግን እነኚህ ባህሪያት አስተዋይነትንና ህግ አክባሪነትን ነው የሚያመለክቱት። ሁሉንም በጉልበት የሚያስፈጽም ማህበረሰብ በሰላም መኖርም አይችልም። በርካታ ታጋዮች የኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክል በማለት የተለየ አመለካከት ባሳየው ላይ ተከታታይ በደልን በመፈጸማቸው ሰዉ ክፉኛ እንዲሸማቀቅ ተደርጎአል። ነገርግን ሕዝቡ የለማኝ ባህሪ ተጠናውቶታል ብሎ መደምደም ከባድ ስህተት ነው። ፕሮፌሰር ደግሞ ሰላማዊ ትግል ብቻ የሚሉ እንደመሆናቸው መጠን ዘራፍ ብሎ ለዱላ ከመጋበዝ ይልቅ መንግስትን በጥሞና መማለድን የሚደግፉ ኢንጂ እንዴት የሚኮንኑ ሊሆኑ ይቻላቸዋል?

 

የመጽዋችና የተመጽዋች ግንኙነት ያለው ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። ምክንያቱም ያለውና የሌለው በየሀገሩ ነው ያለው። ያለው ደግሞ ለተቸገረው መቸርን የማያውቅ ከሆነ በሰላም ወጥቶ መግባትም አይቻልም። ከመለመን ይልቅ በጉልበት ቀምተው የሚወስዱ ነጣቂዎች የበረከቱበት ሀገር ይሻላል የምንል ካለን የማሰብ አቅማችን ተናግቶአል ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን ካላቸው ላይ ቀንሰው ለሌላው መስጠታቸው የስነምግባርና የሞራል ባለጸጋ መሆናቸውን ያመለክታል እንጂ ልመናን የሚያበረታቱ ሰነፍ ማምረቻዎች አያሰኛቸውም። ጧሪ ያጡ አዛውንቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ህመምተኞች በመሆናቸው ስራ ማግኘት የማይችሉና ጤነኛም ሆነው ስራ ማግኘት ያልቻሉ መለመን ሊገደዱ ይችላሉ። ይህ ሰነፍ አያስብላቸውም። ባደጉት ሀገራትም የ ‘ዌልፌር/ድጎማ’ አሰራር አላቸውና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የተለያዩ እርዳታዎችን ይለግሳሉ። ይህ መንግስታዊ ድጋፍ በሌለባት ኢትዮጵያ ወገን ወገኑን መርዳቱ አስፈላጊና የሚደነቅ እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ይህንን የመረዳዳት ባህል ባያሳድጉ ኖሮ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በተበተነ ጊዜ መሳርያውን ተሸክሞ ሰለ እግዚአብሄር ውሀ ስጡኝ ብሎ ባልጠየቀ ነበር። ተደራጅቶ መዝረፍ ሲችል ወርቅ ቤት ተደግፎ የሚለምን በዲሲፕሊን የታነጸ ጦር ኢትዮጵያ ብቻ በመኖሩ ጨዋና ህግ አክባሪ ያደረገንን ባህል ልናመሰግን ይገባል። ከዚህም ባሻገር ‘ልመና’ የሌለበት አገር የለም። አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ወይም ኤዥያ በውበቱ ከሚያፈዝ ህንጻ ስር ቆቡን ዘርግቶም የሚለምን ሆነ ፕሮፌሰር እንደጠቅሱት የድሬዳዋ ለማኝ ብር ስጠኝ እያለ እንደማዘዝ የሚያደርገው ለማኝ ሞልቶዋል።

 
ልመናና ጸሎት ተመሳሳይ ትርጉም ከተሰጣቸው ደግሞ ሁሉም አገሮች ውስጥ ጸሎት አለና ልመናው አለምን አስጨንቆአል ማለት ነው። ድርድርም ልመና ከተባለ በትህትና የቀረቡ ጥያቄዎች ሁሉ ልመና ይደረጋሉና ጨዋነት እንደክፉ ባህሪ ሊታይ ነው ማለት ነው። ላሊበላነትም የልመና መስክ ሆኖ ተተችቷል። ነገር ግን ዘፋኝ ሲዲ አሳትሞ ለገበያ ሲያቀርብ ለማኝ አንለውም። አዝማሪዎችና ላሊበላዎች ደግሞ ዛሬ ላለው ኪነታዊ ጥበብ መሰረቶች ናቸው። ስለምን የቀድሞውን ነገር ሁዋላ ቀርና እርባና ቢስ እንደምናደርግ አይገባኝም።
የቆሎ ተማሪ በልመና ስለተለከፈ አይደለም የሚቀፍፈው። የሀገሬ ባላገርም የትምህርትን አስፈላገነት ስለተረዳ ካለችው ቆንጥሮ ያካፍላቸዋል። ፕሮፌሰርም ሲማሩ የተሰጣቸው መማርያ፣ የጠጡት ወተትና ልብሳቸውን ያጠቡበት ሳሙና እንደ ቆሎ ተማሪዎች ሰለ ማርያም ብለው ቆዳ ለብሰው ቀፈፋ ባይዞሩም ያው ከንጉሱና ከህዝቡ ቀፈፋ ነበር። እኛ ካልቻልንበት ያልቻልነውን በመጠቆም ማሻሻል እንጂ ያለፈው ትውልድ በቻለውና ባወቀበት መንገድ ሰርቶ ያቆመልንን አገር ማዋረድ ወንጀል ነው።

 
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የቆመችው ባሉን ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ነው። የድሮውን አሳድጎ ዘመናዊ ማድረግ ወይም የተኮረጀውን ከሀገር አስማምቶ ጥቅም ላይ ማዋል ስላቃተን የነበረውን ስንወነጅል ልንኖር አይገባም። አገርን በጅምላ ስንወነጅል ራሳችን የምናበረክተውን እንገምግም። ራስን እያዋረዱ ክብር መሻት ሞኝነት ነው። ከልመና ለመውጣትና ገበና ለመሸፈን አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት እንዲፈጠሩ ማበረታት ያሉትንም ማጠናከር እንጂ ወገን በሀዘኔታ ካለችው ላይ ስለሰጠ የተቸገረም ስለለመነ ማውገዙና በሽሙጥ መውገር ምን ይረባናል? ማንም በእርግጠኛነት ሊናገር የሚችለው ኢትዮጵያውያን ለማኝ፣ ሆዳምና ሥራ-ጠል ሳይሆኑ ዘመናትን የሚሻገር ባህልን ያሳደጉ ሲቸገሩ ተረዳድተው ሲመቻቸው አብረው ተደስተው የሚያኖራቸውን ባህል ያቆዩ ታታሪ ሰራተኞችና የሚረዳዱ መሆናቸውን ነው። የእውቀት መነጽራችን ይህንን ላላስመለከተን መቃወምና መንቀፍ ብቻ የእውቀት ምልክት የሚመስለን ህዝብን ከመስደቡ ብንታቀብና የማስተዋል አቅማችንን ብናዳብረው ይበጃል።

 
ሀገር አዋራጅ መሰረተቢስና ውልየለሽ ጅምላ ስድብን እውነት ነው ብሎ መቀበል ተቀብሎም ስድቡ ይገባናል በማለት እየተቀባበሉ መሰዳደብ ትክክል አይደለም። ስለዚህም በተከበሩ ፕሮፌሰር ስለተጻፈ ብቻ እንደታላቅ ግኝት በየሚዲያው ማሰራጨቱም “ሞኝን አንዴ ስደበው እራሱን ሲሰድብ ይኖራል” የሚለውን ብሂል በተግባር ማዋል ይሆናል። ኢትዮጵያንና በልጆቿ እየተሸረሸረ ያለውን ኢትዮጵያዊነትን እናድን ዘንድ እንትጋ።

 
comment_stage_5biyadegelgne@hotmail.com

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>