በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 58 ላይ ታትሞ የወጣ
ባለትዳር ነኝ፡፡ ከባለቤቴ ጋር ትዳር የመሰረትነው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀን ስራ እንደጀመርን ነበር፡፡ ባለቤቴ እጅግ ሲበዛ ዝምተኛ፤ እና አይን አፋር ነች፡፡ በታማኝት እና በፍቅር በቆየንባቸው ዓመታት ‹‹ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈፀም የለብንም›› የሚል አቋም ስለነበራት እስከምንጋባ ድረስ ቃሏን ጠብቄ ቆይቻለሁ፡፡ ወደ ትዳር ከገባን በኋላ ግን ባለቤቴ ወሲብ ለመፈፀም ያላት ፍላጎት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ወሲብ ከመፈፀም በኋላ የደስታን ስሜት ሳይሆን የመከፋት መንፈስ ነው የሚታይባት፡፡ ወደ ትዳር እንደገባን ባሉት አንድ እና ሁለት ዓመታት ጥሩ የሚባል የትዳር እና ፍቅር ጊዜ የነበረን ቢሆንም ወሲባዊ ህይወትን ግን ከጀመርን በኋላ አስደሳች እና ጣፋጭ ባለመሆኑ የተነሳ ሁልጊዜ አዝን ነበረ፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታትም ከቀን ወደ ቀን የባለቤቴ የወሲብ ፍላጎት መቀነስ እና ደስተኛ አለመሆን እያሳሰበኝ መጥቷል፡፡ በትዳራችንም ላይ የመቀዛቀዝ ስሜትን ፈጥሯል፡፡ አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፤ እኔ እንደምወዳት ሁሉ እሷም ትወደኛለች፡፡ የተፈጠረባት የወሲብ ፍላጎት መቀነስ ችግርን በተመለከተ በግልፅ ለማውራት ፍቃደኝነት ብዙም አይታይባትም፡፡ የወሲብ ጥያቄ ገና በማነሳባት ወቅት የመረበሽ፣ የመደንገጥ እና የመፍራት ስሜትን ስለምታንፀባርቅ እኔም እረበሻለሁ፡፡ በአንድ ጊዜም ፍላጎቱን አጣዋለሁ፡፡ የነገሩ መደራረብ እና መደጋገም እኔን ከትዳሬ ውጪ እንድመለከት እያደረገኝ ሲሆን የወሲብ ፍላጎት ከእኔ እንጂ ከእሷ መጥቶ አያውቅም፤ በእኔው ግፊት በወር አንዴ ወይንም ሁለቴ ግንኙነት ብንፈጽም ነው፡፡ በግልጽም ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላት ነግራኛለች፤ የሚገርመው ነገር እናቷም የተመሳሳይ ችግር ተጠቂ ነበሩ፡፡ ሁኔታው እጅግ እያስፈራኝ ስለሆነ እና ለትዳራችንም አደጋ ስለሆነ መፍትሄ ነው የምትሉትን ነገር ጠቁሙኝ፤ እኔም ምን ማድረግ እንዳለብኝ ምከሩኝ፡፡ ፋንታሁን ነኝ
የዶ/ር ዓብይ ዓይናለም ምላሽ፦ ውድ ጠያቂያችን ፋንታሁን በቅድሚያ ችግርህን ገልፀህ ከዘ-ሃበሻ ጋር ለመመካከር ስለወሰንክ እናመሰግናለን፡፡ በመቀጠል ወደ ጉዳይህ ስንገባ በትዳር አጋርህ ላይ የተፈጠረው የወሲብ ፍላጎት መቀነስ ብሎም መጥፋት እንዳስጨነቀህ እና እንዳሳሰበህ ምንም እንኳን እናንተ ብትዋደዱም በመሀከላችሁ የተፈጠረው ችግር ሊለያያችሁ እንደሚችል ያለህን ስጋትህን ገልፀሀል፡፡ ውድ ጠያቂያችን ፋንታሁን በቅድሚያ አንድ ነገር ተገንዘብ፡፡ ይህ አይነቱ ችግር የአንተ እና የባለቤትህ ችግር ብቻ ሳይሆን የበርካታ ባለትዳሮች ችግር መሆኑን፡፡ ሌላው በቅርቡ በእስራኤል ሀገር በኢየሩሳሌም ዩኒቨርሲቲ በተደረገ አንድ ጥናት ወሲብ የመፈፀም ፍላጎት ከሰው ወደ ሰው የተለያየ መሆኑን እና በተፈጥሮ አንዳንድ ሰዎች ከፍ ያለ ወሲባዊ ፍላጎት ሲኖራቸው ሌሎች ደግሞ አነስተኛ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎትን ይዘው ይወለዳሉ፡፡ በዚሁ ጥናት ላይ በተደረገ ፆታዊ ንጽጽሮሽም ሴቶች ከወንዶች ያነሰ ወሲባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ተደርሶበታል፡፡ ይሁን እንጂ የአንተ ባለቤት ላይ እንደሚታየው አይነት ዝቅተኛ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎት (ሴክሽዋል ዲዛየር) በእንግሊዝኛ ሀይፓ አክቲቭ ሴክሽዋል ዲዛየር ዲስኦርደር በመባል የሚታወቅ ሲሆን ዋነኛ መገለጫውም ምንም አይነት አካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ ችግር ሳይኖር ወሲባዊ ፍላጎትን ማጣት እና በወሲባዊ እንቅስቃሴ ምንም አይነት የደስታ ስሜት ያለመስማት ይልቁኑ፣ በተግባሩ የመረበሽ ስሜትን ማስተናገድ ነወ፡፡ ይህንን መሰል ስሜት በርካታ ሴቶች በተለያየ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ የሚያስተናግዱት ሲሆን በአንዳንድ ሴቶች ላይ መጠኑም ሆነ የጊዜ ርዝማኔውም ከፍ ያለ ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ይህ አይነቱ የወሲብ ፍላጎት መጥፋት እንደ ችግር አይቆጠርም ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የስነ ወሲብ ባለሞያዎቹ ዊልያም ማስተር እና ቨርጂኒያ ጆንሰን ጥናት እና ምርምር ካካሄዱ በኋላ ግን እንደ ችግር ትኩረት እያገኘ የመጣ፡፡ በተመሳሳይ ሄለን ሲንገር ካፕላን በተባለች የስነ ወሲብ ባለሞያ አማካኝነት በተደረገ ጥናት ወሲባዊ ፍላጎት (ሴክሽዋል ዲዛየር) በወሲብ ዑደት ውስጥ ወሲባዊ ፍላጎት (ሴክሽዋል ዲዛየር) በወሲብ ዑደት ውስጥ ከመነቃቃት፣ ከእርካታ እና ወደነበርንበት ቦታ ከመመለስ (Arousal, orgasm and resolution) በፊት የሚከሰት የዑደቱ የመጀመሪያው ክፍል መሆኑን ጠቅሳለች፡፡ ስለዚህ በውስጣችን የወሲባዊ ፍላጎት መፈጠር በወሲባዊ እንቅስቃሴ ዑደት ውስጥ የመጀመሪያው እና ወሳኙ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አንተ ባለቤት ወሲባዊ ፍላጎት ከነጭራሹ ማጣት በእንግሊዝኛ ሀይፓ አክቲቭ ሴክሽዋል ዲዛየር ዲስኦርደር የሚባል ሲሆን፣ ዋና መገለጫውም ምንም አይነት አካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ ችግር ሳይኖር ወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ ወይንም መጥፋት ሲሆን፣ ይህን አይነት ስሜት የሚያስተናግዱ ሴቶች ወሲብ መፈፀምን ሲያስቡ እሱን ተከትሎ የሚመጣው ደስታ ሳይሆን የሚያስቡት የሚሰማቸውን ህመም እና የሚመጣባቸውን ጥሩ ያልሆነ ትውስታ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሁልጊዜ የወሲብ ጥያቄ ሲቀርብላቸው የመከፋት፣ የመደበር እና የመነጫነጭ ስሜትን ያንፀባርቃሉ፡፡ በዊልያም ማስተር እና በቨርጂኒያ ጆንሰን አማካይነት የተደረገው ጥናት እንደሚጠቁመው የወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ ችግር ሶስት አይነቶች አለው፤ እነሱም፡-
- በህይወት ዘመን ውስጥ ዘላቂ እና አጠቃላይ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎት ማጣት
ይህ አይነት ችግር ያለባት ሴት ዝቅተኛ ወይንም ምንም አይነት ወሲባዊ ፍላጎት የላትም ኖሯትም ላያውቅ ይችላል፡፡
- ከጊዜ በኋላ የተፈጠረ እና ቦታ ለይቶ የሚጠፋ ወሲባዊ ፍላጎት፣
ይህ አይነቱ የወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ ጤናማ የሚባል ወሲባዊ ባህሪ የነበራት ሴት ከጊዜ በኋላ ከትዳር አጋሯ ጋር ወሲብ የመፈፀም ፍላጎትን ታጣዋለች፡፡ ከሌላ ሰው ጋር ግን የመፈፀም ፍላጎት ሊኖራት ይችላል፡፡
- ከጊዜ በኋላ የተፈጠረ እና አጠቃላይ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎት ማጣት፣
ይህ አይነቱ ወሲባዊ ፍላጎት የማጣት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጠር እና ቦታ እና ጊዜን ሳይለይ ሙሉ ለሙሉ ፍላጎት ማጣት ነው፡፡
ውድ ጠያቂያችን ፋንታሁን ከላይ ከተዘረዘሩት የወሲብ ፍላጎት መቀነስ አይነቶች በመነሳት ባለቤትህ በየትኛው ምድብ ውስጥ እንዳለች እወቅ፡፡ ሌላው ስለ ሴቶች ወሲባዊ ባህሪ ማወቅ ካለብን በርካታ ነገሮችን መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነገር ሴቶች እንደ ወንዶች በፍጥነት ወሲባዊ ፍላጎታቸው አይነሳሳም፣ ሌላው ሴቶች ወሲባዊ እርካታን ማስተናገድ የሚጀምሩት በስጋዊ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት በሚደረጉት ጨዋታዎች እና አካላዊ መቀራረቦች ጭምር ነው፡፡ ውድ ጠያቂያችን ፋንታሁን በቀጥታ ወደ አንተ ባለቤት ጉዳይ ስንመጣ በባለቤትህ ላይ የሚታየው የወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህን ምክንያቶች በአራት ዋና ዋና ክፍል ማስቀመጥ እንችላለን፡፡
- ግለሰባዊ ችግር
- የመጣንበት ቤተሰብ ሁኔታ
- በጥንዶች መካከል ያለው የመቀራረብ ደረጃ
- የሌላ ጤና ችግር ተጽዕኖ
እነዚህን ዋና ዋና ምክንያቶች ሰፋ አድርጎ ለመመልከት ያህል፣ ግለሰባዊ ችግር በምንልበት ወቅት ከዚህ በፊት በነበረን ህይወት ከወሲብ መፈፀም ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የፍርሃት ስሜት፣ በተለያየ ምክንያት የሚከሰት የድብት ስሜትት የትዳር ወይንም ወሲብን አስመልክቶ የሚኖር የተሳሳተ እምነት፣ በራስ ያለመተማመን እና ለራስ ዝቅተኛ የሆነ ግምት መስጠት፣ የስራ ጫና እና የሀሳብ ብዛት በራሱ ወሲባዊ ፍላጎት መቀነስን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኃይል በተቀላቀለበት መንገድ የሚፈጠር ወሲባዊ ጥቃት እና ጥቃቱን ተከትሎ የሚፈጠር የስሜት ስብራትም ወሲብን ከዚያ መጥፎ አጋጣሚ ጋር በማስተሳሰር ስለወሲብ ጥሩ ያልሆነ ስሜትን ማዳበር ነው፡፡ ይህ ስሜት ደግሞ የወሲብ ፍላጎት መጥፋትን ሊያስከትል ይችላል፡፡
በተመሳሳይ የመጣንበት የቤተሰብ ይንም ያደግንበት ሁኔታም መሰል ችግርን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይ ያደግንበት ቤተሰብ ጥብቅ እና ሃይማኖታዊ ከነበረ እና ወሲብን እንደ ሐጢያት፣ እንደ እርከሰት እና አሳፋሪ እንደሆነ ነገር እንድንመለከት አድርገው ካሳደጉን ወሲብን የመጥላት እና ፍላጎት የማጣት ስሜት እንዲፈጠር ሊያደርገን ይችላል፡፡
በሌላ በኩል በጥንዶች መካከል ያለው የመቀራረብ ሁኔታም ወሲባዊ ፍላጎት መቀነስን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በጥንዶች መካከል ያለው መተሳሰብ፣ መከባበር እና መቀራረብ ከወሲብ የሚገኘውን የእርካታ ደረጃ ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ በጥንዶች መካከል ያለመከባበር እና የመናናቅ ስሜት ካለ፣ መተቻቸት እንዲሁም መከራከር እና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እና መሰል ጤናማ ያለሆኑ ግንኙነቶች ካሉ ፍቅርን የማሻከር ብሎም ወሲባዊ ፍላጎት መቀነስን ከፍ ሲልም የማጥፋት አቅም አላቸው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ በውስጣችን ወሲባዊ መነቃቃት እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑት ሆርሞኖች በተለያዩ የጤና ችግሮች የተነሳ ምርታቸው መቀነስ እንዲሁም ለተለያዩ ህመሞች ተብለው የሚወሰዱ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳትም የወሲብ ፍላጎት የመቀነስ ችግርን ሊከስት ይችላል፡፡
ውድ ጠያቂያችን፡- ፋንታሁን የወሲብ ፍላጎት መቀነስ በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ አነስተኛ ይሁን እንጂ ይከሰታል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው አራት ዋና ዋና ምክንያቶች በተለይ በሴቶች ላይ የወሲባዊ ፍላጎት መቀነስን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆን፣ የፍላጎት መቀነሱ ወይንም መጥፋቱ ጊዜው አሊያ ዘላቂ ሊሆን የሚችል ሲሆን አንዲት ሴት ግን የዚህ ችግር ተጠቂ ነች ብሎ ለመደምደም የሚከተሉት ባህሪያት መስተዋል አለባቸው፡፡ የመጀመሪያው የወሲብ ፍላጎት መጥፋቱ ጊዜን እና ቦታን ሳይለይ ሁልጊዜ የሚከሰት ከሆነ፣ ሌላው ወሲብ ለመፈፀም ውስጣዊ የሆነ ፍላጎት ቢኖርም እንኳን ሰውነት እና ወሲባዊ አካላት ለግንኙነት ዝግጁ ያለመሆኑ ዋና መገለጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች በስፋት ከታዩ ያቺሴት የዚህ ችግር ተጠቂ ነች ማለት እንችላለን፡፡
ወደ መፍትሄው ስንመጣ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው ወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ ወይንም መጥፋት በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች የሚከሰት በመሆኑ የተነሳ እንደ መንስኤው ሁሉ መፍትሄውም የተለያየ ነው፡፡ ምን አልባትም መፍትሄው የህክምና እና የስነ ልቦና ድጋፍን ያጣመረ ስለሚሆን የችግሩ ባለቤትም ሆነ የትዳር አጋሯ ጥንካሬን እና ከችግሯ ለመውጣት ያላትን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ህክምናን መሰረት ያደረገው መፍትሄ ስንመጣ ለድብርት ማስለቀቂያ ተብለው የሚሰጡ አነቃቂ እንክብሎች አዕምሮንም ሆነ አካልን የማነቃቃት እና ዘና የማድረግ ባህሪ ስላላቸው ወሲባዊ ፍላጎትን ከፍ የማድረግ አቅምም አላቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን መሰል መድሃኒቶች የወሲብ ፍላጎት መቀነስ ችግር ሲከሰት የሚሰጡም ናቸው፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ችግር ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ባለሞያዎችን ቀርቦ ማነጋገር የግድ ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ ወይንም መጥፋት በስነ ልቦና ባለሞያ አማካኝነትም ሊደገፍ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ አልፈለግም ከሚል እና ከመሰል ለራስ አነስተኛ ግምት ከመስጠት ጋር የሚገናኝ ችግርም ስለሆነ ለራስ የምንሰጠው ግምት እና ክብር ከፍ ባለ ቁጥር እየተስተካከለ ሊሄድ ይችላል፡፡ ስለዚህ የስነ ልቦና ባለሞያው ይህንን ሂደት ሊደግፍ ይችላል፡፡ ውድ ጠያቂያችን በጥንዶች መካከል ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ካለ ማለትም ያልተፈታ ቅራኔ፣ ግጭት ወይንም አለመግባባት ካለ በዚያ ባልተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሆነው ለግንኙነት መነሳሳት አስቸጋሪ ስለሚሆን የወሲባዊ ፍላጎ መጥፋት ይከሰታል፡፡ ስለዚህ በጥንዶች መካከል የተፈጠረን ቅራኔ ወይንም ግጭት ካለ በቶሎ መፍታት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወሳኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከላይ ወሲባዊ ፍላጎ መቀነስን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ስንዘረዝር ቀደም ባለው ህይወታችን ላይ የተፈጠረ እና ከወሲብ ጋር የተከሰተ መጥፎ አጋጣሚም የወሲብ ፍላጎት መቀነስን ስለሚያስከትል ስለአጋጣሚው በግልጽ በማውራት በዚያ አጋጣሚ የተፈጠረውን ፍርሃት እና የተሳሳተ እምነት ከውስጣችን እንዲወጣ ማድረግ አለብን፡፡ በግልፅ መነጋገር ሲባል ደግሞ በመወነጃጀል እና በጭቅጭቅ መንፈስ ሳይሆን በመረዳዳት እና ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኝነት በማሳየት መሆን ይኖርበታል፡፡