Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የሳምንቱ የአብርሃ ደስታ በፌስቡክ ላይ የተለቀቁ ምርጥ ጽህፎች

$
0
0

እኔ ምለው?!
——————

Abrha Desta‘የተምቤንና የዓጋመ ህዝቦች ባላቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዓቅም የህወሓት ስጋት በመሆናቸው ይጨቆናሉ’ ብዬ በፃፍኩት ላይ ‘አብርሃ ትግራይ በአውራጃዊነት ለመከፋፈል ፈልጓል’ የሚል መልእክት ያላቸው አስተያየቶች ደረሱኝ።

እንዴት ነው ግን አከባቢን ጠቅሰን ችግር አለ ብንል ‘መከፋፈል’ ይሆናል? ወይስ በሁሉም አከባቢዎች ተመሳሳይ ችግር አለ? በመቀሌ የእሳት ቃጠሎ ችግር ካለ በዓዲግራት የሱኳር አቅርቦት እጥረት ሊኖር ይችላል። በየ አከባቢው ያለ ችግር ለየግል ቢነሳ መከፋፈል ነው?

ስለ ተምቤንና ዓጋመ በደል ስፅፍ ለምን ይህን ሁሉ ካድሬ ለየት ባለ መልኩ ተንጫጫሳ? የመከፋፈል ችግሩ ከሌለ እኔ በፌስቡክ ስለፃፍኩት ብቻ ትግራይ ልትከፋፈል ትችላለች? ስጋቱና መጨናነቁ ከየት መጣ? ይሄ ሁሉ የሚንጫጫ የፃፍኩት ነገር እውነት በመሆኑ አይመስላችሁም?

ትግራይ ትንሽ ነች። እንኳን ትግራይ (ትንሽ) ታላቋ ኢትዮጵያም እንድትከፋፈል አልፈልግም። እንዳውም የኔ ጥረት የህወሓትን የመከፋፈል ስትራተጂ መቃወም ነው። እኔ ትግራይን በአውራጃዊነት የመከፋፈል ፍላጎቱም ዓቅሙም የለኝም። በኔ የምትከፋፈል ትግራይም የለችም፤ ምክንያቱም ትግራይ ከ1968 ዓም ጀምሮ በህወሓት ተከፋፍላለች። የተከፋፈለች ትግራይ እንዴት እከፋፍላታሁ?

አሁንኮ ሽሬ አውራጃ የለም። በህወሓት ተከፋፍሏል። ዓጋመ አውራጃ የለም፤ ተከፋፍላል። እንደርታ አውራጃ የለም፤ ተከፋፍሏል። እንደርታ አሁን አውራጃ ሳይሆን አንድ ወረዳ ብቻ ነው። ተምቤን አውራጃ የለም፤ ተከፋፍሏል። የአሁኑ ተምቤንም ለሁለት ተከፍሏል፤ ደጉዓ ተምቤን ወደ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ሲወሰድ ቆላ ተምቤን ግን በማእከላይ ዞን ስር ነው። ስለዚህ ተምቤን በሁለት የተለያዩ ዞኖች ነው የሚተዳደረው። ይህ በቅርቡ የተሰራ ተምቤኖችን የማዳከም ስትራተጂ ነው።

ስለዚህ ሁሉም የትግራይ አውራጃዎች በተበታተኑበት ወቅት እኔ የትኛው አውራጃ ነው የምከፋፍለው? ሁሉምኮ ተከፋፍሎ አልቋል። ያልተከፋፈለ ህዝብና አውራጃ እስቲ ንገሩኝ? ስለዚህ እኔ የምከፋፍላት ትግራይ የለችም፤ በህወሓት ተከፋፍላ አልቃለችና።

‘በሁሉም የትግራይ ክልሎች ጭቆና እያለ ለምን ተምቤንና ዓጋመ መረጥክ?’ ለሚለው ግን አስተያየት መስጠት ተገቢ ነው። አዎ! በሁሉም ቦታዎች ጭቆና አለ። የጭቆናው መጠንና ዓላማ ግን ይለያያል። በዓፋሮች ላይ የሚፈፀም ጭቆናና በአማራዎች የሚደርስ በደል ዓላማው አንድ ላይሆን ይችላል። ህወሓት የሽሬ ህዝብ፣ የሐውዜን፣ የእንደርታ፣ የራያ፣ የሑመራ፣ የኢሮብ፣ የአፅቢ፣ የዓድዋ፣ የአክሱም፣ የወልቃይት ወዘተ ህዝቦች ሲጨቁን ለመግዛት አልሞ ነው። የተምቤንና የዓጋመ ህዝቦች ሲበድል ግን ከመግዛት አልፎ ለስልጣኑ ስለሚያሰጉት ነው።

ሁሉም የትግራይ ህዝቦች በህወሓት የየራሳቸው የተለያየ ስም ወጥቶላቸዋል። በወጣላቸው ስምና ባህሪይ መሰረት አስተዳዳሪዎች ይላክላቸዋል። በተለያዩ አከባቢዎች የሚደርስ የተለያየ በደል ማንሳት ህዝቦችን መከፋፈል አይደለም።

ህዝቦች ሳነሳ ‘በአውራጃዊነት መከፋፈል ነው’ ካላች ሁኝ ግለሰቦችን ላንሳና ‘አብርሃ ትግራይን በግለሰቦች ደረጃ ለመከፋፈል እያሴረ ነው’ ብላች ሁ አስተያየት ለመስጠት እንዲመቻቹ።

በእንዳ አብርሃ ወ አፅብሃ አከባቢ የሚንቀሳቀስ ‘ዳደ’ የተባለ ሽፍታ ነበር። ህወሓቶች በጣም ይፈሩታል። ከደርግ ወታደሮች ጋር ለመፋለም ያልፈሩት የህወሓት ታጋዮች አንድ ግለሰብ ‘ዳደ’ ግን መድፈር አልቻሉም። እናም በስንት መከራ ህወሓቶች ትግራይን ከተቆጠጠሩ በኋላ ብዙ ወታደር ልከው ያዙት፤ ከዛ ግፍ በተሞላበት ተግባር አረዱት።

ህወሓቶች አንድ ግለሰብ ያስፈራቸው እንደነበር የምፅፈው አስፈላጊ ስለሆነ ሳይሆን ልክ የተምቤኖችና የዓጋሜዎች ያነሳሁት ያህል ‘በግለሰብ ደረጃ አትከፋፍለን’ የሚል አስተያየት ለመስጠት እንዲመች ነው። ታሪኩ ግን እውነት ነው።

ተምቤንና ዓጋመ
——————–

ስለ ተምቤንና ዓጋመ ህዝቦች አንስቼ ነበረ። ‘ግልፅ አይደለም’ የሚል አስተያየት ተሰጥቷል። አሁን ጉዳዩ ግልፅ ለማድረግ ግዜው አይደለም። ለመረጃ የሚሆን ግን እነሆ።

ከህወሓት የትጥቅ ትግል ወቅት ጀምሮ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ህዝቦች ዓቅሙ እያላቸው በህወሓት የተንኮል አገዛዝ ምክንያት ተጨቁነው (ታፍነው) የሚኖሩ ህዝቦች የተምቤንና የዓጋመ ናቸው። የተምቤን ህዝብ የፖለቲካ ዓቅም አለው። የዓጋመ ህዝብም የኢኮኖሚ ዓቅም አለው። ሁለቱም ህዝቦች (የተምቤንና ዓጋመ) መቀስቀስ ከተቻለና አብረው ከሰሩ መላው ትግራይ አንቀሳቅሰው ህወሓትን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ ይችላሉ። ህወሓት አሁንም የሁለቱም ህዝቦች መነሳት ያስፈራዋል። ተምቤኖች በፖለቲካ እንዳይሳተፉ ይደረጋል፤ ዓጋሜዎቹም በኢኮኖሚ እንዲዳከሙ ይደረጋል። ተምቤኖች እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ለዚህም ነው የህወሓት አስተዳዳሪዎች በተምቤን ለሚደረግ የስብሰባ ቅስቀሳ ለመረበሽ የተነሱት (የተምቤን አስተዳዳሪዎች የተምቤን ተወላጆች አይደሉም)። ህወሓት በተምቤንና ዓጋመ ምንም ድጋፍ የለውም። በጠመንጃ ሃይል ነው የሚገዛው።

‘ለውጥ የለም’?!
—————–

“አሁን ባለንበት ሁኔታ ‘ለውጥ የለም’ ብለን መከራከር እንችላለን?” አለኝ። በኢህአዴግ ዘመን የተገነቡ ህንፃዎችና አስፋልት መንገዶች ዋቢ በማድረግ ለውጥ መኖሩ የማይካድ እንደሆነ ሊነግረኝ ፈልጎ ነው።

ግን “ለውጥ የለም” ብዬ ማለት እችላለሁ። “ለውጥ የለም” ማለት ምን ማለት ነው? “ለውጥ የለም” ማለት ምንም የተሰራ ነገር የለም ማለት አይደለም። ለውጥ የለም ማለት ትምህርትቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ አስፋልት መንገዶች ወዘተ አልተገነቡም ማለት አይደለም። የመጣው ለውጥ ምን ያህል ነው? ባሁኑ ግዜ መታየት ያለበት ለውጥ ምን ያህል ነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ አለብን እንጂ ለውጥማ ሁሌ ይኖራል። ለውጥ ላይኖር አይችልም። ሁሌ ለውጥ አለ። ለውጥ የተፈጥሮ ሕግ ነውና።

እንኳን ግብር የሚሰበስብ፣ ደሞዝ የሚከፈላቸው ሰራተኞች ያሉት መንግስት እያለ ማእከላዊ መንግስት ባይኖርም ህዝብ እስካለ ድረስ ለውጥ ይኖራል። ጉዳዩ መሆን ያለበት … ለውጡ ምን ያህል ነው? ከዚህ በላይ ለውጥስ ማምጣት ይቻላል ወይ? በኢኮኖሚው ዘርፍ ለውጥ ካለ በፖለቲካውስ ለውጥ አያስፈልግም ወይ? ወዘተ ነው።

‘ለውጥ የለም ወይ?’ የሚል ጥያቄ ሲቀርብልኝ የማስታውሳት ነጥብ አለች። (ደግሜ ልፃፋት)። ባልና ሚስት ነበሩ። የቤት ሰራተኛ ቀጠሩ። የቤት ሰራተኛዋ በሆነ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ለባልና ሚስት ምግብ (ቁርስ፣ ምሳና እራት) እንድታዘጋጅ ተስማማች። ቤት ገባች። የመጀመርያው ቀን ቁርስ አዘጋጀች (ምሳና እራት አልሰራችም)። ባልና ሚስት ሆቴል ተጠቀሙ።

በሁለተኛው ቀን ምሳ አዘጋጀች (ቁርስና እራት የለም)። በሦስተኛው ቀን እራት አዘጋጀች (ቁርስና ምሳ የለም)። በአራተኛው ቀን ባልና ሚስት የቤት ሰራተኛዋን ጠርተው ምግብ እያዘጋጀች እንዳልሆነች ይነግሯታል። የቤት ሰራተኛዋም “እንዴት አልሰራም? ምግብ እየሰራሁ ነው” ብላ ትከራከራለች። ባል “ለምሳሌ ቁርስ ከሰራሽ ምሳ አትሰሪም፣ ምሳ ከሰራሽ እራት አትሰሪም” ይላታል። ሰራተኛዋ መልሳ “ሁሉም ሰርቻለሁ፤ የመጀመርያው ቀን ቁርስ አልሰራሁም? በሁለተኛው ቀን ምሳ አልሰራሁም? በሦስተኛው ቀን እራት አልሰራሁም? ሁሉም (ቁርስ፣ ምሳና እራት) ሰርቻለሁ” አለች።

ለሰራተኛዋ ምን መልስ አላቹ? ‘ቁርስ ወይ ምሳ ወይ እራት አልሰራሽም?’ አይባልም። ልንላት የምንችለው ‘ምግብ ማዘጋጀት ማለት በቀን ሦስቱም (ቁርስ፣ ምሳና እራት) ማዘጋጀት መቻል ነው’። ልንላት የምንችለው ‘ቁርስ አልሰራሽም’ ሳይሆን ‘በቀን መስራት የሚጠበቅብሽ ነገር አልሰራሽም። ስለዚህ የተቀጠርሺበት ምግብ የማዘጋጀት ስራ በአግባቡ እየተወጣሽ አይደለሽም። (ስለዚህ) አንድም ስራህሽን በአግባቡ ስሪ አልያም ደግሞ ዉጪና በቀን ቁርስ፣ ምሳና እራት ማዘጋጀት የምትችል ሌላ የቤት ሰራተኛ እንቁጠር’ ነው። (ሰራተኛዋ ኢህአዴግ ናት፤ ባልና ሚስት ደግሞ ህዝብ ናቸው)።

ኢህአዴግ ‘ለውጥ አምጥቻለሁ’ ሲለን ልክ እንደቤት ሰራተኛዋ ነው። ኢህአዴግ ለውጥ አላመጣም ስንል ምንም ዓይነት ለውጥ የለም ማለታችን አይደለም። እንደ መንግስት መስራት የሚገባውን እየሰራ አይደለም። ስለዚህ ሌላ ከኢህአዴግ በተሻለ መጠንና ፍጥነት መስራት የሚችል መንግስት ያስፈልገናል ነው ሐሳቡ።

ለውጥ ማእከላዊ መንግስት በሌለባት ሀገረ ሶማሊያም አለ። በሶማሊያ ለውጥ እየመጣ ስለሆነ መንግስት አያስፈልግም ወይም ሌላ ተጨማሪ ለውጥ አያስፈልግም ማለት ግን አንችልም። ሶማሊያ በኢንተርኔትና ቴሌፎን አገልግሎት አሰጣጥ ከኢትዮጵያ ትሻላለች። ኬንያና ሱዳን በመብራት ሃይል አገልግሎት ከኢትዮጵያ በደንብ ይሻላሉ። የኬንያና የሱዳን የገጠር ዜጎች ከኢትዮጵያውን በተሻለ ሁኔታ የመብራት አገልግሎት ያገኛሉ። ‘ኢትዮጵያ ለሱዳንና ኬንያ የኤለክትሪክ ሃይል ትሸጣለች’ ሲባል ገርሞኛል።

ኢህአዴግ የሰራው ነገር Physical Infrastructure ላይ ነው። ለምሳሌ የመንገዶች ግንባታ። የመንገድ ግንባታ የለውጥ መሰረት እንጂ በራሱ ለውጥ አይደለም። ምክንያቱም የአስፋልት መንገድ ግንባታው የለውጥ ዉጤት አይደለም። መንገዱ የተገነባው በሀገሪቱ በመጣ ዕድገት በተገኘ ካፒታል ሳይሆን በብድርና ባላስፈላጊ የገንዘብ ህትመት ምክንያት ነው።

የኢትዮጵያ አስፋልት መንገዶችና የባቡር ሃዲዱ ከየት በመጣ ገንዘብ ነው የሚገነባው? በብድርና በእርዳታ በተገኘ ገንዘብ ነው። ተበድረህ ገንዘብ አገኘህ ማለት ዕድገት አገኘህ ወይ ለውጥ አመጣህ ማለት አይደለም። (ግን ባግባቡ ተጠቅመህ በተበደርከው ገንዘብ ለውጥ ልታመጣ ትችላለህ፤ ሙስና ከሌለ ማለት ነው)። ኢህአዴግ የብድር ገንዘቡ ሲያቋርጠው ገንዘብ ያትማል። ገንዘብ ማተም ማደግ ወይ ለውጥ ማምጣት አይደለም።

በፖለቲካ ለውጥ የለም ሲባል ለውጡ በቂ አይደለም፣ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፣ ለውጥ እንፈልጋለን፣ ባለው ለውጥ አልረካንም ወዘተ ማለት እንጂ ምንም የተሰራ ነገር የለም ማለት አይደለም፤ ምንም ላይሰራ አይችልምና። ለውጥ ማስቆም እስካልተቻለ ድረስ ለውጥ ይኖራል።

በኢህአዴግ ዘመን ለውጥ አለ እንበል (እንተባበራቸው)። ለውጥ አለ እየተባለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ነው። ‘እኛ የምንፈልገው የኢኮኖሚ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ (የስርዓት) ለውጥም ያስፈልገናል’ ብንልስ? የኢኮኖሚ ለውጥ አስፈላጊ ነገር እንጂ የፖለቲካ ለውጥ የሚተካ በቂ መልስ አይደለም። የኢኮኖሚ ለውጥ ሲኖር የፖለቲካ ለውጥም ያስፈልጋል።

አንድ መንግስት በስልጣን ለመቆየት የሚያስፈልገው ነገር የኢኮኖሚ ለውጥ ማምጣት አንዱ ቢሆንም የፖለቲካ ተ አማኒነትም ያስፈልገዋል። ኢህአዴግ ‘መንገድና ባቡር ሃዲድ ስለገነባሁ በስልጣን መቀየት አለብኝ’ ብሎ ማለት የለበትም። የሀገረ አሜሪካ ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች በየአምስትና አስር ዓመት የሚቀያየሩ አንዱ ፓርቲ መንገድና ባቡር ሃዲድ መገንባት ስላልቻለ አይደለም። ከኢኮኖሚው ለውጥ በተጨማሪ የፖለቲካ ለውጥም ስለሚያስፈልግ ነው።

አሁን ካለው ለውጥ (ለውጥ አለ ብላቹ ለምትከራከሩ) የተሻለ ለውጥ ያስፈልገናል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>