የዓለም ዋንጫ በሰኔ ወር ይከናወን የፕላኔታችን እግርኳስ አፍቃሪ ምርጥ ስፖርታዊ ፉክክር በሚጠበቅበት ወቅት ብራዚል በፖለቲካዊ ተቃውሞና ትዕይንተ ህዝብ ልትናጥ ትችላለች፡፡ ይህን ያለው ሮማሪዮ ደ ሱዛ ፋሪያ ነው፡፡
ይህ ሰው ተራ ዜጋ አይደለም፡፡ እግር ኳስን ካልን በፒኤስቪ፣ ባርሴሎና እና ብራዚል ብሔራዊ ቡድን አንፀባራቂ ህይወትን ያሳለፈ የ364 ጎሎች ጌታ ነው፡፡ ዓለም ዋንጫንም ከጠቀስን የ1994ቱ ውድድር ኮከብ ጎል አስቆጣሪና ኮከብ ተጨዋች ተብሏል፡፡ ፖለቲካም ቢሆን የሮማንዮ አዲሱ ህይወት ይገልፀዋል፡፡ የ47 ዓመቱ ብራዚላዊ የሶሻሊስት ፓርቲ አባልና የፓርላማ አባል ነው፡፡ የተራው የብራዚል ዜጋ ምሬት የሚገባው ሰው በመሆኑም የዓለም ዋንጫው የብሶት መግለጫና የተቃውሞ መድረክ መሆኑ አይቀርም ይለናል፡፡ ውድድሩም በቀለጠ የተቃውሞ ሰልፍና ትዕይንተ ህዝብ እንዳይፈገግ የሮማሪዮ ስጋት ነው፡፡
ብራዚልና እግርኳስ ይዋደዳሉ፡፡ ሆኖም ፖለቲካዊ ውሳኔዎች በፍቅራቸው መሀል ነፋስ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ የብራዚል መንግስት የ2014ቱን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ 7.6 ቢሊዮን ፓውንድ ፈሰስ እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡ ሚሲዮኖች በድህነት ወለል ላይ መከራቸውን በሚቆጥሩበት ሀገር ከአንድ ወር ገደማ ቆይታ በኋላ ከፊታቸው ለሚሰወር ውድድር ይህን ያህል ገንዘብ ማፍሰስ የሃገሪቱን ብዙሃን ዜጎች የሚያሳምን አይደለም፡፡ ባለፈው ክረምት በተዘጋጀው የኮንፌዴሬሽንስ ካፕ ወቅት እንኳን 120 ሺ የተቃውሞ ሰልፈኞች ጎዳና ላይ ወጥተው ብሶታቸውን አሰምተዋል፡፡
የብራዚል መንግስት ከፊፋ ጋር ያለው ግንኙነት ሮማሪዮን የሚያስደስት አይደለም፡፡ ለዓለም ዋንጫው ዝግጅት የተመደበው በጀት ሊዋጥለት አልቻለም፡፡ የሀገሪቱ ህዝባዊ አገልግሎቶችን ሊጎዳ በሚችል መልኩ ገንዘብ መመደቡ ደግሞ አስቆጥቶታል፡፡ ‹‹ፊፋ እዚህ ብራዚል የሚመጣው ለገንዘብ ሲል ብቻ ነው፡፡ ኪሳቸውን ለማድለብ ካልሆነ በስተቀር ምንም ምክንያት የለውም›› ይላል ሮማሪዮ፡፡ ‹‹ብራዚል በከተሞቿ ተገቢ የትራንስፖርት አገልግሎት ይኑራት አይኖራት የፊፋ ጉዳይ አይደለም፡፡ የፊፋ ጭንቀት ስታዲየሞቹ ግንባታቸውን ጨርሰው በሰዓቱ ዝግጁ እንዲሆኑ ብቻ ነው፡፡
‹‹ዛሬ በብራዚል አዛዡ ማነው?›› ሮማሪዮ ይጠይቃል፡፡ ‹‹ፊፋ ነው፡፡ ወደ እዚህ መጥተዋል፡፡ ውድድሩን ያካሂዳሉ፣ ታክስ አይከፍሉም፣ ከዚያም ትርፋቸውን ያጋብሳሉ፡፡ በዓለም ዋንጫ የብራዚል ህዝብ አይጠቀምም፡፡ ፊፋ፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ስፖንሰሮችና ኮንትራክተሮች ብቻ ይጠቀሙበታል፡፡ ባለፈው ክረምት ግዙፍ ትዕይንተ ህዝቦች ጎዳናዎቻችንን በማጨናነቃቸው አልገረምም፡፡ ተመሳሳዩ እንደሚደገም እጠብቃለሁ፡፡ ሆስፒታሎቻችንና ትምህርት ቤቶቻችን የገንዘብ ችግር ላይ ናቸው፡፡ በማህበራዊ የኑሮ ደረጃ በመደቦች መካከል ሰፊ የልዩነት ርቀት ተፈጥሯል፡፡ እንዲህም ሆኖ ቢሊዮን ዶላሮችን በግዙፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ በማፍሰስ እያባከንን ነው፡፡ የዓለም ዋንጫም የመጀመሪያው ነው›› በማለት ሮማሪዮ ዓለም ዋንጫው ለብራዚል የሚሰጠው ፋይዳ እንደማይኖር በአፅንኦት ያስረዳል፡፡
ጋዜጠኛ እና የተቃውሞ አስተባባሪ የሆነው አልፎንሶ ሞራይሳ እንዲሁ ትዕይንተ ህዝብ ይኖራል ብሎ እየጠበቀ ይገኛል፡፡ በኮንፌዴሬሽንስ ካፕ ሰሞኑን የታየው ተቃውሞ ከሶስት ቀናት በኋላ ዓርብ በኮስታ ደ ሳውፔ ባህያ የዕጣው ድልድል ሲወጣም እንዲሁ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ይገምታል፡፡ የክፍለ ሀገሩ ዋና ከተማ ሳልቫዶር ባለፈው ክረምት በጎዳና ላይ ተቃውሞ ከተናጡት አንዷ ነች፡፡ ሞራይስ እንደሚለው ትዕይንተ ህዝብ አድራጊዎቹ የተነሳሱት በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ እና በቀድሞው የብራዚል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሪካርዶ ኳክሴይራ ተግባራት ላይ ባላቸው ቁጣ ነው፡፡ ቴክሴይራ በአንድ ወቅት የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡ አሁን ግን በታክስ ማጭበርበርና በጉቦ ቅሌት ውርደት ተከናንበው ከስፖርቱ ርቀው ተቀምጠዋል፡፡ ሞራይስ ስለ ፕሬዝዳንት ሉካ እና ስለ ቴክሴይራ ይናገራል፡፡ ‹‹ሁለቱ ሰዎች ለእኛ ለብራዚል ህዝቦች ቃል ሲገቡልን የዓለም ዋንጫ ወጪ ይሸፈናል ያሉን በግል ባለሀብቶች ነበር፡፡ ዋሽተውናል፡፡ የበዛው ወጪ የህዝብ ሀብት ነው፡፡ ለጤና፣ ለትምህርትና ለሌሎች ማህበራዊ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ መዋል የሚገባው ገንዘብ በአንድ ውድድር ላይ እንዲህ መባከኑ ያስገርማል፡፡ ትቶት የሚሄደውም ጥሩ ነገር አይኖርም›› ይላል፡፡
‹‹ግዙፎች ግንባታዎቹ ከሀገሪቱ አቅም በላይ ናቸው›› የሚለው ደግሞ ቦሪዮ ዴ ጄኔይሮ የሚኖረው የስተዲየሞች ጉዳይ ኤክስፐርት ክሪስ ጋፍኔይ ነው፡፡ ‹‹ዚል ስታዲሞቹ ተገንብተው በሰዓቱ መጠናቀቅ ስለመቻላቸው የሞቀ ክርክር አለ፡፡ ነገሩ ሁሉ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ በምን አይነት ጫና ስር እንዳለ ያሳያል›› ይላል፡፡ ጨምሮም ‹‹ለዓለም ዋንጫ የሚመጡ እንግዶች በግንባታ ላይ ያለች ግዙፍ ሀገር ሆና ያገኟታል›› በማለት ለውድድሩ ዝግጅት የተጀመሩት ግንባታዎች ምን ያህል ሰፋፊ መሆናቸውን ለማስረዳት ይሞክራል፡፡
ጋፍኔይም በመጪው ክረምት የህዝብ ተቃውሞ በድጋሚ ይነሳል ብሎ ይጠብቃል፡፡ ፖሊስም በሰልፈኞቹ ላይ የወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ይደገማል የሚለው ፍራቻም አብሮ አለ፡፡ ‹‹በኮንፌዴሬሽንስ ካፕ ሰሞን በትዕይንተ ህዝቡ ላይ አዎንታዊ ነገሮች ነበሩ፡፡ ሆኖም ፖሊስ ጨከን ያለ ምላሽ በመስጠቱ ህዝቡን አርቆታል፡፡ የጥይት ራት መሆንና በአስለቃሽ ጭስ የመጎዳቱን ነር በመፍራት ሸሽተዋል፡፡ ይህ ህዝብን እንደ አስጊ ኃይል የሚቆጥር የወታደር ፖሊስ ነው፡፡ ህዝብን ከመጠበቅ ይልቅ ህዝብን ያጠቃል›› ይላል ጋፍኔይ፡፡
የብራዚል ፖሊስ ጭካኔ በተሞላበት እርምጃው ይታወቃል፡፡ በተለይ በጭርንቁስ መንደሮች ውስጥ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ጭካኔው ይበረታል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ወንጀል ይበዛል፡፡ ሀገሪቱን እንደ ወረርሽኝ የሚያሰቃየው ወንጀል በብዛት የሚፈፀመው በእነዚህ ሰፈሮች ነው፡፡ የወንጀለኞች መፈልፈያ ናቸው፡፡ ኦፊሴላዊ አሃዞች እንደሚያረጋግጡት የብራዚል ፖሊስ ባለፈው ዓመት ብቻ 1890 ሰዎችን ገድሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 1300 ያህሉ በሶስት ክፍለ ሀገሮች ማለትም በሪዮ ዴ ጄኔይሮ፣ በሳኦፖሎ እና በባህያ የተመዘገቡ ግድያዎች ናቸው፡፡
ከተገደሉት መካከል አንዳንዶቹ ‹‹በቁጥጥር ስር ላለመዋል ባደረጉት ጥረት›› መሆኑን ፖሊስ ገልፅዋል፡፡ ከእነዚህ ግድያዎች ጋር ተያይዞ መንግስት የሚሰጣቸው ምላሾች ለህዝብ ያደላ አይመስልም፡፡ የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ዋና ፀሐፊ የሆኑት ጆዜ ማሪያኖ ቤልትራሜ ተጠይቀው ‹‹ዕንቁላሉን ሳትሰብር የዕንቁላል ፍርፍር መስራት አትችልም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ ወንጀልን ለመቆጣጠር መግደል የግድ ያስፈልጋል የሚል እምነት ያላቸው ይመስላል፡፡
በ2007 አሜሪካዊው የእህቷ ልጅ በሪዮ ፖሊስ ጥይት የተገደለባት ሊዝ ማርቲን አሁን በብረራዚል ፖሊስ ጭካኔ ላይ የተቃውሞ ዘመቻ እያስተባበረች ትገኛለች፡፡ ወንጀልን ‹‹የማፅዳት›› ሩጫ የዓለም ዋንጫው በተቃረበበት ሳይቀር ትከራከራለች፡፡ ሊዝ ከወዲሁ መሆኑ እንደማይቀር ትከራከራለች፡፡ ሊዝ ከወዲሁ ‹‹Dont kill for me›› የተሰኘ ዘመቻን በማስተባበር ገቢውን ለበጎ አድራጎት ለማዋል ስራ ላይ ተጠምዳለች፡፡ ዘመቻው ፊፋና ዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የብራዚል ፖሊስ ጭካኔውን እንዲተው ጫና እንዲያሳድሩ ለማድረግ ይሰራል፡፡ ‹‹ሪዮ ውብ ከተማ ናት፡፡ የሚፈፀምበት ወንጀል ብዛት ግን አስደንጋጭ ነው›› ትላለች ሊዝ፡፡ ‹‹የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴው ወንጀሉን እንደሚያፀዳ ተናግሯል፡፡ በቅጡ ያልሰለጠኑ ተጨማሪ ፖሊሶች ስለሚሰማሩ፤ ሁከት እና የሟቾች ቁጥር የበለጠ ይጨምራል፡፡ ፖሊስ እንኳን በሙታኑ ቁጥር ይስማማል፡፡ ሆኖም ለማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ሰዎችን መግደል ካስፈለገ መግደሉ ተገቢ መሆኑን ያምናሉ›› ትላለች፡፡
የብራዚል ደሃው ማህበረሰብ በዓለም ዋንጫው ፕሮጀክት እጅት ተጎድቷል፡፡ በሪዮ ብቻ 19 ሺ የሚደርሱ ነዋሪዎ በግድ ከመኖሪያ ቤቶቻቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ ቤቶቻቸው ፈርሰው ለዓለም ዋንጫው የሚሆኑ ግንባታዎች እንዲካሄዱባቸው በመደረጉ ነው፡፡ የሪዮ ዴ ጄኔይሮ ዩኒቨርሲቲ ምሁር የሆነችው ጊሴል ታናካ እንደምትናገረው በከተማይቱ ተጨማሪ 30 ሺ ድሆች በዓለም ዋንጫውና በ2016ቱ ኦሎምፒክ ግንባታዎች ምክንያት ከቤቶቻቸው እንዲለቁ ተገድደዋል፡፡ ሁለቱ ግዙፍ ስፖርታዊ ውድድሮች በድምሩ ከመኖሪያ ቤታቸው ያፈናቀላቸው ነዋሪዎች ቁጥር 200 ሺ ይደርሳል፡፡ ‹‹ለወሳኝ የትራንስፖርት መስመር ግንባታ መነሳት እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል›› ትላለች፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ቤቶቹ ፈራርሰው የሚገነቡት አዳዲስ ጎዳናዎችና ባለ አራት መመላለሻ የአስፋልት መንገዶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለልዩ እንግዶች ማለፊያ ብቻ ተብለው የሚገነቡ የአስፋልት መንገዶች ይገኙባቸዋል፡፡ እኛ ብራዚላዊያን ነን፡፡ የዓለም ዋንጫን እንወዳለን፡፡ ህዝቡ በእግርኳስ እንደሚደሰት እርግጠኛ ነኝ፡፡ የብራዚል ብሔራዊ ቡድንንም እንደግፋለን፡፡ ነገር ግን የተቃውሞ ትዕይንተ ህዝብም ይኖራል፡፡ ብዙ ሰዎች በውድድሩ ላይ ላለመገኘት ይወስናሉ፡፡ የአየር ትራንስፖርት እና የነገሮች ዋጋ ከማሻቀቡ የተነሳ ሀብታሞች እንኳን ላለመክፈል እየወሰኑ ነው››
የሪዮ ባለስልጣናት ጭርንቁሶቹን መንደሮች የማጥፋት ይፋዊ ፕሮግራም አላቸው፡፡ የአደንዛዥ ዕፅ አመላላሾች መናኸሪያ ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን ሰፈሮች የማፅዳቱ ነገር ግን በይበልጥ ጎብኚዎች እንዳያይዋቸው ከሳቸው ፍላጎት የተነሳ የታቀደ መሆኑ ይታመናል፡፡ ከእነዚህ ሰፈሮች ብዙዎቹ ከዕውቁ የኮፓካባና የባህር ዳርቻ፣ የማራካኛ ስታዲየምን ወይም የኤምካሪዮ ኒክ ኦሎምፒክ ፓርክ አቅራቢያ የሚገኙ ናቸው፡፡ የፖሊስ አባላት አማሪልዶ ደ ሶዛ የተባለ የእነዚህ አካባቢ ነዋሪን ደብድበው ገድለዋል በሚል ተከስሰዋል፡፡ ግድያው የተፈፀመው ሮቺንሃ በተባለው ጭርንቁስ ሰፈር ነው፡፡ በመጪው ሰኔ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ያርፍበታል ተብሎ የሚጠበቀው ሮያል ቱሴፕ ሆቴል ለዚሁ ሰፈር ቅርብ ነው፡፡
ሮማሪዮ የዓለም ዋንጫን ማዘጋጀት ለብራዚል ቂልነት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሀገሪቷ ለህዝቧ ማውጣት የነበረባትን ገንዘብ በእግርኳስ ላይ ብቻ ማፍሰሷን አይቀበለውም፡፡ ‹‹መንግስታችን ለጤና እና ትምህርት መስፋፋት ቅድሚያ መስጠት ነበረበት›› ሮማሪዮ ሮሮውን ያሰማል፡፡ ‹‹ስታዲየሞችን በተመለከተ ከፊፋ የተላለፈውን ቀጭን ትዕዛዝ መንግስታችን ሊቀበለው አይገባም ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫን አገኙም፣ አጡም ብራዚላዊያን ወጪውን የመሸፈኑን ኃላፊነት ተሸክመዋል›› ይላል ሮማሪዮ፡፡
የፊፋ ቃል አቀባይ ግን የዓለም ዋንጫ ብራዚልን ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ‹‹እንደ ኦፊሴላዊው የብራዚል መንግስት ዳታ የህዝብን ገንዘብ በዓለም ዋንጫና በኦሎምፒክ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ከ2007 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ የሀገሪቱ አጠቃላይ ገቢ በ0.15 በመቶ ከፍ ያደርገዋል›› ብሏል፡፡ ቃል አቀባዩ ትችቶችን በማጣጣል ፊፋ ጽ/ቤቱ በሚገኝበት ስዊዘርላንድ ታክስ እንደሚከፍል ሁሉ ከቲኬት ሽያጮች ከሚገኘው ገቢ ለብራዚል መንግስትም ታክሱን እንደሚከፍል አስታውቋል፡፡ ሆኖም ሌሎች ከታክስ ነፃ የሆኑ የዓለም ዋንጫው ገቢዎች መኖራቸውን አልካደም፡፡ ፊፋ ጥሩ የውድድር ጊዜ ቢጠብቅም ብራዚላዊያኑ ግን አመፅ የማይቀር መሆኑን ይተነብያሉ፡፡ ‹‹በመጪው ጁን የሚፈጠረውን ነገር ማንም ሊገምት አይችልም፡፡ የኮንፌዴሬሽንስ ዋንጫ ግን ለጨዋታ እና ለውድድሩ የተዘጋጁት የፀጥታ ጥበቃዎች በአግባቡ መስራታቸውን አሳይቷል፡፡ ጨዋታዎቹም በደህና ተከናውነዋል›› ብሏል ቃል አቀባዩ፡፡ የሮማሪዮ የመጨረሻ ቃል ግን የቀድሞው የፊት አጥቂ ጥሩ ነገረ ይኖራል ብሎ እንደማይጠብቅ ያረጋግጣል፡፡ ‹‹የዓለም ዋንጫ›› አለ ሮማሪዮ፡፡ ‹‹የዓለም ዋንጫ ጥሩ ጠባሳ ትቶ አያልፍም››
↧
Sport: ሮማሪዮ ‹‹ዓለም ዋንጫ በአመፅ መደብዘዙ አይቀርም›› ይላል
↧