Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: በወር አበባ ሰሞን ህመም እና ምቾት ማጣትን የምትቀንሺባቸው 6 ስልቶች

$
0
0

ከቅድስት አባተ

(በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 57 ላይ ታትሞ የወጣ)

የሴቶች ጉዳይ ብንላቸው የምንግባባቸው ጥቂት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ወር ጠብቆ ፅንስ ለመፍጠር ዝግጁ መሆናቸውን ለመናገር የሚመጣው የወር አበባ ነው፡፡ እጅግ በርካታ የሆኑ እና ሴቶች የወር አበባቸው በሚመጣ ወቅት ከቀላል መነጫነጭ አንስቶ ሁሉን ነገር እስከመጥላት የሚያደርስ የህመም እና ምቾት የማጣት ስሜት ይገጥማቸዋል፡፡ ሁነቱ ተፈጥሯዊ የሆነና ለክፉ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ይሁንና የዚያን ሰሞን ስሜት እና ህመም ማቅለል እና ንጭንጩንም ጭምር ማቃለል እንደሚቻል ባለሞያዎች ያስረዳሉ፡፡ የዛሬው ትኩረታችንም ይህ ነው፡፡ ቀላል የሚባሉ እና የህክምና ጥበብን እጅግም በማይጠይቁ ስልቶች የወር አበባ ሰሞንን ማቅለል የምትችይባቸውን ስልቶች እነሆ ብለንሻል፡፡

women health

የወር አበባ ለምን?

ተፈጥሮ የወር አበባን ስትፈጥር መራባትን አስባ ነው፡፡ ሴቶች አዲስ ነፍስ የመፍጠር ስልጣን በየወሩ ይሰጣቸዋል፡፡ አብሮ ለመፍጠር የተዘጋጀ ጥንድ እስካለ ድረስ ይህ ይሰራል፡፡ በየወሩ የሚዘጋጁት እንቁላሎች የሚዳብርና ፅንስ የሚያደርጋቸው የወንድ ዘር ሲያገኙ እዚያው ሆነው ጽንሱ ሲፈጠር ያ ካልሆነና ሴቲቱም በመፀነስ እቅድ ውስጥ ካልሆነች ደግሞ እንቁላሎቹ ወደ ውጪ መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ እንግዲህ በየወሩ ከደም ጋር ተቀላቅለው የሚወጡት እነዚህ እንቁላሎች ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ ክስተት በብዙ ሆርሞኖችና የሰውነት ውስጥ ውስብስብ ተግባራት የሚከወን እንደመሆኑ ብዙ ለውጦችን ሴቶች ማስተናገዳቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቢያንስ 80 ከመቶ የሚሆኑ የዓለማችን ሴቶች ከቀላል ህመም አንስቶ እስከ ከበዱት ድረስ በወር አበባ ሰሞን ይገጥማቸዋል፡፡ እጅግ አሳማሚ የሆድ ቁርጠት፣ የስሜት መቀያየር፣ መነጫነጭ ራስ ምታት እና ሌሎቹም የሚጠቀሱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህን የወር አበባ ሰሞን ችግሮች ማቅለያ ዘዴዎችን ታዲያ የህክምና ሰዎች ለሴቶች ሁሉ ያጋራሉ፡፡ የዲስከቨሪ መፅሔት እና ውሜን ሄልዝ ኤክስፐርቶች ካነሷቸው መካከል ዮጋ ማዘውተር ጨው መቀነስ፣ አመጋገብ ማስተካከልና አንዳንድ ቀለል ያሉ መድሃኒቶችን መውሰድን ያነሳሉ፡፡

የወር አበባ ሰሞን ጨው ቀንሺ

በወር አበባ ሰሞን እንቁላሎች ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁት ልጅ እንደሚፈጠር በማሰብ ነው፡፡ ስለሆነም ጽንሱ ቢፈጠር የሚያስፈልገውን የጨው ፈሳሽ እና ኤሌክትሮላይት ለመሙላት ሰውነትሽ ብዙ ጨው የዚያን ሰሞን ይኖረዋል፡፡ ብዙ ጨው መኖሩ ደግሞ ውሃን የመሳብና በሰውነት ውስጥ መጠራቀምን ይፈጥራል፡፡ ይህ በራሱ የሚፈጥረው ሰውነትን የማስጨነቅ ተፅዕኖ ስለሚኖር ከውጪ የምትወስጂውን ጨው የወር አበባ ከሚመጣባቸው ቀናት አስቀድመሽ ቀንሽ፡፡ በተለይ የተጠባበሱ ምግቦች ውስጥ ከፍተኛ የጨው ክምችት ስለሚኖር ከእነዚህ ምግቦች በዚያ ሰሞን መቆጠብ ጥሩ እንደሆነ ባለሞያዎቹ ያሰምሩበታል፡፡

ዮጋ እንደ መዝናኛም እንደ መድሃኒትም

የወር አበባ ወቅትን ህመም ለማስታገስ መዝናናት፣ ውጥረትን መቀነስ እና የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በእጅጉ የሚመከሩ መላዎች ናቸው፡፡ ዮጋ ደግሞ ሁሉንም በአንድ አዋህዶ የያዘ የተመስጦ ስፖርት ከመሆኑ አንፃር ቁጥር አንድ ተመራጭ ስፖርት ያሰኘዋል፡፡ ‹‹ዮጋ ስፖርት ብቻ አይደለም፣ አዕምሮና አካልን በአንድነት ከውጥረት መንጥቆ የሚያወጣ መድሃኒትም ነው›› ይላሉ የዲስክቨሪ መፅሔት የህክምና አማካሪ፡፡ በኢንዲያን አካዳሚ ኦፍ አፕላይድ ሳይኮሎጂ የጥናት መፅሔት ላይ የሰፈረ የጥናት ውጤትም ተመሳሳይ ጥቅሞችን ያነሳል፡፡ ጥናቱ ዮጋ የስነ ልቦና እና የአካላዊ መዝናናትን በማጎናፀፍ ከወር አበባ ወቅት ህመምና ምቾት ማጣት በመገላገል በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ይናገራል፡፡

ካልሲየምና ቫይታሚን ዲ ውጤት አላቸው

በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካ ውስጥ በዚህ ላይ ምርምር ያደረጉ ባለሞያዎች ቫይታሚን ዲ እና ካልሲየም ማዕድን የወር አበባ ጊዜዎትን በእጅጉ ቀላል የማድረግ ሚና እንዳላቸው አሳይተዋል፡፡ በጥናቱ በየዕለቱ እስከ ስድስት መቶ ሚሊግራም ካልሲየም የወሰዱ ሴቶች ዘንድ የወር አበባ ወቅት ህመሞች የሚባሉት እንደ ሆድ ቁርጠት፣ ራስ ምታት፣ የምግብ አምሮት እና የስነ ልቦና ጫናው በግማሽ ቀንሶ መገኘቱን በጥናታቸው ፅፈዋል፡፡ ይህ የካልሲየም መጠን አንድ ብርጭቆ ወተትና አንድ ብርጭቆ እርጎ በጋራ ቢጠጡ የሚያገኙት ምጣኔ ነው፡፡ ባለሞያዎቹ ካልሲየምን በክኒን መልክ መውሰድ ቢቻልም ተመራጩ ግን ከወተት ተዋፅኦ ውጤቶች ማግኘቱ እንደሆነ አበክረው ያሳስባሉ፡፡ ቫይታሚን ዲ ተመሳሳይ ተፅዕኖ እንዳለው ባለሞያዎቹ አስረድተዋል፡፡ እንደ ካሮት እና መሰል አትክልቶች ቫይታሚኑን ማግኘት ወር አበባን ቀለል ያደርጋል፡፡

ለማይግሬይንና ራስ ምታቱስ?

በወር አበባ ወቅት የሚከሰተው ራስ ምታት ከወትሮው በተለየ አናትን የሚነቁርና ሁሉን ነገር የሚያስጠላ ሊሆን ይችላል፡፡ ቀደም ሲል ያነሳናቸው የመዝናኛ እና ችግሩን የመቅረፊያ ስልቶች እየሰሩ ካልሆነ በባለሞያ የሚታዘዝ ህመም ማስታገሻን መውሰድ ይመክራል፡፡ ምናልባት ሌላ ጊዜ ከሐኪም ትዕዛዝ ውጪ የምንወስዳቸው ማስታገሻዎች በዚህ በኩል ውጤታቸው አርኪ ስለማይሆን ነው፡፡ ሌላ ማስታገሻ ለመጠየቅ ባለሞያን እንዲያዩ የሚመክረው በውጪ ሀገራት ለዚህ ተብለው የሚሰሩ ልዩ ማስታገሻዎች አሉ፡፡ በእኛ ሀገር ፋርማሲዎች በስፋት የሚገኙ ባለመሆናቸው ባለሞያ መገናኛቸውን ሊያመላክትዎት ይችላል፡፡

ፋይበር ያላቸውን ጠጠር ያሉ ምግቦች ጥቅም

ባለሞያዎቹ እንደሚሉት በወር አበባ መምጫ ሰሞን ህመሙን እና ሆድ ቁርጠቱን የሚያመጡት የሆርሞን ለውጦች የሆድ ህመም እና ተቅማጥ ከሚያመጡት ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ስለሆነም ሆድን ያዝ የሚያደርጉ እንደ ጎመን አጃ፣ ሙዝና የመሳሰሉትን ምግቦች ብትወስጂ ሆድሽን ያዝ አድርገው የምግብ አምሮቶሽን ይገቱታል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ዘንድ የሚታየውንም የዚያን ሰሞን የሆድ መለስለስና መለስተኛ ተቅማጥ ለመቆጣጠር ያግዛሉ፡፡

በዚያ ሰሞን ዋና መዋኘት?

ብዙ ሴቶች በወር አበባ መምጫ ሰሞን ከሰው ራቅ ብለው ቤት አካባቢ ሆነው ቢቆዩ ይመርጣሉ፡፡ የባለሞያዎች ሀሳብ ግን ይለያል፡፡ ከሰው መቀላቀሉ እና ዘና ማለቱ ይመከራል፡፡ በተጨማሪም ዋና መዋኘት ከፍተኛ ጠቀሜታም እንዳለው ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ በዋና ወቅት በሰውነት እና በውሃው መካከል በሚደረገው ፍትጊያ የሚፈጠረው ግፊት የሆድ ቁርጠትና የዚያን አካባቢ ቁስለት የሚመስል ስሜት አዝናንቶ የማፍታትና ህመምንም የመቀነስ አቅም አለው፡፡ በቀን ቢያንስ ለ20 ደቂቃ ብትዋኚ ጥሩ ነው ተብሎ ተመክሯል፡፡ ነገር ግን የግድ ወደ ዋና ገንዳ እንድትገቢ አትገደጂም፡፡ የዋናው ነገር ካልተመቸሽ በቤት ውስጥ መታጠቢያ ቤት ለብ ያለ ውሃ በገንዳው ሞልተሽ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሰውነትሽን ብታሳርፊው የዋናውን ያህል ባይሆንም ጥሩ ውጤት ታገኚያለሽ፡፡

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>