አበራ ሽፈራው
ከጀርመን
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጥር ጥቅምት መጨረሽና ህዳር ወር 2006 እጅግ አሳዛኝና በህይወት እስከአለን ድረስ የማንረሳው ክፉ አጋጣሚ በእህቶቻችንና በወንድሞቻችን ላይ ግድያን፣ መድፈርን፣ እስርን፣ መታረድንም፣ በመኪና እየተገጩም ጭምር መሞትንም መጀመሩን ያየንበትና የሰማንበት:: ክፉ ወር:: ብዙዎቻችን በውስጣችን ከራሳችን ጋር የተሟገትንበት፣ ምን እናድርግ? ብለን ከቅርብ ጓደኞቻችን ጋር የተነጋገርንበት:: ሌሎቻችንም ተሰባስበን በውስጣችን ያለውን ሃዘን በግልጽና በአደባባይ ዓለም ሁሉ እየሰማ የተነፈስንበት:: ሳውዲ አረቢያዎች ለዘመናት አብሮአቸው የነበረውን ጭካኔ በአይናችን የተመለከትንበት ምን አልባትም እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ከዚህ በላይ ሲጨቆኑና ሲረገጡ መኖራቸውንም ለማየት የቻልንበት ጊዜ ይህ ይፋ ወጣ እንጂ::
በእርግጥም ሳውዲዎች ጨካኞች ናቸው ስራቸውም እጅግ አሳፋሪ ነው:: ጊዜ ይለወጣል ሀብትም ይጠፋል ነገር ግን ታሪካቸው በተለይም በወንድሞቻችን ላይ የተፈጸመው ግፍ ግን ለታሪክ ሲታወስ ይኖራል :: በሳውዲዎች ድርጊት ያላዘነ ኢትዮጵያዊ የለም እኔ እስካየሁትና እስከሰማሁት ድረስ:: ታሪክ የእኛን እንግዳ ተቀባይነትን እንደመዘገበ ሁሉ የእነሱንም ውለታ መላሽነት በእኛ ዘመን ለማየት ችለናል ይህንንም ታሪክ መዝግቦታል:: በክፉ ዘመናቸው በአገራችን ተሰደው እንደ እናት ቤት ኢትዮጵያ እንዳልተቀበለቻቸው ሁሉ ዘሬ ሰርተው ሳይሆን አምላክ በተፈጥሮ በሰጣቸው ተመክተው የጥጋብ ዱላ በወገኞቻችን ላይ አዘነቡ የብዙ የኢትዮጵያውያን እንባ በአለም ሁሉ ፈሰሰ፣ የአምላክንም እጅ ተማጸነ፣ ብዙዎች የአምላክንም ምህረት በእንባ ለመኑ በእርግጥም አምላክ ሰምቷል መልሱም አንድ ቀን ለአገሬም ይሠጣል::
ላለፉት 50 ዓመታት አረቦች ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጥላቻ በተለያየ መልኩ ለመፈጸም ሞክረዋል ዋናው መነሻቸውም በሁሉም መልኩ ለመስፋፋት ያደረጉትን እንቅስቃሴ ሁሉ እሽ ብሎ የተቀበላቸው ያለመኖሩና በአፍሪካ ቀንድ የአረቦች አስተሳሰብ ተግባራዊ ሊሆን ያለመቻሉ ሲሆን ይሁንና ሃሳቦቻቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ግን አርፈው ተኝተዋል ማለት ግን አይደለም:: ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ኢትዮጵያን ለመበታተን የተጠቀሙት አንደኛው መንገድ የዛሬዎችን ዘረኛ የህወሓት/ ወያኔ ቡድን እንደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሉ አንደኛው መሳሪያ ሆኖ ያገለገላቸው እኩይ ቡድን መሆኑ ጭምር ነው::
በእርግጥም ኢትዮጵያና ልጆቿ ለአገራችው ሳይሆን የሌሎች ህዝቦችንና አገራትን ሰላም ለማስከበር ለመስወአት የቀረቡ የህወሃት ጀነራሎች የገቢ ምንጭ ሆነዋል፣ የአረቦችን ቆሻሻ ለመጥረግና በዚህ ዘመን የሌለን ባርነት ርካሽ ጉልበታቸውን ለመሸጥ ተገደዋል ይኸም ብሶ ለአስከፊ ችግር መጋለጣቸውም ቢሆን ከኢትዮጵያው የህወሓት ሥርዓት ማንነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ውጤቶች ናቸውና መሰደድና የህወሃት ደላሎች መጠቀሚያ መሆንና ለመከራ መዳረግም ቢሆን የሥርዓቱ መዋቅሮች ለዚህ አስከፊ ችግር መፍትሄ መፈለግ አቅቷቸው ሳይሆን እራሳቸውን እስከጠቀማቸው ድረስ በዝምታ ቆይተው ችግሩ ተባብሶ አስከፊ ደረጃ ሲደርስ ደግሞ “ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል“ እንዲሉ አሳቢ መስለው መነሳታቸው ደግሞ ያሳዝናል::
ለአሁኑ የአረቦችም ሆነ የሌሎች አገሮች ማጥቃት መነሻው በአገራችን ያለው የፖለቲካ ችግር ሲሆን የኢኮኖሚ ችግሩም ቢሆን የዚሁ የፖለቲካው ችግር ውጤት መሆኑ ማንም ይስማማበታል:: ለመነሻም እንዲሆነን የአገሪቷን ፖለቲካ ለ22 ዓመታት የተቆጣጠረው ህወሃት/ወያኔ በግልጽና በአደባባይ የኢትዮጵያ ህዝብ አይኑ እያየ የአዋቀረው የንግድ ብዝበዛ፣ የአገሪቷ የንግድ እንቅስቃሴ ከፓርቲ ንግድ ወይም ከEFFORT በተጨማሪ ትልልቅ የንግድ ተቋማት በህወሃት ሰዎች መያዛቸው፣ ጠቅላላ የንግድ መድሎ መኖሩ፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች በሙሉ በሚያስብል መልኩና በተጠና መልኩ በህወሃት ሰዎች መያዛቸው፣ ለንግድ ስራ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ልዩልዩ የሚንስትር መስሪያ ቤቶች በነዚሁ ሰዎች መያዛቸውና ልዩ ልዩ የአገሪቷን ንግድ በሙሉ በማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ጭምር ለእነሱ የሚጥቅሟቸውን ሁኔታዎች እስከማመቻቸት ድረስ መድረሳቸውን ቀዳሚ እድሎችን የሚያገኙት እነሱ መሆናቸው ጭምር ናቸው::
ለአሁኑ ጥቃጣችን ምክንያት ከላይ የተጠቀሰው ጉዳይና ሌሎች ጉዳዮች ሲሆኑ በተጨማሪም አረቦች በተለይም ሳውዲ አረቢያ ለህወሃት ቅርበት ባለው ሼህ መሃመድ አላሙዲንና በሌሎች የንግድ ሸሪኮቻቸው አማካኝነት ባላቸው የቆየ ቅርርብ ማንነታቸውን በጥልቀት ያወቁ በመሆናቸው ወገኖቻችን ደራሽና ወገን ወይም የሚከላከልላቸው እንደሌላቸው ሰው ሆነው በአሳዛኝ መልኩ እንዲባረሩ መደረጉ ለህዝቡና ለተጎጂ ቤተሰቦች እንጅ ለህወሃት ሰዎች ቅንጣት ያህል እንደማይሰማቸው እርግጠኛ ነኝ:: ለዚህም ደግሞ የህወሃት የጭካኔ መጠንን ለመለካት የኢትዮጵያን ህዝብ ለህወሃት ያለውን አመለካከት በመለካት ማወቅ ቀላል ነው:: ይልቁንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለህወሓት የማፍያ መዋቅር ሌላ የገቢ ምንጭ እንደፈጠረለት በቀላሉ መገመት ይቻላል:: ይህንን በቀላሉ ለመረዳት በተመላሽ ወገኞቻችን ንብረት ላይ የሚደርሰው የንብረት ንጥቂያ ብዙዎች በሳውዲ አረቢያ ከደረሰባቸው ስቃይ ይልቅ በአገራችን በህወሃቶች የጉምሩክና በኤርፖርት አካባቢ የተደረጉት የፍተሻ ዝርፊያዎችና የንብረት ቅሚያ ቀላል ሊባሉ እንደማይችሉ እየተነገረ ይገኛል:: ይህም ችግር በአገር ውስጥ ተባብሶ ብዙዎችን ለተጨማሪ የስነልቦና ችግር ላይ መውደቅ ምክንያት እየደሆነ ይሰማል:: ታዲያ ይህንን የህወሃትን ሥርዓት ምን ልንለው እንችላለን?
ከላይ እንደገለጽኩት የህወሃት የማፍያ መዋቅር የትኛውንም አጋጣሚዎች እንደ አንድ ጥሩ አጋጣሚ የሚቆጥሩ መሆናቸውን ለማየት ከላይ ከጠቀስኩት ተግባራቸው በቀላሉ ለማየት ይቻላል:: አባይ ግድብ ብለው ይነሳሉ ከህዝቡ ከልጆቹ ማሳደጊያ እየነጠቁ ሰብስበው ባልተጠና መልኩ የተጀመረን ፕሮጀክት ለማስፈጸም በሚል የተሰበሰበውን በጀትና ገንዘብ ለህወሃት የንግድ ተቋማት ትልቅ የብዝበዛ ምንጭነት እንዲያገለግል ሲደረግ እያየን እንገኛለን፣ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ከስደት በግድ ሲመለሱ በላብና በደማቸው የሰበሰቡትንና ከሳውዲዎች እጅ አምልጦ በእጃቸው ይዘው የመጡትንም በጥሬ ገንዘብና በአይነት መበዝበዛቸው፣ በዚሁ አስከፊ ጊዜ ለእነዚህ መከረኞች መድረስ ሲቻልና የተሰደዱት ከማቋቋም ይልቅና የኢትዮጵያ ህዝቦች ሆነው ሳሉ በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠርን ብር በብሔር ብሄረሰቦች ስም አውጥተው ሲደንሱበት ከማየት በላይና አሁንም የህወሃት የንግድ ተቋማት የኪስ ማደለቢያ ማድረጋቸውን ስናይ እጅግ የሚዘገንን ተግባር ነው ለማለት ያስችላል::
ትላንት ደርግ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1977 ዓ.ም የወሎና የትግራይ ወገኖቻችን በድርቅ ሲጠቁ የደርግ 10ኛ ዓመትና የኢሠፓን ምስረታን በከፍተኛ ወጭ አከበረ እያሉ ሲሳለቁበትና የትግላቸው መቀስቀሻ አድርገው ሲዘምሩበት እንዳልነበረ ዛሬ የትላንት ነጻ አውጭዎች ነን ባዮች የዛሬዎቹ በዝባዦች በአደባባይ ስራቸውን፣ምግባራቸውንና አላማቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንድናያቸው አድርጎናል:: ደግሞም የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ግዜ በላይ ለራሱ እያሰበ መምጣቱና እየነቃ የትኛውንም የክፋት መዋቅራቸውንም ይዘርጉ ይህንን ሁሉ በጣጥሶ እነዚህን ጎጠኞች አይናችሁ ለአፈር ያለበት ግዜ ላይ ደርሰናል:: በአገር ውስጥ መቃወም ባይችልም ዝምታን መርጠው የነበሩ ሳይቀሩ ዛሬ በአደባባይ ህወሃትን ለመጋፈጥ ቆርጠው ታይተዋል:: ትግሉንም ለመደገፍ ግልጽና ስውር ትግሉን መቀላቀል ተያይዞታል፣ ለህወሃት አስደንጋጭ በሚሆን መልኩ ትግሉን ወደከፍተኛ ምዕራፍ ለማሸጋገር ግልጽና የህቡ የትግል መስመሮችን እየተቀላቀለ ይገኛል::
ከዚህ በላይ የእህቶቻችንንና የወንድሞቻችንን ደምና እንባ ሳይደርቅ ለእነዚህ የሳውዲአረቢያ ጨካኞች የአገራችንን መሬቶችንና ሌሎች የንግድ ፍቃዶችን ለመስጠት ከ300 በላይ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን መስማማታቸውን ስመለከት ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆንንና እነሱን እስከጠቀመ ድረስ ኢትዮጵያዊነት በህወሃቶች ፊት ምንም እንዳልሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል:: እንግዲህ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባይሆንም እና በሌላ ርዕስ የምመጣበት ቢሆንም ከኢትዮጵያ ድንበርን ወደሱዳን ለማካለል መነሳታቸውንም ስመለከት በጣም የሚያሳዝን መጥፎ አጋጣሚ ላይ መኖራችንንና የማንን መሬት ለሱዳን ለመስጠት እንደፈለጉም በደንብ አልገባኝም:: ስለሆነም ህወሃቶች ምን አይነት ትምህርት እንደተማሩ ምን አልባትም ብዙዎቹ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑና በአጋጣሚዎች ኢትዮጵያ በሌሎች እኩይ ተግባርን በሰነቁ የኢትዮጵያ ጠላቶች እጅ መውደቋን ለመረዳት እንችላለን::
ዛሬ አስቸጋሪ እንዲያውም ለአገራችን ህልውና አስጊ የሆነ ጉዳይ ቢኖር ህወሃትን ለመጋፈጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ መሆናችንን ማስብ ካልቻልን ነው :: ስለሆነም እነዚህ የታሪክ ጥቁር መዝገቦች፣የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠላቶች፣ የህዝብና የትውልዱ ጠንቆችንና አጋጣሚዎችን ሁሉ ለራሳቸው የብዝባዛ መሳሪያነት የሚጠቀሙትን ጠላቶቻችንን ለመጋፈጥ አሁንም ያልቆረጥን እንቁረጥ::
ይህ አስከፊ የህወሃት ሥርዓት የሚፈልገውን ሳይሆን እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ የሚመኙትን ነጻነትና ፍትህ፣ ሁሉም ብሔረሰቦችና የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ በእኩልነትና ያለመድሎ የምንኖርባት፣ ፍትህ የሰፈነባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍቃድ የምንመሰርትበት፣ የህግ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከህወሃት የዘር ጭቆና መላቀቅ ያለብን ሰዓት ላይ ደርሰናል:: አጋጣሚዎችን ሁሉ እየተጠቀሙ ለብዝበዛና ለእልቂት ከሚዳርጉን ነውረኞች እራሳችንን እናድን::
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
aberashiferaw.wordpress.com