ዲሴምበር 9 ቀን 2013 ዓ.ም
በቅድሚያ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ። ከአምስት አመታት በፊት ከአንዳንዶቻችሁ ጋር፣ በቅርበት፣ በቅንጅት ድጋፍ ማህበራት ዉስጥ አብረን ሰርተናል። አብረን ለሰላም ለዲሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለሕሊና እስረኞች መፍታት ስንጮህ፣ ስንሰራ፣ ስንደክም፣ ስንመክር ነበር። መሃከል መንገድ ላይ የፖለቲካ ስትራቴጂ ልዩነቶች ተፈጠሩ። «ሁለ ገብ» የሚል የትግል ስልት መርጣችሁ የተለየ መስመር ያዛችሁ። እኛ ደግሞ በዚያ በሰላሙ መንገድ ቀጠልን። አንዳንዴ ልዩነቶቻችን ከረዉ በድህረ ገጾች፣ ፓልቶክ ክፍሎች፣ ጋዜጣዎች ፣ ሬዲዮኖች የተካሰስንበትም ጊዜ ጥቂት አይደለም።
ወቅቱ ትብብርን ይጠይቃል። በተቃዋሚዉ ጎራ ያለው ወገን ሁሉ በአንድነት ይሰባሰብ ዘንድ፣ እናንተም የተቃዋሚዉ አንዱ አካል እንደመሆናችሁ፣ እናንተ ዘንድ ያሉ፣ መሰባሰብ እንዳይኖር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን፣ ትመረምሩና ታስተካክሉ ዘንድ ይሄን ጽፊያልሁ። ክስ ሳይሆን፣ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ምክር አዘል አስተያየት በማቅረብ፣ ቻሌንጅ ላደርጋቹህ እሞክራለሁ።
ኤርትራና ኤርትራ የምትረዳቸው ድርጅቶች
ግንቦት ሰባት የተቋቋመው ሰኔ ወር 1999 ዓ.ም ነዉ። ከስድስት ወራት በኋላ ስድስተኛ አመቱን ያከብራል። ድርጅታችሁ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ብዙ የምናውቀዉ ነገር የለም። ነገር ግን ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳላችሁ ግን ግልጽ አድርጋቹሃል። የኤርትራ መንግስት እናንተ ወታደሮች ስለሌላችሁ፣ ከትግራይ ብሄራዊ ዴሞክራሲ ንቅናቄ(ትብዴን) ጋር አብራችሁ እንድትሰሩ እንደጠየቃችሁና እንደተስማማችሁ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እናንተ ፖለቲካዉን ልትይዙ፣ እነርሱ ደግሞ ሚሊታሪዉን። (ልክ ያኔ ሕወሃት ሚሊተሪዉን ይዞ፣ እነ ታምራት ላኔ ደግሞ ፖለቲካዉን እንደያዙት)
በጎንደር፣ በወሎ በሸዋ.. ፊት ፊት እየቀደሙ ፣ በፕሮፖጋንዳ ሕዝቡን እያሳምኑ፣ ትልቅና ወሳኝ የፖለቲካ ሥራ እየሰሩ፣ ሕወሃትን አዲስ አበባ ያስገቡት እነ ታምራት ላይኔ ነበሩ። ታዲያ፣ ምናልባት የኤርትራ መንግስት፣ ታሪክን ደግሞ፣ እናንተን ዳግማዊ ታምራት ላይኔዎች ሊያደርጋቹህ፣ የርሱን ፍላጎት ሊያስጠብቁ የፈጠራቸዉን ስልጣን ላይ ሊያስወጣ አስቦ እንደሆነ፣ ገምታችሁ ታውቃላችሁ ? እስቲ ጠይቁ፣ ኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር የመሳሰሉ በርካታ ድርጅቶችን በልጦ፣ እንዴት ትብዴን በወታደራዊ አቅሙ ጠንካራ ሊሆን ቻለ ? ምናልባትም የ«ትግራይ ሽምቅ ተዋጊዎች» የተባሉት በርግጥ የትግራይ ሰዎች መሆናቸውን የሚያሳይስ ምን ማረጋገጫ አለ ? ከሰራኤ፣ ሐማሴን አኮሎ ጉዛይ የመጡ ኤርትራዉያን ቢሆንስ ?
ከሕወሃት በስተቀረ የኤርትራ መንግስት የረዳቸዉና የደገፋቸው ድርጅቶች፣ አንዳቸዉም ለቁም ነገር ሲደርሱ አላየንም። አልሻባብ እየተመታ ነዉ። በሶማሊያ በፑትላንድ፣ በሶማሊላንድ፣ በጁባላንድ እና ሞቃዲሾ አካባቢ ለአመታት ታይቶ ያልታወቀ መረጋጋት እየታየ ነዉ። በመሆኑም ኦብነግ መሳሪያና ስንቅ የሚያሳልፈበት ቀዳዳዎች እየተዘጉበት ነዉ። ድርጅቱ እየተከፋፈለ ፣ እየመነመነ፣ አብዛኞቹ አባላቱም ከሕወሃት/ኢሕአዴግ ጋር በመነጋገር ላይ ናቸው።
ኦነግን ከተመለከትን ደግሞ፣ በአስገራሚ ሁኔታ ፈረካክሷል። እንደ ከማል ገልቹ፣ ሃይሉ ጎንፋ የመሳሰሉ ተወዳጅና ኢትዮጵያን ወዳድ ጀነራሎች የቁም እስረኞች ሆነዋል። እንደ ዶር ዲማ ነግዎ፣ ሌንጮ ለታ ያሉ አንጋፋ የቀድሞ አመራር አባልትና መስራቾችም፣ የኦሮሞዎች ጥያቄ በመገንጠል ሳይሆን በዲሞክራሲ ይፈታል ብለዉ፣ እራሳቸዉን ከኤርትራ መንግስት ለይተው፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመታገል፣ የኦሮሞ ዴሞርካሲያዊ ግንባርን መስርተዋል። ብዙ አልተረጋገጠም እንጂ፣ ወደ አገር ቤት ገብተው ለመታገል ሃሳብ እንዳላቸውም የሚገልጹ ዜናዎችም የተናፈሱበት ሁኔታም አለ።
ሌላዉ በኤርትራ በኩል ይንቀሳቀሳል የሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ነዉ። ይህ ግንባር በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ የአመራር አባላት ነበሩት። ነገር ግን ድርጅቱ ጠንከር በሚልበት ጊዜ አመራር አባላቱ እየታሰሩ ፣ ይሰወራሉ። ሻእቢያ ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለው ድርጅት እንዲወጣ በፍጹም ፍላጎት ስለሌለው ፣ የአርበኞች ግንባርም አደግ ሲል እየተኮረኮመ፣ ይኸው ከአመታት በፊት የነበረበት ደረጃ ነዉ ያለው።(እንደዉም ሳይብስ)
እንግዲህ ይሄን ሁሉ የምተነትነዉ ፣ ከኤርትራን መንግስት ጋር መስራት ታክቲክሊና ሚሊታሪሊ እንደማያዋጣ ለማሳየት ነው። በኤርትራ በኩል እንታገላለን የሚሉ አንዳቸውም፣ ይኸው ሕወሃት/ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ 21 አመታት አለፉ፣ አንድ ቀበሌ ነጻ አላወጡም። ወኔዉና ጀግንነቱ ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን የኤርትራ መንግስት መዳፍ ዉስጥ ስላሉ እንጂ። እናንተንም ለጊዜዉ መጠቀሚያ ያደርጓቹሃል። ትንሽ አደግ ስትሉ ግን መመታታችሁ አይቀርም። ከኦነግ፣ ከአርበኞች ግንባር ከመሳሰሉት መማር አለባችሁ። ግድ የለም ከሻእቢያ ጥገኝነት ዉጡ።
ኢሳያስና የኤርትራ ሕዝብ
ምን ያህል የኤርትራን ፖለቲካ እንደምትከታተሉ አላውቅም። የኤርትራን ሕዝብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለይቼ ስለማላየው የኢትዮጵያ ድህረ ገጾችን እንደማነበዉ፣ የኤርትራን ድህረ ገጾች እከታተላሁ። እናንተም እስቲ ጊዜ ወስዳችሁ ተከታተሉ። እስቲ ኤርትራዉያንን ቀረብ ብላችሁ አነጋግሩ። የሚያሳዝን፣ የሚያስለቅስ ታሪኮችን ነው የምትሰሙት።በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በሱዳን በኩል አድርገዉ፣ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሰደዱ፣ እባብ እየነደፋቸው፣ ተይዘው እየተገደሉ ሞተዋል። በሳዋና በተለያዩ ቦታዎች የኤርትራ ወጣቶች እየተቃጠሉ ነዉ። ኢሳያስ የኤርትራን ሕዝብ እያረደ ያለ እብድ ነዉ።
እናንተ፣ ቢያንስ ቢያስንስ «ለሰብዓዊነት ፣ ለፍትህ፣ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ የቆምን ነን» ትላላችሁ። ለዚያም ስትሉ አንዳንዶቻችሁም በቃሊቲ ትልቅ ዋጋ ከፍላቹሃል። ነገር ግን ከዚህ እብድ ጋር መስራታችሁ ምን ይባላል? ይሄስ አያሳንሳችሁምን ? በጣም ያሳንሳቹሃል። ከዚህ እብድ ጋር ባበራችሁ ቁጥር፣ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር እየተጠላችሁ ነዉ። ኢሳያስ የጉበት በሽተኛ ነዉ ይባላል። እንቁላላችሁን ሁሉ እርሱ ቅርጫት ዉስጥ ከከተታችሁ፣ ነገ ሰዉዬው የሞተ እለት፣ ምን ልትሆኑ ነው ?
እርግጥ ነዉ ኢሳያስ ጥቂት አየር መቃወሚያዎችን ፣ ጥቂት ሺህ ዶላሮችን ፣ የወታደር ጫማዎችን ሊወረወርላችሁ ይችላል። ኮምፖሽታቶ ዳር፣ ከፈራረሱ ፎቆች አንዱ ዉስጥ ጽ/ቤት ሊሰጣችሁ ይችላል። ነገር ግን ሕሊናችሁን ከመሸጥ፣ በአፍሪካ ከነኢዲአሚን ጎን በሚሰለፍ ቡድን፣ ሰይጣናዊ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሲፈጸም እያያችሁ፣ እንዳላየ ሆናችሁ ዝም ከማለት፣ ከሕዝቡ ጋር በመጣላትና ታሪካዊ ጠባሳ ከመፍጠር ፣ ከወዲሁ ከዚህ ያበደ አገዛዝ እንድትለዩ እማጸናቹሃለሁ። ግድ የለም ከሻእቢያ ጥገኝነት ዉጡ።
ኤርትራና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ
እንደምታውቁት ኢሳያስ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ የተገለለ ነዉ። ከቀይ ባህር አሳዎች ጋር በስተቀረ፣ ከኤርትራ አጎራባቾች ሁሉ ጋር ጦርነት ገጥሟል። የኤርትራዉያን ደም ቢፈስ ምንም የማይመስለው፣ የሕዝቡን ደም በመጠጣት የሚረካ የተረገመ ሰው ነዉ።
በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት፣ በኤርትራ ላይ በርካታ ዉሳኔዎችን አላስልፏል። ከዉሳኔዎቹ መካከል ፣ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ወደ ኤርትራ እንዳይገባ፣ ኤርትራ የጎሮቤት አገሮች ላይ የምታደርሰውን «ሽብር» እንድታቆም፣ ከጎሮቤት አገሮች ጋር ያላትን ችግር በሰላም እንድትፈታ፣ በግዛቷ ያሉ ሽምቅ ተዋጊዎችን መደገፍ እንድታቆም የሚጠይቁ ዉሳኔዎች ይገኙበታል።
እንግዲህ ይሄ የሚያሳየው ከሻእቢያ ተወዳጅቶ የሚደረግ እንቅስቃሴ ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር የሚያጋጭ መሆኑን ነዉ። በተዘዋዋሪ መንገድ የጸጥታው ምክር ቤት ዉሳኔን እየጣሳችሁ ነዉ። የአለም አቀፍ ማህብረሰብን ከበሬታ እያጣችሁ ነዉ። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። በቅርቡ ከግንቦት ሰባት አመራር አባላት ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው የተከበሩ አና ጎሜዝ አዲስ አበባ መሄዳቸዉን እና በዚያም ከነአባ ዱላ ጋር መነጋገራቸው በሰፊው ተዘግቧል። የአና ጎሜዝ ወደ አዲስ አበባ መሄድ፣ የተለያዩ ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል። ነገር ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ የግንቦት ሰባት ድርጅታችሁን የዲፕሎማሲ ሽንፈትና ኪሳራ በግልጽ ያሳየ ነዉ። ግድ የለም ከሻእቢያ ጥገኝነት ዉጡ።
ማጠቃለያ
እንግዲህ የመከራከሪያ ነጥቦቼን በግልጽ አስቀምጫለሁ። እዉነት ለመስማት ከለመፈለግ የተነሳ፣ የቀረቡ ሃሳቦች ላይ ሳይሆን፣ ሃሳብ አቅራቢዎች ላይ ማነጠጠሩን ልትመርጡ ትችላላችሁ። እንግዲህ የእናንተዉ ምርጫ ነዉ። ነገር ግን ተስፋ አደርጋለሁ፣ ቆም ብላችሁ እንደምታስቡ።
ይሄን መረዳት አለባችሁ፣ ነጻነታችንን ኢሳያስ አፈወርቂ አይሰጠንም። ጠዋትና ማታ አገዛዙን ስለረገምን ለዉጥ አናመጣም። በአሁኑ ወቅት ብቸኛው አማራጭ እኛው እራሳችን የምናደርገዉ የተባበረ ሰላማዊ ትግል ነዉ። ኢትዮጵያዉያን በአንድ ላይ ተባብረን፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ጥቂቶች የዘረጉትን ቀንበር መስበር እንችላለን። እባካችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኃይል አሳንሳችሁ አትመልከቱ። ከሻእቢያን ጥገኝነት ዉጡ። ወደ ቀደሞዉ ወደ «ቅንጅት» መንፈስ ተመለሱ። ያኔ በዘጠና ሰባት የጠበቅነዉን ያላገኘነው፣ በቂ ድርጅታዊ ሥራ ስላተሰራና በአመራር አባላት መካከል መከፋፈል ስለተፈጠረ፣ ሕዝቡ በአንድ ላይ በተደራጀት መልኩ፣ በሁሉም ክልሎች ማንቀሳስቀስ ስላልተቻለ እንጂ፣ የሰላማዊ ትግል ስላልሰራ ወይን የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅም ስለደከመ አልነበረም። ካለፈዉ ትምህርት በመዉሰድ፣ ጥንቃቄ በተሞላበት፣ በክልሎች ሁሉ መረብን በመዘርጋት ፣ አቅማችንን፣ ገንዘባችንን በሙሉ አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ የሚደረግ ሕዝባዊ ፣ ሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘምቻ በርግጥ ዉጤት ያመጣል።
ሸንጎ፣ የብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ የመሳሰሉ በርካታ ደርጅቶች ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተማምነዉ፣ አገር ቤት ለሚደረገዉ ሰላማዊ ትግል አጋርነታቸውን እየገለጹ ነዉ። የእናንተ ድርጅት፣ ግንቦት ሰባት፣ ከሻእቢያ ጋር ያለዉን ግንኙነት በአስቸኳይ በጥሶ፣ ከነዚህ ድርጅትች ጋር አብሮ ለመስራት ይሞክር። እዚህ ላይ አበቃለሁ። የሚሰማ ጆሮ ካለ እንግዲህ ይሰማል።