Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ሴትን ልጅ ስቀርብ አልረጋጋም፤ በጣም እፈራለሁ፤ ምን ይሻለኛል?

$
0
0

ውድ የዘ-ሐበሻ የ እንመካከር አምድ አዘጋጅ፡ ዛሬ ችግሬን ይዤ ብቅ ብያለሁና እንደማታሳፍረኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በጣም የዓናፋርነትና የድብቅነት ባህሪይ አለብኝ። ሰዎች ምን ይሉንኛል ብዬ ስለምፈራ የምገልገውን ነገር መጠየቅ አልችልም። ሴት ልጅ ለመቅረብ ዳገት ስለሚሆንብኝ አሜሪካን ሃገር ከመጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴክስ ማድረግ አልቻልኩም። ስለዚህ ራሴን በራሴ አረካለሁ። በፊት እንዲህ ያለ ችግር ነበረብኝ፤ ሆኖም ራሴን አረጋግቼ ነበር፤ ግን አሁን ይህ ችግር ተመልሶ መጥቶብኛል።  ሴት ልጅ ስቀርብ አልረጋጋም፤ በጣም ችግር አለብኝ። ምን ትሉኛላችሁ?          ስሜን ደብቁልኝ

shy boy የኢሳያስ ከበደ ምላሽ፦ ውድ ጠያቂያችን ጥያቄህ ብዙ ማብራሪያ ቢያስፈልገውም የተረዳነውን ያህል ለመመለስ እንሞክራለን። ወደ ጥያቄዎችህ ስንመጣ ግለ ወሲብ መፈፀምህ፣ አይናፋርነትህ፣ ድብቅነትህ፣ ይሉኝተኛነትህና እራስህን መጥላትህ ችግሮችህ እንደሆኑና መፍትሄ እንድንሰጥህ ጠይቀኸናል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያግዙህን ነገሮች ከመጠቆማችን በፊት ችግሮቹ ከምን መነጩ? /መንስኤያቸው ምንድነው?/ የሚለውን መመለሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ የነዚህ ሁሉ ችግሮች መንስኤ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም በራስህ ያለህ እምነት ዝቅተኛ /Low self-confidence/ በመሆኑ ነው፡፡ በራስህ ያለህ እምነት ዝቅተኛ ሲሆን አይንአፋር፣ ይሉኝተኛ፣ ድብቅ እንደምትሆን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይተነትናሉ፡፡ ይህ እምነት ደግሞ የሴት ጓደኛ የመፈለግ ሁኔታህን ደካማ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ግለ ወሲብ ወደ ማድረግ እንድታተኩር ያደርግሃል፡፡ ምክንያቱም ወሲባዊ ፍላጎትህን /sexual desire/ መቀነሻ ብቸኛው አማራጭ ሆኖ ስለሚታይህ ይህን ተግባርህን ደግሞ በተደጋጋሚ ስትፈጽመው ወደ ሱስነት ይቀየራል፡፡ ተነግሮህ እያለ ደግሞ ማቆም አልችል ስትል የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማህና እራስህን ወደ መጥላት ትጓዛለህ፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው ችግሮችህ በራስህ ላይ ባለህ እምነት ምክንያት የመጡ ናቸው ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ በራስህ ያለህ እምነት ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ ከቻለ ችግሮችህ በሙሉ ከመሰረታቸው መነቀል ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱን ችግርህን በተናጠል ለመቅረፍ በመሞከር የችግሮቹን መንስኤ ነቅሶ አውጥቶ መቅረፍ የተሻለ እና አዋጭም ስለሆነ በራስህ ላይ ያለህ መተማመንን ለመጨመር የሚረዱ መፍትሄዎችን ልጠቁምህና አንተም ተግብራቸው፣ በስተመጨረሻ የጠቀስካቸው ችግሮች በሙሉ በራሳቸው ጊዜ ከባህሪህ ውስጥ እየጠፉ ይመጣሉ፡፡ በመጀመሪያ ስለ ራስህ ያለህ እምነት ከየት መጣ? እና እንዴትስ ዝቅተኛ ሆነ የሚለውን መመለሱ ተገቢና አስፈላጊ በመሆኑ በእሱ እንጀምር፡፡

በራስ መተማመናችን እንዴት ተፈጠረ?

አንድ ህፃን እንደተወለደ የሚመራው ንቁ ባልሆነው የአዕምሮው ክፍል /the unconscious mind/ ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውንም ስሜቱን የመደበቅ፣ የመፍራት፣ በይሉኝታ ማለፍም ሆነ ማፈር የሚባል ነገርን አያውቅም፡፡ እያደገ ሲመጣ ከአካባቢው ጋር መስተጋብር የሚፈጥርበትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን /reality/ የሚቃኝበት የአዕምሮ ክፍል ስለሚያስፈልገው ንቁ የሆነውን የአዕምሮ ክፍል /conscious mind/ በመገንባት ከአካባቢውና ከተጨባጭ ዓለም ጋር ግንኙነትን ይፈጥራል፡፡ ይህኛው የአዕምሮው ክፍል የተለያዩ መረጃዎችን በመሰብሰብ ወደ ንቁ ያልሆነው የአዕምሮ ክፍል በማስገባት እዛው ይጠራቀማል፡፡

እነዚህ የተጠራቀሙ መረጃዎች ደግሞ የኔን ማንነት ይወስኑታል፡፡ በመሆኑም በራሴ ያለኝ እምነት ከነዚህ መረጃዎች ይገነባል ማለት ነው፡፡ መረጃዎቹን በሁለት መንገድ ላገኛቸው እችላለሁኝ፡፡ እነሱም፡-

1. ከራሴ ልምዶች፡- /experience/ ልጅ ሆኜ የተለያዩ ነገሮችን መስራት /መሞከር/ እጀምራለሁ፡፡ በዚህን ጊዜ ለመስራት የሞከርኩት ነገር ውጤታማ ከሆነልኝ መስራት እችላለሁ በሚል እምነትን ሳያጎለብት በተቃራኒው ካልተሳካልኝ ደግሞ ‹‹እኔ አልችልም›› የሚል እምነትን እያጎለበትኩ እመጣለሁ፡፡

2. ከሌሎች ሰዎች ገለፃ /Other explanation/፡-

እያደግሁ በምመጣበት ሰዓት እኔ ከራሴ ልምድ ከማገኘው ነገር በተጨማሪ በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች ስለኔ የተለያዩ ገለፃዎችን ለአዕምሮዬ ያቀብሉኛል፡፡ ያም ከአዕምሮዬ ውስጥ ተቀርፆ ይቀርና በራሴ እምነት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ ለምሳሌ አንድን ስራ ለመሞከር ስነሳ ‹‹ተው አትችለውም /አይሆንልህም/›› የምባል ከሆነ ንቁ ያልሆነው የአዕምሮዬ ክፍል እንደማይችል አድርጎ ይቀበላል፡፡ በመሆኑም ለራሴ ያለኝ አመለካከት ዝቅተኛ ሆኖ ያድጋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያንኑ ስራ ስሰራ ‹‹ጎበዝ አንተኮ ትችላለህ›› ወይንም ‹‹አያዳግትህም›› ወዘተ… ከተባልኩኝ እኔ መስራት እችላለሁ የሚል ስሜት /sense of initiative/ አዕምሮዬ ውስጥ ይጎለብታል፡፡ ስለሆነም ለራሴ ያለኝ እምነት ጥሩ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከእነዚህ ሁለት የመረጃ ማግኛ መንገዶች በማገኘው መረጃ መሰረት እያደግሁ ስመጣም በራሴ ያለኝ እምነት እየጨመረ ወይም እየቀነሰ ይመጣል፡፡

(ለዚህ ጽሁፍ የተሰጠው ምላሽ ረዥም ነው። ሙሉውን ለመጨረስ ከፈለጋችሁ በድረ ገጻችን ላይ ማግነት ትችላላችሁ)

በተጨማሪ እያደግንና ወደ ወጣትነት ደረጃ እየገባን ስንመጣ ሁሉን ነገሮች የኛ የማድረግ ፍላጎት ይፈጠርብናል፡፡ በመሆኑም የምፈልጋቸውን ነገሮች ማግኘት አልችልም ስል ‹‹እኔ ደካማ ነኝ፣ አልችልም፣ ይህን ማድረግ የሚችሉት ሌሎች ናቸው፣ እድሌ ጠማማ ነው፣ ወዘተ…›› የሚሉ አፍራሽ ቃላቶችን በተደጋጋሚ መጠቀም እጀምራሁ፡፡ እነዚህን ነገሮች ንቁ የሆነው አእምሮዬ በተደጋጋሚ ሲያብሰለስለውና ምናልባትም ከውጪው ዓለም /ከአካባቢዬ ሰዎች/ ሲነገረው ንቁ ያልሆነው የአእምሮ ክፍል አምኖ ይቀበልና በራሴ ያለኝ እምነት እየቀነሰ ይመጣል ማለት ነው፡፡

ውድ ጠያቂያችን ኤል ያንተን የአስተዳደግ ሁኔታህን ከላይ ከጠቀስኩልህ ሁኔታ ጋር ለማያያዝ ሞክር፡፡ እንደገለፅክልን ቤተሰቦችህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከልጅነትህ ጀምሮ የተለያዩ ነገሮችን የመሞከር እድልህ ዝቅተኛ ነበር፡፡ ብትሞክርም ተው አትችለውም የመባል እድልህ ከፍተኛ ነበር፡፡ በተጨማሪም እስከ ዘጠነኛ ክፍል ጎበዝ ተማሪ እንደነበርክ ከዛ ግን ትምህርታዊ ብቃትህ እየቀነሰ እንደመጣ ነግረኸናል፡፡ ለዚህ መንስኤው ምንድን ነው? ብለን ስንነሳ በመጀመሪያ በልጅነትህ የነበሩት ልምዶችህና ከአካባቢህ ሰዎች ስለ አንተ የሚነገርህ በተለይም ላንተ ቅርብ የሆኑ ሰዎች /significant others/ የነገሩህ ነገር ነው፡፡ በተጨማሪም ወደ ወጣትነት የምትገባበት ዕድሜ በመሆኑና ብዙ ነገሮችን የማድረግ ፍላጎትህ በተለያዩ ምክንያቶች መገደባቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በራስህ ያለህን እምነት ዝቅተኛ አድርገውታል፡፡

ይህንንም የሳልከው ስዕል በሚገባ ይገልፀዋል፡፡ ዛፍ ስር ቁጭ ብለህ ስታነብ የሆነ ቅርንጫፍ ከላይ ሊወድቅብህ ሲል አንተ መሸሽህን ያሳያል፡፡ ምን ማለት ነው የማጥናት ፍላጎት አሁንም እንዳለህ ነገር ግን አንድ ነገር ከሌላ አካል እየመጣብህ እንዳለና አንተ ደግሞ ተቋቁሞ ማለፍ ወይንም መከላከል ስለማትችል እየሸሸህ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በቀላል አማርኛ ለመግለፅ ውጫዊ ግፊት ሲመጣብህ የምትፈልገውን ነገር ትተህ የምትሸሽ ሰው መሆንህን ይገልፃል፡፡ ያ ማለት አንተ ስለ ራስህ ያለህ እምነት ችግሮችን መቋቋምና ማለፍ የማልችል ነኝ›› የሚል ነው ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ ከአካባቢህ በመጡ ገለፃዎችና አንተም በልምድ /በሙከራ/ ካገኘሃቸው ነገሮች በመነሳሳት አሁን ያለህን የራስ እምነት እንድትይዝ ሆነሀል ማለት ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን አሁን ያለኝ የራስ እምነት ዝቅተኛ ነው ብሎ ማሰቡ ሳይሆን ያለህን የራስ እምነት ማሻሻሉ ነው፡፡ በመሆኑም የራስ እምነትህን ለማሻሻል ወደሚያግዙህ ዘዴዎች ጥቆማ ላምራ፡፡

በራስ መተማመንን ለማሻሻል የሚያግዙ ዘዴዎች

አንድ ሰው በራሱ ላይ ያለውን እምነት ለመለወጥ /ለማሻሻል/ የሚያግዙ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እነሱን ተግባራዊ ከማድረጋችን በፊት አንድ ልናውቀው የሚገባ ሀቅ አለ፡፡ ይኸውም አሁን ያለው የራስ እምነታችን ከልጅነት ጀምሮ እያደገ የመጣና አብሮንም የኖረ በመሆኑ ለመለወጥ ስንነሳ ቀስ በቀስ መሆን አለበት፡፡ አንድ ዛፍ በለጋነቱ እየተጣመመ ያደገ ከሆነ ቀጥ እንዲል ከተፈለገ ቀስ በቀስ እያቃናነው መምጣት አለብን፡፡ አለበለዚያ ግን በአንዴ ልናቃናው ከሞከርን መሰበሩ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም የራስ እምነታችንን ቀስ እያልን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻልነው መምጣት አለብን፡፡

ውድ ጠያቂያችን ኤል ይህንን አምነህ ከተቀበልክ በራስ መተማመንህን ለማሻሻል ወደሚያግዙህ ዘዴዎች ላምራ፡፡

1. በመጀመሪያ ወረቀትና እስክሪብቶ ይዘህ የህይወት ታሪክህንና ለወደፊቱ ምን መሆን እንደምትፈልግ ወይንም እንዳለብህ አጠር አጠር አድርገህ ፃፍ፡፡ ይህ ማንነትህን፣ ከየት እንደመጣህና ለወደፊትስ የጉዞ አቅጣጫህ ወደየት እንደሚያመራህ ጠቋሚ ነገር ነው፡፡ ይህንን የፃፍከውን ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት ማታ ልትተኛ ስትልና ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ አንብበው፡፡

2. ሁላችንም እንደምናውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው ፍፁም፡፡ በመሆኑም አንተ ፍፁም እንዳልሆንክና ሁሌም ግን እየተሻሻልክና እየተለወጥክ የምትሄድ ሰው መሆንህን አምነህ ተቀበል፡፡ ብዙዎቻችን ይህንን እናምናለን የምንል ቢሆንም ተግባራችን ግን አይመሰክረውም፡፡ እነሱ ይህንን እየሰሩ እኔኮ መስራት አልችልም ወይንም ለመስራት አልታደልኩም እያልን ስናማርር እንደመጣለን፡፡ ይህ ፈፁም እንዳልሆንን ችግሮች ያሉብን ግን የማንሻሻል መሆናችንን አለመቀበላችንን ያሳያል፡፡ በመሆኑም ራስህን ከሌሎች ሰዎች ጋር አታወዳድር፡፡ ይልቁንም ራስህ ውስጣዊ ደረጃዎችን አዘጋጅና ከአንዱ ወደ ሌላኛው መሸጋገርህ ላይ ብቻ ትኩረት አድርግ፡፡ ትላንትና ቤተሰቦችህን አትረዳም ነበር፡፡ ዛሬ ቤተሰቦችህን ወደ መርዳት መሸጋገር ከቻልክ እየተለወጥክ ነው ማለት ነው፡፡ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የህይወት ዙሪያ ደረጃ አውጣና ትኩረትህን ከአንዱ ወደ ተሻለው ደረጃ መሸጋገር ላይ አድርግ፡፡

3. ጥሩና ደካማ ጎኖችህን የሚያመላክት ሰንጠረዥ አዘጋጅና አስር ጥሩ ጎኖችን በአንደኛው ረድፍ ፃፍ፡፡ አስር ደካማ ጎኖችህን ደግሞ በሌላኛው ረድፍ ፃፋቸው፡፡ ከደካማ ጎኖችህ ውስጥ አንዱን ብቻ ለይተህ አውጣውና እሱኑ ብቻ ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት አድርግ፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎቹን ደካማ ጎኖችህን አታስታውሳቸው፡፡ በተቃራኒው ግን አስሩንም ጥሩ ጎኖችህን በተደጋጋሚ እያቸው አስታውሳቸው፡፡ ከዛም ያን ደካማ ጎን አሻሽየዋለሁ ብለህ ካሰብክ ሌሎቹን ተራ በተራ እያነሳህ ለመለወጥ ተንቀሳቀስ፡፡

4. ቀጥና ቀና ብለው በፍጥነት የሚራመዱ ሰዎች በራሳቸው የሚተማመኑ ብሎም ወዴት እንደሚሄዱ የሚያውቁ ሰዎች እንደሆኑ የስነ ልቦና ባለሙያዎች በጥናት አረጋግጠዋል፡፡ ስለሆነም ቀጥና ቀና ብለህ በፍጥነት መራመድን ተለማመድና ቋሚ ባህሪህ አድርገው፡፡

5. ምንም እንኳ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ቢሰጡህም ሁሌም ልብሶችህን እያጠብክ ንፁህ ልብስ ልበስ /ሽክ በል/፣ አዳዲስ ሰዎች ጋር ስትገናኝ ቀድመህ ስምህን ተናገር፣ ፈገግታ አይለይህ፣ ሰዎች ሲያሞግሱህና ውለታ ሲውሉልህ ትሁት በሆነ መልኩ ምስጋናህን አቅርብ፡፡

6. ብዙዎቻችን ለመልመድ የሚያዳግተን ነገር ግን በጣም ውጤታማ የሆነ ዘዴ ልጠቁምህና ፅሑፌን ላብቃ፡፡ ለራስህ ጊዜ ስጠው፡፡ በቀን ውስጥ ከራስህ ጋር የምትወያይበት 30 ደቂቃ መድብ፡፡ በዚህ በመደብከው 30 ደቂቃ ውስጥ ብቻህን ቁጭ በልና እራስህን በራሱ የሚተማመን፣ እራሱን የሚለውጥና ለወደፊት ያለውን አላማ ጠንቅቆ የሚያውቅ አድርገህ በአአምሮህ በመሳል ተደሰት፡፡ መድረስ የምትፈልገው ደረጃ ላይ ደርሰህ ምን ምን እንደምታደርግ ከራስህ ጋር ተነጋገር፡፡ ለምሳሌ የሀገር መሪ መሆንን የምትፈልግ ከሆነ በዚህች 30 ደቂቃ ውስጥ ስለ ራስህ ስታስብ የሀገር መሪ እንደሆንክና ምን ምን መስራት እንዳለብህ አስብ፣ ከየትኛው ሀገር መሪ ጋር መገናኘት አለብህ፣ ስታገኘውስ ምን ትለዋለህ? ወዘተ…

ውድ ጠያቂያችን ኤል እነዚህን ዘዴዎች በሚገባ ተግባራዊ ካደረክና የሚያጋጥሙህን መሰናክሎች በትዕግስት ማለፍ የምትችል ከሆነ ትልቅ ደረጃ የማትደርስበት ምንም ምክንያት የለምና በብርታት ስራ ባይ ነኝ፡፡

መልካም ጊዜ!!

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>