Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ዘላቂ ጉዳት የማያስከትል ለውጥ!  –አስራት አብርሃም

$
0
0
asrat abereha

አስራት አብርሃም


በአሁኑ ሰዓት የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የማይፈልግ ያለ አይመስለኝም፤ ሁላችንም ለውጥ እንዲመጣ እንፈልጋለን። መሰረታዊው ጥያቄ ግን ዘላቂ ጉዳት የማያስከትል፤ ሁሉንም አሸናፊ፤ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የስርዓት ለውጥ እንዴት ማምጣት ይቻላል? የሚለው ነው። ከደርግ ወደ አሁኑ ስርዓት ለመሻገር እንደ ሀገር ብዙ አላስፋለጊ ዋጋ ከፍለናል፤ የብዙ ኢትዮጵያውያን ቤት ፈርሷል፤ በመቶ ሺዎች ህይወታቸውን አጥቷል፤ አካለ ጎደሎ ሆኗል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የባህር በራችን አሳልፈን እንድንሰጥ ተደርገናል፤ ይሄኛው ከደረሱብን ጉዳቶች ሁሉ የከፋ፣ ለቀጣይ ትውልዶች ሳይቀር ዋጋ የሚያስከፈል ነው። አሁን ማሰብ ያለብን እንደነዚህ ዓይነቶቹ ተጨማሪ ጉዳቶች ሳናስተናግድ እንዴት ነው ከዚህ መንግስት መላቀቅና የተሻለ ስርዓት ማምጣት የምንችለው የሚለው ጉዳይ ነው። ለዚህ የተሻለ መፍትሄ ለማግኘት በጉዳዩ ላይ በስፋትና በጥልቀት መወያየት፣ መግባባት መቻል አለብን፤ ፍላጎቶቻችን ማቀራረብና ማስማማት መቻል አለብን።

ስርዓቱን የሚቃወም ሁሉ ለውጥ ለውጥ ፈላጊ መሆኑ እውነት ቢሆንም ሁሉም ግን ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ እየታገለ ነው ማለት አይቻልም። አንዳንድ የምናያቸው ምልክቶችም የሚያሳዩት ይህኑኑ ነው። ስለመጭው ጊዜ፣ ስለሀገር አንድነት፣ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት ስለሚኖርባት ኢትዮጵያ እያሰበ የሚታገለው ኢትዮጵያዊ ድምፁ እየሰለለ ነው፣ እዚህም እዚያም በጎጥ በተደራጁ ቡድኖች እየተዋጠ ነው ያለው። አንዳንዶች ደግሞ አንድም በተስፋ መቁረጥ አንድም ደግሞ በራራቸው መንደር በሚኖረው ጊዚያዊ ሞቅታ ልባቸው እየተሰለበ ከነበሩበት የዜግነት ከፍታ ወርደው ወደ ጎጣቸው ገብቷል፤ እርግጥ ነው በዚህ መንገድ መታገል ቀላልና ጥረት የማይጠይቅ ነው። በጎጥ ተደራጅቶ እንደፈለጉ ማውራት፣ በቀላሉ ህዝብን ማነሳሳትና ማሰለፍ ይቻላል። ዘላቂ ውጤት፣ ሰላምና አብሮነት ማምጣት ባይቻልም፤ ለራስህ ጠባብ ቡድን ጊዜያዊ ድልና ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል በህወሀትም እያዩት ስለሆነ ሊያጓጓቸው ይችላል።

በመሆኑም እኔ በዚህ ፅሁፍ በወደፊቷ ኢትዮጵያ የሁሉም የዜግነት መብት በእኩልነት የሚረጋገጥበት፤ ተከባብሮ በፍቅርና በአንድነት መኖር ስለሚቻልበት ነው ሀሳብ መስጠት የምፈልገው። ከአሁን በፊት እንደገለፅኩት ሁላችንም በኢትዮጵያ የተገኘነው መርጠነው አይደለም፤ ተፈጥሮ ነች አንድ ላይ እንድንሆን ያደረገችኝ። መለያየት ብንችል እንኳ ሀሳባዊ ልዩነት እንጂ ከቦታው ነቅለን መሄድ የምችል አይደለንም። ስለዚህ አንድ ላይ መኖር እጣ ክፍላችን ከሆነ እንዴት ነው አብረን ሳንጎዳዳ፤ ተጠቃቅመን፤ ተደጋግፈን መኖር የምንችለው የሚለው ጉዳይ ላይ መነጋገር አለብን።

በአሁኑ ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች የተለያዩ ሀሳቦች እየሰጡ ነው ያሉት፤ እኔም የበኩሌን ሳቀርብ ሀሳቡን ለማዳበር ይረዳ ይሆናል በሚል እምነት ነው። ከሌሎች፤ ከሚመስሉኝ ሰዎች ጋር ሆኜ በጋራ ለመስጠት ብችል ደስ ይለኝ ነበር፤ ነገር ግን በፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ እንዳይሆን የነበርኩበት ፓርቲ (አንድነት) ተወስዷል። ከዓረና ከወጣሁም ቆይቻለሁ (ይሄ የምለው አንዳንድ ሰዎች አሁንም ዓረና የምመስላቸው ስላለሁ ነው) በእርግጥ ዓረና ሲታሰብ ጀምሮ የነበርኩበት፤ የፖለቲካ ጥርሴ የነቀልኩበት፤ በሁኔታዎች የማይለዋወጡ ጓደኞች ያፈራሁበት ቢሆንም በአንዳንድ አካሄዶች ላይ በነበረኝ ልዩነት ምክንያት ከፓርቲው እንደተለየሁ የሚታወቅ ነው። ከተለመደው የሀገራችን የመለያየት ባህል በተለየ ሁኔታ በሰላምና በክብር ነው የተለየሁት። ስለዚህ ከቀድሞ የአንደነት አመራሮች ጋር በግል ከማደርጋቸው ውይይቶች ውጪ በአሁኑ ሰዓት የየትኛውም ፓርቲ አባል አይደለሁም።

ወደ ዋናው ዳጉይ ስገባ፣ በመጀመሪያ ምን እናድርግ በሚለው ጉዳይ ላይ እየቀረቡ ባሉት አማራጮች ላይ የራሴን ምልከታ ላስቀምጥና ወደ መፍትሄ ሀሳብ እሻገራለሁ። በአንዳንድ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ ቡድኖች በቀዳሚነት እየቀረበ ያለው አማራጭ የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚል ነው። የሽግግር መንግስት ጥያቄ አቶ ግርማ ሰይፉ እንዳሉት ያለህዝብ ውክልና በአቋራጭ ስልጣን የሚገኝበት መንገድ እንጂ በአሁኑ ሰዓት አዋጭ የመፍትሄ ሀሳብ አይደለም፤ ኢህአዴግም በዚህ መንገድ ወደ ድርድር ማምጣት የሚቻል አይመስለኝም፤ ይህን የሚያደርግበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል ብዬም አላስብም። ስለዚህ የሽግግር መንግስት የሚለው አማራጭ አሁን ባለው ሁኔታ እውን የሚሆን ነገር አይደለም፤ ከዚህም ባሻገር ደግሞ ሁሉንም ነገሮች ከዜሮ እንዲጀመር የሚያደርግ በመሆኑ ጠቃሚነቱም ያን ያህል ነው።

ሁለተኛው አማራጭ የባለአደራ መንግስት ነው። ይህ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሲቪል ተቋማት፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የባለአደራ መንግስት ተቋቁሞ ሀገሪቱን በጊዚያዊነት እንዲመራ ማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነቱ መንግስት ሰላምና ስርዓት ለማስፈን ሰራዊቱንና የፀጥታ አካላትን እንዴት አድርጎ ሊያዛቸው እንደሚችል ግልፅ አይደለም፤ ምን ዓይነት የህግ መሰረት እንደሚኖረውም ለመገመት የሚያስቸግር ነው። ከሽግግር መንግስትም ብዙ የሚለይ አይመስልም፤ የሚለየው ነገር ቢኖር የሽግግር መንግስት በፖለቲካ ኃይሎች የሚቋቋም መሆኑ ላይ ነው።

በሶስተኛው ረድፍ የሚቀመጡት ደግሞ ከኢህአዴግ ጋራ ጥምር መንግስት መመስረት የሚፈልጉ ናቸው። ከሁሉም በላይ ይሄ አማራጭ የከፋ ይመስለኛል። አንዳንድ የስልጣን ጥማት ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች በአቋራጭ ስልጣን እንዲያገኙ ይረዳ እንደሆነ እንጂ ወደ ለውጥ ጎደና የሚወስድ አይደለም። በአንፃሩ ገዢው ፓርቲ ራሱን ዳግም ለማጠናከር እድል የሚሰጥ ነው የሚሆነው። ከኢህአዴግ ባህርይና አሁን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ካየነው የጥምር መንግስት ጥያቄ የፖለቲካ ሽርሙጥና ነው። በእርግጥ ጥምር መንግስት መመስረት ተገቢ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፤ ህዝባዊ ምርጫ ተካሄዶ አንዱ ፓርቲ አሸናፊ ሳይሆን ሲቀር ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ፓርቲዎች ባገኙት የህዝብ ድምፅ መሰረት ድርድር አድርገው በስምምነት የጥምር መንግስት ሊያቋቁሙ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ የሆነ ጥምር መንግስትም እንበለው ሽግግር መንግስት ዘላቂ መፍትሄ የማያመጣ ያለህዝብ ውክልና በአቋራጭ ስልጣን ፍለጋ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ ለእኔ የተሻለ አማራጭ የሚመስለኝ ፓርላማውን በትኖ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ነው። ኢህአዴግ ከልብ ለበጎ ነገር የሚነሳ ከሆነ፣ በዚች ሀገር ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ከቆረጠ ማድረግ ያለበት በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ፣ በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ፤ በሰላማዊ መንገድም በጥትቅም እየተንቀሳቀሱ የሚገኙትን ቡድኖች ሁሉ ጠርቶ ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡና በሰላም እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ነው፤ ቀጥሎ ምርጫ ቦርድን ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተነጋግሮ በስምምነትና በመተማመን አዲስ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም፤ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ እንዲካሄድ አድርጎ በህዝብ ለተመረጠው አካል ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ማስረከብ ነው።

እዚህ ላይ መታየት ያለበት ዋናው ነገር ሁሉንም ነገር እንደአዲስ ከመጀመር ይልቅ አሁን ያሉትን የመንግስት ተቋማት ገለልተኛ ሆነው የሚሰሩበትና የሚጠናከሩበት መንገድ ነው። ለምሳሌ ጦር ሰራዊቱ ከላይ ያሉትን የጦር አዛዦች ጡረታ እንዲወጡ በማድረግ የብሄር ተዋፅኦ የጠበቀ አመራር እንዲኖረው በማድረግ ማስተካከል የሚቻል ነው። የደህንነት መስራቤቱንም እንደዚሁ፤ ሌላውም በተመሳሳይ መንገድ ማስተካካል ይቻላል። ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ሙሉ ለሙሉ መፍረስና መቀየር ያለበት ምርጫ ቦርድ ነው፤ ከሁሉም ገለልተኛ የሆነ በሁሉም ዘንድ ተአማኒነትና ከበሬታ ያለው፤ በሰው ኃይል፤ በአደረጃጀት ጠንካራ የሆነ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም ያስፈልጋል።

ሌላው መስማማት የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር የህገ መንግስት ማሻሽያ ጉዳይ ነው፤ ህገ መንግስቱ ለሚደረገው የስርዓት ለውጥና እንዲኖር ለሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሚያመች መልኩ መሻሻል መቻል አለበት። በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖረው አስተዳደርም ለልማትና አስተዳደር በሚያመች መልኩ፤ የብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳችው የማስተዳደር መብት ሳይገፋ፤ ቋንቋቸውን ለመጠቀም፣ ባህላቸውን ለመጠበቅና ለማሳደግ እንቅፋት በማይሆን መልኩ መስተካከል አለበት። ይህ ማለት ግን አንድ ቋንቋ የሚናገር ሁሉ በአንድ ክልል መጠቃለል አለበት ማለት ላይሆን ይችላል። ይህም የሚሆነው በህዝብ ፍላጎትና ፍቃደኝነት ተመስርቶ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ አከባቢዎች ያሉት የአከላለል ጥያቄዎች በኗሪው ህዝበ ውሳኔ እንዲፈቱ በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚደረግባቸው መስማማት ያስፈልጋል። እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ ግን መደረግ ያለባቸው ቅድመ ሁነቶች ይኖራሉ፤ ከላይ ለመግለፅ እንደፈለኩት ኢህአዴግ ስልጣኑን በህዝብ ለተመረጠ አካል ለማስረከብ ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጥ መቻል አለበት። በምትኩ ለኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚሰጥ ልዩ ልዩ ዋስትና ሊኖር ይችላል።

በነገራችን ላይ “የኢህአዴግ ባለስልጣናት ስልጣን ይልቀቁልን እንጂ በወንጀል ያለመጠየቅ ዋስትና መስጠት ይቻላል” የሚሉ አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ እኔ የተለየ አቋም ነው ያለኝ። “አተርፍ ባይ አጉዳይ” እንደሚባለው ወንጀልና ወንጀለኞችን ማበረታታት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በግልፅ የሚታወቅ በተለይ ከሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር የተገናኘ ወንጀል ያለባቸው ባለስልጣናት ያለመክስስ መብት ሊሰጣቸው አይገባም። በአንፃሩ ምንም ወንጀል የሌለባቸው የስርዓቱ ባለስልጣናት በሰላም የመኖር መብት ሊከበርላቸው፤ ከዚያም ባሻገር በቀሪ ህይወታቸው ሊያኖራቸው የሚችል ነገር ሊሰጣቸው ይችላል።

ዋስትና ስለመስጠት ጉዳይ መነጋገር ካለብን በእርግጥም ዋስትና የሚያስፈልገው የትግራይ ህዝብ ነው። በተለይ ከክልሉ ውጩ የሚኖረው ትግርኛ ተናጋሪ ዜጋ ከለውጥ በኋላ አሁን ካለው ስርዓት ጋር በተያያዘ ምንም ነገር እንደማይደርስበት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እንደማነኛውም ዜጋ በፈልገው ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት፤ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። ይህ ስጋት ተገቢ ይሁንም አይሁንም ሊታይና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በእርግጥም ይሄ ሀሳባዊ ስጋት አይደለም፤ በአሁኑ ሰዓት በኢህአደግ በኩልም በአንዳንድ ፅንፈኛ ኃይሎችም ተደቅኖበት ያለ ስጋት ነው። ስጋት ካለ ደግሞ አንድም የለውጡ ሂደት የሚያዘገየው ነው የሚሆነው፤ ሌላው ደግሞ የሆነ ህዝብ መስዋዕት በማድረግ የሚመጣ ለውጥ ከሞራልም ከህግም አንፃር ተቀባይነት የለውም፤ ይሄ የህወሀት መንገድ ነው። ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ሲደርስ የነበረው መፈናቀል፤ ጭቆናና ስቃይ ዳግም በየትኛውም ህዝብ ላይ እንዲደርስ መመኘት የለብንም። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት የሚታገል ማነኛውም ኃይል አንድን ህዝብ በሌላ ህዝብ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ተደጋጋሚ ስህተት አይሰራም፤ የጥላቻ፣ የፍረጃና የፍርሀት ፖለቲካም አያራምድም።

በተወሰነ መልኩ በጎንደርና በመተማ አከባቢዎች እንደተየው ዓይነት በስርዓቱ ምክንያት የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጠር ያልነበረበት ነው። እንዲህ ማድረጉ ለትግሉም የሚጨምረው ነገር የለም፤ በእርግጥ “ከስርዓቱ ጋር ግንኙበት ያላቸው ብቻ ናቸው ጥቃት የደረሰባቸው” የሚል ነገር ተደጋግሞ ሲነግር ሰምቻለሁ፤ በእነዚህ አከባቢዎች ከሚኖረው የትግራይ ተወላጆች ብዛት አንፃር ጉዳት የደረሰባቸው ጥቂት መሆናቸው ሲታይ የተባለው እውነትነት ሊኖረው እንደሚችል መገመት ይቻላል። ነገር ግን አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር አለ፤ አንድ ሰው ከስርዓቱ ጋር ያለው ትስስር በማስረጃ ማረጋገጥ የሚችል የተደራጀ አሰራር በሌለበት ህዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ንፁሃን ሰዎች አይጎዱም ማለት አይደለም። በራሴ አቅም በተለያየ መንገድ ለማጣራት ሞክሬ የተረዳሁትም ይሄኑኑ ነው። በአጋጣሚው ንፁሃን ዜጎች ላይም ጉዳት ደርሷል። በመሰረቱ ህዝቡ በየአከባቢው እንደመሰለው እርምጃ ይውሰድ ብሎ መቀስቀስ በደርግ ጊዜ እንደነበረው ዓይነት ሁኔታ መፍጠር ነው የሚሆነው፤ በየቀበሌው ለሚገኘው አብዮት ጥበቃ ሳይቀር እንደመሰለው እርምጃ እንዲወስድ በመፈቀዱ ጉዳዩ ሀገር ከመከላከል ወደ ግል ቂም በቀል ወርዶ የብዙ ንፁሃን ህይወት ጠፍቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ ስርዓትና ቁጥጥር የሌለው እርምጃ እንዲኖር መፍቀድ በህዝብ ላይ ጉዳት ማድረስና ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ማድረግ ነው የሚሆነው። የዘር ፍጅትም የሚከተለው እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ነው።

ስርዓቱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ማውገዝ አለብን፤ መታገልም ያስፈልጋል። በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈፀመው የህይወት መጥፋት እጅግ የሚያንገበግብ ነው፤ የወገን ህይወት ነው የጠፋው፤ የወገን ደም ነው የፈሰሰው፤ ይሄ መታገል ያስፈልጋል። ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው አካላትም ተለይተው በህግ መጠየቅ አለባቸው። ህወሀትን ይደግፋሉ በሚል መነሻ ጥረው ግረው በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ማድረስ ግን ፈፅሞ ተቀባይነት ያለው ጉዳይ አይደለም። ህወሀት ባጠፋ ቁጥር የራስ ወገን በሆነ የትግራይ ህዝብ ላይ ጥቃት ማድረስ መቼም ቢሆን ተገቢነት ሊኖረው አይችልም። እንኳን ዛሬ ዓለም በሰለጠነበት፤ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ በሆነበት ዘመን ቀርቶ በድሮ ጊዜም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ ነገር ተቀባይነት አልነበረም። ለዚህ አንድ የሚገርም በአፄ ምኒልክ ዘመን የሆነ ጉዳይ ብጠቅስ ደስ ይለኛል፤ የእንደርታ ገዥ የነበሩት ደጃች አብርሃ በማመፃቸው ምክንያት በሸዋና በሌሎች አከባቢዎች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ደርሶ ነበር ይባላል፤ በዚህ ምክንያት አፄ ምኒልክ አዋጅ አውጥተው ነበር፤ እንዲህ የሚል፦

…አንድ ሰው ደጃች አብርሃ ቢከዳ እዚህ የተቀመጡትውን እኔን የሚወደኝን የትግሬ ሰወ ሁሉ ታስቀይማለህ አሉ። አባያ ወንድሙ ይታሰርበታል እንጂ ይታረዳልን። አሁንም ዳግመኛ በአደባባይ ያለውን የትግሬ ሰው የሚያስቀይም ነገር የተናረ ትቀጣለህ። አደባባይ ያለውን የትግሬ ሰው የሚያስቀይም የተናገረውን ተያይዘህ አምጣልኝ ዳኝነት ይታይልሃል።

                    (የአጤ ምኒልክ የሀገር ውስጥ ደብዳቤዎች፣ ገፅ 589)

የድሮ መሪዎቻችን ቢያንስ ፈሪሃ እግዚአብሄር የነበራቸው በመሆኑ ከአሁኖቹ በእጅጉ ይሻላሉ። የራሳቸው የሆነ ጥሩ ነገርም እንደነበራቸው የምንረዳው እንዲዚህ ዓይነቱ ነገር ስናገኝ ነው። በሌላ በእኩል ደግሞ አሁን ያለንበት ሁኔታ፣ የሞራል ድቀት ከመቼም ጊዜ የከፋ መሆኑ እንረዳለን። ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መጠቀል አለባቸው፤ ግን ደግሞ በስርዓቱ ላይ ያነጣጠሩ እንጂ ፍፁም ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ መሆን የለባቸውም፤ እንደዚህ ዓይነት አሰራር በግልፅ ነው መወገዝ ያለበት። በራስ ወገን ላይ በፖለቲካ ምክንያት ጥቃት ማድረስ ዘላቂ ሰላምና አብሮነትም የሚፈጥር አይሆንም። በአንድ ወገን የሚኖርን ተቃውሞና ውግዘት በመፍራት ዝም መባል የለበትም፤ እንደህ ዓይነቱ አካሄድ አደርባይነትና እወደድ ባይነት ነው (opportunism and populism) ነው።

እስካሁን እንደታዘብኩት በዚህ ጉዳይ ላይ አፅንኦት ሰጥተው ሲናገሩ የሰማቸው ፕሮፌስር መስፍን ወልደማርያም እና ፕፎሰፌር ብርሃኑ ነጋ ይመስሉኛል። ፕሮፈሴር መስፍን ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ “ወያኔን ትግሬ እያደረጉ፣ ትግሬን ሁሉ ወያኔ እያደረጉ የሚኬድበት ሁኔታ መታረም አለበት፤ አደገኛ መርዝ ነው፡፡ሀገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡” ማለት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በትግራይ ህዝብ እየተደገሰ ያለው አደጋ እንደሚያሳስባቸው ተናገሯል። ፕሮፈሴር ብርሃኑ ነጋም በዴምህት ሁለተኛ ጉባኤ ላይ “ከትግራይ አብራክ የወጡና ይህን ስርዓት የሚቃወሙትን በቆራጥ ወኔ ነው የምናደንቀው” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ንግግር የጥላቻ ፖለቲካ ስለሚያራምዱ ወገኖች እንዲህ ብሏል፦

…ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጉልበትነት እንጠቀምበታለን ብለው የሚያስቡ አክራሪና አጥፊ ኃይሎች ትግሉን ወደ ጥላቻ ትግል ለማስቀየስ የሚሞክሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ እናውቃለን። እንደነዚህ አይነት ጥቂት ኃይሎች በህዝቡ ትግል ውስጥ ተመሽገው የሚወስዷቸው እርምጃዎችንና የሚያካሂዷቸውን የጥላቻ መርዛማ ፕሮፓጋንዳ ህወኃት/ኢህአዴግን ስለተቃወሙ ብቻ ዝም ብለን “የህዝቡ ትግል አካላት ናቸው” ብለን የምናልፋቸው ሊሆኑ በፍጹም አይገባም። እንዲህ አይነት እኩይ ኃይሎችን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን አስቀያሚ ገጽታቸውን በሚያሳዩበት ጊዜ ሁሉ እነሱን ማጋለጥና ከህዝቡ ፍትሀዊ ትግል ማግለል ለእውነትና ለፍትህ፤ ኢትዮጵያችንን ከተጋረጠባት አደጋ ለመታደግ፤ ብሎም ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንታገላለን የምንል ኃይሎች ሁሉ ያለማሰለስ ልንሰራው የሚገባን ስራችን ነው።

ይህ የሁሉም ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ አቋም ነው ሊሆን የሚገባው፤ እንደ ዜጋ ከፍ ሲል ደግሞ እንደሰው ለሰብአዊነት፣ ለእውነትና ለትክክለኛነት መቆም ያስፈልጋል። በመሰረቱም አንድን ህዝብ በጠቅላላ ማስፈራራት ውጤት የሚያመጣ ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ህዝቡ የስርዓት ለውጥ ቢመጣ ስለሚኖረው የተሻለ ነገር በማስረዳት ነው ማሰለፍ የሚቻለው። ከለውጥ በኋላ ከህወሀት ጋር በተያያዘ ምንም የሚደርስበት ጉዳት ሊኖር እንደማይችል፤ እንደማነኛውም ዜጋ አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ በነፃነት ሰርቶ የመኖር መብቱ እንደሚከበርለት ማሳየት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የዘረኝነት ቅስቀሳ የሚያካሄዱ ግለሰቦችና ቡድኖች በማሻማ ሁኔታ ማውገዝና ራስን ከእነዚህ አካላት መለየት ያስፈልጋል። ከእስትራቴጂ አንፃርም የተደባለቀ ትግል ለውጤት የሚበቃ አይደለም፤ ለውጤት ቢበቃም እንኳ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ አይችልም፤ ሀገር ከመበታተን፤ ህዝብ ለህዝብ ከመተላለቅ የሚያድን አይደለም። አዋጪው መንገድ ኢትዮጵያ የሁላችን እንድትሆን፤ የጋራ ራዕይና ህልም መፍጠር እንጂ የተወሰነ ህዝብ በመነጠል እንዲመጣ የምንፈልገው የተሻለ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ጠቡ ህዝብ ለህዝብ ስለሚሆን አሸናፊ ወገን አይኖርም፤ ተያይዞ መውደቅ ነው የሚሆነው፤ የፖለቲካ ኃይላት ናቸው ሊሸናነፉ የሚችሉት፤ ህዝብ እንደህዝብ ሊሸነፍ አይችልም።

የመጣህበትን ህዝብ ከቻልክም ደግሞ በማነኛውም ህዝብ ላይ በደልና ጭቆና ሲደርስ መጮህና መታገል ተገቢ ነው። ከዚህ ባለፈ ሁኔታ የራስህን ህዝብ የተጎዳ፣ ከሌላው በተለየ ሁኔታ አደጋ ያንዣበበት በማስመሰል ፖለቲካ መስራትና የኑሮ መሰረት እንዲሆን ማድረግ ከሞራልም ከሰብአዊነትም አንፃር ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ነው። በተለይ ለለውጥ ከሚታል ሰው የሚጠበቅ አይደለም። አብሮ ለዘላለም የሚኖር፤ ተለያየቶ ላይለያይ ህዝብ መሀል ዘላቂ ጠብና ቂም መፍጠር ተገቢ አይደለም። ስልጣን መፈለግ ኃጢአት ባይሆንም በዚህ መንገድ የሚገኝ ስልጣን ግን ቢቀር ነው የሚሻለው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከቋንቋ በስተቀር በዘርም፣ በኃይማኖትም፣ በባህልም፣ በመልክም አንድ ዓይነት በሆነው የትግራይና የጎንደር ህዝብ ማሀል የጥላቻ ግንብ እንዲገነባ ማድረግ ይቅር የማይባል ስህተት ነው። ለወደፊት በሚኖሩት ትውልዶች ፊትም የሚያሳፍር ኋላቀር ተግባር ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ የትግራይና የአማራ ህዝብ ተመሳሳይ ዕጣ ክፍል ያለው፤ ተደጋግፎና ተገባብቶ ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ ተፈጥሮም ታሪክም ያልሰጠው ህዝብ ነው። በመሰረቱ በሁለቱም ወገን ባሉት የስልጣን ኃይሎች እንጂ በሁለቱም ህዝብ መሀል ጥላቻ አለ ብዬ አላምንም።

የምናደርገው ትግሉ ሁሉም የሚያሳትፍ፤ ለሁሉም ተስፋ የሚሰጥ፤ በማንም ህዝብ ላይ ስጋት የማይፈጥር እንዲሆን መጣር ያስፈልጋል። እንኳን በአንድ ሀገር የሚኖር፤ በደም፣ በአጥንት፣ በታሪክ፣ በዜግነት የተሳሰረ ህዝብ ይቅርና ከአውሮፓ ድረስ መጥተው ለብዙ መቶ ዓመታት ህዝቡን በቀኝ ግዛት ይዘው ሲገዙትና ሲጨቀኑት የነበሩትን የደቡብ አፍሪካ ነጮችም የሚያቃፍ ትግል እነማንዴላ አድርጓል። ታሪክ ሰርተው፤ ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚያገለግል ስርዓት መስርተው አልፏል፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም እንዲህ ያለ የተገባ ትግል እንዳናከሄድ የሚያግደን ነገር ምንድነው?!

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>