Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የማለዳ ወግ…በጅዳ 3 ሽህ ታዳጊዎችን ለመታደግ መምህራን ሲተጉ … ! -ነቢዩ ሲራክ

$
0
0

* በጅዳ የኢትዮ አለም አቀፍ ት/ቤት ዘንድሮም በአደጋ ላይ
* በትውልድ ላይ መቀለድ ይቁም … !
* መምህራንና ሰራተኞችን ተቆጥተዋል

እለተ ሃሙስ መስከረም 19 ቀን 2009 ዓም ምሽት ላይ በጅዳ አለም አቀፍ ት/ቤት ዙሪያ አንድ ሰበር መረጃ አቅርቤ ነበር ። ሰበሩ መረጃ ለአመታት ከግል ጥቅማ ጥቅም ባለፈ ከሶስት ሽህ በላይ (3000) ታዳጊ ኢትዮጵያውያንን ተማሪዎች ጉዳይ “ያገባናል ” ብለው የማያውቁት መምህራን ዘንድሮ ” ያገባናል ” ብለው ከጅዳ ኮሚኒቲ አመራሮችን ጋር ስብሰባ ላይ መፋጠጣቸውን ይመለከት ነበር ። ዛሬ የምናዎጋው በስብሰባው ዙሪያ ቢሆንም እንደ መግቢያ ትናንት መምህራኑ ሲዎሱ አሞን የባጀው ግዴለሽነትና ዝምታቸውን እናዎሳለን ፤ ዛሬም ሌላ ቅን ነውና መምህራኑ ለታዳጊዎች መብት መከበር ያሳዩትን ትጋት በጨረፍታ እንቃኛለን ! የፈቀደ ይከተለኝ …

nebiyu-1-satenaw-news

አሞን የባጀው የመምህራኑ ግዴለሽነትና ዝምታ …
===========================
አዲስ አመት በመጣና በሄደ ቁጥር ሁሌም ለጅዳና አካባቢው ቀዳሚው ህመም “የትምህርት ማዕከሉ አደጋ ላይ ወደቀ !” የሚለው መረጃ ነው ፤ በእርግጥም የትምህርት ማዕከሉ ማደግ ባለበት ፍጥነት ቀርቶ ለመቀጠል አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ የመኮላሸት አደጋው መረጃ አሳሳቢ ነው ። ይህ ላለፉት በርካታ አመታት ወላጅ ነዋሪውን ሲያመን ቢከራርምም የውስጥ ብክለቱን አሳምረው ከሚያውቁት ከመምህራን የሚሰማው ሮሮ በተናጠል ከንፈር ከመምጠጥ የዘለለ እንዳልነበር በቅርብ የምናውቅ የምንመሰክረው እውነታ ነው ። ተማሩ ተመራመሩ የተባሉት መምህራን የውስጥ ችግሩን እያወቁና ትውልድ የሚቀረጽበት ማዕከል ወዳልተፈለገ አደጋ እየተጓዘ ዝምታን መርጠው ከርመዋል ። ባንድ ወቅት ” ት/ቤቱ አስተዳደርና ኮሚኒቲው በመኖሪያ ፍቃዳችን ዝውውር ዙሪያ መጉላላት አደረሰብን !“ ብለው የማስተማር ማቆም አድማ አድርገው መብታቸውን ያስከበሩ መምህራን የታዳጊዎችን የትምህርት ማዕከልን የውስጥ ገመና ከማናችንም በላይ እያወቁትና ችግሩን ለመፍታት ቀዳሚ መሆን ሲገባቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ከርመው አሳዝነው ያውቃሉ ። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ልጅ ወልደን በአሳር በመከራ የምናሳድግ ስደተኞች ልጆች ትምህርት አሰጣጥና ግዙፉ የመቀጠል ያለመቀጠል አደጋን ችግር ቀድመው ቢረዱና መድሃኒቱን ቢያውቁትም ሊያክሙት ተስኗቸው ባጅቷል … እኒሁ ተስፋ የጣልንባቸው መምህራን እንኳንስ በታዳጊዎች መማሪያ ማዕከል የመጣውን ችግር ሊቀርፉ የውስጥ ህብረት አጥተው ግዙፉን ችግር በግድ የለሽነትና በትዝምታ ማለፍ መምረጣቸው መላ ነዋሪው አስከፍቶና አሳዝኖን መክረሙም ሌላው የማይደበቅ ነጭ እውነታ ነው …

አደጋው ገዝፎ መምህራን ሲቆጡ …
==============================
ዘንድሮ ግን ነገሮች ተለዋውጠዋል ፤ በጅዳ አለም አቀፍ ት/ቤት መምህራንና ሰራተኞች በህብረት ተቆጥተው ታይቷል ፤ ምክንያታቸው ደግሞ ከሶስት ሽህ (300) በላይ ታዳጊ ተማሪዎች ትምህርት የሚገበዩበት ማዕከል እያደር የመዝቀጡ እውነታ ገንፍሎ መውጣቱ ነበር ። መምህራንና ሰራተኞች ከላይ እስከታች ፤ ከኮሚኒቲው እስከ ት/ቤቱ አስተዳደር በኢህአዴግ አደረጃጀት በተዋቀረው አመራር የውስጥ ህብረት አጥተውና ተፈራርተው ቢባጁም ዘንድሮ እንደባጁት ፈርተው መቀጠልን አልፈቀዱም ። ለአመታት አርቆ የያዛቸውን ፍርሃት ሰብረው ከመውጣት ባለፈ ተቀናጅተው ወደ ትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ቀርበው ” ግፍ በዝቷልና ሊቆም ይገባል ” ብለው ድምጻቸውን ማስማት ጀምረዋል ። በትምህርት ማዕከሉ የሚሰራው ሸፍጥና ግፍ ” መቆም አለበት” በማለት ተቃውሞ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል ! ከሶስት ሳምንት በፊት የተቆጡት መምህራንና የት/ቤቱን ባለቤት ከሆነው የኮሚኒቲውን አመራሮች ጋር ለመምከር ደጋግመው ቢጠይቁም አመራሩ እድል አለመስጠቱ ይጠቀሳል ። ዳሩ ግን ኮሚኒቲው አሻፈረኝ ሲል የወላጅና መምህራን ህብረትን በማማከር ወደ ቆንስላው ኃላፊዎች ቀርበው ብሶታቸውን ቢያሰሙም “ ህብረታችሁን አጽንታችሁ ከተጓዛችሁ ወላጁን በማቀፍ ለውጥ እንደምታመጡ ለታዳጊዎች ማዕከል ማንሰራራትና ትንሳኤ ተስፋ ያለው በእናንተ በመምህራን ላይ ነው ” ከሚል ዲፕሎማሲዊ የኃላፊዎች ምላሽ ባለፈ ላቀረቡት ስሞታ የረባ መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው ከአስተባባሪዎች መካከል አንድ መምህር አጫውተውኛል … በያዝነው ሳምንት ግን ሳይታሰብ የኮሚኒቲው አመራር ከመምህራኑ ጋር ለመገናኘት ፕሮግራም መያዛቸው በተነገራቸው መሰረት ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2009 ዓም ምሽት ተቃውሞ ጥያቄያቸውን ከትምህርት ቤቱ ባለቤት ለት/ቤቱ አስተዳደር ፤ ለት/ቤቱ ባለቤት ለጅዳ ኮሚኒቲ አመራር አባላት እና ለመንግስት ዲፕሎማቶች አቅርበዋል !

በጦፈው ስብሰባ ምን ተባለ … ?
===========================
በእርግጥም ሐሙስ ምሽት የጅዳ ኮሚኒቲ አዳራሽ መምህራንና ሰራተኛች በነቂስ ተገኝተዋል ፤ በት/ቤቱ በኩል ስብሰባው ይጀምራል ተብሎ የተነገረው ሰዓት የተወሰነ ክፍተት ቢፈጥርም ስብሰባው ዘግይቶ ጀመረ … አጀንዳ ያልያዙት የኮሚኒቲው አመራሮች ያለ አጀንዳ ስብሰባውን መምራት ሲጀምሩ እርምት ተደረገ … እናም በቀጥታ ወደ ውይይቱ ተገባ ፤ መምህራን ጥያቄያችውን አዘነቡት … እንዲያ እያለ ቀጠለ ! …በእርግጥ መረጃውን ሳዳምጠው ማመን አልቻልኩም ፤ ብዙዎች እንደኔ መገረማቸውንም ሰምቻለሁ … በጦፈው ስብሰባ የተሰማው የመምህራንና ሰራተኛ ጥያቄ ፡ ቁጣ ፡ ሮሮና ተማጽኖ በወገናዊ ስሜት የተነገረ ፤ ከዚህ ቀደም ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ ነበር ማለት ይቻላል !
…በዚሁ ስሜት ቀስቃሽ በሆነ ስብሰባ በመምህራን የት/ቤቱ ፈቃድ አለመታደስ ፣ ካለው የተማሪ ብዛት አንጻር ተጨማሪ ት/ቤት ለመከራየት እቅድ ቢኖርም ፣ ት/ቤቱን መከራየት አለመቻሉን እንኳ የሰሙት በቅርቡ መሆኑን ተናግረዋል ። ዘንድሮም ወላጅ በፈረቃ ሊያስተምር ሲወሰን ፣ በጉዳዩ ባለድርሻ መምህራን እንዲመክሩና እንዲወያዩ አለመደረጉንም አንስተዋል ። ከሽዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች ትምህርት የሚቀስሙበት ማዕከል አደጋ ላይ መሆን ያስቆጣቸው መምህራን በድፍረት ” ድብቅብቁ ይቁም! ” በማለት ሞጋች ጥያቄዎችን ለኮሚኒቲው ምክር ቤት አመራሮ ች ፤ ለት/ቤቱ አስተዳደር እና ለዲፕሎማቶች ያቀረቡ ሲሆን የቀረቡት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው :-

በመምህራንና ሰራተኞች የቀረቡት ጥያቄዎች…
==========================
* የትምህርት ቤቱ ህጋዊነት ተረጋግጦ ተማሪዎች ወላጅ ብሎም ሰራተኛው ከስጋት ነፃ ይሁን
* በሳውዲ ት/ሚኒስትር ፈቃድ ይታደስ ፣ ትምህርት ቤቱ በአስቸኳይ በቦርድ ይተዳደር
*የት/ቤቱ የተወላከፈው አስተዳደር በአግባቡ ተዋቅሮ ተጠያቂነት እና ህግና ስርአትን የተከተለ አሰራር ይኑረው
*የት/ቤቱ አስተዳደር ከዝምድና ከጎሰኝነት እና ከመሳሰሉት ነፃ ይሁን
* ማህበረሰቡ የራሱ የሆነ ት/ቤት እንዲገነባ ሁነኛ ስራ ይሰራ
* አዲስ አመት ምዝገባ ላይ የሚስተዋለው በዘመድ አዝማድና በመሳሰሉት መሆኑ ኢ-ፍትሀዊነት ነው ይቁም
* መሰረታዊ የአሰራር እና የአስተዳደር ለውጥ ይኑር
* በትምህርት ደረጃቸው ማስተርስ ያላቸው ሰራተኞች ማግኘት ያለባቸውን ቦታ ይሰጣቸው
* የኮሚኒቲው ምክር ቤት በብቃት ሀላፊነቱን ይወጣ
* ት/ቤቱ ባለቤት አልባ እና ተቆርቋሪ አጥቷል
* በማዕከሉ አላፈናፍን ያለው ” ኪራይ ሰብሳቢነት” ተነቅፏል
* “የኪራይ ሰብሳቢነት” ምንጩ ቢታወቅም ኪራይ ሰብሳቢዎች ተሸፋፍነዋል ተለይተው ይታወቁ የሚሉት ከብዙው በጥቂቱ ይጠቀሳሉ

ለመምህራኑ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ …
=====================
ከዚህ በላይ በመምህራኑ የቀረቡትን ጥያቄዎችና ያነሷቸውን አንኳር መሰረታዊ ጥያቄዎችም የጅዳ ኮሚኒቲ አመራሮችንጨምሮ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ምላሽ ሰጥተውባቸዋል። በምላሹም የኮሚኒቲው አመረሮች ” ኃላፊነታችንን ለመወጣት ወደ ኋላ አላልንም ፣ ነገር ግን መንገድ ከያዝን በኋላ ይበላሽብናል ። በተበላሸ መሰረት ላይ ስለገባን ስራው አስቸጋሪ ሁኖብናል ” ብለዋል ። … ለትምህርት ቤቱ የተሻለ አማራጭ ለማፈላለግ በሚደረገው ሂደት እግር በእግር እየተከታተሉ የሚያበላሹት ” ኪራይ ሰብሳቢዎች ” እንደሚያስቸግሯቸው በሚያሳብቅ ሁኔታ በሂደቱ ተማረው ምላሽ ሰጥተዋል። በሳውዲ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል “ ቦርድ አቋቁሙ ” ተብሎ የተጓተተበትን ሂደትና ምክንያት አጥጋቢ ምላሽ ባይሰጥም ቦርድ ለማቋቋም በቅርቡ የተጠቆሙ የቦርድ አባላት ስላሉ ኮሚኒቲው ተመራጮችን እንደሚያጸድቅ ቃል ገብተዋል ።

ባልተለመደ መልኩ የህዝብ ወገናዊነትን ያሳዩትና ፍርሃትን አስወግደው ኮሚኒቲውን የሞገቱት መምህራን በስብሰባው ላይ ብሶት ስጋታቸውን ለማቅረብ ተደራጅተው በነቂስ መገኘታቸው ይጠቀሳል ። ” የትምህርት ማዕከሉ እያደረ መዝቀጥ የለብትም ፣ አሉ ያላችኋቸውን ኪራይ ሰብሳቢዎችን አጋልጡ!” ተብለው ለተጠየቁት የኮሚኒቲ አመራሮችን በምላሻቸው “ኪራይ ሰብሳቢ” ያሏቸውን ለማጋለጥ አልደፈሩም። የኮሚኒቲው አመራሮች ት/ቤቱን ለማሰራት እየተደረገ ስላለው ጥረት ሲዘረዝሩ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ሳውዲ በመጡ ቁጥር የነዋሪውን ብሶት ማሳዎቃቸውን አስረድተዋል ፤ ወደ ኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስቸኳይ የትብብር ደብዳቤ መላካቸውን ገልጸዋል ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አልፎ « ትምህርት ቤት ይሰራልን!» የሚል ደብዳቤ ተልኮ ከጠቅላይ ሚኒስተሩ እጅ መግባቱንም ለተሰብሳቢው አሳውቀዋል ። በዚህ ላይ አስተያየት የሰጡት የጅዳ ቆንስል ኃላፊ አምባሳደር ውብሸት “ ከመንግስት የተጠየቀው ድጋፍ በአሁኑ ሰአት ባለው የፓለቲካ አለመረጋጋት ትኩረት ላይሰጠው ይችላል ” የሚል ግምት እንዳላቸው ጠቁመዋል ። ከአንባሳደሩ ጋር ተቀራራቢ አስተያየት የሰጡት መምህራኑና ሰራተኞች በበኩላቸው ” ነዋሪው የሚያስተባብረው ቢያገኝና ኮሚዩኒቲው ከጉቦኝነት ነፃ ከሆነ ማንንም ሳይፈልግ ማህበረሰቡ የራሱን ህንፃ ይሰራል!”ሲሉ ተናግረዋል ። በዚህም በዚያም ተብሎ የጅዳ ኮሚኒቲ አመራሮች የመምህራኑን ጥያቄ ለመመለስ በሞከሩበት ምሽት በሁለት ወር ውስጥ አዲስ ነገር እንደሚታይ ቃል በመግባት ” ጥረታችን እንዲሳካ ታገሱንም እርዱንም ” በማለት መምህራንና ሰራተኞቹን ተማጽነዋል!

የዳይሬክተር አብዱ አባ ፎጌ ዲስኩር …
======================
የኮሚኒቲው አመራሮች በፈታኝ ጥያቄዎች ሲፋጠጡ የኮሚኒቲውን አመራር ትንፋሽ ለመስጠት የት/ቤቱ ዳይሬክተር አብዱ አባ ፎጌም የተለመደ ረዠምና አደንዛዥ የማይጨበጥ ትንተናቸውን ማቅረባቸው ይጠቀሳል። ለትምህርት ቤቱ አለመቀየር ብዙው ነዋሪ ጣቱን የሚቀስርባቸው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አብዱ አባፎጊ የተናገሩትን ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም ትተን ወደ ፍሬ ነገሩ ስናመራ የፈቃዱን ጉዳይ እና ተዛማጅ ጉዳዮችን በሚመለከት በሰጡት ምላሽ ” ለማስተካከል የበኩላችንን ጥረናል ፣ ወደ ሳውዲ ት/ሚኒስተር ከአመት በላይ ተመላልሰናል። ብዙ በጀት ለዚሁ ጉዳይ ወጪ አድርገናል ። በእርግጥ የተጨበጠ ነገር በማጣቴ ሰራተኛውን ሰብስቤ ማወያየት አልቻልኩም ” በማለት የተለመደ እርባና ቢስ ዲስኩር ማሰማታቸው ይጠቀሳል ።

አስተያየት ፤ የምክር ቤቱ አባል …
===================
ከኮሚኒቲና ለት/ቤቱ ቅርብ የሆኑ የኮሚኒቲ ምክር ቤት አባልን የትምህርት ማዕከሉን ለማዳን መፍትሔው ምንድነው ? ብዬ ጠይቄያቸው ዋናው እየታየ ሰው ሊናገረው የማይደፍረው የኮሚኒቲው እና ት/ቤቱ በፖለቲካ ድርጅቶት አባላት ተጽዕኖ ስር መውደቃቸው እንደሆነ አጫውተውኛል ፣ ከኮሚኒቲው ስራ አስፈጻሚዎች መካከል ( 7 ለ 3 )አብዛኛው የኢህአዴግ አባላት በመሆናቸው በውሳኔ ድምጽ አሰጣጡ ተጽዕኖ መፍጠሩን ያስረዳሉ ። ከዚህም አልፎ የኢህአዴግ አባላት የበላይ መሆን ”በት/ቤቱ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ፤ ስብሰባ ሲጠራ ፤ መዋጮ ሲጠየቅና ለመሳሰሉት ድርጅታዊ ጥቅማ ጥቅሞችን ለማስፈጸም ተብሎ የትምህርት ማዕከሉ እየተጎዳ ነው ።” ካሉ በኋላ ከዚህም አልፎ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ገብ ላለው መሰረታዊ ችግር ተጠያቂ የሆነውን የት/ቤቱን አስተዳደር ለመቀየር የሚደረገውን እንቅስቃሴ እስካሁን የሚያሰናክለውና የማይደፈርበት ምክንያት ዳይሬክተሩና የአስተዳደር ኃላፊው የድርጅት አባላት መሆናቸው እንደሆነ ዘርዝረው አውግተውኛል ። ይህም ዛሬ ኮሚኒቲው አስቸግሮኛል ያለው ኪራይ ሰብሳቢነት ተዛማጅ ችግሮች ተጠናክሮ መቀጠል ምክንያት መሆኑን “ ስሜን አትጥቀስ ” ያሉኝ የምክር ቤት አባሉ አስረድተውኛል ! ቀጠሉና “ አንተ ስታስበው የትምህርት ቤቱ ቁንጮ አስተዳደር በኦሆድድ ፤ በህዎሃት እና በብአዴን ወፍራም ተጽዕኖ ሹሞች ተይዞ ለውጥ ለማምጣት እንዴት ይቻላል?ከዚህ ቀደም ይህን ማሰብ የዋህነት ነው፤ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በድርጅት ሸፋን ለውጥ እንዳይመጣ እክል የሆኑትን በማንሳት ብቻ ነው ፤ እመነኝ እስካልሆነ ድረስ ለውጥ ላለመምጣቱ ምክንያት ይህ ብቻ ነው ፤ በዚህ ምክንያት ወላጆች ሁሌም ስለጆቻችን ት/ቤት ስናስብ በስጋት ኖረናል ፤ ከሰሞኑ የነዋሪው ብሶትና የታዳጊዎች ማዕከል ጉዳይ አሳስቧቸው መምህራን እውነቱን መጋፈጥ ጀምረዋል ፡ ትልቅ ለውጥ ነው ! ድሮም ያጠፋን የእነሱ ዝምታ ነበር ። ዘንድሮ ደፍረው ለእውነትና ለህዝቡና ለታዳጊዎች መቆማቸው ትልቅ ተስፋ ነው ። እነሱ ከበረቱ ነዋሪው ይደግፋቸዋል ፤ ነዋሪው ከደገፈ ደግሞ ለውጥ አይቀሬ ነው !” ሲሉ ጥልቅና ዘርዘር ያለ አስተያየታቸውን አካፍለውኛል …
አስተያየት ፤ ዲፐሎማቱ …
========================
ሌላው በትምህርት ቤቱ ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡኝ የጠየቅኳቸው ስማቸው ለደህንነታቸው ሲባል እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሳውዲ የሚገኙ ዲፕሎማት ” ነቢዩ የምሰጥህን አስተያየት እንደ ዲፕሎማት ሳይሆን እንደ ዜጋ ተቀበለኝ ፤ ነዋሪው ከዚህ ቀደምም ሸህ ሁሴን አልሙዲ ይሰራሉ ብሎ በሌለ ተስፋ ፕሮጀክት ይሰራ ተብሎ ኮሚኒቲው ለሙስና ተጋልጧል ፤ አሁን ደግሞ መንግስት ት/ቤት ይስራልን የሚል ጥያቄ መቅረቡን እየሰማን ነው ፡ ይህ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም ፤ መንግስት ትምህርት ቤት ለመስራት በጀት ይመድባል ብሎ ጊዜ ማባከን ተገቢ አይደለም !አሁን እንቅስቃሴ የጀመሩት መምህራን ከጠነከሩ ፣ ወላጅና ነዋሪው ትምህርት ቤት እንዲሰራ የሚያደራጀው ካገኘና ወላጅ ከመምህራን ጎን ከቆመ በአጭር ጊዜ ስኬት ይኖራል ! ” በማለት ሲናገሩ እስካሁን ምንም ማደረግ ያልቻለው የቆንስል መስሪያ ቤት ወደ ፊትም ምንም ማድረግ እንደማይችል ጠቁመውኛል ።

አስተያየት ፤ መምህሩ …
======================
ከስብሰባው በኋላ አስተያየታቸውን እንዲሰጡኝ የጠየቅኳቸው አንድ የስብሰባው ንቁ ተሳታፊ መምህር ” የሚሰራው ስራ አሰላችቶንና አንገሽግሾን ላቀረብነው ተደጋጋሚ መሰረታዊ ጥያቄ የተሰጠው መልስ ቀድመን የገመትነው ነው፤ አያጠግብም ! ዘንድሮ አምና አይደለም ፡ ወላጅ ከጎ ናችን ከቆመ ታዳጊ ልጆቻችን ትምህርት ቅበላ በመምህራን ጉድለት በሚከሰተውን የትምህርት ጥራት ለማካካስ ከመትጋት ባሻገር ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስዎገድና የበከተው አስተዳደር ብቃት ባለው አስተዳደር እንዲተካ ጥረት ከማድረግ አንመለስም ። ፍርሃቱ በቅቶናል ፤ ወላጁም ስለ ልጆቹ ከጎ ናችን ሊቆም ይገባል ” ሲሉ በስሜት አስተያየታቸውን ሲያቀብሉኝ “ጀሮ ያለው ይስማ ! ” በማለት ጭምር ነበር !

አዎ ! በጅዳ ሶስት ሽህ (3000)ታዳጊዎችን ለመታደግ መምህራን ሲተጉ ማየት ያስደስታል ፤ በትውልድ ላይ መቀለድ ይቁም !እኔም እንደሚያገባው ዜጋ ” ጀሮ ያለው ይስማ” እላለሁ !

ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 21 ቀን 2009

– See more at: http://www.satenaw.com/amharic/archives/22232#sthash.EPBrJBJT.dpuf


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>