Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ቴዎድሮስ አድሃኖም ቢያጥቡት የማይጠራ ወያኔ ነዉ (ኤፍሬም ማዴቦ)

$
0
0

ኤፍሬም ማዴቦ

tewedros adhanom with returneesየኢትዮጵያ ህዝብና እናስተዳድረዋለን የሚሉት አምባገነን ገዢዎቹ ተስማምተዉና አንዱ ሌላዉን አክብሮ የኖረበት አንድም የታሪክ አጋጣሚ የለም። የእስከዛሬዉ ታሪካችን ምዕራፍ በጥቅሉ ሲታይ ታሪካችን የሚቋጨዉ ህዝብ ተረገጠ፤ ተጋዘ፤ ገዢዎች ደግሞ ረገጡ፤ገዙ፤ አሰሩ፤ አጋዙ እየተባለ ነዉ። አዎ! የኢትዮጵያ ህዝብ እስከዛሬ ባለዉ ታሪኩ ተግዟል፤ ተረግጧል፤ ተንቋል፤ ተንቋሿል። የዘንድሮዉ በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት እየደረሰብን ያለዉ ብሄራዊ ዉርደትና ንቀት ግን ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ልዩ ከልዩም ልዩ ነዉ። በቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደዛሬዉ ሰብዓዊ መብቱ ተረግጧል፤ ፍትህ ተነፍጓል፤ ነጻነቱን ተገፍፏል፤ ሆኖም አገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም ፈላጊና ባለቤት አንደሌለዉ የቤት ዉስጥ እንስሳ የወገንም የባዳም እጅ አልተረባረበበትም። አንገፍግፎን አንፈልግም በቃ ብለን ያስወገድነዉ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ስርዐት በስልጣን ላይ በነበረበት ግዜ “ኢትዮጵያ” የሚለዉ ስምና “ኢትዮጵያዊነት” አገር ዉስጥም ሆነ አዉሮፓ፤ አሜሪካና አፍሪካ ዉስጥ እጅግ በጣም የተወደደና የተከበረ ስም ነበር። ዛሬ ወያኔ ነጻ አወጣኋችሁ፤ እኩልነት አመጣሁላችሁ እያለ በሚሰብክበት ዘመን ግን የኢትዮጵያ ሀዝብ አገር ዉስጥም በዉጭ አገሮችም ባለቤት አንደሌለዉ ፈረስ ማንም የሚጋልብበት ፈላጊ እንደሌለዉ  ዕቃ ያገኘ ሁሉ እንዳሰኘዉ እጁን የሚያሳርፍበት የተናቀ ሀዝብ ሆኗል። ለመሆኑ ለምንድነዉ ኢትዮጵያዊነት እንደዚህ  እንደ ተራ ዕቃ የቀለለዉ? ኢትዮጵያዉያንስ ለምንድነዉ በየሄዱበት እንዲህ አይነት ዉርደትና ስቃይ የሚደርስባቸዉ? መልሱ ቀላል ነዉ። “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ወይም  “ባለቤቱ ያቀለለዉን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለዉም” ነዉ።

የወያኔ አገዛዝ እኛ ኢትዮጵያዉያን “ኢትዮጵያዊነት” እያልን ስለምንሳሳለትና ስለምንከባከብለት ትልቅና ክቡር ሀሳብ በፍጹም ግድ የለዉም። እንዲያዉም ወያኔ ሽንጡን ገትሮ ከሚታገላቸዉ ዋና ዋና ብሄራዊ እሴቶቻችን ዉስጥ “ኢትዮጵያዊነት” የመጀመሪያዉ ነዉ። ስለዚህም ነዉ ባለፉት ሃያ ሁለት አመታት በግልጽ እንደተመለከትነዉ “ኢትዮጵያዊነት”  ብለዉ የተጣሩ፤የጮሁ፤ ህዝብን ያስተማሩና የታገሉ ግለሰቦች በወያኔ እየተለቀሙ የታሰሩትና የተገደሉት። ከአገር ዉጭም ቢሆን በየዉጭ አገሩ የሚገኙት የወያኔ ኤምባሲዎች ኢትዮጵያዉያን ከአገራቸዉ ዉጭ ማግኘት የሚገባቸዉን የዜግነት አገልግሎት የሚሰጡት ዜግነታቸዉን እያዩ ሳይሆን ቦንድ የገዛ ያልገዛ፤ “ልማታዊዉን መንግስት” የደገፈ ያልደገፈ እያሉ ወይም “የወርቃማዉ ዘር” አባልነቱን እያጣሩ ነዉ። እነዚህንና ሌሎችም እነዚህን የመሳሰሉ ሰንካላ የወያኔ መስፈርቶች ያላሟሉ ኢትዮጵያዉያን አገር ዉስጥም ከአገር ዉጭም ወያኔ በዜግነት ሳይሆነ በጠላትነት የሚመለከታቸዉ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ዜጎች ናቸዉ። ዛሬ ከአፍሪካ፤ ከኢሲያና ከላቲን አሜሪካ አገሮች ስራ ፍለጋ ሳዑዲ አረቢያ ከሄዱ ዜጎች ዉስጥ እንደ ኢትዮጵዉያን እጁንና እግሩን ታስሮ የተገረፈ፤ እንደሴቶቻችን በሳዑዲ ጎረምሶች የተደፈረና እንደ ኢትዮጵዉያን በየአደባባዩ የተገደለ የሌላ አገር ዜጋ የለም። ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ የሚገኙ የሌሎች አገሮች ኤምባሲዎች የዜጎቻቸዉ መብት በሳዑዲ መንግስትና ህዝብ ሲደፈር ለምን ብለዉ ይጠይቃሉ ወይም ለዜጎቻቸዉ ግዜያዊ መጠለያ፤ የህክምና እርዳታና የህግ ሽፋን ይሰጣሉ እንጂ ኤምባሲያቸዉ በራፍ ላይ “ዝግ ነዉ” የሚል ጽሁፍ አይለጥፉም።

የወያኔ ኤምባሲ ግን ከስረ መሠረቱ የተቋቋመዉ የወያኔን የራሱን እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ስላልሆነ ይህንን የሌሎች አገሮች ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸዉ የሚያደርጉትን ጥበቃና እንክብካቤ ለወገኖቹ ለማድረግ አልታደለም፤ ፍላጎቱም የለዉም።  ይህንን ቅሌትና ዉርደት ደግሞ ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት በግልጽ ተመልክተናል። ጂዳና ሪያድ ዉስጥ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰዉን መከራና በደል ተቃዉመዉ ሠልፍ የወጡ ኢትዮጵያዉያን በሳዑዲ ፖሊሶች ታድነዉ እንደታሰሩ ሁሉ አዲስ አበባ ዉስጥም በወንድሞቻችንና እህቶቻች ላይ እንዴት እንዲህ አይነት በደል ይፈፀማል ብለዉ ሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሠላማዊ ሠልፍ የወጡ ኢትዮጵያዉያን በአረመኔዎቹ የወያኔ ፖሊሶች ታድነዉ ታስረዋል፤ተደብድበዋል። አዎ! ኢትዮጵያዉያን ሳዑዲ ዉስጥም ኢትዮጵያ ዉስጥም ለምን የሳዑዲን መንግስት ተቃወማችሁ ተብለዉ በሁለቱም አገር ፖሊሶች እየታደኑ ታስረዋል ተደብድበዋል።

ከወያኔና ከጥቂት ሆድ አምላኪ ደጋፊዎቹ ዉጭ በአገር ዉስጥና በመላዉ ዓለም የሚገኘዉ ኢትዮጵያዊ በአንድ አላማ ዙሪያ የተሰባሰበበትና አንድ ሳምንት ሙሉ አንድ ቃል በአንድ ትንፋሽ የተነፈሰበት ግዜ ቢኖር ወርሃ ህዳር 2006 የመጀመረያዉ ነዉ ማለት ይቻላል። የአንድ አገር ህዝብ በአንድ አላማ ስር ሲሰባሰብና በአንድነት ሲቆም ከማንም ከምንም በላይ በዚህ አንድነት መጠቀምም መደሰትም ያለበት መንግስት ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ የወያኔ አገዛዝ ግን ዕቅዱና ስራዉ ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ማስጨነቅና ማበሳጨት ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰራዉ ስራ ተደስቶ አያዉቅም፤ ለወደፊትም የሚደሰት አይመስልም። ከሰሞኑ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ በኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰዉ ልክ የሌለዉ ስቃይና መከራ መላዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀፎዉ እንደተነካ ንብ ከዳር ዳር ሲያስቆጣ ወያኔና ሞራለ ብልሹ ሹማምንቶቹ ግን ከዚህ ወገኖቻችንን በባዕድ አገር ለከፍተኛ ጥቃት ካጋለጠና ብሄራዊ ዉርደት ካከናነበን ክስተት ትርፍ ለማግኘት የፖለቲካ ቁማር እየተጫወቱ ነዉ። ኢትዮጵያዉያን ሳዑዲ ዉስጥ በአሰሪዎቻቸዉ፤ በመንደር ዉስጥ ጎረምሶችና በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ፤ እንግልትና ዉርደት ሲደርስባቸዉ ኤምባሲዉ በራፍ ላይ “ኤምባሲዉ ዝግ ነዉ” የሚል ጽሁፍ በመለጠፍ ይበላችሁ እያለ አፉን ዘግቶ የተመለከተዉ የወያኔ አገዛዝ ዛሬ የወገን አሳቢና ተቆርቋሪ ለመመሰል የጭቃ ዉስጥ እሾኩን ቴዎድሮስ አድሀኖምንና የአገዛዙን የዉሸትና የቅጥፈት ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲን በግምባር ቀደምትነት በማሰለፍ የፖለቲካዉን ገደል ቁልቁል ተያይዞታል።

ቴዎድሮስ አድሃኖም ቢከፋም ቢለማም የአገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነዉ፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የስራ ሀላፊነት ደግሞ አገሪቱንና ዜጎቿን ከዉጭ አገሮች ጋር በሚያገኛኙ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ነዉ እንጂ በአገር ዉስጥ የሚሰራዉ ይህ ነዉ ተብሎ የሚነገር ስራም ሀላፊነትም የለዉም። አንዴ ወዳጅ አንዴ ጠላት እየመሰለ እንደ እስስት መልኩን የሚቀያይረዉ ቴዎድሮስ አድሀኖም ግን ሳዑዲ ዉስጥ ድረስልን ብለዉ ሲጣሩት ፊቱን ያዞረባቸዉ ኢትዮጵያዉያን አዲስ አበባ ሲመለሱ ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት ሲሞክር ይታያል።  ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ቅርቅር አድርጎ ዘግቶ የወገን ያለህ ብለዉ የመጡትን ኢትዮጵያዉያን እንጃላችሁ ብሎ ፊቱን ያዞረባቸዉ የአዛኝ ቅቤ አንጓቹ ቴዎድሮስ አድሃኖም እነዚሁኑ እንደ ባዳ ፊቱን ያዞረባቸዉን ኢትዮጵያዉያን አገር ቤት ሲመጡ “እንኳን ደህና መጣችሁ” ማለቱ የገደለዉን ወታደር ለማከም ከሞከረዉ የናዚ ጀርመን ወታደር ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ቴዎድሮስ አድሀኖም እንደ ፈረስ ገርተዉ ለዚህ ባደረሱት በነመለስ ዜናዊና ስብሐት ነጋ ጭቅላት ሳይሆን በራሱ ጭንቅላት የሚያስብ ሰዉ ቢሆን ኖሮ የሱ የስራ ድርሻና ሀላፊነት ዜጎቻችን አገር ቤት ከገቡ በኋላ ሳይሆን ሳዑዲ ዉስጥ እያሉ ነበር።

ዛሬ ቴዎድሮስ አድሃኖምም ሆነ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ከሳዑዲ በሚመለሱት ወገኖቻችን ዙሪያ የሚያደርጉት ልታይ ልታይ የፎቶ እሽቅድምድም ወገኖቻችንን ለመርዳት ሳይሆን ዘረኛ መሪያቸዉ መለስ ዜናዊ ሲሞት ሳያስቡት በድንገት ከእጃቸዉ የወጣዉን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ መልሰዉ እጃቸዉ ለማስገባት ወይም በሚቀጥለዉ አመት በሚደረገዉና ወያኔ ከወያኔ ጋር በሚወዳደርበት ትርጉም የለሽ ምርጫ የፈረደበት ኃ/ማሪያም ደሳለኝን በቴዎድሮስ አድሃኖም ለመተካት ነዉ። አዎ! ለመተካት  . . . ለመተካካት። ወያኔ መተካካት እያለ አንዱን ጌኛ በሌላ ጌኛ በልቶ የጠገበዉን አህያ በተራበ አህያ መተካት ከጀመረ ዉሎ አድሯል። የአሁኑም ሩጫቸዉ ቢጭኑት አልሸከም ቢቀመጡበት አልመች ያላቸዉን ኃ/ማረሪያም ደሳለኝን የራሳችን ሰዉ ብለዉ በሚጠሩት በቴዎድሮስ አድሃኖም ለመተካት ነዉ (ኃይለማሪያምማ አሁንስ ቢሆን በቁሙ አልተተካም ብላችሁ ነዉ . . . ድፍን አበሻ ዉጭ አገርም አገር ዉስጥም ሲተራመስ ኃ/ማሪያም አንዲት ቃል አልተነፈሰምኮ)  ሳዑዲ ዉስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻችን ፓስፖርታቸዉን ሲቀሙ፤ ሲደበደቡ፤ሲታሰሩና ሲገደሉ ቴዎድሮስ አድሀኖም የሰጠዉ ምላሽ ቢኖር  የኤምባሲዉንና የቆንስላ ጽ/ቤቶችን በር መዝጋት ነበር።  አዎ መዝጋት። ልክ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ከመለስ ዜናዊና ከአግዓዚ ነብሰ ገዳዮች የጥይት እሩምታ ለማምለጥ ወደ ቤተክህነት ጽ/ቤት ግቢ ሸሽተዉ ለመግባት በሞከሩ ወጣቶችና ህፃናት ላይ አባ ጳዉሎስ በሩን እንደዘጉባቸዉ ዛሬም የአባ ጳዉሎስ ታናሽ ወንድም የሆነዉ ቴዎድሮስ አድሃኖም በባዕድ አገር ዉስጥ አድነን ብለዉ በተጠጉት ወገኖቻችን ላይ የኤምባሲን በር ቀርቅሮባቸዋል።

ለመሆኑ ቴዎድሮስ አድሃኖም በየአመቱ ከ40ሺ በላይ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች በለጋ ዕድሜያቸዉ ከወላጆቻቸዉ ተለይተዉና ትምህርታቸዉን ትተዉ ስራ ፍለጋ ወደ አረቡ አለም የሚጎርፉት እሱ ሊነግረን እንደሚፈልገዉ  በአትራፊ ደላላዎች ተታልለዉ ወይም የአረብ አገር ኑሮ ጥሟቸዉ ሳይሆን ወያኔ በሚከተለዉ የዘረኝነት ፖሊሲና የተበላሸ የኤኮኖሚ ስርዐት የተነሳ መሆኑን ያዉቅ ይሆን? በተለይ ወጣት ሴቶቻችን በአረቡ አለም የሚደርስባቸዉን ዉርደትና መከራ እያወቁ በነጋ በጠባ አረብ አገር የሚሄዱት አገራቸዉ ዉስጥ ሰርተዉ መኖር ስላልቻሉ ከወያኔ ጋር ከመኖር አረብ አገር ሄዶ መሰንበት ይሻላል ብለዉ ነዉ አይናቸዉ እያየ የሞት ወጥመድ ዉስጥ የሚገቡት። ወያኔ በእጥፍ ድርብ አሳደግኩት የሚለዉ የአለማችን ፈጣኑ ታዳጊ ኤኮኖሚ ለእነዚህ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሮ ቢሆንና ዜጎች ስራ የሚያገኙት ችሎታቸዉ ብቻ እየታየ ቢሆን ኖሮ ይህ ዛሬ የምናየዉ ብሄራዊ ችግርና ዉርደት አይኖርም ነበር። ይሉኝታና እፍረት የሚባል ነገር አብሮት ያልተፈጠረዉ ቴዎድሮስ አድሃኖም የዜጎቻችንን ወደ አረብ አገር መጉረፍ በደላሎችም ሊያሳብብ ሞክሯል። አሱ ለሚከስሳቸዉ ደላሎች የስራና የንግድ ፈቃድ ሰጥቶ በዜጎች ንግድ እንዲከብሩ መንገዱን ያመቻቸዉና የከፈተዉ የራሱ የቴዎድሮስ ፓረቲ ነዉ፤ ብዙዎቹ አትራፊ ደላላዎችም የራሱ የቴዎድሮስ ጓደኞች ናቸዉ። የቴዎድሮስ አድሃኖም ጉድ ብዙ ነዉ፤ ተዘርዝሮ አያልቅም።

ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን ሳዑዲ ዉስጥ ሲጋዙና ሲገደሉ ቁጥሩ ተገኗል እያለ በወገኖቻችን ላይ ያፌዝ የነበረዉ ቴዎድሮስ አድሃኖም ነበር፤ ኢትዮጵያዉያን ወገንና ረዳት አለን ብለዉ ወደ ኤምባሲዉ በብዛት ሲመጡ ኤምባሲዉና ቆስንላ ጽ/ቤቶች በራፍ ላይ “ዝግ ነዉ” የሚል ጽሁፍ ለጥፎ ወገኖቻችንን ለባዕዳን ጥቃት አሳልፎ የሰጠዉ ቴዎድሮስ አድሀኖም ነዉ፤የሳዑዲ መንግስት በአገሩ ዉስጥ ወንጀል ሲፈጸም ህጋዊ እርምጃ መዉስድ መብቱ ነዉ ብሎ የወገኖቻችንን መገደልና የሴቶች እህቶቻችንን መደፈር ህጋዊ ለማድረግ የሞከረዉም ቴዎድሮስ አድሃኖም ነዉ። የሚገርመዉ ይህ ወገኖቻችንን በባዕድ አገር “አይናችሁን ለአፈር” ብሎ በሩን የዘገባቸዉ ከሃዲ ሰዉ ነዉ ዛሬ የወገን አሳቢና ደራሽ መስሎ ቀልዱ እንዳማረለት የመድረክ ላይ ኮሜዲያን እዚህም እዚያም ሽርጉድ የሚለዉ። ሳዑዲ ዉስጥ በወገኖቻችን ላይ ለደረሰዉ ይህ ነዉ የማይባል ትልቅ በደልና ጥፋት የኢትዮጵያ ህዝብ በዋናነት ተጠያቂ ከሚያደርጋቸዉ የወያኔ ባለስልጣኖች ዉስጥ ቴዎድሮስ አድሃኖምና ተላላኪዉ ዲና ሙፍቲ የመጀመሪያዎቹ ናቸዉ።

ከሰሞኑ ፊቱን እያሳመረ በየደቂቃዉ ኢቲቪ ላይ መቅረብ የጀመረዉ ቴዎድሮስ አድሃኖም  “ሳዑዲ ዉስጥ ለደረሰዉ ጥፋት መንግስት ተመጣጣኝ እርምጃ ይወስዳል” እያለ ሲዘለብድ ተሰምቷል፤ የሱ ተላላኪ የሆነዉ ዲና ሙፍቲ ደግሞ “በዜጎች ላይ ምን ግዜም ድርድር የለም” ብሎ ሲናገር ተደምጧል። ይህንን በሁለት ባዶዎች የተነገረ ባዶ ንግግር ያዳመጠ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን “ጽድቁ ቀርቶበኝ በወጉ በኮነንከኝ” እያለ የቴዎድሮስንና የዲና ሙፍቲን “ጅብ ከሄደ ዉሻ ጮኸ” ንግግር ሰምቶ እንዳልሰማ አልፎታል። የሚገርመዉ ይህ ወገኖቻችንን በክፉ ቀን ወግዱ ብሎ ፊቱን ያዞረባቸዉ ቴዎድሮስ አድሀኖም ነዉ ዛሬ የሳዑዲ መንግስት በራሱ ወጪ አዲስ አበባ የሚልካቸዉን ዜጎች ዘመድ መስሎ ለመጠየቅ የሚሄደዉ። ደግሞኮ እስከዛሬ ድረስ አዲሰ አበባ ገብተዋል የሚባሉት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎችም ቢሆኑ በተለመደዉ የወያኔ የዘመድ አሰራር እየተመረጡ የመጡ እንጂ ዜግነታቸዉ፤ ዕድሜያቸዉና የጤንነት ሁኔታቸዉ እየታየ የተመረጡ ሰዎች አይደሉም። ባጠቃላይ የተጣለበትን አገራዊ አደራና የተሰጠዉን ህዝባዊ ሀላፊነት መወጣት የተሳነዉን ቴዎድሮስ አድሀኖምን በየሜድያዉና በተገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ እያሽሞነሞኑ ለማቅረብ የሚደረገዉ ጥረት እንደ ህፃን ልጅ ሽንት መቀበያ የቆሸሸዉን የወያኔ ፊት በቆሻሻ ዉኃ ከማጠብ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ወያኔ ከአሳማ አሳማ እየመረጠ ለማሳመርና ለማሽቀርቀር የሚያደርገዉ ጥረት አሳማዉን ወደ ለመደዉ ወደ ጭቃዉ ዉስጥ ይበልጥ ይስበዋል እንጂ በፍጹም አያሳምረዉም፤ ምክንያቱም አሳማ አጌጥነዉ አላጌጥነዉ ምን ግዜም አሳማ ነዉ። የቴዎድሮስ አድሃኖም ነገርም እንደዚሁ ነዉ ፤ ወያኔ ያሻዉን ያክል ቢቀባዉና ቢያሳምረዉ ቴዎድሮስ አድሃኖም ወያኔነቱን አይለቅም! ወያኔ ደግሞ በልቶ የማይጠግብ ታጥቦ የማይነጻ አሳማ ነዉ።

ebini23@yahoo.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>