Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በኢትዮጵያ ሙዚቃ እንደነገሠ 50 ዓመት የደፈነው አሊቢራ

$
0
0

በሚኒሶታ የኦሮሞ ስፖርት ፌስቲቫልን አስታኮ ባለፈው ጁላይ ላይ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ አገልግሎቱ ቢከበርም፤ አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዚህ ብርቅዬ አርቲስት 50ኛ ዓመት በዓል እየተከበረ ነው።
ግንቦት 18 ቀን 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የተወለደው የክብር ዶ/ር አሊ መሐመድ ብራ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ድሬዳዋ ከተማ በቀድሞዎቹ መድረስ ጅዲዳ እና በልዑል ራስ መኮንን ት/ቤቶች፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ት/ቤት ተከታትሏል። በኋላም ካሊፎርንያ በሚገኘው ሳንታ ሞኒካ ኮሌጅ በሙዚቃ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትምህርት ተከታትሏል። አሊ ብራ 8 ቋንቋዎችን አቀላጥፎ መጠቀም ይችላል።
ali b
የፈረንጆቹ አመት 1963 አሊ ብራ ሙዚቀኛ ሆኖ ዳግም የተወለደበት ዓመት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ ዓመት አሊ ብራ በድሬዳዋ ከተማ ከነበረው የአፈረን ቀሎ የሙዚቃና የባህል ቡድን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ ላይ ሙዚቃ የተጫወተበት ነበር።
አሊ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ የተጫወተው “ብራዳ በርሄ – Birraadahaa Barihee” የተባለውን እጅግ ተወዳጅ ዘፈኑን ነበር። ቤተሰቦቹ ያወጡለትን ስም አሊ መሐመድ ሙሳን በመቀየር አሁን ሁለተኛ ስሙ የሆነውና (Second name) በጊዜው ቅፅል ስሙ የነበረውን “ብራ”ን ከህዝብ ያገኘው ከዚሁ ዘፈኑ መሆኑ አመቱ አርቲስቱ አሊ የተወለደበት አመት የመሆኑን ነገር ያጠናክራል፣ ከዚህ በኋላ አርቲስቱ የተጓዘባቸው ሃምሳ አመታት በሀገራችን ሙዚቃ ታሪክ የራሱን ጉልህ ምዕራፍ የፃፈባቸውና፣ በዚህም ሂደት በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን አልፎ ለታላቅ ስኬት የበቃባቸው አመታት ናቸው።
የክብር ዶ/ር አሊ ብራ በተፈጥሮው ተሰምቶ የማይጠገብ፣ ሁሌም የሚወደድ እጅግ ማራኪ ድምፅን የተለገሰና ከፍተኛ የዜማ ተሰጥዖን የታደለ ነው። በዚህ ችሎታውና በብርቱ ጥረቱ እስከ አሁን ከ260 በላይ ድንቅ ዘፈኖችን ዜማዎችን ለሕዝብ አቅርቧል። አሊ ያለውን ቋንቋ የመማር ከፍተኛ ክህሎት በመጠቀም በኦሮምኛና በ8 የተለያዩ ቋንቋዎች (ሶማልኛ፣ አማርኛ፣ አፋርኛ፣ ሀረሪኛ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኪስዋሂሊ እና ስፓንሽ) ሥራዎችን አቅርቧል። በሥራዎቹም በርካታ የሕይወትን ገፅታዎችን ዳሷል።
አሊ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኡድ እና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወት ሲሆን፣ ለራሱና ሌሎች በርካታ ግጥምና ዜማዎችን ደርሷል። የራሱን ለየት ያሉ የዜማ ቅንብርና የአዘፋፈን ስልቶች የፈጠረ አርቲስትም ነው።
አሊ በሀገራችን ታሪክ ታላላቅ ከሚባሉ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ሰርቷል። ከአርባ በላይ ሀገራት (በሁሉም አህጉራት) እጅግ በርካታ በሆኑ መድረኮችም ላይ ተጫውቷል። የአሊ ስራዎች አፋን ኦሮሞንና ሌሎች የዘፈነባቸውን ቋንቋዎች ለሚሰሙ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ እጅግ የሚወደዱ ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ናቸው።
ዶ/ር አሊ ብራ የዘመነኛ (contemporary) ኦሮምኛ ሙዚቃ አባት ሲሆን ለሀገራችን ሙዚቃ፣ ባህል እና ስነ ጥበብ ማንሰራራት፣ እድገትና መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው የኦሮምኛ አልበም የአሊ ብራ ነበር። የእርሱን ፈለግ ለተከተሉ በርካታ ድምፃዊያን አርአያና መምህር በመሆንም አገልግሏል። በርካታ ወጣት ድምጻውያን ስራ ሲጀምሩ፣ ዘፈኖቹን፣ ለልምምድ እንደ አፍ መፍቻ፣ ስራቸውን ለማድመቅ እንደ ማጣፈጫ ሲገለገሉባቸው ኖረዋል። አሊ ምርጥ አርቲስቶችን ያፈራ የአርቲስቶች አባት ነው።
ዶ/ር አሊ ብራ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ሙዚቃዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በስፋት ያስተዋወቀና ለተለያዩ ሕዝቦችና ባህሎች መገናኛ ድልድይ የሆነ የባሕል አምባሳደርም ነው። በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምሁራን ሙዚቃዎቹን አጥንተዋል፣ ስለ ሙዚቃዎቹም በርካታ ጽሁፎችን ጽፈዋል።
አሊ ብራ፣ በሙዚቃ ዓለም በቆየባቸው ዘመናት በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደር የሌለው የሕዝብ ፍቅርና አክብሮትን ተቀዳጅቷል። በሚሊዮኖች ሕሊና እና ልብ ውስጥም ልዩ ቦታ አለው።

ለስኬቶቹና ለአስተዋጽዖዎቹ እውቅና ከሰጡ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተቋማትም ከሃምሳ በላይ ታላላቅ ሽልማቶችንም አግኝቷል። ከጅማ ዩኒቨርስቲ ያገኘው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በእነዚህ ሽልማቶች አንዱ ነው።
አሊ ትምህርትና ጥበብ የዕድገትና የስኬት መሰረቶች መሆናቸውንና፣ አለመማር ሕሊናን እንደሚያሳውር በጽኑ ያምናል። ለአሊ፣ ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ቤት የሚገኝና አእምሮን ብቻ የሚያሳትፍ ሂደት ሳይሆን፣ የሰው ልጅ እድሜ ልኩን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው የሚያካሂደውና ሁለመናን (አካልን፣ አእምሮን፣ መንፈስንና፣ ልቡናን) የሚያሳትፍ ሰፊና ረጅም ሂደት ነው።
አሊ ብራ፣ እነዚህን እምነቶቹን በዘፈኖቹ ውስጥ በማስተላለፍ ብዙዎችን እንዲህ ላለ የትምህርት ጉዞ አነሳስቷል፣ ራሱም እምነቱን በተግባር በመኖር አርአያና ምሳሌ ሆኗል።
አሁንም የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓሉ መሪ ቃል “Barnootaa ammas Barnootaal -መማር አሁንም መማር!” እንዲሆን የወሰነ ሲሆን፤ መሪ ቃሉን በመከተል በበዓሉ አከባበር ዝግጅቶች ላይ በሙሉ ስለ ትምህርት የተለያዩ መልዕክቶች ይተላለፋሉ።
ዶ/ር አሊ ብራ ለሀገራችን እድገትና አዲሲቱንና የበለፀገችውን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በተለይ በትምህርት ዘርፍ የሚያደርገው አስተዋፅዖ ስለ ትምህርት በማስተማር ብቻ የተወሰነ አይደለም።
አሊ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁሞ ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል። ድርጅቱ አሁን በድሬዳዋ አካባቢ ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ እየሰራ ሲሆን፤ በቀጣይነት በመላው የሀገራችን ክፍሎች የተጠናከረ ሥራ ለመስራት እቅድ አለው።
በቀጣዩ የህይወት ክፍለ ጊዜው፣ አሊ ብራ፤ በዋነኝነት በሚከተሉትን ተግባራት ለማከናወን አቅዷል።
- የጀመረውን የበጎ አድራጎት ስራ ማስፋፋትና ማጠናከር፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም እንዲደርስ መስራት፣
- ፈለጉን የተከተሉ አርቲስቶችን በአማካሪነት በመደገፍና፣ እውቀትና ልምዱን በማካፈል ለኪነጥበቡ እድገት ሲያደርግ የቆየውን አስተዋጽዖ መቀጠል፣
የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ የሃምሳኛ ዓመት ክብረ በዓልን የሚያዘጋጀው የፕራክሲስ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት ዘላለም ቻላቸው በአሉን ለምን ማክበር እንዳስፈለገም ይገልፃል።
አንደኛው አሊ ብራ ለሀገራችንና ለሙዚቃው ዓለም ትልቅ ስጦታ ነው። የአርቲስቱ ሕይወት፣ ስራዎቹ እና ያስመዘገባቸው ውጤቶች የታሪካችንና የትውፊታችን ጉልህ አካላት ስለሆኑ፣ ሊዘከሩ፣ ክብር ሊሰጣቸውና ሊጠበቁ ይገባል። እርሱም ላደረገው ሁሉ ተገቢው ክብርና ምስጋና ሊሰጠው ይገባል። ይህ የወርቅ ኢዩ ቤልዩ በአል እነዚህን በይፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚደረግ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ሁለተኛው፣ አሊ ብራ በሃምሳ ዓመታት ጉዞው ላስመዘገባቸው ስኬቶች ዋነኛው መሰረት ከአፍሪቃዎቹ፣ ከአድናቂዎቹና ከህዝብ የተደረገለት ድጋፍና እርዳታ መሆኑን በፅኑ ያምናል። ስለዚህም በአሉ አሊ ለተዋለለት ውለታ ለእነዚህ ሁሉ ምስጋናውን የሚያቀርብበትና የደስታው ማዕድ ከሌሎች ጋር የሚቋደስበት መድረክ ነው ይላል አዘጋጁ ዘላለም ቻላቸው።
ሶስተኛው ደግሞ፣ ታላላቆችን የማያከብር ማህበረሰብ ተተኪ ታላላቆችን አያፈራም ሲልም ተናግሯል። እንደ ዘላለም ገለፃ በዚህ በአል ለአሊ ቢራ የሚሰጠው ክብርና ምስጋና ፈለጉን ለተከተሉ አርቲስቶችና በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ለሚገኙ ሁሉ መነቃቃትን፣ መነሣሣትን እና ብሩህ ተስፋን ይፈጥራል፤ ነገ በየዘርፉ ብዙ አሊ ብራዎች እንዲኖሩ መንገድ ይጠርጋል። በሙያቸው ለሕዝብና ለሀገር ታላቅ ውለታ የዋሉ አንጋፋዎችን የማክበርና የማመስገን ባሕላችንን የምናዳብርበትም ይሆናል።
በአራተኛነት የገለፀው ደግሞ፣ በአሉ አሊ እምነቱን፣ ዕውቀቱን፣ እቅዱን፣ ተስፋውን፣ ራዕዩን በተለያዩ መድረኮች ለሌሎች በማካፈል እስከ ዛሬ ይዞት የመጣውን ችቦ ለሌሎች የሚያስተላልፍበት መድረክም ይሆናል ብሏል ዘላለም ቻላቸው። በመጨረሻም በአሉ፣ አርቲስቱ በቀጣይነት ሊሰራቸው ላሰባቸው ሥራዎች መሠረት የሚጥልበትም ይሆናል።
የአሊ ብራ የሃምሳኛ አመት የመድረክ ውሎው በአል በምን አይነት መልኩ ይከበራል የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር። እንደ ወጣት ዘላለም ቻላቸው ገለፃ የበዓሉ አከባበር፣ የሚከተሉትን ዋና ዋና ዝግጅቶችና ተግባራት ያካተተ ይሆናል ብሏል።
ይህ ዝግጅት ሃምሳኛ አመት በአሉ በይፋ የሚጀመርበትና የሙያ አጋራቱ፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት፣ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆች እና ሚዲያ የሚገኙበት ዝግጅት ነው። ዝግጅት ስለ አሊ ብራ ሕይወትና ሥራዎቹ የሚቀርቡ ጥንታዊ ጽሁፎችን፣ ንግግሮችን እና የሙዚቃ ድግስን ያካትታል።
የአሊ ብራን ህይወትና ሥራዎች የሚያሳዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች እንዲሁም የተሸለማቸውን ሽልማቶች የሚቀርቡባቸው ኤግዚቢሽኖች በአዲስ አበባና በአደማ ከተማዎች ይካሄዳሉ።
በአዲስ መልክ የተቀናበሩ 10 የተመረጡ የአሊ ዘፈኖችን የያዘ አልበም ለወርቅ ኢዩቤሊዩው ይለቀቃል ሲል ወጣት ዘላለም ቻላቸው ተናግሯል። ከዚህ ሌላም ኮንሰርቶች እንደሚቀርቡም ገልጿል። ኮንሰርቶቹም የሚካሄድባቸው ከተሞችም ይፋ ሆኗል።
1. አዲስ አበባ
2. ድሬዳዋ
3. ሌሎች የክልል ከተሞችና የኦሮሚያ ከተሞች
4. በውጭ ሀገራት (አውሮፓ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና እስያ፣ አውስትራሊያ)
አሊ ቢራ በእስከዛሬ ህይወቱ ከ40 በላይ ሀገራት እየተዘዋወረ ሙዚቃዎቹን አቅርቧል። ስለዚህ አለማቀፋዊ ተቀባይነቱ ሰፊ እና ተወዳጅ በመሆኑ በየሐገሩ በጉጉት እንደሚጠበቅ ተናግሯል።

(ዘገባ ከሰንደቅ ጋዜጣ)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>