Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በታላቁ ሩጫ ሕዝቡ በሳዑዲ ላይ ተቃውሞውን ሲያሰማ ነበር፤ ሕዝቡ “አዝኗል ሀገሬ”እያለ ዘፍኗል –ሪፖርተር

$
0
0

“ሥራ አጥነት የስደት አበሳ ማብቂያው ቅርብ ላለመሆኑ ማስረጃ” በሚል ርዕስ ሪፖርተር ጋዜጣ ባስነበበው ዜና ትንታኔ “ታላቁ ሩጫ እሑድ ኅዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በጃንሜዳ ሲካሄድ ተሳታፊው ሁለት ስሜቶችን እኩል ለማስተናገድ ሲታገል ተስተውሏል፡፡ አንዴ የሐዘን ደግሞ ወዲያው የደስታ ስሜቱን ሲያስተጋባ ታይቷል፡፡” ብሏል።
የሪፖርተር (የብርሃኑ ፈቃደ 0 ዘገባ እንደወረደ፦

የተቃውሞ ድምፁን በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ላይ ሲያሰማ ተደምጧል፡፡ የተቃውሞ ድምፁ የወቅቱን የኢትዮጵያን ስደተኞች እንግልት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በተቃወመበት አፍታ ደግሞ ዋልያዎቹን እያወደሰ ይደሰታል፡፡ መንግሥትንም በአሽሙር ይሸነቁጣል፡፡ የአርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) አዲሱ ‹‹ኧረ ያምራል አገሬ›› ዘፈን፣ በሯጩ ሕዝብ ‹‹ኧረ አዝኗል አገሬ›› ተብሎ ተዘፍኗል፡፡

ከታላቁ ሩጫ ባሻገር የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሁኔታ በቢቢሲና በሌሎች የመገናኛ ብዙኃንም መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል፡፡ በሩጫው ዕለት ከሰዓት ቢቢሲ ‹‹ዎርልድ ሀቭ ዮር ሴይ›› በሚባለው ፕሮግራሙ ሁለት ኢትዮጵያውያንንና አንዲት ሳዑዲትን አሟግቷል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ስለስብዕናና ስለሰብዓዊነት አጥብቀው ሞግተዋል፡፡ ሙግታቸውም በርትዕ ነበርና መሬት ጠብ አላለም፡፡ ሳዑዲቷ በአገሯ ፖሊሶችና በመረን ነዋሪዎች ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ላይ የተፈጸመውን ግፍ ልታናንቀው ብትሞክርም አላዋጣትም፡፡ ይልቅም በአግባቡ ባልሠለጠኑ ፖሊሶች የተወሰደ ዕርምጃ ነው፣ በማለት ልትለሳለስ ስትሞክር ታየች፡፡ የሳዑዲ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ የአገሩን ኢኮኖሚ መሠረት በማድረግ እንደሆነ ቢነገርም፣ ዕርምጃው ግን አሳማኝ ምክንያት እንዳልሆነ ይህ ጽሑፍ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ ከዚህ በፊት ስለወቅታዊው የተመድ ሪፖርት መመልከት ይበጃል፡፡

great runከሳዑዲው አደጋም ቀድሞ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ አምሳያ ከሆኑ ድሃ አገሮች የሚሰደዱ ዜጎች ላይ ሰው ማሰብ ከሚችለው በላይ የሆኑ ኢሰብዓዊ፣ የክፋት ተግባራት ሲፈጸሙ ዓለም በዝምታ ስትመለከት ቆይታለች፡፡ ስደተኞች የውስጥ አካላቸው እየተጎለጎለ ሲወጣ፣ በየበረሃው እንደውዳቂ ዕቃ የተጣሉ ኢትዮጵያውያን ጥቂት አይደሉም፡፡ በባህር ጉዞ ለአሳነባሪ የተወረወሩ፣ ሰጥመው የቀሩ፣ የየብስና የባህር ቀለብ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ የሳዑዲው ግን በጠራራ ፀሐይ፣ በአደባባይ የተፈጸመ አሰቃቂና አዋራጅ ተግባር መሆኑ አሳቀቀን እንጂ ከዚህም የከፉ የሰቀቀን ድርጊቶች በኑሮ ፈላጊና ነገን ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ሲፈጸሙ ኖረዋል፡፡ ስደት ግን የሚቆምም ወይም የሚገታ አይመስልም፡፡

ከሰሞኑ ይፋ የተደረጉ የኢኮኖሚ ሪፖርቶች ስደትና ስደተኞችን ይብቃችሁ ለማለት የሚያስደፍሩ አይደሉም፡፡ ይልቁንም መጪውን ጊዜ ‹‹አስፈሪ›› እንደሚያደርጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ኮንፈረንስ ተቋም በኩል ይፋ የተደረገው፣ በልማት ኋላ የቀሩ አገሮች ሪፖርት፣ የኢትዮጵያን ጨምሮ የ49 አገሮችን አበሳ ይፋ አድርጓል፡፡ የሥራ ዕድል፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና፣ የአመራረት ስልትና አቅም ያተኮረባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ እነዚህ ኋላቀር አገሮች፣ በፍጥነት ለሚጨምረው የሕዝብ ቁጥራቸው ተመጣጣኝ የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ እየፈጠሩ አለመሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ምንም እንኳ ኢኮኖሚያቸው እያደገ ቢሆንም፣ የሚፈጥሩት ሥራና የገቢ ምንጭ ግን አስፈሪ ልዩነት እንደሚታይበት ይፋ ሆኗል፡፡

ባለፈው ሳምንት በ30 አገሮች አማካይነት ለመላው ዓለም ይፋ የተደረገው የተመድ ሪፖርት፣ ኋላቀር አገሮች በየዓመቱ ከ16 ሚሊዮን ላላነሱ ሕዝቦች የሥራ ዕድል መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡ ይህን ሲያደርጉ በየዓመቱ ለሥራ ብቁ ሆነው ወደ ገበያው ለሚገቡ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይችላሉ፡፡

የድሃ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት በአብዛኛው ወደውጭ በሚላኩ ጥሬ ዕቃዎችና የማዕድናት ሽያጭ ላይ ተመርኩዘው የውጭ ምንዛሪ ገቢን ያገኛሉ፡፡ እንደ ተመድ ሪፖርት ደግሞ በዚህ ዘርፍ ላይ የተመረኮዘ ኢኮኖሚ የሚወዛወዝ ሸምበቆ ነው፡፡ ይኸውም የዓለም ገበያ ለእነዚህ ምርቶች በየጊዜው የሚሰጠው ዋጋ ስለሚዋዥቅና ድሆቹን አገሮች ተጋላጭ ስለሚደርግ ነው፡፡

ይህ ባለበት የድሃ አገሮች የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በመጪዎቹ 25 ዓመታት በእጥፍ አድጎ 1.7 ቢሊዮን ይደርሳል፡፡ የድሃ አገሮች ከ60 በመቶ በላይ የሕዝብ ቁጥራቸው ከ15 እስከ 25 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከሚኖሩ አራት ወጣቶች አንዱ በምስኪኖቹ አገሮች ውስጥ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት 168 ሚሊዮን የነበረው የወጣቱ ሕዝብ ቁጥርም ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ 300 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡

እንዲህ የሚገሰግሰው የሕዝብ ቁጥርን የሚመጣጠን የሥራ ዕድልም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት በድሆች አገሮች እየተመዘገበ አይደለም ያለው ተመድ፣ በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ ብቻ 95 ሚሊዮን የሥራ መስኮችን ወደሥራው ዘርፍ ለሚገቡ የጉልበት ገበያው ተሳታፊዎች ተዘጋጅተው መጠበቅ አለባቸው፡፡

የተመድን የድሃ አገሮች ሪፖርት በአዲስ አበባ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በመገኘት ይፋ ያደረጉት፣ የድሃ አገሮች ጉዳይ ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ተስፋቸው ታፈረ ናቸው፡፡ በፍጥነት እያደገ የሚገኘው የድሆች አገሮች ሕዝብ ቁጥር፣ ወደአስፈሪነት ደረጃ እየገሰገሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በድሆች አገሮች የሚመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ለሥራ ብቁ በሆነው የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ለማስተናገድ እጅግ የሰለለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጉዳይ

በየዓመቱ በኢትዮጵያ ለሠራተኛነት አቅመ ዕድሜ ደርሰው ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች ቁጥር ከዘጠኝ ዓመት በፊት በነበረ አሃዝ መሠረት 1.4 ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ሥራ እንደሚፈልግ የሚታወቀው ሕዝብ ቁጥር ነው፡፡ በመጪዎቹ 25 ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ሲጨምር የሥራ ፈላጊው ቁጥር ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ የሚገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት በተመድ አሃዝ መሠረት ሰባት ከመቶ ነው፡፡ በአንፃሩ እየተፈጠረ የሚገኘው የሥራ ዕድል በዓመት ሦስት ከመቶ ያልዘዘ በመሆኑ ኢኮኖሚው የቱንም ያህል ፈጣን ቢሆን፣ በቂ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሆኖ አልተገኘም፡፡ በመሆኑም መጪውን ጊዜ፣ በተመድ አገላለጽ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡

መንግሥት በሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶችና ልዩ ልዩ ግንባታዎች አማካይነት በየዓመቱ ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቋል፡፡ በ2005 በጀት ዓመት ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የከተማ ልማት፣ የቤቶችና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ መንግሥት በሚያካሂዳቸው ግንባታዎች አማካይነት የሚፈጠሩት የሥራ መስኮች በተባበሩት መንግሥታት ዕይታ ለዘለቄታው አስተማማኝ አይደሉም፡፡ እምነትም አይጣልባቸውም፡፡ መጠነ ሰፊ ሊባሉ የሚችሉ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያና በሌሎች ድሆች አገሮች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ግን የቱንም ያህል የሥራ ዕድል ቢፈጥሩና በርካቶችን ቢደጉሙ፣ ለጊዜያዊ ካልሆነ በቀር በወቅታዊነታቸው ምክንያት ተመራጭ የሥራ መስኮች ሆነው እንዳይወሰዱ ተመድ አሳስቧል፡፡

በዚህ መንገድ የሚጓዙ አገሮች በተሳሳተ የፖሊሲ አቅጣጫ እየሾፈሩ መሆናቸውንም የተመድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ግን ከሚታሰበው በላይ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን፣ ይህም መንግሥት ባካሄደው የመሠረተ ልማት ግንባታ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በአንፃሩ የሚገነቡት መሠረተ ልማቶች የግሉን ዘርፍ ለማበረታታትና ወደኢኮኖሚው ለመሳብ ድልድይ እንደሆኑ ተመድ ይተነትናል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱን የግሉ ኢኮኖሚ ክፍል መምራት እንዳለበትም በመፍትሔነት አመላክቷል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ድሆች አገሮች በቴክኖሎጂ ምርጫቸው ላይ ጥንቃቄ እንደሚጎድላቸው ዶ/ር ተስፋቸው አብራርተዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን እናስፋፋለን በሚሉ አገሮች ውስጥ፣ ኮምፒውተር ለማስገባት ሲፈለግ የሚጠየቀው ከፍተኛ ታክስ ለዚህ ምስክር ነው ይላሉ፡፡

በአንድ ጎኑ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህነኑ እውነታ ይቀበለዋል፡፡ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በተመድ ይፋ የተደረገው ሪፖርት የያዛቸው አንኳር ሥጋቶችን እንደሚጋራ አስታውቋል፡፡ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እንዳረጋገጡት፣ መንግሥታቸው በተመድ ይፋ የተደረጉትን ትችቶችና ሥጋቶች ይቀበላል፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት ወዲያውኑ ሥራ አለመፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን የመንግሥት ኢንቨስትመንት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብና ዕድገቱን ለማቀጣጠል ወሳኝ በመሆኑ የመንግሥት የፖሊሲ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከ26 ከመቶ በላይ የሥራ አጥ ቁጥር መኖሩን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ሥራ አጥነት በገጠሩ የሚኖረውን ወጣት የሚያካትት አይመስልም፡፡

ክሬዲት ስዊስ የተባለው የጥናት ተቋም በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያትተው ድሆች ድሆች ሆነው፣ ሀብታሞችም የበለጠ ሀብታም ሆነው እንደሚቀጥሉ የሚያመላክት ነው፡፡ ኢትዮጵያና በተርታዋ የሚሰለፉ ድሆች አገሮች በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በቤተሰብ ደረጃ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው ሀብት ከአምስት ሺሕ ዶላር በታች ነው፡፡ በአንፃሩ ሀብታሞቹና እንደቻይና ያሉት ተንደርዳሪ አገሮች፣ በአምስት ዓመት ውስጥ የሚኖራቸው ሀብት በቤተሰብ ደረጃ ተደምሮ፣ 334 ትሪሊዮን ዶላር ተገምቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ሀብታሞች ያካበበቱት ሀብት ከ241 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ በዚያም ላይ የዓለም ሚሊየነሮች ቁጥርም 47 ሚሊዮን እንደሚሆን የመጪዎቹ አምስት ዓመታት ግምቶች ይናገራሉ፡፡

የሳዑዲዎች ምክንያት

እንዲህ ክፉኛ የተራራቀው የሀብታሞችና የድሆች አኗኗር፣ በገዛ አገራቸው ሠርቶ ለመኖር ያዳገታቸውንና ጥሩ እንጀራ ፍለጋ የሚባዝኑትን ሰዎች ብዛት በየጊዜው እንዲያሻቅብ ለማድረጉ ጠቋሚ ነው፡፡

ለተሰዳጅ ምስኪኖች ምቹ ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ በአገሬው ዘንድ የተጠሉ የሥራ መስኮች ላይ የውጭ ዜጎች እንዲንሰራፉባቸው መመቸታቸው ነው፡፡ ሳዑዲዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች ለሥራ ወደ ዓረብ አገር እንዳይሄዱ ለወራት የመከልከሉን ዜና ከማሰማቱ አስቀድመው፣ በየወሩ ከአሥር ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ለቤት ውስጥ ሥራና ሠራተኛነት እንደሚፈልጉ አስታውቀው ነበር፡፡ ይህንን መግለጫ ሲሰጡም በሁለት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች አመካይነት ሕፃናት መገደላቸውን ሰበብ አድርገው ነበር፡፡ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ያስፈልጉናል የሚለውን መግለጫ ለማውጣት ተገድዶ የነበረው፣ አብዛኛው የሳዑዲ ሕዝብና ሚዲያው፣ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በጅምላ ወንጀለኛ ብሎ መፈረጁን በመቃወም ነበር፡፡

ሳዑዲዎች በዝቅተኛ የሥራ መደብ ላይ ለመሥራት ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ ሳቢያ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ የድሃ አገር ዜጎች ላይ ጥገኛ ለመሆን መገደዳቸው ወድደውና ፈቅደው ያደረጉት ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ቀድሞም የተንሰራፋ ነበር፡፡ የአሁኑን ሰቆቃ ያባባሰው ግን የሳዑዲ መንግሥት በራሱ ፖሊሶች በወሰደው ዕርምጃ ጭምር የተፈጸመ መሆኑ ነው፡፡ ለሰባት ወራት የጊዜ ገደብ በመስጠት ከአገር ውጡ ያላቸው ሰነድ አልባ ዜጎች፣ በቀነ ገደቡ አልወጡም በማለት በፖሊስ የተወሰደው ዕርምጃ ከጭካኔ በላይ አረመኔያዊነት ባህርይ እንዳለው በማኅበራዊ ድረ ገጾች በመጋለጡም ነበር፡፡

የሳዑዲ መንግሥት ዜጎችን ከአገር ሲያባርር ምክንያት ካደረጋቸው ነጥቦች ውስጥ ኢኮኖሚ አንዱ ነው፡፡ ይኸውም እየጨመረ ለሚገኘው የሳዑዲ ሕዝብ፣ የሥራ መስኮችን ለማፋፋት ያለመ ነው፡፡ በዝቅተኛ የሥራ መስኮች ላይ ለመሰማራት አገሬው ድፍረቱም ፍላጎቱም ባይኖረውም ቀስ በቀስ ይላመደዋል የሚል ምክንያት መሰጠቱን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡ ይህ ግን አገሪቱ ላይ ወቅታዊ ሊባል የሚችል ጫና ማሳደሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቢያንስ በመካከለኛ ትራንስፖርት ዘርፍ በሹፍርና የተሰማሩ በርካታና ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ዜጎች በመባረራቸው ዕቃዎችን ለማጓጓዝ የሚጠይቀው ወጪ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡

የቢቢሲዋ ሳዑዲት ጨምሮ በርካቶቹ እንደሚስማሙበት፣ በዝቅተኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ከሳዑዲ መባረራቸው ገንዘብ ለማዳን እንደረዳቸውም ይናገራሉ፡፡ ይኸውም ስደተኞቹ የለፉበትን ገንዘብ ወደየአገሮቻቸው፣ ወደየዘመዶቻቸው ይልኩታል፡፡ ብዙ ገንዘብ ከሳዑዲ ይወጣል፡፡ አሁን ግን ያን ገንዘብ እዚያው ሳዑዲ ስለሚቀር፣ ሸማቾች ለፍጆታ እዚያው አገራቸው ውስጥ የሚያውሉት ተጨማሪ ገንዘብ ይኖራቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለኢኮኖሚው የሚፈለግ ምክንያት ነው የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ ከተሰነዘሩት መላምቶች ይሄ ብቻ ሚዛን ሊደፋ ይችላል፡፡ ሆኖም ሳዑዲዎች ወደማጀቱና ወደሌላውም ዝቅተኛ ሥራ መግባት እስከቻሉ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚለወጥ አይደለም፡፡

ስለዚህ የሳዑዲ መንግሥት ከየአገሩ የተጠራቀሙትን ምስኪን ስደተኞች ለማስወጣት ያስቀመጠው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ብዙም ሚዛን የሚደፋም ባይሆንም፣ ከአገሩ ማባረር የግዛት መብቱ በመሆኑ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እምቢ ማለት አይቻልም፡፡ በሰው አገር ውጣ ሲባል አልወጣም ማለትም የሚሆን አይደለም፡፡ ሰውን እንደእንስሳ በየጎዳናው ማሰቃየትና መግደል ግን አረመኔነት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑን በቢቢሲ መስኮት ልትሞግት የከጀለችው ሳዑዲት ሰዎችን እንዴት ማባረር እንዳለባቸው ባልሠለጠኑ ሰዎች የተወሰደ ዕርምጃ ነው ለማለትና ለማስረዳት ሞክራለች፡፡ የቱንም ያህል ምክንያት ቢቀርብ ሲደረግ የታየው የሳዑዲ መንግሥትና ዜጎቹን ጭካኔ ያጋለጠ ተግባር ነው፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቱ ይልቅ ሌላ ሰበብ እንደሚመዘዝበት ያመላክታል፡፡

ከኢትዮጵያ ዜጎች ባሻገር በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሳዑዲ ሲወጡ ምነው አልተገደሉ? ምነው ሰብዓዊ ክብራቸው አልተዋረደ? ለምን ኢትዮጵያውያን ብቻ? ለእነዚህ ጥያቄዎች የመላምት ሰበቦችን የሚያቀርቡ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ተቺዎች፣ መንግሥት ወደሳዑዲና ወደሌሎችም አገሮች ኢትዮጵያውያን እንዳሄዱ በመከልከሉ የተወሰደ የከሰረ የበቀል ዕርምጃ ያደርጉታል፡፡

ስደት በዚህ አስከፊ ገጽታው ሊቀጥል እንደሚችል ሥጋት የገባው ተመድ፣ እያደገ የሚገኘውን የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ምክንያት ማድረጉ ወቅታዊ ያደርገዋል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ‹‹የሮጠ አይቅደምህ፣ የታገለ አይጣልህ›› የሚለው የአበው ምርቃት ከምንጊዜውም በላይ አሁን ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል አንጋፎቹ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

ምንጭ፦ http://ethiopianreporter.com/index.php/business-and-economy/item/4146-%E1%88%A5%E1%88%AB-%E1%8A%A0%E1%8C%A5%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%88%B5%E1%8B%B0%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%88%B3-%E1%88%9B%E1%89%A5%E1%89%82%E1%8B%AB%E1%8B%8D-%E1%89%85%E1%88%AD%E1%89%A5-%E1%88%8B%E1%88%88%E1%88%98%E1%88%86%E1%8A%91-%E1%88%9B%E1%88%B5%E1%88%A8%E1%8C%83


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles