Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አሥሩ ዋንጫዎች:- አሥሮቹ ጀግኖችና አሥሩ ዓመታት በኦልድትራፎርድ –ክፍል 1

$
0
0

ከይርጋ አበበ

ዓለማችን ተወዳጅ ሊግ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በየዓመቱ 20 ክለቦችን ያፋልማል። የእንግሊዟ ዋና ከተማ ለንደን በየውድድር ዘመኑ ከአምስት ያላነሱ ክለቦች ሲወክሏት ትልቋ የንግድ ከተማ የላንክሻየሯ ግዛት ማንቸስተር ደግሞ ሁለት ክለቦቿን በአምባሳደርነት መድባ ላለፉት ረጅም ዓመታት ተሳትፋለች። የዛሬ የእዚህ ገጽ ትኩረት በውጤታማው ስኮትላንዳዊ አሠልጣኝ ሰር አሌክሳደር ቻፕ ማን ፈርጉሰንና ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ ይሆናል። የእንግሊዝ እግር ኳስ ሻምፒዮና ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከተቀየረበት 1992 ጀምሮ ላለፉት 21 ዓመታት (የዘንድሮውን ጨምሮ)የተካሄዱትን ውድድሮች ለበርካታ ጊዜያት በበላይነት የተቆጣጠረውን ክለብ የ10 ዓመታት ጉዞ ለመቃኘትም እንሞክራለን።
በ2003 የክረምት የተጫዋቾች ዝውውር ሲከፈት የዓለማችንን ከዋክብት ተጫዋቾች ካሉበት እያደነ ወደ ክለቡ የሚሰበስበው የፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ጋላክተኮስ ፍልስፍና የማንቸስተር ዩናይትድን በር ከማንኳኳት አላረፈም ነበር። መልከ መልካሙን የቅጣት ምት ስፔሻሊስት ዴቪድ ጆሴፍ ቤካምን ለመውሰድ። ሮናልዲንሆ ጎቾን ችላ ብለው እና ክሎድ ማኬሌሌን ሦስት ሜትር ርቀት ላይ ላለ ጓደኛው ኳስ በትክክል ማቀበል የማይችል ብለው የሸኙት ቱጃሩ የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት ዴቪድ ቤካምን ከአሌክስ ፈርጉሰን እጅ ለመንጠቅ ብዙም አልተቸገሩም ነበር። በቤካም ወደ ሳንቲያጎ በርናባው መኮብለል ልባቸው ያዘነውን የቲያትር ኦፍ ድሪምስ ታዳሚያንን ለማጽናናት ሲባል አንጋፋው አሠልጣኝ ዓይናቸውን ወደ ሌሎች ክለቦችና የአውሮፓ ሊጎች ላይ ማንከራተት ጀመሩ። ኤሪክ ጀምባ ጀምባን ጨምሮ ሌሎች ተጫዋቾችን ወደ ክለባቸው አመጡ። የዛሬውን ጨምሮ ለተከታታዮቹ እትሞቻችን በአሌክስ ፈርጉሰን መነጽር ታድነው ኦልድ ትራፎርድ ደርሰው ክለቡን ውጤታማ ማድረግ የቻሉትን ተጫዋች እናያለን።
ክፍል 1
man 41. ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶሳንቶስ ኤቬሮ
ስለ 2008ቱ የዓለም ኮከብ ምን ይባላል? በማንቸስተር ዩናይትድ ያላገኘው የግልና የቡድን ክብር የለም። በ12.24 ሚሊዮን ፓውንድ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ማንቸስተር ዩናይትድ የደረሰው ወጣት ዴቪድ ቤካም ለባሽ አልባ ያደረገውን «7 ቁጥር» ከአሌክስ ፈርጉሰን ተበረከተለት። ጆርጅ ቤስት፣ ብሪያን ሮብሰን፣ ኤሪክ ካንተናና ዴቪድ ቤካም ለብሰውት ታሪክ የሠሩበትን ቁጥር ለብሶ መጫወት ለወጣቱ ከባድ ፈተና ቢሆንም ሁሉንም ጫናዎች ተቋቁሞ ውጤታማ ግልጋሎትን ለሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቡድን አበርክቷል። በ80 ሚሊዮን ፓውንድ ነጭ ለባሾቹን ከመቀላቀሉ በፊት በኦልድትራፎርድ 3 ተከታታይ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ አንድ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ አንድ አንድ የዓለም ክለቦች ሻምፒዮን እና ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን ጨምሮ ሌሎች ዋንጫዎችን በቀዩ ማሊያ አጣጥሟል። የዓለም እና የአውሮፓ ኮከብ ተጫዋችን ሽልማት ከጆርጅ ቤስት ቀጥሎ የወሰደ ሁለተኛው የቀያይ ሰይጣኖቹ ተጫዋች ሲሆን፤ ከሉይስ ፊጎ በኋላ ፖርቹጋል ያፈራችው የዓለም ኮከብ የሆነውም በእዚሁ ግዙፍ ክለብ ውስጥ ነው። 8የሻምፒዮንስ ሊግ ጎሎችን በአንድ የውድድር ዓመት አስቆጥሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ኮከብ ጎል አግቢነትን ክብር ጨምሮ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ጎል አግቢ ሽልማትን ለግሉ አድርጓል። ለተከታታይ አራት ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉን የዓመቱ ምርጥ ሽልማቶች የተጎናፀፈው በላንክሻየሩ ክለብ ቆይታው ነው። እነዚህ እና ያልተጠቀሱት ብዙ ምክንያቶች ያለምንም ጥርጥር ክርስቲያኖ ሮናልዶ የ10 ዓመቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ምርጥ ያስብለዋል።
2. ዋይኒ ማርክ ሩኒ፡-
በኤቨርተን አካዳሚ እግር ኳስን አሀዱ ብሎ የጀመረው ታጋዩ ዋዛ ( የሩኒ ቅጽል ስም) በ2003 በየንስ ሌህማን መረብ ላይ ያሳረፉት የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጎሉ የታላላቅ ክለቦች አሠልጣኞች ዓይን እንዲያርፍበት አደረገው። የእነ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አገር ባዘጋጀችው የ2004 የአውሮፓ ዋንጫ በሦስት አናብስቶቹ ማሊያ ደምቆ የታየውን የኤቨርተን ወጣት ለማግኘት ኒውካስትል ዩናይትድን ጨምሮ ሌሎች የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ፍላጎታቸውን ቢገልጹም ስኮትላንዳዊው ውጤታማ አሠልጣኝ ሰር አሌክስ በ25.60 ሚሊዮን ፓውንድ የቀያይ ሰይጣኖቹ ንብረት አደረጉት። 8 ቁጥር ማሊያ ለብሶ የመጀመሪያ ጨዋታውን በኦልድትራፎርድ ፌነርባቸን የገጠመው ሩኒ 3 ጎሎችን ለአዲሱ ክለቡ አስቆጥሮ ጅማሬውን አሳመረ። በነገራችን ላይ ከ20 ዓመት በታች 25.6 ሚሊዮን ፓውንድ ለዝውውር ወጪ የተደረገበት የዓለማችን ተጫዋች ዋይኒ ሩኒ ብቻ ነው። በመጀመሪያ ዓመት የክለቡ ቆይታው የዓመቱ ወጣት ተጫዋች ሽልማትን ያገኘ ሲሆን፤ 12ቱ የፕሪሚየር ሊግ ጎሎቹም የክለቡ ከፍተኛ ጎል አግቢነት ክብርን አጎናጽፈውታል። ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የዘንድሮውን ጨምሮ 5 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን፤ ባለግዙፍ ጆሮውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫንም ማግኘት ችሏል። በጃፓኑ የዓለም ክለቦች ሻምፒዮና ክለቡ ሻምፒዮን ሲሆን፤ ሩኒ ደግሞ በግሉ የውድድሩ ምርጥ በመሰኘት የቶዮታ ቁልፍ ተሸላሚ ሆኗል። ከሚያስቆጥራቸው ጐሎች በላይ ለጓደኞቹ አመቻችቶ የሚያቀብላቸው ኳሶች ብዛት በየውድድር ዓመቱ ለክለቡ የሚከፍለው መስዋዕትነት ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ቀጥሎ የዩናይትድ የ10 ዓመቱ ምርጥ ፈራሚ ያሰኘዋል።
3. ኤድ ዊን ቫን ደር ሳር
በአያክስ አምስተርዳም እጅግ ውጤታማ ዓመታት ማሳለፉን ተከትሎ ወደ ቱሪን ተጉዞ ውጤት አልባ ጊዜያትን በአሮጊቷ ቤት ያሳለፈው ሆላንዳዊ ግብ ጠባቂ የእግር ኳስ ህይወቱን በክራቨን ኮቴጅ ካደሰ በኋላ ነበር 2 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ተደርጎበት ኦልድትራፎርድ በር የደረሰው። 154 ጨዋታዎችን ለምዕራብ ለንደኑ ፉልሀም ያደረገው ሆላንዳዊ ሰኔ አሥር 2005 ማንቸስተር ሲደርስ ክለቡ ለ2 ተከታታይ ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በለንደን ባላንጣዎቹ ተወስዶበት ነበር።
ቀጭኑ ሆላንዳዊ ለ266 ጨዋታዎች የኦልድትራፎርዱን ክለብ የግብ መስመር በጀግንነት የጠበቀ ሲሆን፤ ማንም ግብ ጠባቂ ያልሠራውን ጀብዱ የፈጸመውም በእዚህ ክለብ ውስጥ ነው። ለ1,311 ደቂቃዎች በፕሪሚየር ሊግ መረቡን በኳስ ሳያስነካ የዘለቀው ጎልማሳ እስከአሁንም ይህ ክብረወሰን በእጁ ይገኛል። በ40 ዓመት ከ211 ቀናት ዕድሜው በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ የክለቡን አንድ ቁጥር በመልበስም አንጋፋው የፍጻሜ ተፋላሚ የሚል ስም የተሰጠው ሲሆን፤ በአጠቃላይ በክለቡ አራት የፕሪሚየር ሊግ እና አንድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨምሮ የዓለም ክለቦች ሻምፒዮና፣ የኤፍ ኤ ካፕ፣ የካርሊንግ ካፕ እና ኮምዩኒቲ ቮልድ ዋንጫዎች በሙሉ ማሳካት የቻለው በእግር ኳስ የመጨረሻዎቹ ዕድሜው ላይ በቀያይ ሰይጣኖቹ ቤት ነው። ከፒተር ሹማይክል በኋላ የጎል መስመራቸውን በብቃት የጠበቀላቸውን ሆላንዳዊ የኦልድ ትራፎርድ የታዳሚዎች የ10 ዓመቱ ምርጥ ጉዟችን ሲሉ የሚጠሩት ሲሆን፤ ሰር አሌክሰ ፈርጉሰን ደግሞ «ጀግና» ብለው የጠሩት ግብ ጠባቂ በእዚህ ምርጫ የ3ኛ ደረጃን ቦታ ሲያገኝ ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም።
4. ኒማኒያ ቪዲች
የ31 ዓመቱ ምሥራቅ አውሮፓዊ ከስፓርታክ ሞስኮ በ2006 ታኅሣሥ መጨረሻ የ7 ሚሊዮን ፓውንድ ቼክ የግሌዘር ቤተሰቦችን አስከፍሎ ቀይ ሰይጣን ሆነ። ከያኘ ስታም ወደ ላዚዮ ጉዞ በኋላ የኦልድ ትራፎርዱን የኋላ ክፍል በጀግንነት የመራ ሲሉ ጋዜጠኞች ያሞካሹታል። ከእንግሊዛዊው ሪዮ ፈርድናንድ ጋር የፈጠሩት የተዋጣለት ጥምረት እነ ጀራርድ ፒኬ፣ ዌስ ብራውን እና ሚኬል ሲልቨስተር የኦልድትራፎርድን የመውጫ በር እንዲመለከቱ አድርጓል። ኤድዊን መረቡን ሳያስደፍር ለ15 ጨዋታዎች ሲጓዝ ከቫንደር ሳር ፊት ለፊት እየቆመ የፕሪሚየር ሊጉን አጥቂዎች በብቃት የታገለው ይህ ሰርቪያዊ ወጣት ነው። በኒኮላስ አኔልክ ጎል የተደፈረው የቫንደር ሳር መረብ አኔልካ ይህን ዕድል ሲያገኝ ቪዳ ሜዳ ውስጥ አልነበረም። ከ260 በላይ ጨዋታዎችን በቀዩ ማሊያ ተጫውቶ 18 ኳሶችን ከተቃራኒ ቡድን መረብ ላይ ያሳረፈው ኒማኒያ ቪዲች ለሁለት ዓመታት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋችነት ዘውድ የደፋ ሲሆን፤ ለአራት ዓመታት ደግሞ የዓመቱ ምርጥ 11 ውስጥ መካተት የቻለ ተጫዋች ነው። ተደጋጋሚ ጉዳቶች የቀድሞ ምርጥ ብቃቱን ቢያሳጡትም የማንቸስተሩ አምበል ግን በደጋፊዎች ዘንድ ምርጥ ከመባል አላገደውም። «ለተከታተይ ሦስት ዓመታት በቸልሲ እና አርሴናል የበላይነት የተወሰደባቸውን የበላይነት ለማስመለስ ቀያይ ሰይጣኞቹን ወደ ሻምፒዮንነት የመራ ጀግና» ሲሉም ያሞካሹታል። በአራተኛነት ሲቀመጥ የሠራው ሥራ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ያሳያል።
5. የፓትሪስ ኢቭራ
ትውልደ ሴኔጋላዊው የፈረንሳይ የኋላ ደጀን በ5.5 ሚሊዮን ፓውንድ ከሞናኮ ወደ ማንቸስተር ዝውውር ሲያደርግ እውቅናው እምብዛም ነበር። የማንቸስተሩ ሁለተኛ አምበል ከክለብ ጓደኛው ኒማኒያ ቪዲች ጋር በአንድ ሳምንት ውስጥ ኦልድትራፎርድ የደረሰ ሲሆን፤ የአርጀንተናዊውን ጋብርኤል ሄንዝ ቦታ ሲቀበል ጊዜ አልወሰደበትም ነበር። የተጋጣሚ ቡድን የክንፍ ተጫዋቾችን ማቆም የሚፈራው አርጀንቲናዊ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የክለቡ ድክመት እየተባለ ይተች ስለነበር የፈረንሳዊው ኦልድትራፎርድ መድረስ ቀያይ ሰይጣኞቹን እፎይ ያሰኘ ዝውውር ነበር። ታላላቁቹ ማድሪድና ሊቨርፑል ፊርማውን ለማግኘት የሞናኮን ደጅ ደጋግመው ቢጠኑም የወጣቱ ልብ ሊከፈትላቸው አልቻለም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የምንጊዜም ፍላጎቱ ቀይ ሰይጣን መሆን እንጂ የሌላ ክለብ ማሊያ መልበስን አስቦ አለማወቁ ነው። ኒማኒያ ቪዲች ያገኛቸውን ዋንጫዎች በሙሉ ያገኘ ሲሆን፤ በግሉም በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል። እስከአሁን ድረስም ቀያይ ሰይጣኖቹን በታማኝነትና በጀግንነት እያገለገለ ይገኛል። አምስተኛው የአሥር ዓመቱ ምርጥ የማንቸስተር ዩናይትድ ፈራሚ።
ይቀጥላል


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>