- ግርማ ካሳ
Muziky68@yahoo.com
ሚያዚያ 21 2005 ዓ.ም
ዶር ቴዎድሮስ አዳኖምን ጨምሮ በርካታ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት፣ በተለያዩ የአሜሪካና የአዉሮፓ ከተሞች በመዘዋወር፣ ለአባይ ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሞክረዋል። ነገር ግን በበርካታ ከተሞች፣ ከዚህ በፊት ከነበረዉ በተለየ ሁኔታ፣ ጠንካራ ተቃዉሞ የደረሰባቸዉ ሲሆን፣ አንዳንድ ከተሞችም፣ ተቃዋሚዎች ስብሰባዉን ሙሉ ለሙሉ እስከመቆጣጠር የደረሱበት ሁኔታም እንደነበረም ታዝበናል።
በሚነሱ ተቃዉሞዎች ዙሪያ፣ በዋሺንግተን ዲስ አስተያየት የሰጡት ዶር ቴዎድሮስ «በሃሳብ አለመስማማት በጣም ጤነኛ ነገር ነዉ። ነገር ግን እንደ ሰዉ ማመን የሚከብደኝ፣ ድህነትን ከአገራችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርገዉን የልማት እንቅስቃሴ በመቃወም፣ ሳይሰለቻቸው የሚጮሁትን መታዘብ ነዉ» ሲሉ በሚነሱ ተቃዉሞዎች ላይ ያላቸውን ንዴት አዘል ዘለፋ አሰምተዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ በሂዉስተን ቴክሳስ፣ ባደረጉት ንግግር፣ የአባይን ግድብ ለመገንባት ለምን እንዳስፈለገ የሚያስረዱ ነጥቦችን ካስቀመጡ በኋላ ፣ ወደ ንግግራቸዉ መጨረሻ ላይ ድህነትን ከአገራችን ለመቅረፍ የሚረዳ ፕሮጀክትን መቃወም ከ«ጸረ-ኢትዮጵያዊነት» ተለይቶ እንደማይታይ በማሳሰብ ነበር፣ በተቃዋሚዎች ላይ ጠንካራ ትችት ያቀረቡት።
ለአባይ ግንባታ ያለኝን የጸና ድጋፍ፣ በተለያዩ ጊዜያት በጽሁፍ ይፋ አድርጊያለሁ። ወደፊትም ይሄንን አቋሜን ከማንጸባረቅ ወደ ኋላ አልልም። አባይን መገንባት ይቻል ዘንድ፣ ኢትዮጵያዉያንን በሙሉ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ኢትዮጵያውያንን ለማሰባሰብ ደግሞ፣ በፖለቲካዉና በሰብአዊ መብት አከባበር ዙሪያ ለዉጥ መደረግ እንዳለበትም አሳስቤ ነበር። ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ለብሄራዊ እርቅ ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ፣ ዳያስፖራዉ እነ ዶር ቴዎድሮስ አዳኖምን በተቃዉሞ ሳይሆን በአክብሮት ይቀበላቸው ነበር።
አምባሳደር ግርማ ብሩም ሆኑ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቴዎድሮስ አዳኖም፣ ያጡታል ብዬ አላሳብም፤ ካጡት ግን እንዲገነዘቡ የምፈልገዉ ነጥብ አለኝ። እርሱም አባይ እንዳይገነባ የሚፈልግ ማንም ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ነዉ። ጥያቄዉ አባይን የመገንባት አስፈላጊነት ላይ አይደለም። ኢትዮጵያዉያን «አባይ አይገንባ» የሚል መፈክር አላሰሙም። ጥያቄዉ የፍትህ ፣ የእኩልነት፣ የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄ ነዉ። «አባይ ይገደብ። ግን ከአባይ በፊት ዘረኝነት ይገደብ» ነዉ እየተባለ ያለዉ። የሪፖርተር አባባልን ልዋስና «አባይን የመገደብ ሥራ ዴሞክራሲን ባለመገደብ ይታጀብ » የሚል ነዉ አንዱና ዋነኛዉ የኢትዮጵያዉያን ጥያቄ።
አባይ የሚገነባዉ እኮ ሕዝብን ለመጥቀም ነዉ። አሁን እየሆነ ያለዉ ግን ኢሕአዴግ አባይን፣ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት የሚጠቀምበት መሳሪያ እያደረገዉ፣ ለፖለቲካ ፍጆታና ጥቅም እየተጠቀመበት እንደሆነ ነዉ። አባይ ለሕዝብ መሆኑ ቀርቶ፣ ሕዝብ ለአባይ፣ አባይ ደግሞ ለኢሕአዴግ እየሆነ ነዉ። ከፈረሱ በፊት ሰረገላው እየቀደመ ነዉ። አንድ በሉ።
«አቶ መለስ ሞተዋል። የርሳቸዉን ነገር ለታሪክ እንተወዉ። ከልብ የሚወዷቸዉ ደጋፊዎቻቸውን ላለማስከፋት፣ ለእርቀ ሰላም በሩን እናመቻች» በሚል ሃሳብ ነዉ እንጂ ዝም የምንለዉ፣ ወደ ኋላ ተመልሰን ነገሮችን መምዘዝ ከፈለግን እኮ፣ ብዙ ስለ አቶ መለስ ግፍና ወንጀል መዘርዘር እንችላለን። ኢሕአዴጎች ግን ዝምታችንን እንደ ሞኝነት ቆጥረዉት ነዉ መሰለኝ፣ መለስ ዜናዊን «አምልኩት» ለማለት እየከጀላቸው ነዉ። የአባይንም ግድብ እንደመሳሪያ በመጠቀም የአቶ መለስን «ጀግንነት»፣ «ሕያውነት» በአይምሯችን ዉስጥ ሊቀርጹ ይፈልጋሉ። አባይን ብሎ የሚመጣዉ ሰው ሁሉ የአቶ መለስን ምስል ተሳልሞ እንዲመለስ ነዉ መሰለኝ፣ በዊዉስተን ቴክሳስ በተደረገው የአባይ ግድብ ስብሰባ፣ አምባሳደር ግርማ ብሩ ንግግር ያደርጉበት ከነበረዉ መድረክ በስተቀኝ፣ ትልቅ የአቶ መለስ ዜናዊ ምስል እንደ ታቦት ተቀምጦ ያየነዉ።
እንግዲህ ሁለተኛው የሕዝብ ጥያቄ «አባይን የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ለምን ታደርጉታላችሁ ?» የሚል ነዉ። «አቦ ሰለቸን። ሱካርም ሲበዛ ይመራል! አባይ አባይ ፣ መለስ መለስ እያላችሁ አታደንቁርን» እያለ ነዉ ሕዝቡ። ሁለት በሉ።
ኢሕአዴግ ለአቶ መለስ ዜናዊ ቀብር ስነ-ስርዓት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች አቃጥሏል። ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት አሉት። አብዛኞቹ አንድ ለአምስት በሚለዉ አሰራር፣ ሌላ ሥራ የሌላቸው፣ ሕዝብን የሚሰልሉና የሚያስጨንቁ ካድሬዎች ናቸው። በርካታ የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዶላር እየከፈሉ ፣ ልጆቻቸዉን እጅግ በጣም ዉድ በሆኑ ዉጭ አገር ባሉ ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች ያስተምራሉ። የአዲስ ፎርቹኑ ጋዜጠኛ ታምራት ወልደ ጊዮርጊስ እንደዘገበዉ፣ ለአባይ ግድብ ከሚያስፈልገው ወጭ ሁለት እጥፍ የሚሆን፣ ወደ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የዉጭ ምንዛሪ፣ ከኢትዮጵያ በሚስጥር ተዘርፎ ወጥቷል። መቼም ወደ 99.9 በመቶ የሚሆነው ድሃዉ ሕዝባችን ዶላር በእጁ ይነካል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነዉ። በአብዛኛዉ ለአባይ ግድብ ገንዘብ የሚሰበስቡ የኢሕአዴግ መሪዎች፣ አባላትና ደጋፊዎቻቸዉ ናቸው ዶላር ወደ ዉጭ አገር የሚያሸሹት። [1]
እንግዲህ አንድ፣ እነዶር ቴዎድሮስ አዳኖም የዘነጉት ነገር ቢኖር፣ የተቃዋሚዎችና የአብዛኛዉ ሕዝብ ሌላው ጥያቄ፣ በአባይ ግድብ ላይ ሳይሆን፣ «ለአባይ ግንባታ ብላችሁ፣ ከሕዝብ የምትሰበስቡት ገንዘብ፣ ለአባይ ጥቅም ሳይሆን ወደ ባለስልጣናቱ ካዝና አለመግባቱ ምን ማረጋገጫ አለን?» የሚል መሆኑን ነው።
እነ ዶር ቴዎድሮስ፣ በዚህ ጉዳይ ሊጠይቋቸው የሚችሉ፣ እንደ አቶ እስክንድር ነጋ፣ ርዮት አለሙ፣ ዉብሸት ታዬ ያሉ ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት ወንጀል ከሰዋቸዋል። በሕዝቡ ፊት የኢሕአዴግ ባለስልጣናትን ቻሌንጅ ሊያደርጉ የሚሞክሩ እንደ አቶ አንድዋለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ በቀለ ገርባ ያሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አስረዋቸዋል። እንደ ፍትህ፣ ፍኖት ያሉ ነጻ ጋዜጦችን ዘግተዋል። ሶስት በሉ።
ዶር ቴዎድሮስ በዋሺንገትን ዲሲ የተናገሩት፣ አንድ የምጋራላቸው አባባል አለ። «የሃሰብ ልዩነቶች መኖራቸው በጣም ጤነኛ ነገር ነዉ» ባሉት እስማማለሁ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በሃሳብ ከሚለይዋቸዉ ጋር ለመነጋገርና ለመመካከር ፍቃደኛ የሆኑም ይመስለኛል። የሃሳብ ልዩነቶች ሊያጣሉን፣ ሊለያዩንና ሊያቃቅሩን አይገባም። ነገር ግን፣ አንድ መረሳት የሌለበት ነጥብ ቢኖር፣ የሃሳብ ልዩነትን የማያክብረዉ፣ ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጠ፣ አገር ቤት በሰላም ከሚታገሉ የፖለቲክ ድርጅቶች ጋር አልነጋገርም በማለት ግትር የሆነዉ፣ ለወንድማማችነትና ለብሄራዊ እርቅ በር የዘጋዉ፣ «ለምን ተቃዉሞ ተነሳብኝ ? » ብሎ ዜጎችን የሚያስረዉና የሚያስጨንቀዉ፣ የርሳቸው ድርጅት ኢሕአዴግ መሆኑን ነዉ።
የሃስብ ልዩነቶች የሚንሸራሸሩባት፣ የመቻቻል፣ የመቀባባል ባህል የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማየት የሚሹ ከሆነ፣ ዶር ቴዎድሮስ በቀዳሚነት ድርጅታቸውን ይፈትሹ ዘንድ እመክራቸዋለሁ። እርሳቸዉና ጓዶቻቸው፣ የሚነሱ ተቃዉሞዎችን ለማውገዝ ከሚቸኩሉ፣ ተቃዉሞዎች ለምን እንደሚነሱ ቆም ብለዉ ቢመረምሩ፣ እንደ ከፍተኛ አመራር አባል ለሚነሱ ጥያቄዎች መፍትሄ ቢፈልጉ መልካም ነዉ እላለሁ።
እንደዉም እዉነት እንነጋገር ከተባለ የአባይ ጉዳይ እንደ ጉዳይ መነሳትም አልነበረበት፤ የለበትምም። አባይ የፖለቲክ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነዉ።
ዶር ቴዎድሮስ ሃሳብ ሊገባቸው አይገባም። እርሳቸዉና ድርጅታቸው በነርሱ በኩል ማድረግ ያለባቸዉን ካደረጉ፣ እርግጠኛ ነኝ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በጋራ አገሩን ለማልማት፣ አባይን ለመገንባት ይነሳል። ኢትዮጵያዉያን በአባይ ጉዳይ ቀሳቀሽና አስታዋሽ አያስፈልጋቸውም። እንኳን፣ አንዱን አባይ፣ አሥር የአባይ አይነት ግድቦች የመስራት አቅሙና ጉልብቱ አላቸው። የሚያስፈልገው ይሄንን የሕዝብ ኃይል ማዳመጥ፣ ማክበር፣ ለሚያነሳቸውም መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ብቻ ነዉ። አለቀ። ጆሮ ያለው፣ ይስማ፣ ልብ ያለው ያስተዉል።
በተለይም የሚከተሉትን በማድረግ፣ ኢሕአዴግ ግልጽ የሆኑ የፖሊሲ አቅጣጫ ለዉጦች ከወሰደ፣ እጅግ በጣም በርካታ የአገራችን ችግሮችና እንቆቅልሾች መፍትሄ ያገኛሉ ብዬ አምናለሁ።
- እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ርዮት አለሙ፣ ዉብሸት ታዬ፣ ናትናኤል መኮንን፣ በቀለ ገርባ የመሳሰሉ የሕሊና እስረኞች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ። እነዚህን ወገኖች ሽብርተኞች ናቸው ብሎ ፈርጆ ማሰር፣ አስቂኝ ከመሆኑ ባሻገር፣ አሳፋሪና አሳሪዎቹንም ምን ያህል የጫካ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ያነሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነዉ።
- እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ሜዲያ፣ ፍርድ ቤቶችን የመሳሰሉ ተቋማት፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ለመመካከርና፣ ስር የሰደዱ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ይቻል ዘንድ፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር/ውይይት ይጀመር። ኢትዮጵያ ቻይና አይደለችም። ተቃዋሚዎችን በመርገጥና በማፈን ብቸኛ አዉራ ገዢ ፓርቲ ሆኖ መቀጠል አይቻልም።
ይሄን አባባሌን አንዳንድ ኢሕአዴጎች ላይስማሙ፣ በጡንቻቸዉ ተማምነው፣ «ባለህበት ቀጥል» ሊባባሉ ይችላሉ። ነገር ግን እነርሱ ዉስጥ ያሉ፣ ብስለት ሊኖራቸው የሚችል ጥቂቶች፣ የ«ባለህበት ቀጥል» ፖለቲካ እንደማያዋጣና ኢሕአዴግ በሰብአዊ መብቶች መከበርና በዲሞራሲያዎዊ ለዉጦች ዙሪያ ትልቅ ማሻሻል ማድረግ እንደሚገባ ያጡታል ብዬ አላስብም።
- የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ፣ የ«ኢሕአዴግ ፕሮጀክት» ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፕሮጀክት ይሆን ዘንድ ከኢሕአዴግ እንዲሁም ከተቃዋሚዎች የተወጣጡ ባለሞያዎች ያሉበት፣ ገለልተኛ የሆነ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነትን አሰራር ያለው፣ ኮሚሽን እንዲመራ ይደረግ።
ያኔ፣ በአባይ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ የሚነሱ ተቃዉሞች አይኖሩም። ያኔ ገንዘብ ለማሰባሰብ ብዙ ዝግጅቶችም ማድረግም አያስፈልግም። በአጭር ጊዜ ዉስጥ፣ የሚያስፈልገዉን አራት ቢሊዮን ዶላር፣ አገር ቤት ያለዉ ድሃ ሕዝባችን የአንድ ወር ደሞዝን እንዲከፍል ታንቆ ሳይገደድ፣ ዳያስፖራው ብቻ፣ በራሱ አነሳሽነት ሊሸፍነዉ ይችላል።
እንግዲህ ዶር ቴዎድሮስም ሆነ ጓዶቻቸው ልብ ይላሉ ብዬ አስባለሁ። የሚነሱ ተቃዉሞዎችን አናንቀዉ፣ ለኢትዮጵያዉያን መሰረታዊ የመብት ጥያቄ ችላ ብለው የሚቀጥሉ ከሆነ ወደፊት የተወሳሰበ ሁኔታ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ አሳስባለሁ። የሕዝብ መብት እየተረገጠ የሚደረግ የልማት እንቅስቃሴ ዘለቄታ አይኖርም። ምናልባት እድሜ ዘመኑን በጫካ ያሳለፈ ጠባብና እንጭጭ የኢሕአዴግ አመራር አባል፣ ይሄን ላይረዳ ይችላል። እንደ ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም፣ አቶ ደምቀ መኮንን ያሉ፣ የተማሩ፣ በሳልና ትሁት ምሁራን የኢሕአዴግ አመራር አባላት ግን ይረዱኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።