በፋኑኤል ክንፉ (ሰንደቅ ጋዜጣ) በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ለፍትህ ሚኒስቴር በይቅርታ እንዲፈታ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን ከፍትህ ሚኒስቴር በደብዳቤ እንደተገለፀላቸው ባለቤቱ አስታወቁ።
የጋዜጠኛ ውብሸት ባለቤት ወይዘሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለሰንደቅ እንደገለጹት፤ “ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ከፍትህ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት በተፃፈ ደብዳቤ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ፈርሞ ተረክቧል። በደብዳቤው የጠየቀው ይቅርታ እንዳልተፈቀደለት በሁለት መስመር ከመግለፁ ባለፈ ይቅርታው ለምን ተቀባይነት እንዳላገኘ የሚገልፅ ኀሳብ አልያዘም” ብለዋል።
አያይዘውም፣ “ከዚህ በፊት የአቶ ኤልያስ ክፍሌ እህት የሆኑት ወ/ሮ ሂሩት ይቅርታ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር ምክንያቱ ተገልፆ ነበር። ለውብሸት ግን ምክንያቱ አልተገለጸም። ጉዳዩን ለማወቅ ለፍትህ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቤ ነበር። የውብሸት ደብዳቤ ወጪ ተደርጓል። አድራሻው ለማረሚያ ቤት ስለሚል እኛ ምን እንደተፃፈ አላወቅንም። ስለዚህም ማረሚያ ቤት ጠይቂ ብለውኛል። ማረሚያ ቤት የመጣው ደብዳቤ ሁለት መስመር ላይ የሰፈረ ነው። ይዘቱም የይቅርታ ጥያቄው ተቀባይነት አላገኝም የሚል ነው” ሲሉ ለሰንደቅ ገልፀዋል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ከታሰረ ሁለት አመት ከሶስት ወራት የሞላው ሲሆን፤ የተፈረደበት የእስር መጠን አስራ አራት ዓመት ነው። ጋዜጠኛ ውብሸት የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው።¾
↧
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ይቅርታው ተቀባይነት እንዳላገኘ የሚገልጽ ደብዳቤ ከፍትህ ሚኒስቴር ደረሰው
↧