Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: እህቴን ሔፕታይተስ ከውጭ ጉዞዋ ያስቀራት ይሆን?

$
0
0

እህቴን ወደ አሜሪካ ለማምጣት ያልቆፈርኩት ድንጋይ አልነበረም። ሆኖም አልተሳካልኝም። እርሷ በጣም ወደ ውጭ ለመሄድ ከፍተኛ ፍላጎት አላት። ካልሆነ ወደ አረብ ሃገርም ቢሆን ላከኝ በሚል ገንዘብ ልኬላት መሰናዳት ጀመረች። በኋላ ላይ ወደ ውጭ ለመሄድ ባደረኩት የጤና ምርመራ ሔፖታይተስ ‹‹ቢ›› አለብሽ ተባልኩኝ አለችኝ። ወደ አረብ አገር ሄጄ ሰርታ ራሷን ለማሻሻል ባደረረባት ፍላጎት መሰረት በአንድ ኤጀንሲ በኩል እንቅስቃሴ ጀምራለች። ከጉዞዋ በፊት የተለያዩ የላብራቶሪ እና የአካል ምርመራዎች ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ አድርጋ ሁሉን ነፃ ስሆን ሔፕታይተስ ‹‹ቢ›› የሚባል ሰምቼ የማላውቀው ችግር በደምሽ ይታያል ተባልኩ አለችኝ። ምን አይነት በሽታ ነው? ምንድነው የእህቴ የወደፊት እጣ ፈንታዋ?
የከበቡሽ ወንድም

የዶ/ር ዓብይ ምላሽ፡- ውድ ጠያቂያችን እህትህ በአጋጣሚ ለሜዲካል ቼክ አፕ ሄዳ የሔፖታይተስ ‹‹ቢ›› (ሔፖታይተስ ‹‹B›› ሰርፌስ አንቲጅን) ከሌሎች ምርመራዎች መካከል ይህ ምርመራ በደምዋ ውስጥ የሔፖታይተስ ቫይረስ እንዳለ ጠቁሟል፡፡ በአጠቃላይ ወደ አምስት የሚደርሱ ሔፖታይተስ ‹‹A›› ሔፖታይተስ ‹‹B›› ሔፖታይተስ ‹‹C›› ሔፖታይተስ ‹‹D›› እና ሔፖታይተስ ‹‹G›› የተባሉ ጉበትን ለጉዳት የሚያጋልጡ የቫይረስ አይነቶች (cirrhosis) እስከ ጉበት ካንሰር በሄፖታይተስ B,C እና D የበሽታ ደረጃዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሔፓታይተስ ቫይረሶች የሚከፋፈሉት በሞለኪዩላቸው እና በአንቲ ጅን ፀባያቸው ነው፡፡
hepitates Bየ እህትህ ችግር የሚያያዘው ከሔፖታይተስ B ጋር ሲሆን ይህ ቫይረስ ከሌሎቹ አራቱ ይለያል፡፡ ይኸውም ሌሎቹ አር ኤን ኤ (RNA) ቫይረሶች ሲሆኑ ሔፖታይተስ ‹‹B›› ዲ.ኤን.ኤ ቫይረስ ነው፡፡ ሔፖታይተስ ‹‹B›› ከነሙሉ አካሉ ‹‹ዳን›› ፓርቲክል ሲባል 42 ናኖ ሜትር ይለካል፡፡ ይህም በኤሌክትሮን ማክሮስኮፕ እንደ ባክቴሪያዎች ለመታየት አያስችለውም፡፡ ቫይረሱም 22 ናኖ ሜትር የሚሆን የውስጥ አካል ሲኖረው ከላይ የሚሸፍነው ከፕሮቲን የተሰራ ሽፋን ወይም የሔፖታይተስ ቫይረስ ሽፋን አንቲጅን አለው፡፡
ይህም ሽፋን በቫይረሱ በተጠቁ የጉበታችን ሴሎች በብዛት ይመረትና በደማችንና በሰውነታችን ፈሳሾች ከቫይረሱ ተለይቶ መጠኑ 22 ናኖ ሜትር በሚሆን ብናኞች (particle) መልክ በብዛት ከቫይረሱ ውጭ ይሰራጫል፡፡ በጠያቂያችን ደም ውስጥ ሔፖታይተስ ‹‹B›› ቫይረስ እንዳለ የታወቀውም በዚህ የቫይረሱ ሽፋን አማካኝነት ነው፡፡
ሔፖታይተስ ‹‹B›› በቀጥታ የሰውነታችን ሴሎችን አያጠቃም፡፡ ነገር ግን በጉበታችን ላይ የሚደርሰው ጉዳት የሚፈጠረው የራሳችን መከላከያ ኃይል ቫይረሱን ለማጥፋት በሚከፍተው ጦርነት ነው፡፡
ሔፖታይተስ ‹‹B›› በመላው ዓለም ሲገኝ እስካሁን ከ2 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ውስጥ እንዳለ ይገመታል፡፡ ይኸውም ከዓለማችን ከሶስት ሰዎች መካከል በአንዱ ውስጥ አለ እንደ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 300 ሚሊዮን የበሽታው ተሸካሚ እንዳሉ ይገመታል፡፡ አሜሪካ እና እንግሊዝ ዝቅተኛ የተሸካሚ ቁትር ሲኖራቸው ማለትም ከአንድ ሺ ሰዎች መካከል አምስቱ የተያዙ ሲሆን በአፍሪካ በመካከለኛውና በሩቅ ምስራቅ ኤሺያ የተሸካሚ ቁጥር 15 በመቶ ይደርሳል፡፡
ይሄ ቫይረስ የሚተላለፈው በደም (ማለትም ለበሽተኛ የተበከለ ደም ሲሰጥ፣ የተበከለ መርፌ በመጠቀም፣ በተበከለ ስለት ንቅሳት ሲደረግ)፣ ከታማሚው ጋር የቅርብ ግንኙነት (ንክኪ)፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት (በተለይ የግብረ ሰዶም) ናቸው፡፡ ስለዚህ መተላለፊያው መንገድ ከኤች.አይ.ቪ ጋር ሲመሳሰል የጤና ባለሙያዎች በስራ ጊዜ ከበሽተኛ ፈሳሽ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በኤች.አይ.ቪ የመያዛቸው ዕድል ወደ 2 በመቶ ሲሆን ሔፖታይተስ ‹‹B›› ግን 35 በመቶ ነው፡፡ በተጨማሪም በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ይተላለፋል፡፡
በአብዛኛው በዚህ ቫይረስ የተለከፈ ሰው በሽታው አይታይበትም፡፡ ቫይረሱ (ሔፖታይተስ ‹‹B›› በደሙ/ዋ ውስጥ መኖሩ የሚታወቀው በአጋጣሚ በሚደረግ የጤና ቼክአፕ ምርመራ ነው፡፡ በጠያቂያችን እህትም የተፈጠረው ይኸው ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ቫይረሱ በርካታ የህመም ስሜት ይፈጥርና ተጠቂው ወደ ሐኪም ዘንድ ይመጣል፡፡ በመጀመሪያም በሽተኛው የህመም ስሜት ይሰማዋል፣ ቋቅ ቋቅ ይለዋል፣ ምግብ ያስጠላዋል፣ ሲጋራ የሚያጤስ ከሆነ ሲጋራ ያስጠላዋል በዚህ ጊዜም አይኑ ላይ ቢጫ የመሆን ምልክት አያሳይም፡፡ ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት በኋላ አንዳንድ በተለምዶ የወፍ በሽታ የሚባለው ሌላው የህመም ስሜታቸው ጎልቶ ይታያል፡፡
የዓይን ቢጫ መሆኑ እየደመቀ ሄዶ ሽንት ጠቆር ሰገራም ነጣ ይላሉ፡፡ ጉበትና ቆሽት መጠነኛ ማበጥ ያሳያሉ፡፡ አልፎ አልፎ የንፍፊቶች ማበጥ ሊታይ ይችላል፡፡ ከዚህ በኋላ የዓይን ቢጫ መሆን በራሱ ጊዜ እየጠፋ ታማሚው ከሶስት እስከ ስድስት ሳምንታት ይሻላታል ወይም ይሻለዋል፡፡ ከጉበት ውጭ በጣም አልፎ አልፎ፣ መገጣጠሚያ፣ የደም ስሮች፣ የልብ ግድግዳ፣ ኩላሊትንም ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሽታው ሊያገረሽ ሲችል በዚህን ጊዜ የዓይን ቢጫ መሆኑ በድጋሚ ይከሰታል፡፡ በጣም አልፎ አልፎ በሽታው ጉበትን እጅግ አጥቅቶ አጣዳፊ ደረጃ ደርሶ የጉበት ኮማ የሚባል ፈጥሮ በሽተኛውን ሊገድለው ይችላል፡፡
10 በመቶ የሚሆኑት አክዩት ሔፖታይተስ ‹‹B›› (acute hepatitic B…) በሽታ የያዛቸው ደግሞ በሽታው ወደ ክሮኒክነት (Chronic Hepatitic B infection) ይለወጥባቸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ከ70-90 በመቶ የሚሆኑት ጤናማ ተሸካሚ ሲሆኑ ጠያቂያችን ከዚህ ግሩፕ እንደምትመደብ እገምታለሁ፡፡ ሌሎቹም ክሮኒክ ከሆነባቸው ከ10-30 በመቶ የሚሆኑት ክሮኒክ ሔፖታይተስ የሚባል ደረጃ ሲደርሱ ከዚያም የጉበት መሸብሸብ (Cirrhosis) ብሎም የጉበት ካንሰር (Hepatocellular carcinoma) ይሆንባቸዋል፡፡ ነገር ግን ጤነኛ ተሸካሚ ይሆናሉ ከተባሉ ስንቱ ወደ ፊት የጉበት ካንሰር ከጊዜ ብዛት እንደሚይዛቸው ገና ግልፅ አይደለም፡፡
ድንገተኛ የሔፖታይተስ ‹‹B›› ኢንፌክሽን (የወፍ በሽታ) የሚታይበት ታማሚ ወደ ሐኪም ዘንድ ሲሄድ የተለያዩ ከጉበት ጋር የተገናኙ የደም ምርመራዎ፣ ሌሎች የአንቲቦዲ ምርመራዎች፣ የሽንት ምርመራ ወዘተ… ይደረግለታል፡፡ ሌሎች ተቀራራቢ ምልክት የሚያሳዩ በሽታዎች መኖር አለመኖራቸው መረጋገጥ አለባቸው፡፡
ወደ ክሮኒክነት ያልተለወጠ አክዩት ሔፖታይተስ ከድጋፍ ሰጪ ህክምና በስተቀር አያስፈልገውም፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በራሱ ጊዜ እየዳነ ይሄዳል፡፡
ክሮኒክ የሆነ ሔፖታይተስ ‹‹B›› ኢንፌክሽን ያላቸው ታማሚዎች መታከም አለባቸው፡፡ የህክምናውም አላማ ሔፖታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ኢ›› የተባለውን አንቲጂን እና የሔፖታይተስ ‹‹ቢ›› ቫይረስ ዲኤንኤ ከደም ውስጥ ማጥፋት ነው፡፡ ይህም በጉበት ሴሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ይቀንሰዋል፡፡ ሔፖታይተስ ‹‹ቢ›› ቫይረስ ዲ.ኤን.ኤ ከደም ውስጥ ማጥፋት ነው፡፡ ይህም በጉበት ሴሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ይቀንሰዋል፡፡ ሔፖታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ኢ›› አንቲጅን ከደም ውስጥ ከጠፋ የበሽታው የመመለስ ዕድል ይቀንሳል፡፡ ታማሚው ከደሙ ሔፖታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ኤስ›› አንቲጅን ቢታከመውም በደም ውስጥ ቆይቶ የበሽታው ተሸካሚ መሆኑ ይቀጥላል፡፡ አብዮተኞቹ ግን በስተመጨረሻም ይሄም አንቲጅን ከደማቸው ይጠቀፋላቸዋል፡፡
አሁን አሁን በየዓመቱ አዳዲስ መድሃኒቶች ይህንን ክሮኒክ ሔፖታይተስ ለማከም ፈቃድ እየተሰጣቸው ሲሆኑ ዋና ዋናዎቹ መድሃኒቶች አልፋ ኢንተርፌሮን (a interferon) እና ፀረ ቫይረስ (anti viruses) ናቸው፡፡
መከላከያው ለበሽታ የማያጋልጡ ሁኔታዎችን ለምሳሌ የተበከሉ (ሊበከሉ የሚችሉ መርፌዎችን) ማስወገድ፣ በርካታ የግብረ ስጋ ጓደኞችን መተው (ልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማስወገድ)፣ ለበሽተኛ የሚሰጥ ደም ከቫይረሱ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ፣ የጤና ባለሙያዎች ከበሽተኛ የአካል ፈሳሽ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቀነስ ወይም ጓንት መጠቀም እና ክትባት መውሰድ ናቸው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>