ከብርሃኑ ዓለሙ
በቅርቡ ከ25 በላይ በሆኑ ፀሐፊዎች፣ ገጣሚዎችና ሰዓሊዎች ስለ ስብሐት ያላቸውን የነፍስ ወከፍ ልቡሰ ጥላ አንድ ላይ አጣምረው መንጉለዋል፡፡ መንጎላቸው ዳጎስ ያለና ባለ 278 መጽሐፍ ተገላግሏል፡፡ ስለ ስብሐት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ይፃፋል፡፡ በሁለት ጎራ በጅር በጅር ሆኖ በብዕር መፋለሙ፣ በመድረክ መከራከሩ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም ስብሐት አወዛጋቢና አከራካሪ ደራሲ ነውና፡፡
ክርክሩ “መልክአ ስብሐት” የሚል ሥያሜ በተሰጠው መድበልም ታይቷል፡፡ “ሰለሜ ሰለሜ” እንደተሰኘው የአገራችን የደቡብ ጭፈራ ተያይዘው መስመር ያበጁ የደራሲው አድናቂዎችና «አምላኪዎች» በአንድ ወገን፣ «ቤተ ክርስቲያን እንደገባች ውሻ» የሚጠየፉት ደግሞ በሌላ ወገን የብዕር ሙግታቸውን አፋፍመዋል፡፡ የንግግር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን በነፃነት ያለምንም ከልካይ መግለፅ ከዚህ እንደ ምሣሌ መውሰድ ይቻላል፡፡
ዓለማየሁ ገላጋይ፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ልቦለድ ከስብሐት ይጀምራል የሚለው ሃሳቡን እጅግ ከሚቃወሙት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነኝ፡፡ በሃሳብ ልዩነት መፍጠር የሥነ ጽሑፍም በሉት የጥበብ አንዱ መገለጫ፣ ከፍ ሲልም ውበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይ ሳያውቀኝ ሳላውቀው እንዲሁ በደምሳሳው ብቻ “አምባ ገነን ” ይመስለኝ ነበር፡፡ ልክ እንደ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1ዱ የ“ርዕዮት” ፕሮግራም አዘጋጁ ቴዎድሮስ፡፡ ዓለማየሁ በዚህ መድበል ስመለከተው ግን “ተሳስቻለሁ ማለት ነው?” ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡ ዝርዝር ባህርዩን ለማወቅ የዓለማየሁ “ማንዋ” መጠየቄ አይቀርም፡፡
አንዳንድ የአገራችን ጋዜጠኞች ይገርሙኛል፡፡ እነሱ ልክ ነው ብለው ያመኑበትን ሃሳብ የሚቃወም ሲያጋጥማቸው ዱላ ከማንሳት አይመለሱም፡፡ ስለ ዴሞክራሲ አስፈላጊነት እያወሩ፣ ነገር ግን ሰው ተቃራኒ ሃሳብ ሰጠ ብለው ይወነጅላሉ፡፡ ዴሞክራሲ መጀመሪያ ነገር ከራስ ይጀምራል፡፡ ከሚስት/ከባል፣ ከልጅ፣ከጎረቤት ወዘተ እኔ የባለቤቴን የመናገር ወይም አስተያየት የመስጠት መብት የምፃረር ከሆነ እንዴት አድርጌ ነው የሌላውን መብት የምጠብቀው? በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መፃፍና ብዙ መነጋገር ይቻላል፡፡ አሁን ግን ወደ ጀመርኩት ርዕሰ ጉዳይ መመለስ ግድ ይለኛል፡፡
“ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን ከሌላ ማዕዘን” የሚለው የሚካኤል ሽፈራሁ(ው?) መጣጥፍ በጥሩ ሁኔታ ጊዜ ተሰጥቶና ታስቦበት የተሠራ በመሆኑ ሳላደንቅ ባልፍ ኅሊናዬ ይታዘበኛል፡፡ ይሁን እንጂ ሚካኤል ያነሳቸው ነጥቦች ሙሉ በሙሉ ልክ ናቸው ማለቴ አይደለም፡፡ ሚካኤል ያየበት መንገድ የግሉ አተያይ(አንግል) ነውና አስተያየቱን አከብራለሁ፡፡
ብዙዎቹን ፀሃፊዎች በጅምላ መፈረጁ ከባድ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ ግን ሌሎች ያሉትን መነሻ በማድረግ የፃፏቸው፤ ያው የተለመደ የመወዳደስ፣ የመካካብ፣ ወይም በሌላ አገላለጽ የጓደኝነት ስሜት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ በርዕስ ከፋፍዬ መተቸትና መተንተን እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ይሄ የጋዜጣ ገጽ እንጂ የመጽሔት ያህል እንኳ ነፃነት የሚሰጥ ስላልሆነ በዚያ መሠረት አልሄድኩበትም፡፡
ስብሐት፣ በኢትዮጵያ ረዥምና አጭር ልቦለድ ታሪክ ውስጥ ሁነኛ ሥፍራ የያዘ ትልቅ ደራሲ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም፡፡ ስብሐት በቋንቋ ውበቱ፣ በአፃፃፍ ስልቱ፣ በጭብጥ አመራረጡ፣ በገፀ ባህሪያት አሳሳሉ፣ ከመቀመጫዬ ተነስቼ “ዱስቱር” እለዋለሁ፡፡ የስብሐት፦ “አምስት ስድስት ሰባት” አጭር ልቦለድ፣ በኢትዮጵያ አጭር ልቦለድ ታሪክ “ማስተር” ነው ብዬ ባሞካሸው አይበዛበትም፡፡ እነ “እቴ እሜቴ”፣“እኔ ደጀኔ”፣“ሞትና አጋፋሪ እንደሻው”፣”አምስት ስድስት ሰባት” የአጭር ልቦለድ መመዘኛን ከሟሟላታቸው በተጨማሪ ለማስተማሪያ የሚሆኑ ታሪኮች ናቸው፡፡
ስብሐት፣ ከሌሎች ደራስያን የሚለይባቸው ብዙ ባህሪያት አሉት፡፡ አንደኛው፣ ከአብዛኛው ሰው በሃሳብ የማይስማማውን አካፋን አካፋ በማለት ልማዱ የተነሣ ነው፡፡ ስብሐት፣ የመሰለውን እንደመሰለው እንደወረደ ይጽፋል፤እንደወረደ ይናገራል፡፡ በተለይም በወሲብ ዙሪያ ያለው አቋሙ ለብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን (በድብቅ ተወልደን በድብቅ እንደግ ለሚሉት) መራራ እውነት ነው፡፡ የወሲብ ርዕስ እንዲህ እንደወረደ መፃፍ “ብልግና ነው” ብለው ፈርጀው ያበቁት፣ ዓይንህን ለአፈር ይሉታል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በሚያጨሰው እፀ ፋሪስ ምክንያት እጅግ ይኮንኑታል፡፡ ደግሞ ሌሎቹ፣ ትውልድን አበላሽቷል (አኮላሽቷል) ብለው ይከሱታል፡፡ “ኲሉ አመክሩ አጽንኡ ወ ዘሰናየ” ተብሎ በተቀኘበት አገር ይህን ያህል ማማረር ግን ተገቢ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ አንስቼ ባልፍ ደስ ይለኛል፡፡
የስብሐት መንገድ ለየት ያለ ነው፡፡ እኔ ብመኘውም ወይም እሆናለሁ ብዬ ፀጉሬን ባንጨባርር፣ ጺሜን ባጎፍር፣ ለመፈላሰፍ ያዙኝ ልቀቁኝ ብል፣ እንደወረደ እናገራለሁ ብዬ ባቅራራ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ስብሐት የተሠራበት ቀመር የሚያገለግለው፣ ለስብሐት ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሌላ ቀመር ነኝ፡፡ ብዙዎቹ በእሱ ፍቅር አበድን ብለው፣ የእሱ መንገድ የጥበብም የሕይወትም ነው ብለው ያመኑ፣ ከማመንም በላይ የተጠመቁ አጓጉል ሲወድቁ የምናየው ለዚህ ነው፡፡ የስብሐትን ጎዳና እንከተላለን ብለው ተነስተው ከጎዳናው አፈንግጠው እንደ ገል ተሰባብረው የወደቁ የትየለሌ ናቸው፡፡
ስብሐት፦ በኢትዮጵያ ምድር ሊደገም የማይችል፣ በእኛ እምነት ጥሩም መጥፎም ልማድና አስተሳሰብ የነበረው ደራሲ ነው፡፡ የስብሐት የቋንቋ አጠቃቀም ቀለል ያለ፣ እንደ ውኃ የሚጠጣ የማያነቅፍና ውብ ነው፡፡ ገፀ ባሕሪያቱን ሲያዋቅር ደምና ሕይወት በመስጠት ነው፡፡ የአእምሮው ምጡቅነት ገና፣ ገና አንብበንና ተመራምረን አንጨርሰውም፡፡ በኢትዮጵያ የድርሰት አፃፃፍ ያልተለመደ ጭብጥ፣ “እንዴ እንዲህም አለ እንዴ?” ሊያሰኝ የሚችል፣ ግርምትን የሚፈጥር የጥበብ መንገድ በማሳየት ስብሐት ፋና ወጊ ነው፡፡ ስብሐት ዝና ከአገር አገር የሚንቦገበገው፣ ኖቤል የሚያሸልመው ከዓመታት በኋላ ነው፡፡ ስብሐት የቀደደው የጥበብ መንገድ፣ ድንቅነቱ ፍንትው ብሎ የሚወጣው አዎ ወደፊት ነው፡፡ እነ አጋፋሪ እንደሻው፣ ኮምቡጡር…
ስብሐት መሞቱን የሰማሁ ዕለት አላለቀስኩም፡፡ ነገር ግን ማስቀበር እንዳለብኝ አምኜ ሎሚ ሜዳ ከሚባል ለኑሮዬም ለመቀበርያዬም ከመረጥኩት አካባቢ መጣሁ፡፡ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ከሰው በፊት ተገኝቼ፣ ከሰው በፊት ወጣሁ፡፡ “ለምን ወጣህ?” ካላችሁኝ መልስ አለኝ፡፡
በቅድስት ሥላሴ በወቅቱ በአፀደ ነፍስ በነበሩት አባታችን አቡነ ጳውሎስ አጋፋሪነት የተካሄደው የቤተ ክርስቲያንና የቀብር ሥነ ሥርዓት በፍፁም ሊዋጥልኝ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ስርዓቱ ረጅም ነበር።
በጥበብ ሐድራ ከገባ በኋላ ኃይማኖት ለስብሐት ምኑ ነበር? በእርግጥ በልጅነቱ በወላጆቹ ሣቢያ “ሥጋ ወደሙ” ተቀብሎ ይሆናል (ክርስትና መነሳቱን ሰምቻለሁ)፡፡
እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አንዳንዴ የማምንበትን ሳይሆን፣ የሚያምኑበትን እከተላለሁ፡፡ የማልፈቅደው እንኳ ቢሆን ከማኅበረሰቡ የኑሮ ማዕቀፍ ላለመውጣት እተጋለሁ፡፡ በዚህም ባሕሪዬ በአደባባይ፣ “እኔ አድር ባይ ነኝ” ብዬ ተናዝዤ ንስሃ ከገባሁ ቆይቻለሁ፡፡ አድር ባይ ፀሐፊ እንደምን የጥበብ ማኅበርተኛ ሊሆን ይችላል? ካላችሁ፣ “የምወዳችሁና የማፈቅራችሁ ጥበበኞች ከልብ ካሰቡበት እምባ አይገድም፡፡ ይቻላል” እላችኋለሁ፡፡ ትንሽ ምሣሌ ልስጣችሁ፡፡ ወሲብን በሚመለከት የዕድሜ እርከን ተጠብቆ በግልጽ መነጋገር ቢቻል ደስ ይለኛል፡፡ በዚህም አቋሜ ከጓደኞቼ ከሠራዊት ፍቅሬ ጋር በገደብ፣ ከመሐልየ መሐልየ ዘ ካዛንቺስ ደራሲ ተድባበ ጥላሁን ግን ያለ ገደብ በነፃነት እናውራ፣ አንዳንዴም እንፈላሰፍ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ተድባበ ነፍሱ ይማር ተአምረኛ ሰው ነበር፡፡ እኔና እርሱ ባለንበት “ታቡ” የሚባል የለም፡፡ ከሌሎች ወግ አጥባቂዎች ጋር ስደባለቅ ግን አመሌን በጉያዬ እይዛለሁ፡፡ እኔ በባህሪዬ በጣም ጥብቅ ዲሲፕሊን አላቸው ከሚባሉት ተርታ እንደምመደብ ይሰማኛል፡፡ “እኔ የማምነው በዚህ መንገድ ነው ብዬ ግን ከጀማው መነጠል አልፈልግም፡፡ አንድ ሰው ባጣሁ ቁጥር፣ አንድ ጣቴ የተቆረጠ ያህል ያመኛል፡፡ ለክርክር ስጋበዝ፣ አቋሜን ስጠየቅ ግን በይፋ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ በመሆኑም አድር ባይ ፀሃፊ ተገኘ ብላችሁ አደራችሁን “ጊነስ ቡክ” ላይ እንዳታስመዘግቡ፡፡ በጣም ብዙ ምክንያቶችና እውነቶች ስላሉኝ፣ ከፍርድ በፊት ቃሌን ብትቀበሉኝ ማለፊያ ነው፡፡ የለም እንፈርድብሃለን የምትሉም ከሆነ የጋዜጣ ገጽ ስለማይበቃ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር መድረኩን ያዘጋጅና ዲሞክራቲክ የሆነ ክርክር አካሂደን ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ፡፡
እኔ አልቃታለሁ እንጂ የስብሐት ገድል፣ የስብሐት ዘመን ተሻጋሪ ምልከታ አያልቅም፡፡ ስብሐት፣ ሞትን ሲሸሽ ኖሮ በሞት የተሸነፈ፣ ነገር ግን ድንቅ ሥራዎቹ ሞትን መቶና ሁለት መቶ ጊዜ ያሸነፈ ጊዜ የማይሽረው ደራሲ ነው፡፡ በእርግጥ በእኛ ዓይን የባህሪ ችግር ነበረበት ማለት እንችላለን፡፡ የማኅበረሰቡ እሴት፣ ወግና ልማድ መጠበቅ አልፈቀደም፡፡ ይሄ ደግሞ እምነቱም ፍላጎቱም አልነበረም፡፡ ስብሐት፣ በኢትዮጵያ ምድር ለጉድ ፈጥሮት ለጉድ አኖሮት ያመለጠን ደራሲ ነው፡፡ ስብሐት የሞተ ዕለት አላለቀስኩም ብያችኋለሁ፡፡ አሁን፣ አሁን ግን በዚች ምድር ቀድሞም፣ አሁንም ወደፊትም ወደር የማላገኝላት እናቴ ብዙነሽ ሐብቴንና ስብሐትን ባስታወስኩ ቁጥር አለቅሳለሁ፡፡ እንባዬ ጉንጬ ላይ ባይወርድም በሆዴ አነባለሁ፡፡ ወንድ ልጅ እፊቱ ላይ እንባ ከማውረድ ይልቅ ሆዱ ውስጥ ያለቅሳል?
በሃሳቡ በጣም የወደድኩት ሚካኤል፣ የስብሐት ነውር ብሎ ከገለፃቸው መካከል ብዙ ወጣቶች እሱን እንከተላለን ብለው ከመስመር መዛነፋቸው አንዱ ነው፡፡ እሱ ራሱም የስብሐት እንደነበር ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ማንነቱን ፈልጎ፣ የራሱን መንገድ አግኝቶ ከጀማው ተገነጠለ፡፡ የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል የተፈቀደ ነውና ይህ አቋሙን ልንኮንነው አይገባም፡፡ ነገርግን አቶ ሚካኤልን የምጠይቀው ስብሐት የሚናገረውን፣ የሚያወራውን፣ ውሎውን… ተመልክቶ ወዶና ፈቅዶ በገዛ ሥልጣኑ እጁን ሰጥቶ ተማርኮ ለደረሰበት ጉዳት ስብሐት ምን ያድርግ? ስብሐት፣ አይደለም ሌላውን የገዛ ራሱንም ጥሏል እያልነው ሌላውን የማዳን ሥራ እንደምን ሊሆንለት ይችላል? ስብሐት የቀይ መስቀል መልዕክተኛ እኮ አይደለም፡፡ ለተጎዱ ወገኖች ድንኳንና ቀለብ አያቀርብም፡፡ ስብሐት፣ ለየት ያለ የጥበብ ሰውና “ሕይወትን ከእነ ብጉንጇ” ማሳየት የሚችል ደራሲ ነው፡፡
እኔ ይህ ጽሑፍ የፃፍኩላችሁ ዳተኛ፣ ከስብሐት ጋር አንድም ቀን ቁጭ ብዬ በግንባር ተነጋግሬ አላውቅም፡፡ በ1986 ዓ.ም የዘንባባ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሳለሁ፣ “ልብ ያለው ልብ ይበል” የሚል ገጽ ላይ ስጽፍ አንድ ስታይል ለማውጣት ሞክሬ ነበር፡፡ “ይድረስ ለሰማይ ቤቱ አጋፋሪ እንደሻው፣ ግልባጭ ለምድሩ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር -ደራሲ” በሚል ርዕስ ከሰማይ ቤት ወደ ምድር፣ ከምድር ደግሞ ወደ ሰማይ ቤት ጥበባዊ መልዕክት እንዲተላለፍ አደርግ ነበር፡፡ ገጹን የፈጠርኩት ለእርሱ በነበረኝ ፍቅርና ክብር ምክንያት ስለነበር፣ አንብቦት ከሆነ አስተያየት እንዲሰጠኝ ብዬ አንድ ቀን ስልክ ደወልኩለት፡፡ በትህትና ራሴን አስተዋውቄ፣ ርዕሰ ጉዳዩና ስታይሉን እንዴት እንዳገኘው ስጠይቀው ሰደበኝ፡፡ ለስድቡ ምላሽ በስክ ከመስጠት ተቆጥቤ በዚሁ ተለያየን፡፡ በዚህም ቂም ይዤበት በ17 ዓመታት የጋዜጠኝነት ዘመኔ አንድም ቀን ኢንተርቪው አድርጌው ወይም እርሱን የሚመለከት ጽሑፍ ጽፌ አላውቅም፡፡ በዚህ ሙያየዬ እጅግ ብዙ የጥበብ ሰዎችን ኢንተርቪው አድርጌያለሁ፡፡ ሚኒስትሮች፣ የመምሪያ ሥራ አስኪያጆች፣ ዘፋኞች፣ የተለያዩ ባለሙያዎች …፡፡
በወዳጄ ስንዱ አበበ አማካኝነት የስብሐት የታተሙና ያልታተሙ ሥራዎችን ቀደም ብዬ አንብቤ ልዩ ሥፍራና ክብር ሰጥቼዋለሁ፡፡ ታዲያ ስብሐትን ይህን ያህል አውቄው ኢንተርቪው አለማድረጌ ወይም በነበረኝ የመፅሔትና የጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ስልጣኔ ኢንተርቪው እንዲደረግ አለማድረጌ ወይም ደግሞ ቀርቤ አለማነጋገሬ ጥፋት ነው ካላችሁም የምትቀጡኝን ቅጣት እስከ “ስቅላትም” ቢሆን፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ዝግጁነቴን ሳረጋግጥላችሁ ከልብ ነው፡፡ ቂመኛ የጥበብ ሰው ግን አለ? ሰላም ሁኑ!