አንድ ዠብራራ ወያኔ በማህበራዊ ገፅ ላይ ሲመፃደቅ አገኘሁት – ነገሩ አባይ ፀሀዬ የሚባል ቱባ ወያኔ በል ሲለው እየተነሳ ‘…ልክ እናስገባችሁዋለን…’ እያለ መደንፋቱ ካስከተለው ቀወስ ጋር ተያይዞ የመጣ ጉዳይ ነው። አባይ በድንፋታ የዘባረቀው ፀያፍ ቃል በህዝብ ስሜት ውስጥ ያሳደረውን ቁስል እና አሉታዊ ዝንባሌ ለማስታገስ በሚል ‘እኔ ይህን አላልኩም – የኦሮሞ ህዝብ ማን እንደበደለው ያውቃል…’ ሲል ጣቱን ወደ ሆነ አቅጣጫ ለመጠቆም እየደዳው ማስተባበያ ቢጤ ይደሰኩራል። ማስተባበያ በሉት ማብራሪያ ይዘቱ ያው የተለመደው የወያኔ የዘር ልክፍት ድንፋታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም።
ታዲያ ግልገል ወያኔው ጉዳዩ በደንብ እንደገባው ሊያብራራልን ከጅሎ ‘የኦሮሞ ህዝብ አዳማን ማን ናዝሬት እንዳላት ፣ ቢሾፍቱን ማን ደብረዘይት እንዳላት ያውቃል’ የሚል ጨቅላ እንቶ ፈንቶ ይለጥፋል። ይህን ከቁም ነገር ቆጥሮ ቴድሮስ አድሀኖም የተባለው የወቅቱ የወያኔ ውጪ ጉዳይ ሀላፊ ደግሞ የግልገል ወያኔውን ማብራሪያ like አድርጎ እሱም በዚህ ተራ ፕሮፓጋንዳ እንደሚስማማ ያረጋግጣል። ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ይጠቅማል ከተባለ ግልገሉም ቱባውም ወያኔ ባንድ ረድፍ ተሰልፎ ሲያራግብ ታገኙታላችሁ – የወያኔ ብስል የለውም። ጉዳዩ ብዙ ግምት የሚሰጠው ባይሆንም የወቅቱ ህዝባዊ አመፅ ወያኔን ከግልገል እስከ አውራዎቹ ምን ያህል እያወራጨ መሆኑን ያለጥርጥር ያሳያል።
ናዝሬት ወይንም ደብረዘይት የሚል ስያሜ ከአንድ ከተማ መቆርቆር ጋር ተሳስሮ የመጣ አካባቢው ባንድ ታሪካዊ ወቅት በይዘቱ መለወጡን የሚያመለክት ለውሱን ክልል የተመረጠ መለያ መሆኑ ግልፅ ነው። ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ግን አዳማ ከናዝሬት ፣ ቢሾፍቱም ከደብረዘይት የሰፉ ብዙ ትናንሽ ከተሞችን ጨምሮ የገበሬ መንደሮችን ያቀፉ ወረዳዎች መሆናቸው ናቸው – ከቶውንም የአዳማ ወይንም የቢሾፍቱ ስም ተቀይሮ የሚያውቅ ጉዳይ አልነበረም። በአዳማ ወረዳ ናዝሬት ፣ ሶደሬ ፤ በቢሾፍቱ ወረዳ ደግሞ ደብረዘይት እና ሞጆ እንዲሁም ዱከም ሌሎችም ትናንሽ ከተሞች መኖራቸውን ሁሉም ያውቃል። አዲሶቹ ሹማምንት እነሱ እንግዳ ስለሆኑበት አካባቢ የጠለቀ ዕውቅት ስለሚጎድላቸው ሁሉም ነገር የተጀመረው እነሱ ስልጣን ከተቆናጠጡ ወዲህ ይመስላቸዋል።
አሁን ጥያቄው አዳማን እና ቢሾፍቱን በልማት ስም ወረራ በመፈፀም የመሬቱን ባለቤት አራሽ ገበሬ ካላንዳች የህይወት ዋስትና እያፈናቀለ ያለው ስግብግብ ቀማኛ ማነው የሚለው ነው!
እንጂ ጉዳዩ ስለ ከተማ ስም ከሆነ መርካቶ ፣ ፒያሳ ፣ ፖፖላሬ ፣ ካዛንቺስ አማርኛ አይደሉም። ጣሊያን ሲቆረቁራቸው ያወጣላቸው ስም ነው – ይህም አካባቢው ባንድ ታሪካዊ አጋጣሚ መለወጡን ጭምር የሚያመለክት ነው። መርካቶ በሉት ፒያሳ ይኸው እስከ ዛሬ ህብረተሰቡ ይጠቀምባቸው የለም? ቴድሮስ አድሀኖም ያደጉትስ አስመራ ኮምፐሸታቶ አልነበረም እንዴ ወይንስ ገዛ ባንዳ ይሆን?
የጣሊያንኛ ነገር ከተነሳ ሸሚዝ ፣ ካልሲ ፣ አንሶላ ፣ ሙታንታ ስንል የምንጠቀምባቸው ብዙዎቹ ዘመን አመጣሽ ቁሳቁስ አሁንም ቢሆን በራሳችን ቋንቋ ስም የላቸውም – ምን ችግር አለው?
እነ ኮልፌ ፣ ጉለሌ ፣ ኮተቤ ፣ ገፈርሳ የቀድሞ ስያሜቸውን ሳይሽሩ መቆየታቸውስ ምን ያመለክታል። እነ ቴድሮስ አዳኖም የኦሮሞ ስያሜ ያላቸው ስፍራዎች ላይ ዘመቻ ተከፍቶ በሙሉ በአማርኛ እንደተተኩ እና ይህም እንደ ጠላትነት እንዲቆጠር የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠር ይሻሉ። ይሁንና ጉዳዩን ስንመረምር እነኝህ ወያኔዎች ምንም ትንሽ ቢሆን አንድን ህዝብ ከለሌላ ጋር ለማጋጨት ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ስለሚያወሩት ነገር ላፍታ ጉዳዩን ለማጤን እንኳ አይፈልጉም – በቃ ተነስቶ አፍ መክፈት ብቻ ነው ፤ እኛም በተከፈተ አፋቸው ጭንቅላታቸውን ለማየት እና ለመታዘብ እንገደዳለን።
ስለ ስም አወጣጥ ማህበራዊ እውነታ ትንሽ እንዲማሩም በዚህ አጋጣሚ ሀሳብ እናካፋልቸዋለን።
ሰፋ ያለ አግዳሚ መቀመጫ ያለውን ታክሲን ውይይት ብሎ ህብረተሰቡ ስም ሲሰጠው በጊዜው አንድ የተለወጠ ነገር መኖሩን ያመለክታል። ጠ/ሚኒስትር ደሳለኝ ሀ/ማርያም ሶስት ረዳት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ሲመደቡባቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ባጃጅ ጠ/ሚኒስትር የሚል ስም እንደወጣላቸው ሰምቻለሁ። ባጃጅ የሚሏት ታክሲ ባለ ሶስት እግር ጎማ መሆኗን በማጣቀስ… በሶስት ጎማ ኩር ኩር የምትል ታክሲ።
መለስ ዜናዊ ባንድ ወቅት አንድ የአሜሪካ የፓለቲካ ሰው ‘ትግላችሁ ብሔረሰብ ነፃነት ዙርያ ያጠነጠነ መሆኑ አገሪቱን አይጎዳም ወይ’ ብሎ ሲጠይቀው ‘ትግላችን የአማራን በተለይም የሸዋ አማራን ትምክህተኝነት ለማስወገድ ነው’ ብሎ መልስ መስጠቱን ብዙዎቻችሁ ታስታውሳላችሁ። ሸዋ ላይ ያነጣጠረው የወያኔ ትግል ሸዋ የሚባል ለምእተ ዓመታት የቆየ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈ ክፍለ ሀገር ከኢትዮጵያ ካርታ ላይ ጨርሶ አንዲሰረዝ በማድረግ ተጠናቋል። ዛሬ የሸዋ ሰው የሚባል የለም – ሸዋ ደግሞ የማንም ብሔረሰብ ንብረት አልነበረም – ከሁሉም የአገሪቱ ማእዘናት የመጡ ዜጎችን ጨምሮ ጉራጌው ፣ ኦሮምው ፣ አማራው ፣ ከምባታው ፣ ሀድያው … ወዘተ የተሰበሰቡበት ፣ በጋራ ተከባብረው በኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚኖሩበት ክልል ነበር። ሸዋ ኢትዮጵያዊነት የተወሀደበት እንጂ የማንም አልነበረም።
በሸዌነት የሚከሰሰው ደርግ በዘመኑ ጥናት ላይ ተመስርቶ እንዲስተካከሉ ካደረጋቸው የክልል ስያሜዎች መካከል – ትግሬ ወደ ትግራይ ፣ ወላሞ ወደ ወላይታ እንዲሁም በጌምድር ወደ ጎንደር መቀየራቸው ይገኙበታል። ፊውዳሊዝም ዘመኑን ጠብቆ የተፈጥሮ ሞት ሲገጥመው መሻር የሚገባቸው ነገሮች እንዲህ ተሽረዋል። ይህ የተደረገው ግን በስሜታዊነት ወይንም አምባጓሮ ለመቀስቀስ አልነበረም። ተገቢው ጉዳይ ተገቢ ስፍራ እንዲይዝ ለማድረግ ሲባል ብቻ የተደረገ ይመስለኛል። የተዛባ ነገር ካለ ቀኑን ጠብቆ ማስተካከል ይቻላል – ለተራ የፖለቲካ ሸፍጥ መቀስቀሻ መጠቀም ግን ደካማነት ብቻ ሳይሆን የጥፋት መልዕክተኛነት ነው።
በዚያው የደርግ አስራሰባት ዓመታት በአስራምስት ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ፊደል ማስቆጠር ተጀምሮ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ ጥረት ሲጀመር ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ሆኜ ትምህርት ሚኒሰቴር ያደረገውን ዝግጅት ለመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር። በቂ ምርምር እና ጥናት ተደርጎበት ፣ ዘላቂነት ባለው መልኩ በሚዳብርበት መንገድ ተይዞ ነበር ማለት ግን ባይቻልም ሙከራው ነበር – በጎ አጀማመር መሆኑንም መካድ አይቻልም። አፈፃፀሙን ለማሳካት አቅም ነበር ወይ የሚለው ጥያቄ ግን የተጤነ አልነበረም።
የተነሳሁበት ጉዳይ ተለጠጠ… የኢትዮጵያ ነገር ሆነና ተዛማኝ ጉዳዮችን መጠቃቀስ ገባሁ…
አዎ የኦሮሞ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል…
ኦሮሞ ለኢትዮጵያ ነፃነት ፣ ክብር እና ዳር ድንበር መከበር በባለቤትነት የታገለ ፣ የሞተ እና ድል የተጎናፀፈ ክቡር ዜጋ ነው። ኢትዮጵያ ክፉ ቀን በገጠማት ታሪኳ ሁሉ በተለይም ከዘመናዊ አስተዳደር ምስረታ ጥረት እስከ አለም አቀፍ ዕውቅና ትግል ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ደም እና ላብ ፣ ዕውቀትና ጉልበት ወይንም የተፈጥሮ ሀብት አና ጥሪት በጉልህ ደረጃ ያልፈሰሰበት አንዳችም የታሪክ ምዕራፍ የለም።
የማወራው ስለ አያና ብሩ ፣ አበበ ቢቂላ ፣ አብዲሳ አጋ ወይንም ሀይሌ ፊዳ ብቻ አይደለም – ከዚያ የጠለቀ የሰፋ ጉዳይ ነው። ህልውናችን በጀግኖች አባቶቻችን አጥንት እና ደም ተጠብቆ ቆየ ስንል እነኛ አባቶች ያለፉበትን ውጣ ውረድ በምን መለኪያ እንገልፅዋለን ፣ በምን መስፈርት እናበራራዋለን? እንደሚመስለኝ ኢትዮጵያን ጠብቆ ያቆየን ማን እንደሆነ ተጨንቀን ማሰብ እንዳንፈልግ ተደርገናል። እንዲህ እንደ አሁኑ ዘመን ፈተና ላይ ስንወድቅ ግን ዞር ብለን የነበረውን እንደ ሰበር ዜና ለማወቅ እንገደዳለን።
ለኢትዮጵያ ህልውና ሲሉ የኦሮሞ ልጆች በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ተሰልፈው ደማቸውን ገብረዋል። እነ ገረሱ ዱኪ ፣ በቀለ ወያ ፣ ደላሳ ጎቡ ፣ ጃ ጋማ ኬሎ ፣ አብዲሳ አጋ… የቅርቦቹ እነ ደምሴ ቡልቶ ፣ መርዳሳ ሌሊሳ ፣ ባጫ ደበሌ… ሚሊየኖች ዘርዝሮ ማቅረብ ይቻላል… ኦሮሞ ለኢትዮጵያ ክብር ሲል እንዲህ መራራ መስዋዕትነት ሲከፍል መቆየቱ ደብዘዝ ያለባቸው ከኦሮሞውም ከኦርማውም በረከትከት ያሉ ይመስላል – የስማዕቱ የሀይማኖት መሪ አቡነ ጴጥሮስ ኦሮሞነት ሰበር ዜና የሆነባቸው አይነት ማለቴ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ስማዕት አቡነ ጴጥሮስ ውልደት ስማቸው መገርሳ በዳዳ መሆኑ አዲስ ታሪክ የሆነባቸው እንዳሉ ሳትታዘቡ አይቀርም። የሀይማኖት መሪዎች ለከፍተኛው የሀይማኖት መሪነት ሲጠሩ ስማቸውን ከመፅሀፍ ቅዱስ ከሚገኙ ቅዱሳን ስሞች አንዱን ይወርሳሉ። ነገስታትም ፣ ‘ታጋዮችም’ እንዲሁ – አፄ ሀይለስላሴ ተፈሪ መኮንን ፣ በዝብዝ ካሳ አፄ ዮሀንስ እንደ ነበሩ ሁሉ። መለስ ዜናዊ ለገሰ ፣ አባዱላም ምናሴ እንደ ነበሩ ሁሉ። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም ሲሰራበት የቆየ ወግ ነው።
ባለፈው ሰሞን “እኛም ኦሮሞዎች ነን” በሚል ርዕስ ከትግራይ ክልል የተገኙ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ ወገኖች ተጠራርተው ያንፀባረቁትን ትብብር ሳነብ ያሳደረብኝን ስሜት እዚህ መግለፅ ፈልጋለሁ። ምኞታችን ፍትሀዊ ስርዓት እንዲሰፍን መሆኑ እሙን ነው። ትናንት እንደ ሰለጠነው አለም ሁሉ ጭቆናን ፣ አፈናን እና ብዝበዛን በዚህ በዚያ መደቦች የጋራ ትግል እናስወግዳለን ስንል እንዳልነበር ሁሉ ለወያኔ ምስጋና ይግባውና ትግሉ በብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች መካከል የሚደረግ ትብብር ጉዳይ እንዲሆን ጊዜው ግድ ብሏል።
ወዛደሩ ለአርሶ አደሩ ትግል የጀርባ አጥንት ነው በሚለው ምትክ ፤ ተራማጅ ምሁር ከጭቁን ህዝቦች ጎን ይሰለፋል በሚለው ምትክ ዛሬ ጨዋታው ትግሬ ከኦሮሞ ፤ ኦሮሞ ከአማራ… ከዚህ ከዚያ ብሔረሰብ ድጋፍ እና ግንባር መፍጠር የሚል ሆኗል። ለፍትሀዊ አንድነት ሳይሆን ለጎጣዊ ምንነት መስፈን እንድንታገል በወያኔ መገደዳችን ገሀድ ይታያል። እናም የዚህ ብሔር ብሔረሰብ አባላት የትግል አጋርነት ለዚያኛው ብሔር ብሄረሰቦች ትግል ተገለፀ ወደሚል ደረጃ ዝቅ ብለናል – ዕድሜ ለወያኔ።
ግን በዚህ የትግል ሂደት የሚረጋገጠው የፍትህ እና የህግ በላይነት ወይንስ የብሔር ብሔረሰብ ነፃነት? እና ውጤቱ ኢትዮጵያ የተነፈገችውን ፍትሀዊ ስርዓት ማስፈን ወይንስ ካንዱ የጎጥ መንግስት ወደ ሌላ ሽግግር? ወይንስ አስከናካቴው ኢትዮጵያ ባለቤት የሌላት ፣ ተቆርቋሪ የሌላት እንደ አየር ተንና በመክሰም ላይ ያለች አገር? ሁኔታው አሳሳቢ ነው።
እነ ዶክተር መሳይ ከበደ እንኳ ሳይቀሩ ዛሬ ጭንቀታቸው እንዴት ኦሮሞ ሲነሳ ሌላው ብሔረሰብ ዝም ብሎ ይቀመጣል? የሚለው ጉዳይ ሆኗል። አልፈርድባቸውም – ምን ምርጫ አለ። ይሁንና አራት አመታት ሙሉ የፍልስፍናን ጥበብ ያስተማረኝ ምሁር ፣ ፍትህ አንፃራዊ ቢሆንም መደባዊም ነው ብሎ ያስጠናኝ የጥበብ ሰው ዛሬ የብሔረሰቦች ትብብር ጥሪ ውስጥ ተዘፍቆ ሳየው አዝናለሁ። ይህ ጉዞ ወቅታዊነቱ ስህተት ነው ማለቴ ሳይሆን በሁሉም አቅጣጫ ወያኔ በፈጠረው ኩሬ ውስጥ ተደፍቀን መገኘታችን ግን ጉዳዩ ለዘለቄታው ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን ለማመልከት ነው።
ህብረተሰብን በመደብ ከፋፍሎ በዚያ መሰረት ሊሰፍን ስለሚገባው ፍትሀዊ የሀብት ስርጭት ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ድርሻና ስለሚጠይቀው የሰብአዊ መብት መስፈን ጉዳይ መነጋገር ጊዜው ያለፈበት የፋራ አጀንዳ ሆኗል። ባለ አገር ሳይሆን ዛሬ የሚያኮራው ባለ ብሔረሰብ መሆን ነው – የወርቅ ብሔረሰብ… የታጋይ ብሄረሰብ ፣ የሀብታም ብሄረሰብ ፣ የጭቁን ብሔረሰብ… ስልጣን ለመጋራት ጥሮ ግሮ የብሔረሰብ ነፃነት ማወጅ… የብሔረሰብ ነፃነት ገበያ ደርቷል።
የመደብ ትግል ጥያቄ ሳይነጋ የመሸበት ፣ ሳይዳክር ወገቡ የጎበጠበት ታሪካዊ ውነት ሆኗል። የመደብ ትግሉ ሰራዊት በአይነቱም በይዘቱም ውጥንቅጡ የወጣ የጋራ በሚለው የመደብ ጠላት ላይ እንኳ ባንድ ረድፍ ተሰልፎ የመፋለም ብቃት የጎደለው ሰነፍ ሆኖ ተገኝቷል። እናም ድሉ አዲስ ውነት አለን ብለው በተሰለፉ የብሔረሰብ ነፃ አውጪዎች እጅ ወድቋል – የብሔር ብሔረሰቦች ነፃነት እስከ መገንጠል…
እኔ አስከሚገባኝ ድረስ ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋዎች እና ባህሎች ባለፀጋ ናት። ስለ ኢትዮጵያ ስንናገር ስለ ነኝህ የተለያየ ቋንቋ እና ባህል ባለቤት ህዝቦች ነው። እናም የትኛውም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ አድጎ በልፅጎ የመማሪያ ፣ የመመራመሪያ ቋንቋ መሆን ቢበቃ ኩራቱ የኢትዮጵያ ነው። ባህሉ ተጠብቆ ዳብሮ ቢቀጥል አሁንም ኩራቱ የኢትዮጵያ ነው። ይሄ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ የሚመለከት ነው።
ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ ያንድ ወይንም የሌላ ብሔረሰብ ሰዎች የግል ጉዳይ ተደርጎ መታየት የለበትም። ይሔ ወይም ያ ብሔረሰብ የግሌ የሚለው ኢትዮጵያን የማያኮራ ፣ የማያደምቅ አጀንዳ ይዞ ቢነሳ አካሄዱ ንትርክ እና አማባጓሮ ከማስነሳቱ በስተቀር ለህዝቡ የሚፈይደው ነገር አይኖርም።
ህብረተሰብ ዳይናሚክ ነው – ይዳብራል ፣ ያድጋል ፣ ይለወጣል – የሚለወጠው እና የሚዳብረው ከቋንቋው ፣ ከባህሉ ፣ ካኗኗሩ ፣ ከመስተጋብሩ… ከብዙ ክስተቶች ጋር ነው። ህብረተሰባችን እየተለወጠ ሲሄድ ብሔራዊ ምንነቱን ይበልጥ ማሸብረቅ በሚችልባቸው ቋንቋዎቹ የጥበብ እና ምርምር ውጤቶች ተጠቃሚ እየሆነ እንጂ ባለበት እየረገጠ አይደለም። የብዙ ቋንቋዎች ባለቤት መሆናችን ለውሱን አመለካከት እና ጠባብ አላማ ሰለባ ሊያደረገን አይገባም። ጉዳዩ የሰብአዊ ርህራሄ እና የበጎ ፈቃድ ሳይሆን ዕድገት እና ዘመን ግድ የሚለው እርምጃ ነው። ትናንት መደበኛ መሰረታዊ ትምህርት ይሰጥ የነበረው በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነበር። ነገ አቅሙ ከፈቀደልን በሌሎች ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ትምህርት የማይሰጥበት ምን ምክንያት አለ? አንድን ቋንቋ አዳብሮ እና አበልፅጎ የምርምር ማካሄጃ ደረጃ ላይ ማድረስ የዕድገት ውጤት ነው።
አፄው እና የጉልተኛ ስርዓቱ የተገረሰሰው በብሔር ብሔረሰቦች ግምባር ሳይሆን ግፍና ብዝበዛ ይወገድ ብለው በተነሱ ስለ ፍትህ እና የአገር አንድነት የጋራ ራእይ በነበራቸው ከሁሉም የኢትዮጵያ ማእዘናት በተነሱ እንግልት ዜጎችና አጋር ሆነው በተሰለፉ ተራማጅ ምሁራን ትግል መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ለዘለቄታው ፍትሀዊ ስርዓት ማምጣት ባይበቃም ምልአተ ህዝቡ ግን ታሪካዊ ድል መጎናፀፉ ውነት ነው።
የጣሊያን ወረራ በሉት የሶማሊያ መስፋፋት የተገታው እና የተደመሰሰው በሁሉም ዜጎች ሙሉ የባለቤትነት ተሳትፎ በተካሄደ ርብርብ ነበር። የብሔረሰብ ነፃ አውጪዎች ትግል በዚህ ሂደት ውስጥ ያበረከተው አንዳችም በጎ ነገር የለም። እንዲያውም ኢትዮጵያውያን በጋራ ተሰልፈው የዚያድ ባሬን ወረራ ለመመከት ሲዋደቁ የትግራይን ብሔረሰብ ነፃ እናወጣለን ያሉ የወያኔ መሪዎች በሱማሊያ ፓስፖርት እና ጦር መሳሪያ ድጋፍ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ሴራ ይደቁሱ ነበር – ለወያኔዎቹ ኢትዮጵያ ወረራ ቢፈፀምባት ፣ ያን ጊዜ ዚያድ ባሬ በለስ ቀንቶት ቢሆንና ኢትዮጵያ ብትፈራርስ ደንታቸው አልነበረም።
ለብዙሀኑ ዜጋ ግን በወረራው የተደፈረችው አገር ነበረች ፣ የታደጓትም ዜጎቿ ነበሩ። ያኔ ከፋም ለማም አገር ብለው የሚያስተዳድሩ መሪዎች ነበሩን… እነሱ ባቆዩት አገር ውስጥ ነው እንግዲህ ዛሬ ለብሔረሰብ ነፃነት እስከ መገንጠል ለመታገል የሚጠራሩት።
በወዛደሩ ፣ በአርሶ አደሩ ፣ በጭቁኑ መለዮ ለባሽ እና ተራማጅ ምሁራን የጋራ ግንባር ኢትዮጵያ ትለመልማለች የሚለው ስሜት ቢያንስ ቢያንስ ደብዝዟል – ያንን መርሆ ኮለኔሉ ለስልጣናቸው መደላደያ አድርገው ስላረከሱት ፋይዳው ወድቋል።
አዎ የኦሮሞ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል…
ጀግኖቹ የኦሮሞ ልጆች እንደ ማንኛውም ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጣልያንን ሲዋጉ ፣ የሱማልያን ወረራ ለመመከት ሲዋደቁ ፣ ተገንጣዮችን እና አስገንጣዮችን ሲፋለሙ ፣ አገሬን አሳልፌ ለማንም ስግብግብ ወራሪ አሳልፌ አልሰጥም ሲሉ… አቡነ ጴጥሮስ የፋሺስት ግፋዊ ፍርድ አስፈፃሚ በሆኑ ባንዳ ተኳሾች በጥይት ሲደበደቡ ጉዳዩ አገርን እንደ አገር ለማቆየት ሲባል የተፈፀመ መሆኑን ማንም ሊዘነጋው አይገባም።
የዛሬው ትውልድ ወያኔ ከዘረጋው የጥፋት ወጥመድ ውስጥ ወድቆ የማይሽር ጉዳት ከመድረሱ በፊት ስልት እና ግብ ላይ ያነጣጠረ ተግባር መከናወን ይገባዋል። ብሔረሰቦቻችን መኩሪያችን ናቸው – ብሔረሰቦቻችን የታቀፉባት ኢትዮጵያ ከሌለች ሁሉም ነገር ይቀራል። ኢትዮጵያን አጥፍቼ እኔ በነፃነት እኖራለሁ የሚል ብሔረሰብ ካለ አካሄዱ ግብዝነት ብቻ ሳይሆን አርቆ ማስተዋል የጎደለው ዝንባሌ ነው። የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዳይሆን ጉዳዩን ማስተማር የሁሉም ሀላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ድርሻ ነው።
ሉአላዊነት የሌለው ህዝብ አንድም አገሩን የተቀማ ፣ ብሔራዊ ክብሩን የተገፈፈ ፣ ወሰኑ እና ዳር ድንበሩ እንዳሻ የሚጠብ እና የሚሰፋ ብሎም እንደ ዜጋ ምንም አይነት የባለቤትነት ድርሻ የሌለው ማለት ነው።
አገር ፣ ብሔራዊ ማንነት ለይስሙላ ወይንም ለፈሊጥ የሚኖር ሳይሆን ከግለሰብ እስከ ህብረተሰብ ብሎም ብሔር እና ብሔረሰብ ህልውናቸው ተረጋግጦ ፣ ዋስትና አግኝቶ በስርአት የሚተዳደሩበት ማዕቀፍ ነው። አገር የተለያየ ቀለም ፣ ቋንቋ ፣ ባህል ስነ-ልቡናዊ ዝንባሌ ባላቸው ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር ተፀንሶ በተለያየ ዕድገት ጎዳና ፣ ውጣ ውረድ ፣ መውደቅ እና መነሳት ያልፋል – ይሄ በሁሉም የአለም አገሮች ታሪክ ውስጥ የሚገኝ ውነት ነው። አገሮች ያንን የዕድገት ደረጃ አልፈው ዛሬ እንደ ፍትህ ፣ ሰብአዊ መብት ጥበቃ እና የህግ በላይነት ጉዳዮች ያሉ ይበልጥ የሚዳብሩበትን ብልሀት የሚመረምሩበት ዘመን ላይ ናቸው።
ሀይሌ ገ/ሥላሴ የተባለው እውቅ አትሌት ሰሞኑን ቢቢሲ ራዲዮ ላይ ቀርቦ ሲናገር ‘…ለአፍሪካውያን ዲሞክረሲ የቅንጦት ጥያቄ ነው’ ማለቱን ሳታዳምጡ አልቀራችሁም። አቃቂ እና ዱከም አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬወች ከአፅመ ርስታቸው ተፈናቅለው በሪል ስቴት ስም ሀይሌ ገ/ሥላሴ ኮንዶ እየገነባባቸው መሆኑን ከፊሉንም የተንጣለለ የግጦሽ መሬት በራሱ ስም አጥሮ ማስቀመጡን ሳታውቁ አትቀሩም። ከአካባቢው የተነፈናቀሉ ዘመዶች ስላሉኝ ጉዳዩን በቅርብ አውቃለሁ። ዛሬ ህዝቡ ተነስቶ የመሬት ወረራ ይገታ ብሎ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥያቄ ማንሳቱ ለገ/ሥላሴ ልጅ የቅንጦት ጥያቄ ሆኗል። የድህነትን ዳገት በሩጫ የወጣው አትሌት ስለ ዲሞክረሲ ፅንሰ ሀሳብ ለማወቅ ዕድል የነበረው አይመስለኝም። እሱ ዛሬ የቅንጦት ህይወት ውስጥ እንዳለ ሳልዘነጋ ስለ ዲሞክረሲ ማይም ቢሆንም ስለ ቅንጦት ጉዳይ ግን የጠለቀ ዕውቀት እንዳካበተ አልጠራጠርም። የስንቱን አንጎል አንይ!
ለተፈናቀሉት ዘመዶቼ የገ/ሥላሴ ልጅ ሌላ ስግብግብ ወራሪ እንጂ ጀግና አይደለም።
ተነሱ እናንት የርሀብ እስረኞች
ተነሱ የምድር ጎስቋሎች
ፍትህ በሚገባ ይበየናል
ሻል ያለ አለምም ይታያል…
አዎ የኦሮሞ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል…
የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው – የመሰረታዊ ሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው ፤ የአገር ሉአላዊነት ጥያቄ ነው። ስለሆነም ዘረኞችን እና ስግብግብ ዘራፊዎች ወደ ታሪክ አተላነት እስከሚቀየሩ ድረስ ትግሉን ይቀጥላል።
ኦሮሞን ኦርመ ሚቲ – ኢትዮጵያ ኦርማፍ ሂንላቱ!!
The post ማንስ ኦሮሞን በኦሮማዊነት ያማል? | ከታሪኩ አባዳማ appeared first on Zehabesha Amharic.