ከሊሊ ሞገስ
(በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 54 ላይ ታትሞ የወጣ)
ፓፒስ ዴምባ ሲሴ ሃይማኖቱን አ ጥባቂ ሙስሊም ነው፡፡ እስልምና ደግሞ ወለድን መብላት ይከለክላል፡፡ የወለድ ስርዓት ያለበት የፋይናንስ አሰራር ውስጥ ተከታዮቹ እጃቸውን እንዳያስገቡ ይደነግጋል፡፡ ኒውካስል ዩናይትድ wonga ከተባለው ኩባንያ ጋር የማሊያ ላይ ስፖንሰርሺፕ ስምምነት መፈራረሙ ለሲሴ አመቺ አልሆነም፡፡ ኩባንያው የአጭር ጊዜ ብድር የሚሰጥና ከፍተኛ ወለድን የሚጠይቅ ኩባንያ ነው፡፡ ኒውካስል ደግሞ የሲሴ ቀጣሪና ደመወዝም ይከፍለዋል፡፡ የሲሴ እምነት ደግሞ ከwonga ጋር ምንም አይነት የስራ ግንኙነት መፍጠርን አይፈቅድም፡፡ በዚህ ላይ በጨዋታዎች ላይ የኩባንያው አርማ የሰፈረበትን ማሊያ ለብሶ የመጫወት ግዴታ አለበት፡፡
የተጨዋቹ ተቃውሞ ከመነሻው ጠንካራ ነበር፡፡ ማሊያውን አልለብስም በሚለው አቋሙ መጽናቱን ለማሳየት ክለቡ ለቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ወደ ፖርቹጋል ያደረገው ጉዞ አካል አልሆነም፡፡ ጓደኞቹ ወደ ዝግጅት ሲጓዙ ሲሴ ቀርቶ ከቤተሰቦቹ፣ ከጓደኞቹና ከሃይማኖት ሊቃውንት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መከረ፡፡
በዚህ መልኩ ተቃውሞን ሲያቀርብ ሲሴ የመጀመሪያው እግርኳስ ተጨዋች አይደለም፡፡ በ2006 ለስፔኑ ሲቪያ በሚጫወትበት ጊዜ ፍሬዲሪክ ካኑቴ 888.com የሚል ፅሑፍ የሰፈረበትን ማሊያ እንደማይለብስ አስታውቋል፡፡ የኢንተርኔት ቁማር ኩባንያ በመሆኑ ነው፡፡ እንደ ሲሴ ሁሉ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ካኑቴ ደግሞ ይህን በማድረግ የመጀመሪው ስፖርተኛ አልነበረም፡፡ ሃሺም አምላ የተሰኘው ደቡብ አፍሪካዊ የክሪኬት ተጨዋች castle lager የተሰኘውን ቢራ ጠማቂ የኩባንያ ዓርማ የሰፈረበትን መለያ ከመልበስ ታቅቧል፡፡
እስልምና በምንም አይነት መጠን ቢሆን አልኮልን መጠጣትንም ሆነ ለሌሎች እንዲጠጡ ማበረታትን ይከለክላል፡፡ እናም አምላ ከማሊያው ላይ ምልክቱ እንዲነሳለት ጠይቋል፡፡ አስተዳዳሪውም የስፖርተኛውን ጥያቄ ተቀብለው በጨዋታ ላይ አምላ ማስታወቂያ ያላፈረበትን ማሊያ ለብሶ ተጫውቷል፡፡
የሲሴ ጥያቄ የአምላ አይነት ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ዘግይቶም ማሊያውን ለመልበስ ወስኗል፡፡ ይሁን እንጂ ሲሴ አቋሙን የቀየረበት ምክንያት ዝርዝር አልታወቀም፡፡ ይልቅ ከፖርቹጋል ዝግጅት በቀረበት ሰዓት የብሪታኒያ ጋዜጦች ተጨዋቹ በካዚኖ (የቁማር ማዕከል) ሳለ የሚያሳይ ፎቶግራፍ በአምዶቻቸው ላይ አትመው ነበር፡፡ ፎቶው ሴኔጋላዊው ቁማሩን ሲጫወት ባያሳዩም ከመቆመሪያው ጠረጴዛ አጠገብ (በሚጫወት ሰው ሁኔታ) ተቀምጦ ነበር፡፡ ቁማሩን ተጫውቶ ከሆነ ማሊያውን ላለማድረግ የነበረው አቋም ከልብ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ተሰንዝረውበታል፡፡ ሆኖም የተጫዋቹ ወኪል ‹‹ሲሴ ቁማርተኛ አይደለም›› ሲል ማስተባበያ ሰጥቶለታል፡፡ የካዚኖው ኩባንያ ቃል አቀባይ ግን ሲሴ ከአንድ ጊዜ በላይ ወደ ቁማር ቤት ለመምጣቱ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ በቁማር ቤት መገኘቱን እንጂ ቁማር መጫወቱን ግን አልገለፀም፡፡
የኒውካስል ከተማ ከንቲባ ዲፑ አሃድ ሲሴ ማሊያውን አልለብስም ባለበት ሰዓት ላይ ለተጨዋቹ ድጋፋቸውን ሰጥተው ነበር፡፡ በኋላ አቋሙን መቀየሩ ግን ሰውየውን ለትችት የዳረጋቸው ይመስላል፡፡ በተለይ በቁማሩ ቤት የመገኘቱ ዜና ከንቲባውን አበሳጭቷቸዋል፡፡ አሃድ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹በድርጊቱ በጣም አፍሬያለሁ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን በአቋሙ የደገፉትን ሁሉ አሳፍሯል፡፡ በቁማር ቤት መገኘቱ (ቁማር ባይጫወትም እንኳን) መጥፎ መልዕክት ያስተላለፈ ይመስለኛል››
ለሃይማቱ ተከታዮች ፆም ሌላው ግዴታ ነው፡፡ ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያ ድረስ ከምግብ፣ መጠጥ፣ ማጤስ እና ወሲብ መፈፀም መራቅ ግድ ነው፡፡ በረመዳን ወር ሙስሊሞች በዚህ ይተጋሉ፡፡ ወቅቱ የፀሎት ጊዜም ነው፡፡ በዚህ ወር ሙስሊሞች ከበዛ መዝናናት ሳይቀር ይታቀባሉ፡፡
ለስፖርተኞች ደግሞ ፈታኝ ጊዜ ነው፡፡ አንዳንዶች ጭራሹኑ አይጾሙም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የመጣውን ሁሉ ተጋፍጠው ይፆማሉ፡፡
ከማይፆሙት መካከል አንዱ ኒኮላ አኔልካ ነው፡፡ በፆም ወቅት ጉዳት እንደሚደራረብብኝ አረጋግጫለሁ ያለው ፈረንሳዊ የማይፆምበትን ምክንያት አቅርቧል፡፡ አንዳንድ አሰልጣኞች ደግሞ ተጨዋቾቻቸው እንዳይፆሙ ይከለክሏቸዋል፡፡ እንደማሩዋን ሻማክ ያሉት ደግሞ የአሰልጣኞችን ትዕዛዝ ወደ ጎን በማለት የሃይማኖታቸውን ግዴታ ይወጣሉ፡፡ በአንድ ወቅት ካኑቴ ሲናገር ‹‹በፆሙ ወቅት የማደርገውን ሁሉ የቡድን ጓደኞቼ በአንክሮ ይከታተላሉ›› ብሏል፡፡ ይከታተሉ እንጂ በፀሎቱ ጊዜ አይረብሹትም፡፡ እምነቱን ያከብሩለታል፡፡ ‹‹ስለዚህ እየጾምኩኝ መጫወቴ የተለመደ ነው›› ይላል፡፡
ሙስሊም ተጨዋቾች በረመዳን ወር በተቻላቸው መጠን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ቢገደቡላቸው አይጠሉም፡፡ ፆሙን በአግባቡ ለመፆም ሲሉ ነው፡፡ በአብዛኛው በሙስሊሞች የተገነባ ቡድን ያለው የግብፁ አል አህሊ ክለብ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የካይሮው ክለብ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ከኦርላንዶ ፓይሬትስ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከሐምሌ 28 ወደ ነሐሴ 3 ቀን 2005 እንዲቀየርለት ጠይቆ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ጥያቄውን ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ጨዋታውን ከፆሙ መጠናቀቅ በኋላ ይደረግ ነበር፡፡ ሆኖም ካፍ ጨዋታው በተያዘለት መርሐ ግብር እንዲቀትል (እንዳይቀየር) ወስኗል፡፡
አፍሪካዊያን እግርኳስ ተጨዋቾች ሁሉ ሙስሊሞች አይደሉም፡፡ ወይም ሙስሊም ተጨዋቾች ሁሉ አፍሪካዊያን ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ግን የአፍሪካዊያን ሙስሊም እግርኳስ ተጨዋቾች ቁጥር ብዙ ነው፡፡
muslimpopulation.com እንደተሰኘው ድረገፅ መረጃ ከሆነ ከግማሽ በላይ አፍሪካዊያን የእስልምና እምነት ይከተላሉ፡፡ ለእንግሊዝ አገር ሙስሊም ተጨዋቾች ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን በመወጣት እንዲጫወቱ ለማድረግ ድጋፍ ሰጪ ተቋም አላቸው፡፡ ቀድሞ ያልነበረውን ይህን አገልግሎት የሚሰጠው ተቋም በ2011 ናታን ኤሊንግተን በተባለ የክሪው አሌክሳንድራ አጥቂ የተመሰረተው የሙስሊም ተቋም በ2011 ናታን ኤሊንግተን በተባለ የክሪው አሌክሳንድራ አጥቂ የተመሰረተው የሙስሊም እግርኳስ ተጨዋቾች ማህበር ነው፡፡ በሊቨርፑሉ የስፖርት ህክምና ቡድን ኃላፊ ተጨዋቾች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምክር ይሰጣል፡፡ በማፍጠሪያ ሰዓት ጥቂት ብቻ እንዲመገቡና በኋላም በዛ ያለውን ምግብ እንዲያስከትሉ የዶክተሩ መመሪያ ይመክራል፡፡ በተጨማሪም ማህበሩ ከቢቢሲ ጋር በመተባበር ‹‹THE MUSLIM PREMIER LEAGUE›› የተሰኘ ጥናታዊ ፊልም ለማዘጋጀት እየሰራ ይገኛል፡፡ ፊልሙ በእንግሊዝ ከፍተኛው የእግርኳስ ዲቪዚዮን ውስጥ ሙስሊም ተጨዋቾች የሚገጥማቸውን ጉዳዮች ይዳስሳል፡፡ በ20 ዓመቱ የሊግ ታሪክ ሊጉ በሙስሊም ተጨዋቾች ላይ ያሳደረውን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ሁሉ በፊልሙ ላይ ይዳስሳል፡፡