Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ክፉን ሰውና ክፋተኝነትን እንዴት እናውቃለን? በይሄይስ አእምሮ

$
0
0

ይሄይስ አእምሮ

comment pic  ርዕሴ በጣም እንዳይጮኽብኝ ፈርቼ እንጂ ላደርገው አስቤና ፈልጌም የነበረው “ሰይጣንና ሰይጣናዊነት እንዴት ይታወቃሉ?” የሚል ነበር፡፡ ይህ ጽሑፌ በዚሁ ተመሳሳይ ጉዳይ ዙሪያ ባለፈው ሰሞን በአንዳንድ ድረ ገፆች የወጣውን በሴቴኒስቶች የሰላምታ መለዋወጫ ምልክቶች ምስል የተደገፈ አነስተኛ መጣጥፍ የተከተለ  ነው፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ቀጣዩን ሥነ ቃላዊ ትውፊት ለነገሬ መነሻነት ባስቀድም ደስ ይለኛል፡፡

የቸገረው ሰው ከገባበት የችግር ማጥ ለመውጣት የማያደርገው ነገር የለም፡፡ አንዲት ሴት፣ ልጅ መውለድ እምቢ ይላትና ለዐርባ አራቱም ታቦት ትሳላለች፤ በዚያም አልሆነላትም፡፡ በየጠንቋዩና በየደብተራው ቤትም ደጅ ትጠናለች፤ በዚያም አልሆነም፡፡ በየጠበሉና በየሀኪም ቤቱም ትንከራተታለች፤ አሁንም በዚያም አይሆን ይላታል፡፡ ቢጨንቃት ለሰይጣን ትሳላለች፡፡ ስለቷም “አንተ እንደኔው የእግዜር ፍጡር የሆንክ ሰይጣን ሆይ! ልጅ እወልድ ብዬ ብዙ ተሳልሁ፤ ወጣሁ ወረድሁ ግን አልሆነልኝም፡፡ አሁን ደግሞ ባንተ በኩል ልሞክር ወስኛለሁ፡፡ ስለዚህ እስከዛሬ ዓመት ድረስ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ከሰጠኸኝ ራሴው ፈትዬ አንድ ቡልኮ በስለት አስገባልሃለሁ” የሚል ነው፡፡

የአጋጣሚ ነገር ሆነና ልክ ባመቱ የሰማ ሰምቷት አንድ ወንድ ልጅ ከነቅጭልጭሉ ትወልዳለች፡፡ ደስታዋም ከጣሪያ በላይ ይሆናል፡፡ ከአራስ ቤት ጀምራ ትፈትልና በክርስትናው ማግሥት ለሰይጣን የተሳለችውን ቡልኮ በዕውቅ ሸማኔ አሠርታ ዝግጁ ታደርጋለች፡፡ ነገር ግን ያላሰበችው ችግር ይገጥማታል፡፡ ሰይጣንን የት አግኝታ ትስጠው? ችግር እኮ ነው፤ አንዱ ሲሟላ አንዱ አይሟላም፡፡

በየመንደሩና በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እየዞረች “የሰይጣንን ቤተ ‹ክርስቲያን› ያያችሁ ነይ ወዲህ በሉኝ” ብትል ማን ዐውቆት ያሳያት? ብዙ ትለፋለች፤ ትደክማለችም፤ ነገር ግን በክንዷ አንጠልጥላ የምትዞረውን ቡልኮ ወይም ጋቢ የሚረከባት አንድም ሰይጣን ይጠፋል፡፡

ችግሯን ያስረዳቻቸውና የገባቸው አንድ ብልህ ሽማግሌ ግን እንዲህ ሲሉ ይመክሯታል፡፡ “አንቺ ሴትዮ፣ ልጅ ለመውለድ ያደረግሽው ጥረት በውነቱ የሚገርምና ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማያውቅ ነው፡፡ አሁን ሰይጣንን ካላገኘሽውና ቤቱንም ካጣሽው በአማራጭነት እንዲህ አድርጊ፡- እሁድ ቀን ወደ አንዱ ቤተ ክርስቲያን ሂጂ፡፡ ከዚያም ማርገጃው አካባቢ ሽማግሌዎች ተሰብስበው የተጣሉ ወይም የተቀያየሙ ሰዎችን በሚያስታርቁ ጊዜ የሽማግሌ ቃል አልሰማም ብሎ ንቋቸው ከጉባኤው እመር ብሎ የሚወጣ ሰው ስታገኚ ‹በስምህ የተሳልሁትን ልሰጥህ ስፈልግህ ኖሬ ዛሬ ገና አገኘሁህ፤ ይሄውልህ ቡልኮህ› በይና ትከሻው ላይ ጣይለት፤ ሰይጣን ማለት ዕርቅና ሰላምን የማይወድና የማይፈልግ ነውና እዚያ ማርገጃው ላይ በሰው ተመስሎ ታገኝዋለሽ፡፡” ይላታል፡፡

‹ሞኝ የነገሩትን፤ ብልህ የመከሩትን› ነውና ያቺ ሴት እንደተባለችው ቤተ ክርስቲያን እየሄደች ያን መሳይ ሰው ታጠምድ ያዘች፡፡ አንድ ቀንም እንደድንገት ሃሳቧ የሚሣካበት ምቹ አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ አንድ ደመ ሞቃት ሰው የሽማግሌዎችን ምክርና ተግሣጽ እንዲሁም የማስታረቂያ ሃሳብ ንቆ “ደግሞ እናንተን ብሎ አስታራቂ! ቀልማዳ ሁላ፤ እኔ ነኝ ደግሞ ‹በድየሃለሁና ይቅር በለኝ ብዬ እሱ እግር ላይ የምወድቅ?› የወሬ ቋቶች! …” በማለት ተስፈንጥሮ ከጉባኤው ሲወጣ ታየዋለች፡፡ ይሄኔ በደስታ እየተፍነከነከች አፈንጋጭ ጎልማሣውን ጠጋ ትልና “እሰይ! እንኳን አገኘሁህ! አሁን ገና ገበያየ ሞላ! ለስንት ጊዜ ስፈልግህ ኖሬ ዛሬ ገና ተሳካልኝ፡፡ በል ስለትህን ተረከበኝ” ትልና ቡልኮውን እሰውዬው ትከሻ ላይ ትጥልለታለች፡፡

ሰውዬውም ይደነግጥና ‹እንዴ? ምንድነው እሱ – ምን አድርጌልሻለሁ?…› በማለት ምክንያቱን ይጠይቃታል፤ እሷም በተመከረችው መሠረት ነገሩን ከሥሩ ታስረዳዋለች፡፡ ይሄኔ ያ ሰው ‹ሰይጣንነቱ› ይከሰትለታል፤ እሱ ሰው እንጂ ሰይጣን እንዳልሆነ በማስረዳት ጋቢውን ይመልስላትና ወደጉባኤው ተመልሶ ሽማግሌዎቹንም ይቅርታ ጠይቆ ቀድሞ በተነገረው የማስማሚያ ቃላዊ ሠነድ መሠረት ከባላንጣው ጋር ይታረቃል፡፡

ብልሁ መካሪ ሽማግሌ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታታቸውን ልብ ይሏል፡፡ መግቢያየ ይህን ይመስላል – አሁን ወደዋናው መስመር ልመልሳችሁ፡፡

ሰይጣን እንዴት ይታወቃል? ተከታይ ጋሻ ጃግሬዎቹስ እንዴት ይለያሉ? በጣም ቀላል ነው፡፡ በቅድሚያ ግን እንደመነሻ ከአሥራ አንዱ ሰይጣናዊ መመሪያዎች ሦስቱንና(4ኛውን፣ 7ኛውንና 11ኛውን) ዘጠኙን ሰይጣናዊ ኃጢኣቶች ቀጥለን እንመልከት፡፡

4.  በቤትህ የመጣ እንግዳ ካበሳጨህ ያለአንዳች ርህራሄ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ አጸፋውን መልስለት፡፡ (ዐይንን ላጠፋ ዐይንን ማጥፋት ከሚለው የሀሙራቢ ሕግ ጋር የሚመሳሰል)

7. ፍላጎቶችህን ለማሳካት ጥንቆላና መተት ተጠቅመህ ከሆነ ለዚህ (ሰይጣናዊ) አበርክቶ ዕውቅና ስጥ፤ ምሥጋናም አቅርብ፡፡ ይሁንና በጥንቆላና በምትሃት ስኬት ጫፍ ላይ ከደረስክ በኋላ የበላህበትን ወጪት ሰባሪ ሆነህ ሰይጣንን ብትክድ ያገኘኸውን ሁሉ ታጣለህ፤ የሰይጣን በረከትም ይለይሃል፡፡

11. በየትኛውም ግዛት ስትጓዝ ስለምንም ነገር ሃሳብ አይግባህ፤ በጉዞህ ላይ የሚያስቸግርህ ሰው ቢገጥምህ በቅድሚያ እንዲተውህ አስጠንቅቀው፤ ካልተወህ ግን ድራሹን አጥፋው፤ ድባቅ ምታው፡፡

 

ዘጠኙ ኃጢኣቶች (ሴቴኒስቶች ሊተላለፏቸው የማይገቡ የሃይማኖቱ መሥራች አንቶን ሌቪ የቀመራቸው)

  1. ደደብ መሆንና በሌሎች ተበልጦ መገኘት (ኃጢኣት ነው!)
  2. እውነትን እንዳመጣጧ በኃይልም በዘዴም በተገኘው ሥልት ሁሉ ከመጋፈጥ ይልቅ እንደቀሪው ማኅበረሰብ በአስመሳይነትና በነባር ባህል ለመመሳሰል መሞከር
  3. የኃይል ግብረ መልስ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በታጋሽነት ማለፍ
  4. የሆነን እንዳልሆነ ወይም ያልሆነን እንደሆነ አድርጎ ራስን ማታለል
  5. የራስን ስሜት ከመከተል ይልቅ በይሉኝታና በሀፍረት ታስሮ የሌሎችን ፍላጎት ተቀብሎ በየዋህነት ከጎጋው ሕዝብ ጋር መንከርፈፍ
  6. ወደተፈለገው ግብ የሚያደርስ (ማንኛውም ዓይነት) ራዕይና ዓላማ አለመያዝ
  7. ያለፈን የሃይማኖትና የማኅበረሰብ ትውፊት መርሣት ሲገባ ያን ማስታወስ
  8. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በራስ ስኬት መኩራት ያለመፈለግና ያለመቻል
  9. በሁሉም ዘርፍ ሁሉንም ቀድሞ ለመገኘት በማንኛውም መንገድ የተቻለውን ሁሉ ጥረት አለማድረግ

 

ሰይጣናዊነትና ተከታዮቻቸው (Satanism and Satanists) በይፋ ቤተ አምልኮ (Church of Satan) አቁመው ሰይጣንን ማምለክ የጀመሩበት ዘመን የቅርብ ጊዜ ክስተት ቢሆንም ይህ ሃይማኖት በድብቅም ይሁን ሲቻል በግልጽ፣ በሰይጣን ስምም ይሁን በሌሎች መጠሪያዎች በዚህች ዓለም ውስጥ ኅልውናውን ያገኘው ከሰው ልጆች መፈጠር ጋር እንደሚያያዝ መገመት አይከብድም፡፡ “ሊበሉት የፈለጉትን አሞራ ስሙን ይሉታል ጅግራ” እንዲሉ ሆኖ በስያሜ ለሰይጣን የቀረበም ይሁን የራቀ በተግባር ግን ሰይጣናዊ የሆነ የእምነት አካሄድ በዓለማችን ከረጂም ዘመን ጀምሮ በገሃድ ይታይ እንደነበር ለማንም መዝገብ አገላባጭ እንግዳ ነገር አይሆንም፡፡ ባገራችን የቆሌ ባዲገዝና የቦረንትቻ ባህል፣ ‹እነዚህ ባለውቃቢዎች ለካንስ ክርስቲያኖች ናቸው› በሚል የዋህነት ሰው እንዲከተላቸው ‹ገብርኤልንና አቡየ ፃዲቁን ዘክሪ፣ የሚካኤልን ጠበል ለሦስት ሰባት ጠጪ…› የሚሉትን አጭበርባሪ ባለአውሊያዎች፣ ሌሊት ቅኔ ማኅሌት ላይ ቃለ እግዚአብሔርን በዕዝልና በአራራይ እያንበለበሉ ቀንና ባሳቻ ሥፍራ ግን መጥሐፍ የሚገልጡ ደባትርና ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት… በሙሉ የአጋንንት ጭፍራዎች መሆናቸውንና ይህም ዕኩይ ተግባር ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ማኅበረሰብኣዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔ እንደሆነ መገንዘብ አይቸግርም – የሁለት ጌቶች አሽከር መሆን የሚፈልግ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ሣይሆን የሰይጣን አሽከር ነው፡፡ በዚህ መስመር መጓዙ ብዙ ያደክመናልና ባጭሩ እንመለስ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ “ጣፋጭ ፍሬ ከዛፍ ላይ እንዳለ ያስታውቃል” ይላል፡፡ የክርስትና እምነት ቁንጮ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም እዚህ የምናነሳቸውን ሰዎች “በሥራቸው ታውቋቸዋላችሁ” ይለናል፡፡ አዎ፣ የማን ማንነት በሥራው ይታወቃል፡፡ አዋዋላችንም የሚናገረው ብዙ ነው፡፡ ከነተረቱ “ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ” ይባላል፡፡ ስለዚህ ከየትኛው ወገን እንደሆንን ለመለየት ቀላሉና ብቸኛው መንገድ በሥራችን ማለትም በዘወትር ተግባራችን የምንገልጠው የዕኩይነት ወይም የደግነት መገለጫ ምግባራችን እንጂ የአነጋገራችን ለዛና መስህብ ወይም የአለባበሳችን ማማር ወይም የፂማችን መንዠርገግ አይደሉም፡፡ የምንከተለው ሃይማኖትም ምናልባት ጠቋሚ እንጂ ትክክለኛው የመጽደቃችን ዋስትና አመላካች ሊሆን አይችልም፡፡ በአላህ ስም አንገት እየቀሉ፣ በእግዚአብሔር ስም ግድያን ጨምሮ ሕዝብ ላይ ሰይጣናዊ ቁማር እየተጫወቱ፣ ኩነኔ ካልሆነ ጽድቅ ይገኛል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሰይጣን ደግሞ ብልጥ ነው፤ የምታደርገው ነገር እንጂ የምትከተለው ሃይማኖት ጉዳዩ አይደለም፤ በሥራህ ካከበርከው ፓትርያርክም ሁን ኢማምም ሁን ራባይም ሁን ኮርተህ የመንግሥቱ ወራሽ ነህ፤ እርሱም የአንተን ነፍስ ካለተቀናቃኝ ተረካቢ ነው፡፡ ምሥጢሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ነገር ሁሉ ለ‹ምሁራዊ› ፍልስፍናና ለጉንጭ አልፋ ክርክር ፍጆታ የሚውል እንቶፈንቶ ነው፡፡

ከዚህ በተያያዘ ግን በቅድሚያ የጋራ መግባባት እንዲኖረን የሚያስልግ ጉዳይ አለ፡፡ እሱም ዕኩይ ስንል ምን ማለታችን ነው? ደግ ስንልስ? ለሁለቱም መለኪያችን ምንድነው? በማንስ ዕይታ? ለአንተ ዕኩይ የሆነ ነገር ለእኔ ደግ ከሆነ ዳኛችን ማን ሊሆን ነው? በአንድ ሀገር ወንጀል የሆነ ነገር በሌላ ሀገር ፍቁድ ከሆነ የጋራ መግባቢያው የወል ስምምነት እንዴት ሊፈጠር ይችላል? ነገሩ ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ክርክር ያለው ነገር ነው፡፡

ምሳሌ ወስደን ማየት እንችላለን፡፡ በአንዳንድ የክርስትና ሃይማኖት ዘርፎች የተመሳሳይ ፆታዎች ወሲባዊ ግንኙነት ከቀሲስ እስከ ሊቃነ ጳጳሣት ድረስ እንደሰደድ እሳት የተዛመተ በመሆኑ “የኔ ሶዶማዊ መሆን እግዚአብሔርን በ‹ቅንነት› ከማገልገል ጋር ምን ያገናኘዋል?” በማለት በምድራዊ መንግሥቶቻቸው ሕጎች ብቻ ሳይሆን በቀኖና ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ በቃለ ዐዋዲነት እንዲጽድቅላቸው የሚታገሉ ‹የእግዚአብሔር ቤተሰቦች› በብዛት መታየት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሰይጣን አምላኪዎች አካባቢ ለዘብተኛ የሚባሉት ይህን እኛ ብዙዎቻችን በሰይጣናዊነት የምንፈርጀውን የግብረ ሶዶም ተግባር የሚቃወሙና እንዲያውም ‹ሰው ካልተነኮሰህ አንተ ቀድመህ አትተንኩሳቸው› ብለው የሚያምኑ “ደጋግ” ሰይጣናውያን አሉ፡፡ በክርስትና ሃይማኖት መስጠት (በብቸኝነት ባይሆንም) እንደሚያጸድቅ ይሰበካል፤ በሌላም በኩል በዚሁ ሃይማኖት አንዳንድ የተማሩ ተከታዮች ዘንድ መስጠት ሰውን ስለሚያሰንፍ ከአጽዳቂነቱ ይልቅ አስኮናኝነቱ ይበዛል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ የክርክሬ አካሄድ ለሁሉም ግልጽ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ስለዚህ ዕኩይነትና ደግነት እንደቁንጅና ሁሉ የተመልካቹን ፍርድ የሚጠባበቅ ዋጋው በታሳቢነት የሚሰላ ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ ነገሩን ብዙ አናራቅቀውና ሰይጣናዊነትንና ሰይጣን አምላኪነትን እስካሁን ብዙዎቻችን የሚገባንን ያህል አድርገን እንውሰደው፡፡ በነገራችን ላይ በግርድፍ ግምት አራት ዋና ዋና ቅርንጫፎች እንዳለው ከሚገመተው የሰይጣናዊነት እምነት ውስጥ ‹አማፂ ሰይጣናዊነት/Rebel Satanism›ን ያህል የከፋ የክፋትና የአመፃ ድርጊት የሚፈጽም እንደሌለ በዘርፉ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ዓለምን ከጽንፍ እስከ አጽናፍ እያመሳት ያለው አፍራሽ ኃይል (Negative Energy) እንግዲህ ይሄኛው ነው ማለት ነው፡፡ ተከታይ የጥፋት ኃይሎቹም በሀገራቱ መንግሥታትና በኅቡዕም ይሁን በግልጽ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ቡድኖች ውስጥ የተሰገሰጉ በደም የሚነግዱ ጨካኝ ዜጎች ናቸው፡፡ የነሱ ጭካኔ በጨለማው ንጉሥ በዲያብሎስ ዘንድ የሚያሸልምና የሚያሾም ድንቅ ሥራ ነው፡፡ በገደሉ ቁጥር ደስታቸው ይበዛል፤ ባሰቃዩ ቁጥር የመንፈስ መነቃቃትን ያገኛሉ፡፡ የደግነት ምግባር የሚያስከፋቸው፣ የክፋት ሥራ ጮቤ እሚያስረግጣቸው የተንኮልና ሸር አምባሳደሮች ናቸው፡፡ በግዛታቸውና በዘመነ ሥልጣናቸው የተገኘን ምሥኪኖች ግን እናሳዝናለን – ከልባዊ በስማምና አቡነ ዘበሰማያት ሌላ ምንም ጦር የሌለን ድሃ ወገኖች ይህ ዘመነ ሰልቢያኖስ ክፍላችን አይደለም፡፡

ጉንጭ አልፋ ክርክራችንን ትተናል፡፡ ክፉ ማለት ሆን ብሎና አለ አንዳች ምክንያት – ለሥጋዊ ጥቅምና ፍላጎቱ ሲል የሚገድል፣ የሚያሥር፣ የሚያሰቃይ፣ የሚጠላ፣ የሚያዳላ፣ ሆን ብሎ የሚጎዳ፣ የማይስማማ፣ የሚያስርብ፣ የሚያስጠማ፣ የሚያሰድድ፣ የሚያሳድድ፣ የሚከፋፍል፣  … ነው ብለን ለጊዜው እንስማማ – እንደወያኔዎች፡፡ እነዚህንና ሌሎች ብዙዎቻችን በክፉ ሥራነት የምንስማማባቸውን የክፋተኝነት ድርጊቶች የሚፈጽም ዐወቀውም አላወቀውም – ወደ ቤተ ሣጥናኤል ሄዶ ጸለየ አልጸለየ – የቤተ ሰይጣን ተከታይ (ሴቴኒስት) ነው፡፡ እርግጥ ነው ከሴቴኒስቶችም ‹ዘመናዊ ሴቴኒስቶች(Modern Satanists)› የሚባሉት በስም ብቻ ሣይሆን በተግባርም ‹ክርስቲያን ነን› ከሚሉ አንዳንድ አስመሳይ ወገኖች ጋር የተቀራረበ እንዲያውም የተሻለ ባሕርይና አመለካከት እንዳላቸው በዘወርዋራም ቢሆን ከፍ ሲል ዐይተናል፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ስማዊው የየሃይማኖቶቻችን መጠሪያ ሳይሆን ዋና የማንነት መገለጫችን ተግባራችን ነው፡፡ እናም እንደኔ እንደኔ ክፉኛ ግራ ከመጋባቱ የተነሣ በሰይጣን ግዛት ሥር አድሮ ነገር ግና መልካም ሥራ የሚሠራ ሰው በእግዚአብሔር ግዛት ሥር ሆኖ በማወቅ ክፉ ሥራ ከሚሠራ ሰው ያነሰ ዋጋ ያገኛል ብዬ አልገምትም፡፡ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዋጋችንን የሚተምነውና የየመክሊታችንን የሚሰጠን በሰው – ሠራሽ የልዩነቶች ጎራ ተመሥርቶ ሳይሆን በግብር በምናሳየው መልካም ሥራችን ላይ ተመሥርቶ መሆኑን አምናለሁ፡፡ የሆነው ቢሆን ግን “ዕብድ ቢጨምት እስከ ዕኩለ ቀን ነው” እንዲሉ ነውና በተለይ ሰይጣናዊነትን በምንም መንገድ የማላበረታታ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ ላሰምርበት እወዳለሁ፡፡

ዓለማችንን የሠይጣን መፈንጫ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ እጅግ በጣም የቆዬ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንደዚህ ዘመን ግን ሰይጣናዊነት በምልዓት የተገለጠበት ዘመን ታይቶ አይታወቅም ነው የሚባለው፡፡ በተለይ የፊልምና የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ግዘፍ ነስቶ እንዲህ ጫፍ በደረስ ሁኔታ የዓለም ወጣት ዜጎችን መጫወቻ ማድረግ ከተጀመረ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ የእግዚአብሔር ስም እንዳይጠራ እንኳን እዬተደረገ ያለው ሰፊ ዘመቻ በታላቅነቱ ወደር የሚገኝለት አልሆነም – እውነቱን ለመናገር የእግዚአብሔርን ስም መጥራት በርሱም ማመን ፋራና ኋላ ቀር እያስባለ፣ ብዙዎችንም እስከማሣፈር በደረሰ ሁኔታ ከእውነተኛው መንገድ እያሰናከለ የምንገኝበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ በተቃራኒው ግን ዱሮ ያሣፍር የነበረ ጠንቋይና ደብተራ ቤት እየሄዱ መጎናበስና የሰዎችን ጫማ መላስ ዛሬ ዛሬ የሚያኮራ የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡ ጎረቤትህን፣ ጓደኛህን፣ ሀብታምን፣ ታማሚን፣ ምቀኛ ድሃን… ተመልከትና ይህ የምልህ ነገር እውነት ሀሰትነቱን አጢን፡፡ የጠፋንበት ዘመን ላይ እንደምንገኝ አትጠራጠር፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም ባለፀጋና የተደላደለ ኑሮ የሚኖር አብዛኛው ሰው አንድም የሰይጣን አምላኪ ነው፤ አንድም በተለያዩ ወንጀሎች የሚታማ ነው – ሁሉም ግን የሰይጣናዊነት መገለጫ በመሆኑ ሰውዬው ያው ሴቴኒስት ነው – እንደአካሄድ ቅዱስ ሰይጣንና እርኩስ መልአክ የሉም – ምርጫው አንድና አንድ ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር ወይ ሰይጣን – ብርሃን ወይ ጨለማ፡፡ የምልህ ነገር የምቀኛ ወሬ እንዳይመስልህ፡፡ አንተም ብልጥ ከሆንክ ሰይጣን የመሆንና እንደነሱ የመክበር ቦርቃቃ ዕድል አለህ፤ አለበለዚያ ለፍተህና ጥረህ ግረህ በወዝህ መኖር፡፡ በበኩሌ ሰይጣን የመሆን ዕድሉ ነበረኝ፤አለኝም፡፡ ግን አልተጠቀምኩበትም፤ወደፊትም የምጠቀምበት አይመስለኝም፡፡ ስለወደፊት እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል ነው የተጠራጠርኩ የመሰልኩት፡፡ እንጂ የሰይጣን ሀብት ምኑ ሊያስቀና! በአፍንጫየ ይውጣ!

ከፍ ሲል እንደተገለጸው ወጣቱን ማግኘት የሚቻለው በአብዛኛው በሙዚቃና በፊልም እነዚህንም ዋነኛ መደላድል በሚያደርገው በወሲብ አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማሣካት ደግሞ የገንዘብ አስፈላጊነት አማራጭ የለውም፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፉ “ገንዘብ የኃጢኣት ምንጭ ናት” የሚለው፡፡ በእያንዳንዱ ሀብት በስተጀርባ ወንጀል ስለመኖሩ በተደጋጋሚ የሚወሳውም የገንዘብን የነፍስ አማሣኝነት አጉልቶ ለማሳየት ነው፡፡ አሁን በዘመናችን ከፈጣሪ ይልቅ ቤተ አምልኮ አልቆመለትም ጽላትም አልተበጀለትም እንጂ ገንዘብ እስከመመለክ የደረሰው ሰው ራሱ በሠራው የምድር ንዋይ ፈጣሪን መለወጡን የሚያሳይ የዝቅጠት ምልክት ነው፡፡ በዚህ ዘመን እጅግ ብዙ ሰዎች ሁሉንም የሃይማኖትና የሞራል ድንበሮች ጥሰው አቅላቸውን በመሳት ገንዘብን የሚያሳድዱት የዓለም ብልጭልጭ ነገሮች ካለገንዘብ እንዲሁ በምኞት ብቻ ሊገኙ ስለማይችሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምርጫው ሁለት ነው – ከጤናማ ኅሊና ጋር በእውነተኛው ገቢ በድህነት እየኖሩ መቸገር ወይም በሰይጣናዊ ቀድዶ ሕክምና ኅሊናን ከጭንቅላት አውጥቶ በ‹ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ› ዘይቤ በተገኘው መንገድ ሁሉ ለቁሣዊ ሕይወት ብልፅግና መጣር፡፡ በዚህኛው አቅጣጫ ለሚመራ ሰው ገንዘብ እስካስገኘ ድረስ ማንኛውም እንቅስቃሴ በሕግ ቢከለከልም በተግባር የተፈቀደና ያልተከለከለ ያህል የሚቆጠር ነው፡፡

መንግሥታዊ ሥርዓቶችም የዚሁ የንቅዘት ሥርዓት አባላት በመሆናቸው እነሱም የበኩላቸውን ይሞስናሉ፤ ከቢጤዎቻቸውም ጋር ይተባበራሉ፤ ያስተባብራሉ፡፡ የማይሞስን የነሱ ፀር መስሎ ስለሚታያቸው ባገኙት ዘዴ ሁሉ ያጠፉታል – በ‹የምዬን እከክ ወዳብዬ› ሥልት ሙሰኛ ነው ብለውም ዘብጥያ ሊያወርዱትና በፈጠራ ክስ ሊያሰፈርዱበትም ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ሞሳኝና አስሞሳኝ፣ በራሱ አንጡራ ገቢ የማይኖር፣ ያልተፈቀደለትን ማንኛውንም ነገር ከሰው የሚቀማ፣ ሥልጣኑን ለመጨቆኛ እንጂ ባግባቡ የማይጠቀም፣ ሕዝብን በሥልጣኑ የሚበድልና የሚያጉላላ ሁሉ የሰይጣን ወገን ነው፡፡ በዚህም የሰይጣን ወገን ይታወቃል፡፡

ወደሰይጣናዊ ተቋማትና አመራሮቻቸው እንመለስ፡፡ ብዙዎቹ ምናልባትም ሁሉም የነዚህ ዓለም አቀፍ ታላላቅ ተቋማት ባለቤቶች በኢኒሼሽን ፒራሚዳዊ የደረጃ ሠንጠረዥ ከፍተኛውን ዲግሪ በያዙ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ምሥጢራዊ ሰይጣናዊ ድርጅት አባላት ናቸው፡፡ (ለጠቅላላ ዕውቀት፣ የቤተ ሣጥናኤል አመራር መዋቅር ዲግሪ ከ1-5 ሲሆን ‘the Skull and Bones’ን የመሳሰሉ ከዓለማችን ሀብትና ሥልጣን ጀርባ የሚገኙና ወደጥልቁ የጥፋት ባህርም እያዳፉን የሚገኙት የምሥጢራዊ ድርጅቶች ዲግሪ ደግሞ ከ1-33 እንደሚደርስ ይነገራል፡፡ ይህ ዲግሪ ለነሱ እንደማዕረግ የሚቆጠር ነው – በልፋት(በጥፋት?) የሚገኝ!)

የሚደነግጥ እንዳይኖርብኝ እሰጋለሁ እንጂ በአሁኑ ወቅት ሴተኒስቶች ሁሉንም የዓለም ነገር ተቆጣጥረዋል፡፡ የቀራቸው ያለ አይመስልም፡፡ አንተንም አንቺንም እኔንም ተቆጣጥረውናል፡፡ በምትበላው፣ በምትጠጣው፣ በምትለብሰው፣ በምትጓጓዝበት… ይመጡብሃል – በዕቃዎች ላይ በግልጥም ይሁን በሥውር በሚለጥፉብህ የ666 ምልክታቸው ብቻ እንዳይመስልህ – እስትንፋስህን ሳይቀር ተቆጣጥረውታል እያልኩህ ነው ወንድሜ (ፈገግ በል አስኪ፡- ሽንት ቤት ገብተህ ወደዋናው ጉዳይ ከመግባትህ በፊት በእንትንህ ሙዚቃ ስንቴ እንደተዝናናህ ሳይቀር እነሱ ከፈለጉ ያውቁታል፡፡ አዲዮስ ‹privacy›፣ ገባህ? አትታዘበኝ – አዲስ ነገር የለም፡፡ )

በተለይ ኢትዮጵያን በመሰሉ ድሃ ሀገሮች ውስጥ የሚገኘውን የድሃ ገበሬ ማሣ በማዳበሪያ አፈር ድሜ አብልተውታል፤ በኬሚካላቸው የገበሬውን መተዳደሪያ የተፈጥሮ ማዕድን ሲያቃጥሉት በውድ ከሚገዛው የነሱ ማዳበሪያ ውጪ አፈሩ ዘር ማብቀሉን ተወ – ኬሚካሉን ልግዛ ሲል እነጉናና አምባሰልን በመሰሉ የሀገር ውስጥ ወያኔያዊ ሼሪኮቻቸው አማካኝነት ዋጋውን ሰማይ ሰቀሉት፤ እኛንም ገበሬውንም ለችግር ዳረጉንና ሁላችንም ኤሎሄ እንል ጀመር፡፡ በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪውና በፖለቲካው መስክ ከነሱ ቁጥጥር እንዳትወጣ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ድመት የገደለቻትን ዐይጥ እስክትበላት ድረስ እንደምትጫወትባት ሁሉ እነዚህ ጥቂት የአጋንንት ውላጆች እንዳሳሁርታ በቅጽበቶች እየተራባ የሰባት ቢሊዮንን ጉበን በቅርቡ ያለፈውን የዓለም ሕዝብ ጢባጢቤ እየተጫወቱበት ናቸው፡፡ በቁራጭ አሞሌ ጨው በሬ ወደመታረጃው እንደሚሄድ እነዚህ ገብጋቦች የዓለምን ሀብትና ፖለቲካ በቀጥታና በእጅ አዙር ተቆጣጥረው ወደ አጠቃላይ ውድመት እየመሩን ናቸው፡፡ በዚህም ሰይጣኖችን ታውቃለህ!

የትም ሂድ የትም ግባ ቤተ ክርስቲያንን ሳይቀር በአለቃቸው የሰይጣን መንፈስ ተቆጣጥረዋል – ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ እስከቅርብ ሩቅ ድረስ ዋልድባ ገዳምን ሰይጣን እምብዝም አይደፍርም ነበር (ይባላል)፤ አሁን ግን ገዳሟ መንፈላሰሻቸው ሆናለች – የነደብረ ሊባኖስና የሌሎች ደብረዎች ነገር ተከድኖ ይብሰል፡፡ እነዚህ ገዳማትና አድባራት ዋና መሥፈሪያ ቆጣቸው ናቸው፤ ጸሎቱ የማያርገው፣ ስብከቱ የደነደነ ልብን አሟምቶ ከኃጢኣት መንገድ የማይመልሰው፣ ሕዝበ ክርስቲያን የዳነ እየመሰለው ሃይማኖቱን እንደሸሚዝ የሚቀያይረው ከዚህ የተነሣ ነው – ሀሰት ከተናገርኩ … ዳሩ አይማልም ለኬ፡፡ የምለው ግን እውነቴን ነው!

ዘመኑ የጭንቀትና የጥበት ነው፡፡ መዳን በዚህ ወይ በዚያ አለ የሚባልበት ድኅነት ግን የሌለችበት እጅግ አስጨናቂ ዘመን ላይ ልንገኝ የቻልነው አእምሮኣችንን የስንግ በያዙን ሴቴኒስት መሪዎቻችን አማካይነት ራሱ ዲያቢሎስ የፊጥኝ ስላሰረን ነው፤ አሳዳጃችን ሰይጣን በምንሄድበት ቦታ ሁሉ ቀድሞ ይጠብቀናል፡፡ እሥረኞቹ ደግሞ በጎቹ ብቻ ሣንሆን እረኞቻችንም ናቸው፡፡ አዲስ አበባን ተመልከት፡፡ በዲኤክስና በቪታራ… የሚዝመነመነውን የደብር አለቃና የሀገረ ስብከት ባለሥልጣን ካህን ስታይ፣ የየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ታዋቂ ቀሣውስትና መዘምራን ወሰባኪያን በምቾት አብጠው እንደ እምቧይ ሊፈርጡ ተቃርበው ስታይ ያቺ ካላት ሳይሆን ያላትን ከመቀነቷ ፈትታ ወደ ሙዳየ ምጽዋት የምትጨምር ሴት በዐይነ ልቦናህ ትታይሃለች፡፡ እኛ እየኮሰመንን እነሱ እየተነፉ፣ እኛ እየደኸየን እነሱ እየከበሩ፣ እኛ እየፆምን እነሱ እየፈሰኩ፣ … መኖር ተብሎ አለሃይማኖትና አለመሪ የአጋንንት ወጀብ እያላጋን ተገትረን አለን፡፡ ዘመኑ ቀርቧል የምንለው እንግዲህ ከነዚህ ነገሮች አንጻርም ነው፡፡ ሁሉም የውሸት ነው – የታይታ፡፡ ይህን ግን አስብ፡- ‹የእግዚአብሔርና የሰይጣን ሰዎች በሥራቸው ይታወቃሉ፤ የታይታ ፆምና ስግደት ወይም የፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ዓይነቱ የአለባበስና የአነጋገር ላህይ ሳይሆን – እምነት፣ ሥራና ፍቅር የሰውን ምግባር ይገልጣሉ፡፡› በቃ፡፡

የሌሎችን የእምነት ቤቶችም ተቆጣጥረዋል፡፡ ሚዲያውም በነሱው ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ እነሱ የሚፈልጉት ዜናም ሆነ ሀተታ ይነገራል፤ ሌላውና ከነሱ ፍላጎት ውጪ የሆነው ግን ይታፈናል፡፡ የየሀገራቱ መሪዎች ሴቴኒስት ካልሆኑ ከሥልጣን የሚወርዱበት መንገድ ይጠናና ተግባራዊ ይደረጋል፤ ምክንያቱም እንደኃያላኑ መንግሥታት መሪዎች ሌሎቹም ሴቴኒስቶች ካልሆኑ እንደልብ አይታዘዟቸውም – ሰይጣንና መልአክ – እርኩስና ቅዱስ ውሃና ዘይት ናቸውና፡፡ የሆሊውድንና የሌሎች -ውዶችን ፊልሞችና ሙዚቃዎች ቃኙ፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ አገልግሎታቸው በሰይጣናዊው አዲሱ የዓለም ሥርዓት [The New World Order] መሠረት የተቃኘ ነው፡፡ ለነሱ የማይስማማ ይወገዛል – ተጠርጎ ይጣላልም፤ ለነሱ የሚስማማ ጨካኝና አውሬም ቢሆን እንደጫጩት ጉያ ውስጥ ይታቀፋል(ሳዑዲንና ባሕሬይንን ያስቧል)፤ (የቬንዞላ ሕዝብ አሜሪካ የምትፈልገውን ካፒሪሌን ትቶ ማዱሮን መምረጡ ስህተት ነው፤ እና አሜሪካ የምርጫውን ውጤት አትቀበልም፡፡ የኢትዮጵያው የ97 ምርጫ ግን – ዌል – እንደዴሞክራሲያዊ ተሞክሮ ስለሚቆጠር – ተቃዋሚ በዝረራ ቢያሸንፍም – እርግጥ ነው – ወያኔ አሸንፏል ማለት ይቻላል፡፡ ተቃዋሚዎች የተሰጣቸውን ወንበር መቀበልና በመናጆነት በወያኔ ፓርላማ በረት ገብተው ማንቀላፋት ነበረባቸው፡፡ … የጉዶች ምድር፣ የምፀት ዓለም… “ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው…”ይብላኝ ለንጹሑ ሰላማዊ ሕዝብ! ዐይጥ በበላ ዳዋ ተመታ …

በነገራችን ላይ ሁለት ወጣቶች ብቻ አሜሪካውያንን በ‹ጦር ሜዳ ውሎ›ና በፕሮፓጋንዳ እንዲህ ‹ሽንት በሽንት› ያደረጉ፣ የዓለምን ሚዲያ በመሪና በሰበር ዜናነት ከዳር እዳር ያጥለቀለቁ፣ ፕሬዝደንት ኦባማን ሣይቀር እንቅልፍ አሳጥተው ያስጨነቁና ዕንባ በዕንባ ያስደረጉ አሥርና አሥራ አምስት ቢሆኑ ምን ያሳዩ ይሆን? በዛሬዋ ቀን እያዘንኩም ቢሆን ሁለት ዜናዎች ፈገግ አድርገውኛል፡፡ አንደኛው እነኢራንንና ሰሜን ኮሪያን ፌሽታ በፌሽታ የሚያደርገው ምናልባትም በሣቅ የሚያፈነዳው የቦስተኑ ክስተት ሲሆን ሁለተኛው ያ ሙሻራፍ የሚባል ገልቱ ሰውዬ በሀገር ክህደትና በሌሎች ወንጀሎች ዘብጥያ ሊወርድ ከሞቀ የስደት ኑሮው መመለሱና ዛሬ በፖሊስ መያዙ ናቸው – የሥልጣን ፍቅር አነሁልሎት እውነቱ ተሸፈነበትና ጉድ ተሠራ፡፡ በጊዜያችን ብዙ ነገሮች ከመግረም እያለፉ እንደጅል በሞኝነት ማሣቅ ይዘዋል፡፡ ፈገግ ብትሰኙልኝ አንድ አስቂኝ ታሪክ እዚች ላይ ባጭሩ ላስታውሳችሁ፡፡(የአሜሪካው ትዕይንት ግን ሆሊውድ በቦስተን የቀረጻ ልምምድ እያደረገ አልመሰላችሁም?)

በዱሮ ጊዜ ነው አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ የጦር ቡድን ወደ አንድ ጫካ ይልካል፡፡ ያስቸገረ አስቸግሮ ነበርና፡፡ ከጦርነቱ መልስ አንድ ሰውዬ የጦር አዛዡን ጠጋ ይልና እንደሚከተለው ይጠይቀዋል፡፡

ጠያቂ፡- ውጊያው እንዴት ነበር? በቀላሉ ቀናችሁ ወይንስ ጉዳት ደረሰባችሁ?

አዛዥ፡- ኧረ ምኑ ይወራል! በጣም ኃይለኛ ጦርነት ነበር፤ ያልጠበቅነው ብዙ ጉዳት ደረሰብን…

ጠያቂ፡- እንዴ? ብዙ የጠላት ኃይል ነበር እንዴ የገጠማችሁ? ማለቴ ከእናንተ የሚበልጥ…

አዛዥ፡- አሄሄ… እንደሱማ ቢሆን በማን ዕድላችን፤ የገጠመን አንድ ሰው ብቻ ሆኖ ውር ውር እያለና            እየተሽሎከለከ ፈጀን እንጂ፡፡ በስንት መስዋዕትነት መሰለህ መጨረሻ ላይ የገደልነው …

 

ኢትዮጵያችን በሰይጣን ግዛት ከገባች ቆይታለች፡፡ በፊትም ግማሽ እግር በሰይጣን ግዛት ግማሽ እግር በእግዜር ግዛት ውስጥ በጨለማና በብርሃን በሚመላለስ የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ነበረች፡፡ እየቆዬ ደግሞ በለዬለት ሁኔታ እዚያው እጨለማው ግዛት ገባችና አሁንም ድረስ በዚያው አለች፡፡ እግዚአብሔር ይርዳት፡፡

በእስልምና ስም እየታዬ ያለውም የሚዘገንን ነው፡፡ ሰሞኑን ከድረ ገፆች ስለአንዲት ኢትዮጵያዊት ልጃችን ያነበብኩት ሰቅጣጭ ታሪክ ወደውስጤ አስለቅሶኛል – ወደ ውጪ የማፈስሰው ዕንባ የለኝም፤ ለጊዜው ጨርሻለሁ፡፡ ይህች ልጅ እንደብዙዎቹ ከርታታ ወገኖቻችን ሁሉ ያልፍልኛል ብላ ወደዐረብ ሀገር ትሄዳለች፡፡ ሦርያ ውስጥ ገብታ ሥራ ትይዛለች፡፡ ነገር ግን ‹አንበሣን ፈርቼ ዛፍ ላይ ብወጣ ነብር ጠበቀኝ› እንዲሉ ሀገሯ ያስወጣት ችግር መልኩን ቀይሮ ሦርያ ላይ ጠበቃት – ጦርነት፡፡ ከርሀብ ስትሸሽ ጦርነት አፉን ከፍቶ ጠበቃት፡፡ በዚህ የርስ በርስ ውጊያ ሰበብ ቀጣሪዎቿ ቤቱን ጥለውላት ወደዉጭ ይሰደዳሉ፡፡ ዝርዝሩን ከነዚያው ድረ ገፆች አንብቡ፡፡

ሳላነሳው ማለፍ የማልፈልገው ግን ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ የዚህች ልጅ ስቃይ ነው፡፡ ይህች ልጅ ደማስቆስ የመሬት ለመሬት የውስጠኛ ክፍል ውስጥ በመሸጉ አሸባሪዎች እጅ ትወድቃለች፡፡ በነዚህ የእስላም አክራሪ ሰይጣኖች ቁጥጥር ከገባች በኋላ የምታየው አበሳ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሰይጣኑን የመለስ ዜናዊን ነፍስ ተገቢ ዋጋዋን ይስጣትና በሱ የተንሸዋረረና በዘረኝነት የበከተ አገዛዝ ምክንያት ወደዉጭ የሚሰደዱ ወገኖቻችን ምን ዓይነት መከራና ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ይህች ልጅ አብነት ናት፡፡ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ወገኖቻችንም በዚህ ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ እንደሚኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ የሆነ ሥርዓት በቶሎ ካልተወገደ በሀገራችን ምን ያህል ውድመት እየደረሰ እንዳለና ወደፊትም የሚመጣብን መከራ በዚህች ልጅ አማካይነት ቁልጭ ብሎ ይታያልና ወደየኅሊናችን ተመልሰን ለጋራ ጉዳያችን በጋራ እንድናስብ ይህ ዓይነቱ አስከፊው ተሞክሮኣችን ያስተምረን፡፡ በፈጠረን ይሁንብን!

አሸባሪዎቹ ይህችን ልጅ በሚስቶቻቸው ፊት ሳይቀር ይደፍሯታል፤ ሌሎችን በኮረንቲ እንድትጠብስ ያደርጓታል፤ ሽንታቸውን እንድትጠጣ – የርሷንም ሽንት ሌሎችን እንድታጠጣ ያደርጓታል፤ ሬሣ መሀል እንድታድርና አእምሮዋን ስታ ወደአውሬነትም ተለውጣ ለአጥፍቶ መጥፋት ተልእኮ ፈቃደኛ እንድትሆን ያስገድዷታል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል የዚህችን ልጅ ስቃይ ያላነበበ ከአንዱ ድረ ገጽ ቢያነብ ደስ ይለኛል (በዚህ በኩል ልምዱ ያላችሁ የዘሀበሻ ድረገፅ ሰዎች እባካችሁን እዚህች ቦታ ላይ የዚያን ጽሑፍ አድራሻ አጣቅሱት – እኔ ያነበብኩት በኢትዮሚዲያ ላይ ነው፤ ርዕሱ ‹ኢትዮጵያዊቷ በሦርያ ያሳለፈችውን ስቃይ…› የሚል ነው – ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው የወሰዱት)፡፡ የእርሷ ስቃይ የኛ ስቃይ ነው፡፡ ይህች ልጅ የኔንም ምስል የምታሳይ ሴት ክርስቶስ ናት፡፡ የገማና የሻገተው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓታችን ነፀብራቅ ናት፤ የመለስ ራዕይ ውጤት ያስገኘልን ድል መገለጫ የኅሊና ጸጸታችንና የጋራ ቁጭታችንም መንስኤ ናት፡፡ ያንዳችን ቁስል ላንዳችን ካልተሰማን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ሰዎችም አይደለንም ማለት ነው፤ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ አንዳችን ለአንዳችን እንተዛዘን፡፡ በነገራችን ላይ ይህች ልጅ ፈጣሪ በሰዎች አማካይነት ረድቷት ከዚያ የቁም መቃብር ተርፋ አሁን በሕይወት አለች፡፡

እንግዲህ ሰይጣን ማለት ከፍ ሲል እንደተመለከትነው ነው – ዕልቂትና ትርምስ የሚወድ፡፡ በሦርያ፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ በሕንድ፣ በሶማሊያ፣ በግብጽ፣ በፍልስጥኤም፣ በበርማ፣ በኢንዶኔዥያ፣ በአሜሪካዎች፣ በማሊ፣ በሴንትራል አፍሪካ ‹ሪፓፕሊክ›፣ በጊኒ፣ … ሠይፉን መዝዞ ሕዝበ አዳምን እያንቆራጠጠ የሚገኘው ሰይጣን በሰዎች ተመስሎ ነው – (በነገራችን ላይ ሰይጣንም ሆነ እግዚአብሔር – በጨለማና በብርሃን በሚመሰል የመንፈስ ኃይል እንጂ የራሳቸው ቁሣዊ መገለጫ እንደሌላቸው የታወቀ ነው፡፡) ቦስተን ላይ የፈነዱት ሁለት ቦምቦች የሰይጣን ናቸው፤ ኢራቅ ውስጥ በየቀኑ የሚፈነዱ ቦምቦችና የአጥፍቶ ጠፊ ተልእኮዎች ከሰይጣን የሚላኩ ናቸው፡፡ ሶማሊያ ውስጥ የሚፈነዱ ቦምቦች የሰይጣን ናቸው፡፡ እስላም እማሬያዊ ትርጉሙ ‹ሰላም› ሆኖ ሳለ ሰይጣን አእምሮኣቸውን የሠረራቸው ሰዎች በዚህ ሰላምን በሚሰብክ ሃይማኖት ሽፋን ስም ገብተው ዓለምን ወዴት እያቀጣጯት እንደሆነ ልብ እንበል፡፡ የዕብድ ገላጋይ ድንጋይ እንደሚያቀብል ሁሉ በሌላው ጫፍ ያሉ የሰይጣን ሎሌዎችና ደንገጡሮችም የጠቡን አድማስ ከማጥበብ ይልቅ እዬለጠጡና ነገር እየተነኮሱ አለይዞታቸውም በሰው ግዛት ጥልቅ እያሉ በሚያቀጣጥሉት የ‹አሸባሪነትና ተሸባሪነት› አሸናፊ የሌለው ጦርነት ውስጥ የስንቶች ንጹሓን ዜጎች ሕይወት በየቀኑ እንደሚረግፍ እናስተውል፡፡ አስቂኝ ቀልድ – አሸባሪነትን በአሸባሪነት ለማሸነፍ የመሞከር ልዩ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ትራጂኮሜዲ ድራማ፡፡ በሰዎች ዕልቂት ሰዎች የሚጨፍሩበት አሣዛኝ ተውኔት፡፡ ዓሣሞችና አጋሰሶች – ማነው – ዝኆኖች ሲጣሉ ሣሮች የሚረጋገጡበት ክፉ ዘመን፡፡ ምን ይሻለናል? ጊዜው አያስፈራም? የኔ ስሜት ድብልቅ ነው – ያስፈራል ፤ አያስፈራምም፡፡

የእንቅስቃሴውን ስም አልቃኢዳም እንበለው አልሻባብ፣ አል ኑስራም እንበለው አል ዛዋሪ – ሃይማኖቱ እስልምናም ይሁን ክርስትና ቡድሂዝምም ይባል አይሁድ ተግባሩ ሰዎችን መጨረስ ከሆነ ያው ሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣናዊነት ሰብኣዊነት የሌለው በግድያ እንድትዝናና የሚያደርግ የጭካኔ አምልኮት ነው፡፡ በሰው ስቃይ የሚደሰት ሁሉ ሰይጣን ነው፡፡ የተቀደሰ ግድያ የለም፡፡ ግድያ በማንም ይሁን በማን፣ ማንም ላይና ለምንም ዓይነት ዓላማ  ይፈጸም አስከፊ ነገር ነው፤ አስተማሪነትም የለውም፡፡ የሞተም አልተማረም፤ የተመለከተም ኅሊናውን በሚያሰቃይ ቁስል አነፈረቀ እንጂ ትምህርት አልቀሰመም፡፡ በተጨማሪም ግድያን ምንም ዓይነት ሕጋዊም ይሁን ሞራላዊ ልባስ ቢሰጡት ያው ግድያ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ሞትን አፈጠንከው አዘገየኸው መቼም ቢሆን ለማንም አይቀርም፡፡ እናም የፈጠረ ይግደል፤ ያልፈጠረ ያልፈጠራትን ነፍስ ከሥጋዋ አለጊዜዋ ለምን ይለያል? “አትግደል” የሚለውን የፈጣሪ ሕግና ትዕዛዝ የሚተላለፍ ሁሉ ኃጢኣትን አደረገ፡፡ ስለዚህም ሰውን በመግደልም ይሁን በማሰቃየት የሚደሰቱ ሁሉ ምድባቸው ከሰይጣን መሆኑን በመረዳት ምርጫችንን እናስተካክል፡፡ ከሁለቱ አማራጮች ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፤ አንድም የፍቅርና የሰላም የእግዚአብሄር መንፈስ ያለን መሆን ወይም በተቃራኒው የጠብና የአምባጓሮ፣ የግድያና በሰው ስቃይ የመደሰት ሰይጣናዊ መንፈስ ያለን መሆን፡፡ ምርጫው በእጃችን ነው፡፡ መሆን ወይም አለመሆን – በግዛታችን ያለ ነጻ ምርጫ፡፡

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>