የቀለም አልባ (የገረጣ) ጥፍር
ጥፍርዎ እጅግ የገረጣ ከሆነ ከባድ የሆነ የጤና ችግር መከሰቱን አመላካች ሊሆን ሲችል ከእነዚህ የህመም አይነቶች ውስጥም ደም ማነስ፣ የልብ ህመም፣ የጉበት ችግርና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ያመላክታል።
ነጭ ጥፍር /
white nails/
ጥፍርዎ ነጭ ሆኖ ዳርዳሩ ጠቆር ያለ መልክ ከያዘ ሄፒታይተስን ለመሰሉ የጉበት በሽታ ችግሮች የተጋለጡ መሆኑን አመላካች ሲሆን ምንም እንኳ ሄፒታይተስ ባይገኝም ለሌሎች የጉበት ችግሮች ተጋልጠው ሊሆን ይችላሉና ትኩረትን ይስጡት።
ቢጫ ጥፍር
/Yellow Nails/
የጥፍር ቢጫ መሆን ከምንም በላይ በፈንገስ ኢንፌክሽን የመጠቃት ምልክት ሲሆን ኢንፌክሽኑ እየባሰ ከመጣም በጥፍሮችዎ ስር የሚገኘው ቆዳ የመሰነጣጠቅና የመፈረካከስ ምልክት ያሳያል። ጥፍሮችዎም በጣም ከመጠንከር በተጨማሪ የመሰባበርና የመሰነጣጠቅ ባህሪ ያሳያል። አልፎ አልፎም ቢሆን ቢጫ ጥፍር በጣም አደገኛ በሆነ የታይሮድ ችግር፣ የሳንባ በሽታና ስኳርን የመሰሉ ህመሞች መከሰታቸውን አመላካች ነው።
ሰማያዊ ጥፍር
/Bluise Nails/
ጥፍርዎ ወደሰማያዊነት ያመዘነ ቀለምን ከተላበሰ በቂ የሚባል ኦክሲጅን እያገኙ እንዳልሆነ አመላካች ሲሆን ይህም በሳንባ ኢንፌክሽን ወይም ኒሞኒያን በመሠሉ ከባድ የሳንባ ህመሞች መጠቃትዎን ሊያመላክት ይችላል። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜም ሰማያዊ የጥፍር ቀለም ከልብ ችግሮች ጋር ይያያዛል።
የተሰነጠቀ ጥፍር
/cracked or split Nails/
ደረቅና በቀላሉ የሚሸራረፍ ጥፍር በተለይ ከታይሮይድ ጋር የተያያዙ በሽታዎች መገለጫ ነው። ጥፍር ከመድረቅና ከመሸራረፉም በላይ ለሁለት ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ቦታዎች የሚሰነጠቅ ሲሆን በፈንገስ ኢንፌክሽን ወቅት እንደሚከሰተው ቢጫ አይነት መልክ ሊያሳይም ይችላል።
ባለጥቁር መስመር ጥፍር
/Dark Lines beneate the Nails /
ጥቁር መስመር በጥፍሮቻችን ላይ ሲከሰት አስቸኳይ የጤና ምርመራ ማድረግ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ አይነቱ ምልክት በገዳይነታቸው ግንባር ቀደም ከሆኑት የቆዳ ካንሠሮች አንዱ የሆነው የ‹melanoma› ካንሠር ምልክት ነው።
የተበሉ ጥፍሮች
/gnawed Nails/
ብዙ ሰዎች ጥፍር መብላትን እንደ አጉል ልማድ እንጂ እንደጤና እክል አይቆጥሩትም። ይሁን እንጂ አብዝተው ጥፍራቸውን የሚበሉ ሰዎች በጭንቀትና በውጥረት የተጠቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ‘obsessive compulsive disorder’ ለሚባል ስነልቦናዊ ችግር የተጋለጡ ናቸው።
ከላይ በጥቂቱ እንደተመለከትነው የጥፍራችን ቀለምና ይዘት መቀየር የተለያዩ የጤና ችግሮች መከሠታቸውን አመላካች እንደሆነ ቢታመንም የጥፍራችን ቀለም መቀየር በእርግጠኝነት የጤና ቀውስ ለመፈጠሩ ምልክት መሆኑን ለማረጋገጥ ሀኪም መጐብኘት እንዳለብን ማስታወስ ይገባል። የጥፍር ቀለምን በማየት ብቻም በዚህ ህመም ተጠቅቻለሁ ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ሲሆን ህክምናዎን ሳያማክሩም ምንም አይነት መድሃኒትም መውሰድም አይመከርም።